Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡና ላኪዎች በዓለም ገበያ መቀዛቀዝ ሳቢያ የገቡትን ውል እያፈረሱ በመሆኑ በገቢ ላይ ቅናሽ አምጥቷል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ባለፉት ወራት 394 የሚሆኑ የግብይት ውሎች አልተፈጸሙም

የ2014 የበጀት ዓመት ለኢትዮጵያ የቡና ምርት ኤክስፖርት አፈጻጸም ልዩ የሚባል ዓመት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ዓምና ኢትዮጵያ ወደተለያዩ የዓለም አገሮች ከላከችው ቡና 1.4 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች። ይህ ገቢ ደግሞ አገሪቱ ቡና ወደ ውጭ መላክ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በዓመት ውስጥ የተገኘ የመጀመሪያው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደነበር በስፋት ተነግሯል፡፡

ዓምና የነበረውን የቡና ኤክስፖርት መነቃቃት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በጠቅላላው ባለፈው የበጀት ዓመት ወደ ውጭ የተላከውን 300 ሺሕ ቶን የቡና ምርት መጠን በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ 360 ሺሕ ቶን በማድረስ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን ከዚህ ቀደም አስታውቆ ነበር፡፡

በእርግጥ በተያዘው የበጀት ዓመት ከቡና ለማግኘት የታቀደው ዕቅድ ከባድና የተለጠጠ መሆኑን የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ቀድሞውንም አሳውቆ የነበረ ቢሆንም ፣ ባለስጣኑ የጀመራቸውን የሪፎርም ሥራዎች ፣ የግብይት አማራጮችን አጠናክሮ በማስቀጠል፣ ነባርና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት ዕቅዱን ለማሳከት እንደሚሠራ ተጠቅሶ ነበር፡፡ 

ነገር ግን አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት የቡና ወጪ ንግድ፣ በዚህ ዓመት ለመላክ ከታቀደው መጠን በታች እንደሚሆን ገና በበጀት ዓመቱ አጋማሽ መታወቅ ጀመሯል።

የባለፉት ስምንት ወራት የቡና ኤክስፖርት አፈጻጸም ከዕቅድ አኳያ የ21.5 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የ2015 የበጀት ዓመት የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን በተጠናቀቀው ሳምንት በተመለከተበት ወቅት ተረጋግጧል።

በተጠቀሱት ወራት ለገበያ የቀረበው የቡና መጠን ከዕቅዱ አንፃር ቅናሽ የታየበት ቢሆንም የተገኘው ገቢ ግን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ5.5 በመቶ ብልጫ አለው።

ይህንን ከግንዛቤ በማስገባትም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በቀሪዎቹ ወራት ተግዳሮት የሆኑትን የዋጋ መቀነስና ዝቅተኛ የገዚዎች ፍላጎትን ታሳቢ በማድረግ ዕቅዱን ማሳካት ይቻል እንደሆነ የባለሥልጣኑን ማብራራያ ጠይቀዋል።

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንደተናገሩት በዘንድሮ ዓመት የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ እጅግ በጣም በመቀዛቀዙ የቡና፣ የቅመማ ቅመም፣ የሻይ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ተቀዛቅዟል፡፡

የዓለም የቡና ዋጋ ከዓምና አንፃር ሲመሳከር በ32 በመቶ መውረዱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ዓምና በአንድ ዶላር ሲሸጥ የነበረው አንድ ፓውንድ ቡና (0.45 ኪሎ ግራም) 30 ሳንቲም ቀንሶ 70 ሳንቲም እየተሸጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ያም ሆኖ ከባለሥጣኑ ዕቅድ አንፃር ወደ 143 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ተልኮ 780 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተናግረዋል፡፡

ገቢው ከዓምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑን የተናገሩት አዱኛ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን የተላከው የቡና መጠን ከታቀደው አንፃር ቅናሽ ያለው በመሆኑ የገቢ ዕቅዱን ለማሳካት እንዳልተቻለ ገልጸዋል። በቀሩት አራት ወራት ውስጥ በከፍተኛ ርብርብ ይህንን ማሻሻል የሚችልበት ዕድል ቢኖርም፣ ዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ መውረድ፣ የዩክሬይንና ራሺያ ጦርነት አጠቃላይ የዓለም ኢኮኖሚን በማድቀቁ ምክንያት በተለይም ቅንጡ (ሌግዠሪ) የሚባሉት ምርቶች ላይ የሰዎች ፍላጎት እየወረደ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ እንደስጋት አንስተዋል።

ከገቢ አንፃር በሻይ፣ ቡናና ቅመማ ቅመም ኤክስፖርት 800 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እስካሁን መገኘቱን ያስታወቀው የቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ ይህም የዕቅዱን 78 በመቶ የሚሸፍን መሆኑን አስታውቋል፡፡ በመጠን ደግሞ የተገኘው አፈጻጸም ከዕቅዱ 68 በመቶውን የሚሸፍን እንደሆነ አመላክቷል፡፡

