Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትአምስት ዓመታችን

አምስት ዓመታችን

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የዛሬ አምስት ዓመት መጋቢት ወር መጨረሻ (መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም.) ኢትዮጵያ ውስጥ የተመዘገበው ሁነት ተራ ዜና፣ ዝም ብሎ የተለመደ የጠቅላይ ሚኒስትር፣ የመንግሥት ለውጥ ብቻ አይደለም፡፡ በአገራችን ታሪክ ውስጥ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ፣ አምሳያም የሌለው፣ በውስብስብ የመንግሥት ግርሰሳ ውስጥ ያልገባ፣ የለውጥ ብርሃን የፈነጠቀበት፣ ለዘመናት ተገትሮና ተጓጉሎ የኖረው ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ጉዟችን እንደ አጀማመሩ ለስላሳ ይሆናል ብለን ተመሥገን ያልንበት፣ ይህ አገር ሳይፈርስና መልካው ሳይናጋ የተፈጠረው የለውጥ መንገድ ውስጥ ገብተን ግን ጣጣዎች እየተዘረገፉ አስቸግረው አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡

የደረስንበትን የዕድገት ደረጃ፣ ዓይነትና ምንነት እንደምን ሆነን እዚያ ላይ እንደደረስን ለማመላከት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ሕዝብ እንዳለ የሰጠውን ድጋፍ ምን ነካው ብሎ መጠየቅ፣ የምንነጋገርበትን ጉዳይ ለመረዳት መንገድ ያስይዛል ብዬ እገምታሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው፣ ያለማጋነን ከሞላ ጎደል የመላውን ሕዝብ ልብ የረታ ‹‹ለውጥ›› ሆነው መጡ፡፡ ከቋንቋና ከንግግር ጀምሮ ያታከቱ ጠምዛዛ አባባሎችን ጥለው፣ በሥዕላዊና አይረሴ አነጋገር ከሕዝብ ጋር መነጋገርን ያወቀ ምልከታ ይዘው መጡ፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ንግግርና ቋንቋ ብቻ አልነበረም፡፡ በዕርቅ ለመተቃቀፍ፣ የፓርቲ ወገንተኛ ባልሆኑ አውታራት ላይ ዴሞክራሲን ለመገንባት፣ ብሔረሰባዊ ማንነትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ለማግባባትና እንደ አገር ህልውናን በሚወስኑ የቀጣናችንና የአኅጉራችን አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ለማተኮር መልካም ዕድልን የፈነጠቀ፣ አዲስ የለውጥ ሐሳብ የፈነጠቀ ቃል ገቡ፡፡

እነዚህን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የገለጿቸውን ዴሞክራሲን ለማደላደል የሚያስፈልጉትን ዕርምጃዎች መፈጸም ግን ቀላል ነገር አልነበረም፡፡ የዚህ ምክንያት መወሰድ ያለባቸው ዕርምጃዎች፣ የለውጥ ሥራዎች በገዛ ራሳቸው ምክንያት ከባድ ስለሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተሰባሰበው ድጋፍ ራሱ ባለ ብዙ አቅጣጫ መሆኑ ችግር ነው፡፡ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥትና የፌዴራል አከፋፈሉ እንዳለ ሆኖ ዴሞክራሲ ብቻ ይታከል/ይተከል የሚል አለ፡፡ ዴሞክራሲ ቢቋቋምም፣ የብሔር/ብሔረሰብ መነጽር ያለው ሕገ መንግሥትና የፌዴራል አካላት አከፋፈል ካልተቀየረ፣ የማኅበረሰቦች መንጓለልና መፈናቀል አይወገድም የሚልም አለ፡፡ ያለው የፌዴራል አካላት አከፋፈል የአገረ ብሔርን ድርሻ ሆኖ እንዲታወቅለትና የአገረ ብሔሩን ሀብትና ምድር የብሔሩ ልጆች ብቻ መጠቀሚያ እንዲሆን የሚሻ፣ የሕገ መንግሥቱ ትርጉም፣ የሕገ መንግሥቱ ቃል ይህ ነው የሚልም አለ፡፡ ይህንን በመሰለውና ዘርዝረን በማንጨርሰው ልዩ ልዩ ፍላጎት መሠረት፣ ሁሉምና እያንዳንዱ ወገን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማስጠጋትና ለመሳብ የገመድ ጉተታ ማድረግ ዋናው ትግል ሆነ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ይህን ከመሰለው የትግል ምዕራፍ ወጥተን፣ ያንን ተሻግረንና ከዚያ አልፈን ለውጡን የሚጋጩ ሁለት ክሶች የተመሠረተበትና የተጠመደበት ችግር ውስጥ ገብቶ እናገኘዋለን፡፡ አንደኛው ወገንና ክስ ለውጡ በአክራሪ ብሔርተኞች ተጠልፎ የእነሱ መጫወቻ ሆኗል ይላል፡፡ ሌላው ወገን ለውጡን አሀዳውያን/ትምክህተኞች ጠልፈው አስገብረውታል ባይ ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች እንደ ክሳቸውና አሁን ወደ ለየለት ተቃውሞ እንደተቀየረው አቋማቸው በለውጡና በለውጡ አመራር ላይ ፊት ከማዞር የዘለለ፣ የሰፋና የከፋ ትግል ከፍተዋል፡፡  

ከአምስት ዓመት በፊት ለዶ/ር ዓብይ መንግሥት ከመላው ሕዝብና ከሁሉም ወገን እንደ ጉድ ጎርፎ የነበረውና እ.ኤ.አ. በ2019 የሰላም የኖቬል ሽልማት ጭምር አምሮና አሸብርቆ ያየነውን ድጋፍ ምን ነካው? ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት መዝለቅ ጋር የግልና የቡድን መብቶቻቸውን መከበር የሚሹ፣ በዚያን ወቅት የዓብይ መንግሥት መምጣት ለፈነጠቀው የለውጥ ተስፋ ድጋፍ መስጠታቸው ልክ ነበር፡፡ አሁንም፣ ዛሬም በቀጣናዊ ሰፊ ዕይታ ውስጥ ሁሉንም መብቶች የምታስተናግድ፣ ፌዴራላዊትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመገንባቱ ጉዞ አቅጣጫውን ቀይሯል ወይ? አቅጣጫውን እስካልቀየረና እስካልተሳተ፣ ሁሉንም አስተሳሰብና የሥልጣን ፍላጎት ጭምር በውድድር የሚያስተናግደውና የሚያስተናብረው ዴሞክራሲና መደላድል ይምጣ እስከተባለ ድረስ የየትኛውም አስተሳሰብ ወገኖች ድጋፍ ከለውጡ፣ ከለውጡ መሪዎች፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት ጋር መቆየት ያለበት መሆኑ የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን የግድ ነው፣ የግድ ነበር፡፡ ታዲያ ምን ነክቶን አሁን የምንገኝበት በለውጡ መሪዎች ዙሪያ የተሰባሰበው ድጋፍ የተበተነበት ደረጃ ደረስን?

የዚህ ጥያቄ መልስና ሚስጥር የሚገኘው አሁን በተፈጠረው ‹‹አዲስ›› ሁኔታ ውስጥ ሳይሆን መጀመርያም ከታየው ድጋፍ ባህርይ አኳያ ነው፡፡

ሲጀመርና ያኔ ባየነው፣ አገር ባስገረመና የውጭም አስደናቂ ሽልማት ባገኘ ምልዓታዊ ድጋፍ ውስጥ ሁሉን የሚያጫውት፣ ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተናግድ ሥርዓት ሊደላደልና ሊመጣ ነው ከሚል ተስፋ ባሻገር፣ እንዲያውም ከዚህ ይልቅ የእኔን አቋም የሚያራምድ እኔን የሚያቀርብ ቡድን ሥልጣን ላይ ወጣልኝ የሚል እምነት በሁለት በኩል ለየብቻ መንገሡ አሁን ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ ብሔርተኝነትን ንቆ የኢትዮጵያ አንድነትን ያጠበቀው ከዚህ በኋላ ብሔርተኝነት ሲሰባበርና ኢትዮጵያዊነት ሲገዝፍ ታየው፡፡ ብሔርተኛውም ብሔርተኝነት ተሹሞ ቤተ መንግሥቱ የብሔርተኞች ሲሆን፣ ቄሮዎች የባለድልነት ዋንጫ ሲረከቡ ማየት ጎመዠ፡፡ አልተነገረንም፣ ሲናገሩ አልሰማንም፣ አለዚያም አልገባንም፣ አልተገለጸልንም እንጂ የሁለቱም ተስፋና ግምት፣ እንዲሁም ትግል ውስጥ የወንበር ትሩፋት ጉጉትም አልጠፋም፡፡ ሁለቱም ወገኖች ለድጋፋቸው መቀጠልና አለመቀጠል መለኪያ ያደረጉት ለውጡ ለእኔ ያደላ ነው ባይ ግምታቸውን ነውና/ነበርና ለሁሉም መብቶችና ነፃነቶች፣ ለመብቶችና ለነፃነቶች በሙሉ ዋስትና በሆነው የዴሞክራሲ ዋና የሽግግር አገዳ ላይ ከማተኮር ይልቅ በጊዜ ሒደት ውስጥ አንዱ ከሌላው የላቀ አቅራቢነት ያገኙ ሲመስላቸው ይደሰታሉ፣ ሙገሳቸውን ያደምቃሉ፣ ያንኑ ያጡ ሲመስላቸው ደግሞ ያጉረመርማሉ፡፡

ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ መንግሥት የ‹‹መጤ›› ጥቃትን ከቦታ ቦታ ለማስቆም አለመቻሉ ኢትዮጵያን እጅግ ያፈቀሩ ለሚመስላቸው ጽንፈኞች ትልቅ የቅሬታ መነሻ ሆነ፡፡ ከብሔርተኞች ወይም ጎጠኞች በኩልም፣ በሕወሓቶችና በውስን የኦሮሞ ብሔርተኞች ዘንድ የዓብይ አህመድን ድጋፍ በምንም በምንም አድርጎ የመሞለጭ ፍላጎቱ ዓይኑን ያፈጠጠ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ኃይሎች የሽግግሩን ገጽታዎች፣ ሹመቶችን፣ በተለያየ ሥራ ዘርፍ የሚወሰዱ ዕርምጃቸውን፣ የአካባቢ ጉብኝቶችን፣ በመሪዎች ንግግሮች ውስጥ ያሉ የሐሳብና የቃላት አመራረጦችን፣ የሥራ ባልደረባ አመራረጦችንና የጓዳ ሹክሹክታዎችን ሁሉ የለውጡን መንግሥት ወገናዊ ሥፍራ መመርመርያና ፍንጭ ማግኛ አደረጉ፡፡ ሽግግሩን የማራመድ ፖለቲካ ኃላፊነት ተረሳና የሽግግሩ መንግሥት በሚስጥርም በግልጽም የማንን አጀንዳ አስፈጻሚ እንደሆነ መመርመር፣ ሐሜት ማደራጀትና መንዛት ዋና ፖለቲካ ሆነ፡፡ ሁለቱም ቢያዩ ባያዩ ከመንግሥት ከጠበቁት ውስጥ ያጡትና የተቀናቀናቸው ወገን ተጠቃሚነት በልጦ ይታያቸው ገባ፡፡ ሁለቱም ለውጡን አብጠልጣይ፣ ከድሮ የተለየ አዲስ ነገር የለም ብሎ ሸምጣጭ፣ ዕንከኖችን፣ ጉድለቶችንና ችግሮችን ሁለንተናዊ ባህርይ አድርጎ አናፋሽ ሆኑ፣ ወዘተ፡፡ ሚዲያውም ይህንኑ አሠላለፍ ይዞ አብሮ ‹‹ታገለ››፡፡ ይህን የመሰለው የማይረባ ‹‹ቦትላኪነት›› እና ከዚያም በላይ ሽግግሩን በእጅጉ የጎዳ ሁኔታ አገራችን ውስጥ ለማስፈን፣ ሽግግሩን የሚመራው መንግሥትም የራሱን የማይናቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በተለይ፣ በተለይ ደግሞ የሁለት ዓመቱ ጦርነት በሰላም ስምምነቱ ከተገታ በኋላ፣ የስምምነቱም አፈጻጸም መልካምና ውጤት ያለው ሒደት ውስጥ ገብቶ የተሳካ ሪፖርት በማስመዝገብ ላይ ባለበት ወቅት የተለያዩና ኢተገማች የሆኑ፣ አላባራም እያሉ ያስቸገሩ የመንግሥት ስህተቶች፣ ዝርክርክነቶች፣ ጥፋቶች፣ በአጠቃለይ ሕገወጥነቶች በመንግሥት ዙሪያ ተሰባስቦ/ተከማችቶ የነበረውን ድጋፍ በታትነውታል፡፡ የገባንበት ችግር መልስ የሌለው እንቆቅልሽ ሆኗል ወይም መስሏል፡፡ እየተዘረገፉ ያስቸገሩን አደጋዎችና ዱብ ዕዳዎች እንዳሻቸውና እንዳደረጉ ያድርጉን ካላልን በስተቀር ነገሮችን መርምሮ መልስ ማግኘት በጭራሽ የማይለመጥ አደራችንና ግዴታችን ነው፡፡

ለውጡና ለሽግግሩ እንዲሁም ለለውጡ አመራር ትናንት ሆ ብሎ ድጋፉን የሰጠውም፣ እየቆየም ድጋፉን እየነፈገ ፊቱን ያዞረውም፣ ከዚያም በላይ የተለያየ ልክና መልክ ያለው ተቃዋሚነቱን ያወጀውም፣ እነዚህ ሁሉ በአንድነትና ያለ ምንም ልዩነት ስለዴሞክራሲ ያወራሉ፣ ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ ይላሉ፣ ዴሞክራሲን ካላሳካን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ካልተተከለ በቀር ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ አትሆንም፣ ዴሞክራሲ የአገራችን የህልውና ጥያቄ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ የዴሞክራሲ አስፈላጊነት ላይ የሚስማሙት ከፍ ሲል የጠቀስናቸው በአንድ ወቅት በሌላ ለውጡን የደገፉት ወገኖች ብቻ አይደሉም፡፡ ለውጡን ከመነሻው የተጠናወቱትም፣ በኋላም እስከ መውጋትና ጦርነት እስከ መክፈት የሄዱትም ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲ ይላሉ፡፡ በዚህ አጠቃላይ የዴሞክራሲ ‹‹ስምምነት›› ውስጥ ግን መሠረታዊ የይዘት የትርጉም ልዩነት አለ፡፡ በጠቀስናቸው ወገኖች መካከል ያለው ዴሞክራሲ ላይ ያላቸው ስምምነትና መግባባት፣ ከየትኛውም ፓርቲና ቡድን ወገናዊነት ነፃና ገለልተኛ የሆነ የተቋም ግንባታ ያስፈልጋል የሚል አቋም ድረስ የሚዘልቅ አይደለም፡፡

እውነቱን ለመናገር ዴሞክራሲ ያስፈልገናል፡፡ ወደ ዴሞክራሲ እንግባ ማለት ከሚገባን በላይ፣ መረዳት ከምንችለው በላይ የፖለቲካ ውዝግብ፣ ፖለቲካዊ አለመግባባትና ‹‹ትርምስ›› የሚያስተናግድ ሥርዓት ውስጥ እንግባ ማለት ነው፡፡ የተለያዩና የማይጣጣሙ ሐሳቦች የሚፋለሙበት፣ የሚላተሙበት፣ ፈቃድን፣ ፍላጎትን ወደ ውሳኔ መቀየር የሚያስችል ጨዋታ የሚካሄድበት፣ ለሥልጣን መፋለም ወግና ሕግ ሆኖ የሚስተናገድበት አዲስ ኑሮ፣ አዲስ ሕይወት ውስጥ እንግባ ማለት ነው፡፡ እንደ አሜሪካ፣ እንደ ህንድ ያሉ በአንፃራዊነት ክፍት፣ ግልጽና የተረጋጉ በሚባሉ ዴሞክራሲዎች ውስጥ እነዚህን የመሰሉ የሚጣሉ፣ የሚጋጩ፣ ተፃራሪ የሆኑ ፍልሚያዎችን (ተጋድሎ፣ መዋደቅ፣ ጦርነት ጭምር ማለት ይቻላል) በሰላማዊ መንገድ ደም መቃባት በሌለበት ሁኔታ መፍታት ተችሏል፡፡ መቻል ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ 250 ዓመት የሞላው ባህል፣ ‹‹ጨዋታ›› እና የጨዋታ ሕግ ሆኗል፡፡ ይህንን ባህል ዕውን ያደረገው ግን የጠንካራ ተቋማት መኖር ነው፡፡ የሥልጣን መለያየትና የእርስ በርስ ቁጥጥር፣ የሕግ የበላይነት፣ ሲቪል ሶሳይቲ፣ ነፃ ፕሬስ፣ ተጠያቂነትና ተጠሪነት፣ ወዘተ ስለሚባሉ ጉዳዮች የምር መነጋገርና እንዲገባንም ከፈለግን፣ ሕይወታችንም ውስጥ መኗኗሪያችን ይሆኑ ዘንድ ተደጋግሞ እንደተገለጸው ከፓርቲ ወገናዊነት ነፃ የሆኑ (አሁን በዚህ ደፋ ቀና እያለ እዚህ በደረሰው ለውጥ ውስጥ ምርጫ ቦርድ፣ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ላይ ከሞላ ጎደል የተሳካልን ዓይነት) ነፃና ገለልተኛ የሆኑ ማቋቋም አለብን፡፡ የለውጡና የሽግግሩ ተቀዳሚ ሥራም ይኼውና ይኼው ብቻ ነው፡፡