የቡና ኤክስፖርት በዋናነት የቀነሰበት ምክንያት የአገር ውስጥ ቡና አቅራቢዎች ዓምና ከአርሶ አደሮች ከፍ ባለ ዋጋ የገዙትን ቡና ዘንድሮ ቅናሽ ባሳየው ዓለም አቀፍ ገበያ ለመሸጥ መቸገራቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ምርት በአብዛኛው በአቅራቢዎች እጅ እንደሚገኝ የሚናገሩት አዱኛ (ዶ/ር)፣ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ እየቀነሰ በመምጣቱ ምክንያት በ394 የግብይት ውሎች ለውጭ ገበያ መቅረብ የነበረበት 28 ሺሕ ቶን ቡና ሽያጭ ሳይፈጸም መቅረቱን ገልጸዋል። ይህ የግብይት ውል ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ 133 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይገኝ እንደነበር ጠቅሰዋል።

‹‹ይኼ 28 ሺሕ ቶን ቡና አሁንም በእጃችን ላይ አለ፣ ይኼ ወጥቶልን ቢሆን ኖሮ 133 ሚሊዮን ዶላር በታቀደው መሠረት ይገኝ ነበር፡፡ የዓለም አቀፍ ዋጋ ስለወረደ ይህንን ያህል ኮንትራት ቡና ወደ ኋላ ተመልሶብናል፤›› ብለዋል አዱኛ (ዶ/ር)፡፡

በሌላ በኩል የባንክ ኤልሲ ተከፍቶ ሳይላኩ የቀሩ 334 ቶን ቡና እንደሚገኝ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት የገለጹ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ የቡና መሸጫ ዋጋ ከዓለም አቀፍ የቡና መሸጫ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ይህ የዋጋ አለመናበብ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ውል የተገባበትን ዋጋ በአዲስ ዋጋ የመከለስ ሥራ ተሠርቶ ቡናን መልሶ ወደ ውጪ የሚላክበት ሁኔታ ላይ በርካታ ሥራዎች እንደተሠሩ፣ በዚህ ወቅት ጉዳዩ ተስተካክሎ ቡና ከአገር እየወጣ ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡

‹‹የዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ማሽቆልቆል በጣም ከባድ ችግር ፈጥሮብናል፡፡ ምርት ገዢ ኩባንያዎች በዋጋ መውረድ ምክንያት ምርቶችን ለመቀበል ወደ ኋላ መሸሽ፣ ኤልሲ ያለመከፈት፣ ኮንትራቶችን የመሰረዝ፣ ዲፎልት የማድረግ ሥራዎች በርካታ ናቸው፤›› በማለት አዱኛ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

የእሸት ቡና መሸጫ ዋጋ አርሶ አደሩን የጠቀመ ቢሆንም ነገር ግን ከዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ጋር የተናበበ ባለመሆኑ በራሱ ችግር እንደፈጠረ፣ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረ የፀጥታ ችግር በተለይም ከምዕራብ ወለጋ ቡና እየቀረበ እንዳልሆነ ሌላው የተሰነዘረ ምክንያት ነው፡፡ 

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር እንዳስታወቁት አገሪቱ ዓምና ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ምክንያት ከቡና ኤክስፖርት 1.4 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች፡፡ ዘንድሮ ግን ከመስከረም ወር ጀምሮ የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመቀነሱ (በጦርነት፣ በወረርሽኝ እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች)፣ የዓለም የመግዛት አቅምን እንዲቀዛቀዝ አድርጎታል፡፡ የዓለም የመግዛት አቅም ሲቀዛቀዝ የገዢዎች ፍላጎት በተመሳሳይ መቀዛቀዙን ሻፊ ይናገራሉ፡፡

የኢትዮያን ቡና በብዛት የሚወስዱ ዋና የኢትዮያ ቡና መዳረሻ አገራት ተብለው የሚታወቁት አምስት ትልልቅ አገሮች ሲሆኑ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ጃፓን አሜሪካና ሳዑዲ ዓረቢያ ናቸው፡፡