ለውጡም ሽግግሩም መለካትና መታገዝ ያለበት ከዚህ አኳያ ነው፡፡ ሁሉንም ዓይነት አስተሳሰብ፣ እንዲሁም የሥልጣን ፍላጎት ጭምር በውድድር (በነፃነትና በእልኩነት) የሚያስተናግድና የሚያስተናብር የዴሞክራሲ ሁኔታና ይህንንም መሠረት የሚያስይዝና የሚገነባ የተቋም ግንባታ ሥራ እስከመጣ/እስከተሠራ ድረስ፣ የየትኛውም አቋም አስተሳሰብ ወገኖች ድጋፍ ከለውጡ ጋር መቆየት አለበት፡፡ ለዚህም ነው ያኔ ሲጀመርም አሁንም ከብዙ ውጣ ውረድና ጦርነትን ከመሰለ ፈተና በኋላ ጭምር ለውጡን ከቅልበሳ ማዳን፣ ለውጡ የሁሉንም የተለያየ አቋምና ፍላጎት ያላቸው ፓርቲዎች (የነባርም የአዲሶች)፣ እንዲሁም የምልዓተ ሕዝብን ድጋፍና ርብርብ እንዲጎናፀፍ ማድረግ የአገር የህልውና ጥያቄ የሚሆነው፡፡

በዚህ ምክንያትና ከዚህ በመነሳት መላውን አምስት ዓመት ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› ስሟገት ባጅቻለሁ፡፡ ምክንያቱም ግልጽ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቁ ድል መጀመርያ ይህ ወይም ያኛው አማራጭ ወይም የፖለቲካ አቋም ማሸነፉ ሳይሆን፣ መጀመርያ አማራጮች እንዲቀርቡ የሚፈቅድ፣ አማራጮች ከቀረቡ በኋላም በዕርጋታ ተገላብጠውና በደንብ ተመክሮባቸው በሕዝባዊ አወሳሰን ዕልባት የሚያገኙ መሆናቸው የተረጋገጠበት፣ በተግባር ሲውሉም ሊነቀሱና ሊሻሻሉ የሚችሉበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታና አሠራር አብሯቸው መኖሩና መዝለቁን የሚያረጋግጥ ሥርዓት መገንባት ነው፡፡

ዴሞክራሲ ሁሉንም ዓይነት አስተሳሰብና የሥልጣን ፍላጎት ጭምር በነፃና በሰላም የሚያወዳድር እኛ በጭራሽ የማናውቀው ‹‹አገር›› ነው ብለናል፡፡፡ በመርህና አደባባይ በሚሰማ ‹‹ዲስኩር›› ደረጃ ፓርቲዎች ወደ ሥልጣን የሚወጡበትና ሥልጣን ላይ የሚደርሱበት ብቸኛው ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ወዘተ ፖሊሲዎቻቸውን በነፃነት አወዳድረው በተዓማኒ ምርጫ ሒደት በሚገኝ የድምፅ ውጤት ብቻ ነው እንላለን፡፡

ይህ ዕውንና የአገርና የሕዝብ መኗኗሪያ እንዲሆን ማለትም የቡድኖች/የፓርቲዎች መንግሥታዊ ገዥነት ከነፃና ከትክክኛ ምርጫ የሚመነጭበት አዲስ ምዕራፍ ይከፈት ዘንድ፣ ቀዳሚው ሥራ እኔ እበልጣለሁ እኔ እሻላለሁ የሚሉት የተለያዩ ተፎካካሪ ቡድኖች መጀመርያ የተሻለና የሚበልጥ ነገር ለይቶ የሚያወጣውን ሚዛን በጋራ ማቋቋምና መርቀውም እነሆ ማለት አለባቸው፡፡ እየተሠራ ያለው ግን ይህ አይደለም፡፡ ይልቁንም በጅምር ላይ ያለውን ብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ የሚገኘውን የዚህ ዓይነት ሥራ የሚያጨናግፍና የሚያስፈራራ ነው፡፡

መጀመርያ የመላው የኢትዮጵያን ሕዝብ ድጋፍ ከጎንህ አለሁ ያለውና በዚህ ብቻ ሳይወሰን በኖቬል የሰላም ሽልማት ጭምር ያሸበረቀው የዓብይ አህመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣት፣ እነሆ ባለፈው ሳምንት አምስት ዓመት ሞላው፡፡ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ሰኞ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ላይ የሰማሁት ‹‹የአሜሪካ ድምፅ›› ሬዲዮ እንደ ትናንት አማራና ኦሮሚያ ክልል የሆነውን መነሻ አድርጎ፣ ‹‹በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በዓለ ሲመት የተቃውሞና የድጋፍ ሠልፎች ተደረጉ፡፡ የታዩት ተፃራሪ ትዕይንቶች እንዳሳሰባቸው ተቃዋሚዎች [ፓርቲዎች] ተናገሩ›› ብሎ (በዓብይ ዜናው) ሲነግረን ሰማሁ፡፡

ቪኦኤ አማርኛ አርባ ወይም አርባ አንድ ዓመቱ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በደርግ ጊዜ የኢትዮጵያን ሕዝባዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ፣ በኢሕአዴግ ጊዜ የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አቋቋምን ብለናል፡፡ በሁለቱም ዴሞክራሲዎችና ሪፐብሊኮች ዘመን ነፃና ያልተጭበረበረ ምርጫ እንኳን ተደርጎ አያውቅም፡፡ የአገሪቱን ሕዝቦች ልዕልና መወከል የሰመረለት ሪፐብሊክ አደራጅተናል ወይ? መንግሥታዊ ሥልጣን ከሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት ጋር ተገናኝቶ ያውቃል ወይ? ሕዝብ ተወካዮችን፣ ተወካዮች አስፈጻሚውን መግራትና መጥራት ችለዋል ወይ? የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ለ50 ዓመታት አሰናክሎና አጉድሎት የኖረውን ከፓርቲ ገለልተኛ የሆነ የመንግሥት አውታራት ግንባታ ስናሟላ (ያማላን እንደሆነ የለውጡ ዋና ቀዳሚው ተግባርም ይህ መሆኑን ምልዓተ ሕዝቡ የሚረባረብበት ከሆነ) ገና የምናቀርበው ጥያቄ ነው፡፡ እንኳን በዚያ ጊዜ ውስጥ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥም ጭምር የቪኦኤን አስፈላጊነት ከውስጥና ከእኛ በኩል እያስቀረ የመጣ እዚህ ግባ የሚባል ሚዲያዎቻችን ውስጥ የታየ ለውጥ አላስመዘገብንም፡፡ ቪኦኤ አማርኛው የዘገበውን የሠልፎች ጉዳይ ብቻውን እንኳን ብንወስድ አገር ቤት ውስጥ ‹‹አገር አለኝ›› ብሎ፣ ‹‹ኢቲቪ አለኝ›› ብሎ ዝም ብሎ የተቀመጠ ሰው መጋቢት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚሰማው በኦሮሚያ ክልል የተደረጉ የድጋፍ ሠልፎች ‹‹በሰላም መጠናቀቃቸውን›› ብቻ ነው፡፡ የተቃውሞ ሠልፍ አማራ ክልል ውስጥ ስለመኖሩ ኢቲቪም (አሚኮም ጭምር) ይናገሩ ዘንድ መብታቸው፣ ነፃነታቸው፣ እንዲያውም ‹‹ሥራቸው›› አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት አሁንም ቪኦኤ (ትግራይን ይሁን ኦሮሚኛን ጭምር) አላስፈላጊ ያደረገ የፕሬስ ነፃነት፣ የሚዲያ ግንባታ ሥራ ገና እንዳልተዋጣልን የዚህ መስክ ኋላቀርነታችን አግጥጦ እየነገረን ነው፡፡

ሥርዓት የመገንባት ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን ዝግጁ አድርጎ የማቋቋም በየአቅጣጫው ያለ ግዳጃችን ገና በጅምር ላይ ነው፡፡ በለውጡ ለመግፋትም ሆነ የአገራችንን ህልውና አሁንም ወደ ፊትም ከአደጋ አትርፎ የማስቀጠል ዋና የርብርብ መገናኛችን መንግሥት መሆኑ የማይታለፍ ዕዳ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው በመንግሥት ላይ ፊቱን ከሚያዞረው ይልቅ፣ ሕዝብ የሰጠውንና የሚሰጠውን ውድ ድጋፍና አመኔታ የመበተን አባዜና ችግር ውስጥ የገባው የመንግሥት መዝረክረክ የበለጠ አሳሳቢና አደገኛ የሚሆነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...