በተፈጠሩ አገራዊ ችግሮች ሳቢያ አገሪቱ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የምትልከው ቡና በጣም መቀነሱ የሚገለጽ ሲሆን፣ አውሮፓ ላይ ባለው የዋጋ ንረትና እንዲሁም ቀውሶች ምክንያት ጀርመንና ቤልጂየም የሚላከው የኢትዮያ ቡና መቀነሱ ተሰምቷል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ አገሪቱ ወደ እስያ ገበያ በማምራት ቻይና፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ፣ ፓኪታን ላይ ሰፊ ሥራዎች እንደሠራች፣ በእነዚህ አገሮች ላይ ያለው ግብይት በመጠንና በገቢ እንደጨመረ ተጠቅሷል፡፡ ዘንድሮ የተላከው ቡና በብዛት የተላከው ወደ አዲሶቹ የገበያ መዳረሻ አገሮች እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ፣ ቻይና፣ አውስትራሊያን ጨምሮ ታይዋን ከዚህ ቀደም በአሥር የኢትዮጵያ የቡና ገዢ አገሮች ዝርዝር ውስጥ የማይገኙ አገራት የአውሮፓ ገበያ በመዳከሙ (መቀዘቀዙን) መሠረት በማድረግ በተሠራ የገበያ አድማስ የማስፋት ሥራ ማካተት እንደተቻለ፣ ከላይ የተገለጸውን ጨምሮ ምርጥ አሥር ገዢ ዝርዝር ውስጥ የሚገኙ አገሮች ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው ቡና 81 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚወስዱ ናቸው፡፡ 

እስካሁን ባለው ሁኔታ በበጀት ዓመቱ የስምንት ወራት አገሪቱ በጠቅላላው የበጀት ዓመቱ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በዕቅድ ከያዘችው 360 ሺሕ ቶን የሚጠጋ 143 ሺሕ የሚያህለውን የላከች ሲሆን፣ ለበጀት ዓመቱ ለማሳካት ከተወጠነው ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥ እስካሁን ማሳካት የተቻለው 780 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አራት ወራት ከመቅረቱ አንፃር አገሪቱ በቀሩት ጊዜያት ውስጥ የመጠንም ሆነ የገቢ ዕቅዷን ለማሳከት እንደሚያዳግታት ዘርፉን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

አቶ ሻፊ እንደሚገልፁት፣ በቀሪዎቹ የበጀት ዓመቱ ወራት ገዥ አገሮች የገቡዋቸውንና የተሰረዙ ኮንትራቶች እንዲፈጽሙ ማድረግ፣ በቀጣይ አዳዲስ የኮንትራት ውሎች እንዲገቡ በማድረግ ቡናን የማውጣት ሥራ መጀመሩንና በዚህ ዕቅዱን ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግና ይህ ወቅት ቡና ለውጭ ገበያ በደንብ የሚወጣበት (ፒክ ወቅት) እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በሲዳማ ክልል በንሳ አካባቢ ቡና አምራችና አቅራቢ የሆኑ እንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ሰዎች ያለበቂ ጥናት በቡና ንግድ ውስጥ በመሰማራታቸውና ወደ ቡና ግዢ መግባታቸው የቡና እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉን ይገልጻሉ።

የቡና እጥረት መፈጠሩን ተከትሎ ቡናን በሽሚያ ዋጋ ከፍ ተድርጎ እንዲገዛ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም የዓለም የቡና የመግዣ ዋጋ ዝቅ ባለበት ወቅት እንኳን የአገር ውስጥ የቡና ግዢና ሽያጭ ከፍ ያለበት ሁኔታ መፍጠሩን ይግልጻሉ፡፡

ሁሉም ሰው ዓምና በተገዛበት ዋጋና ከዛ በታች በሆነ ዋጋ ቢገዛ ምርቱ በዓለም አቀፍ ገበያ የፈለገውን ያህል ዋጋው ቢወርድም እንኳን ያን ያህል ተፅዕኖ ፈጥሮ የአገሪቱን ገቢ የሚቀንስበት ዕድል እንደማይኖር ይጠቀሳሉ፡፡

ከውጭ የሚመጡ ገዢዎች በዚህ ወቅት የመግዛት ፍላጎታቸው እምብዛም እንደሆነ፣ ከግብይቱ ራሳቸውን እንዳራቁ የሚናገሩት እኝሁ የቡና አቅራቢና አርሶ አደር፣ በለፈው ዓመት በአራትና አምስት ዶላር የተሸጠ ቡና ላይ በአንድ ጊዜ ሁለትና ከዚያ በላይ ጭማሪ መደረጉ ገዢዎች ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

ከላኪዎች ይልቅ የቡና አቅራቢዎች በዓለም አቀፍ ገበያ የተሻለ ዋጋ ይመጣል በሚል ምርቱን በመጋዘን እንዳከማቹ የሚገልጹት የቡና አቅራቢው፣ ይህ ዕሳቤ በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያልተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት በአገር ውስጥ የቡና ግብይት ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር በጣም ዝቅተኛ መሆኑ ሌላው ችግር መሆኑን በመጥቀስ፣ መንግሥት ትኩረት አድርጎ እስከ ወረዳ ድረስ በመውረድ የቡና ግዢ ላይ ያለውን ነገር በጣም መቆጣጠር እንደሚገባው መክረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች