Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበኢትዮጵያ ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ዘረኝነት›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

በኢትዮጵያ ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ዘረኝነት›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

ቀን:

(ክፍል ሦስት)

በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ)

በክፍል ሁለት ጽሑፌ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በውስጡ ያሉትን ዋና ዋና ችግሮች ለማሻሻል ምን ያህል አዳጋች እንደሆነ በመጥቀስ፣ መፍትሔዎችን ለመጠቆምም ሞክሬያለሁ፡፡ ለእዚህ ከባድ ጥያቄ አጭር መልስ ለመስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ እኔም በቂ መልስ አለኝ ብዬ ራሴን አላሞካሽም፡፡ ሆኖም በእዚህ ቀጣይ ጽሑፌ በተለይ መዋቅራዊ በሆኑት ዋና ዋና የሕገ መንግሥቱ ችግሮች ላይ በማተኮር፣ ቢሻሻሉ መፍትሔ ይገኛል ብዬ የምገምታቸውን ሐሳቦች ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ በዋነኝነት ሕገ መንግሥቱን የማሻሻያ ወይም የመቀየሪያው ቀና መንገድ ግን የሕዝብን ፍላጎት፣ ፈቃድና አመኔታ በማገናዘብ ስኬታማ የሆነ ሁለገብ “አገራዊ ምክክር” ማድረጉ የግድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን ካልኩ በኋላ፣ በቅድሚያ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በሕገ መንግሥቱ ምክንያት ሥር የሰደደው የብሔር ፖለቲካና እሱ የወለደው ዘረኛ ሥርዓት ያስከተለውን፣ ራሱን ሕገ መንግሥቱንም ለማሻሻል ወይም ለመቀየር ትልቅ እንቅፋት የሆነውን ኋላቀር የፖለቲካ ባህል በመጠኑ ዳስሼ ለማለፍ እወዳለሁ፡፡  

የብር ፖለቲካው የወለደው “የአስተሳሰብ ድህነት የተካነው የፖለቲካ ባህል”

ከሰላሳ ዓመት በፊት በአገራችን በሕወሓትና በአጋሩ ኦነግ ተተክሎ ሥር በመስደድ እስከ ዛሬ እያደገ የቀጠለውና በብሔር ፖለቲካ ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ ባህልና የዘረኝነት ሥርዓት ከወለዱት ዋና ዋና ችግሮች አንዱ፣ በቀላሉ ሊፋቅ የማይችል “የአስተሳሰብ ድህነትን” በዜጎች፣ በተለይም በወጣቱና በታዳጊው ትውልድ አዕምሮ መቅረፁ ነው፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ወይም “የአዕምሮ ድህነት”፣ አገራችንን በኢኮኖሚ ድህነት በዓለም ከታወቁትና በዕድገት የመጨረሻዎቹ አንዷ ናት የሚል የመታወቂያ ስም ለዘመናት ካሰጣት በባሰ ነው በኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት ያስከተለው፡፡ በአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ወይም ብልፅግና ሊመጣ የሚችለው በዋነኝነት የመሪዎችና የዜጎች አስተሳሰብ በዕውቀት የዳበረና በአገራዊ ፍቅር የታነፀ ሲሆን፣ ድህነትን ከአገራችን እናጥፋ በሚል ቁጭት በጋራ ቆርጠው ሲነሱ ነው፡፡ ያንን የፖለቲካ ባህል ግን ዛሬ ዓለም በሥልጣኔ በመጠቀበት ዘመን በአገራችን ማዳበር አልቻልንም፡፡ ለእዚህም የብሔር ፖለቲካውና እሱ የወለደው ጠባብ የዘረኝነት አስተሳሰብ ዋና ምክንያቶች ናቸው፡፡   

በርካታ የሠለጠኑና በዕድገት የመጠቁ አገሮች በታሪካቸው ልክ እንደ አገራችን ኢትዮጵያ፣ አንዳንዶችም ከእኛ በባሰ ብዙ ውጣ ውረድና ፈተና፣ ረሃብ፣ የእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት እያሳለፉ ነው እዚያ ደረጃ የደረሱት፡፡ ለስኬታቸው ዋናው ሚስጥር ደግሞ እኛን እስከ ዛሬ ለመማር ያቃተን፣ አዕምሮአቸውን ክፍት አድርገው ካለፈው ታሪካቸውና ተሞክሮአቸው መማር መቻላቸው ነው፡፡ እንደ እኛ አገር ጠባብ የብሔር ፖለቲከኞች በገነኑበት፣ ባሉበት ቆመው እያደከደኩ አባቶቻቸው ባሳለፉት የፈተና ታሪካቸው ከመናቆርና ከመነታረክ ይልቅ፣ በአገራቸው የወደፊት ዕድል ላይ በማተኮር፣ ለችግሮቻቸው መፍትሔዎችን በጋራ እያፈላለጉ በማግኘታቸው ነው ዜጎቻቸውን በፍጥነት ከድህነት የጨለማ ዓለም እያወጡ፣ የተስፋ ብርሃን በመዘርጋት ማደግ የቻሉት፡፡

ለአንድ አገር ዕድገት የውስጥ ሰላምና መረጋጋት፣ አንድነትና ከአገራዊ ፍቅር የሚመነጭ ቁጭት ወሳኝ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን ከብዙ የዓለም አገሮች በፊት አገረ መንግሥት ገንብታ፣ በተለይም በአፍሪካ አኅጉር በብቸኝነትና በነፃነቷ ኮርታ፣ በውስጧም ሰላም ፈጥራና ተረጋግታ በተለይም ከ50 ዓመት በፊት በሥልጣኔ ዓለም በማዝገም ላይ እያለች፣ አርቆ አሳቢና አስተዋይ መሪዎችን በማጣቷ፣ ግፍ የበዛበት ሕዝብ በአመፅ ሲነሳ መውጫው ወደ ጠፋ የፖለቲካ ቀውስ ልታመራ ቻለች፡፡ ከዚያም የተነሳ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በተለይ ወደፊት ለመራመድና ለማደግ ተስኗት በቀውስ አዙሪት ላይ ትገኛለች፣ ዜጎቿም በረሃብ፣ በድርቅ፣ በእርስ በርስ ጦርነትና በግጭት፣ በሰቆቃና በመከራ የሚማቅቁባት ምሳሌ ሆናለች፡፡ ለእዚህ ዋና ምክንያት በተለይም የፖለቲካ “ልሂቃንና” መሪ ነን የሚሉት በአስተሳሰብ ድህነት በሽታ በመበከላቸው ነው፡፡

እርግጥ እኔ ያለፍኩበት ትውልድም ቢሆን ከእዚህ የአስተሳሰብ ድህነት ወላፈን ነፃ ነበር ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይህን ስል ግን በሺዎች የሚቆጠሩ አገራቸውን አፍቃሪ ወጣቶች ዘር፣ ብሔርና ቋንቋ አጥር ሆኖ ሳይገድባቸው ለሕዝባቸው ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት ለማምጣት በአንድነት ሲታገሉ በሕይወታቸው ሳይቀር መስዋዕትነት የከፈሉትን በመርሳት አይደለም፡፡ ሆኖም በተለይም “የብሔሮች እኩልነት” እያሉ በቅንነት የታገሉለት የተቀደሰ ዓላማ በጠባብ ብሔርተኞች ተጠልፎ፣ የሕዝብ ሰቆቃ ሊያስከትልና የአገራቸውን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ግምት አልነበራቸውም፡፡ 

የፖለቲካ አስተሳሰብ ድህነቱ ኋላቀር ባህል ሥር የሰደደውና እየባሰበት የመጣውም በተለይ ባለፉት ሰላሳ ዓመት ውስጥ ነው፡፡ አዕሞሮአቸው በጠባብ ብሔርተኛና የዘር አስተሳሰብ ተበክሎ፣ በአገርና በሕዝብ ጥላቻ ተመርዞ፣ በቂም በቀል ታጥሮ፣ የግል ፍላጎታቸውን እያሳደዱ በመንግሥት ሥልጣን ሽሚያና በአገር ሀብት ዝርፊያ በየተራ ተሰማርተው፣ አገራችን ኢትዮጵያን እንደ ሌሎች አገሮች በሰላምና በጋራ እንዳታድግ ትልቅ እንቅፋት ነው የሆኑባት፡፡ ምንም የማያልፍላት፣ መልካም ዕድሏንና የተፈጥሮ ሀብቷን፣ ግሩም ታሪኳንም ያባከነች አሳፋሪ አገር እየተባለች፣ በተለይም በአፍሪካ አኅጉር መሳቂያና መሳለቂያ እንድትሆን አድርገዋታል፡፡ በተለይም ወጣቱና ታዳጊው ትውልድ የድህነት ኃፍረቱን ለመሸፈን እንኳን ማካካሻ ቢሆነው፣ የጀግኖች አባቶቹን ግሩም ታሪክ እያስታወሰ፣ እነሱ ያወረሱትን የአፍሪካና የጥቁር ሕዝብ መኩሪያ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማውንም ከፍ አድርጎ ይዞ በኩራት ቀና ብሎ ወደፊት እንዳይጓዝ፣ እሱንም ሊያሳጡትና አንገቱን አስደፍተው እንደ እነሱ ህሊና ቢስ፣ ጠባብና ዘረኛ እንዲሆን፣ በአስተሳሰቡ መቶ ዓመት ወደኋላ እንዲሄድ አድርገውታል፡፡ ይህ ነው ዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል!

ጠባብ የብሔር ፖለቲከኞች ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በራሳቸውና በትውልዱ ላይ የተከሉት የአስተሳሰብ ድህነት የጀመረውም የኢትዮጵያን ታሪክ ሆነ ብለው በመበረዝ ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያዊ (አገራዊ) ማንነቱን እንዲስትና በጠባብ አዕምሮው በዘሩ፣ በብሔሩ፣ በመንደሩና በጎጡ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ብዙ ነው የሠሩት፡፡ ካለፈው የአገራችን ታሪክ በቅንነት መማርና አገሪቱን ማሳደግ ሲያቅታቸው፣ የሆነ ያልሆነ ሰበብ እየፈጠሩ፣ ሕዝቡን ከፋፍሎ ለመግዛትና እንደ እነሱ ለማደንቆር እውነተኛውን ታሪክ ለመበረዝ በሐሰት ትርክት መተካትን መረጡ፡፡ ስንትና ስንት መስዋዕትነት ከፍለው ምን የመሰለች አገር ያወረሱንን አባቶቻችንና እናቶቻችንን እንደ ጠላት እያዩ በማውገዝ፣ አገራዊ ግዴታቸውን ፈጽመው ታሪክን ለመማሪያ ያወረሷቸው ሳይሆን፣ የጣሉባቸው ትልቅ “ዕዳ” ወይም ሸክም እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል፡፡ የእዚያ ዓይነት አመለካከት ራሱ የአስተሳሰብ ድህነት አንዱ ምንጭ ነው፡፡ አቅም ማጣትንና ደካማነትን  ያመላክታል፡፡

ታሪክ የአገር ዕዳ ወይም ሸክም ሆኖ አያውቅም፡፡ ላወቀበት መማሪያና የዕውቀት ምንጭ እንጂ! ታሪክን “ዕዳ” ነው ብሎ ማሰብ ራሱ በተለይም ለአዲሱ ትውልድ መጥፎ ትምህርትን ይሰጣል፡፡ አዕምሮውን ክፍት አድርጎ፣ አገራችን ዛሬ ላጋጠሟት ውስብስብ ችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግ ኃላፊነት እንዲሰማውና በራሱ አነሳሽነት እንዲበረታ ማነቃቃት ትቶ፣ ያለፈውን ትውልድ (ዕዳ ያሸከመውን) በሰበብ አስባቡ እየረገመ፣ ህሊናውን ዘግቶ በቂምና በቀል ኑሮውን እያማረረ፣ ተስፋ በመቁረጥ በመጥፎ ባህል ተውጦ መውጫው ጠፍቶት እንዲዳክር ያደርገዋል፡፡ ሲጨንቀው ‹‹ይህን ሁሉ ዕዳ ያሸከመን ያለፈው የ60 ዎቹ ትውልድ ነው›› ወይም “ምኒልክ ነው” እያለ በማማረር፣ ጊዜውን በስንፍና፣ ተስፋ በመቁረጥና በጨለምተኝነት እንዲያሳልፍ አድርገውታል፡፡ እሱ ራሱ ታሪክ ሠሪ መሆኑን ረስቶ አገሩን እንዲጠላና ሕይወቱን ለመቀየር ከመጣር ይልቅ፣ እየጣላት ወደ ባዕድ አገር መሰደድን እንዲመርጥ ይገፉታል፡፡ 

 ይህ ሁሉ ሲሆን የጠባብ ብሔር ፖለቲከኞች ግን በሌብነትና ዝርፊያ ላይ ተሠማርተው ምስኪኑን ደሃ ሕዝብ እያራቆቱና እያፈናቀሉ የአገሪቱን መሬትና ሀብት በቃን ሳይሉ ያግበሰብሳሉ፡፡ ያ አልበቃ ብሏቸው ሕዝቡን እያስጨፈጨፉና እርስ በርስ እያጋጩ ሰላም፣ ፍቅርና ውበት የሰፈነባት የነበረች አገራችንን ወደ ሲኦልነት ቀይረዋታል፡፡ በእዚህ ዓይነት ለማደግ ስንት ተስፋ የነበራትን፣ ከሁሉም ቀድማ በፊት ልትሆን ትችል የነበረች ስመ ጥር አገር ኢትዮጵያችን በኢኮኖሚ ማደጓስ ቀርቶ፣ በሥነ ልቦና በባህልና አስተሳሰብ፣ ቢያንስ መቶ ዓመት ወደኋላ ሄዳለች፡፡ እንባዋን አብሶ፣ ፊቷን አድሶ ለመመለስና ትክክለኛውን የዕድገት አቅጣጫ ለማስያዝ ገና ብዙ ትግል ይጠይቃል፡፡   

  1. የብር ፖለቲካ ዘረኝነትና ኋላቀሩ አስተሳሰብ በማበራዊ ኑሮ ላይ ያስከተለው ከፍተኛ ጉዳት

ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ አርስቶትል፣ ‹‹የሰው ልጅ በተፈጥሮው የፖለቲካ እንስሳ›› (“Man by Nature is a Political Animal”) ነው አለ ይባላል፡፡ በርካታ የፍልስፍና አዋቂዎች ይህን አባባሉን ሲተረጉሙት አርስቶትል የሰው ልጅ ያለ ማኅበራዊ ኑሮ ብቻውን ሊኖር አይችልም፡፡ ወደ ፖለቲካ የሚገባውና መንግሥት የሚመሠርትበት ዋና ምክንያትም በጋራ ተስማምቶ በሰላም ለመኖር ሲል ነው፡፡ ያንን ማድረግ ካልቻለ ግን ከእንስሳ ወይም ከአውሬ ምንም ያህል አይሻልም፣ እርስ በርሱም ሊጨራረስ ይችላል ማለቱ ነው ይላሉ፡፡ የሚያሳዝነው አገራችን በተለይም ባለፉት 50 ዓመታት በመጥፎ የፖለቲካ ባህላችን ምክንያት ያጋጠማት ችግር ከእዚያ አርስቶትል ጥንት ከሰጋበት ‹‹የሰው ልጅ ጥሩ የፖለቲካ ባህልና ማኅበራዊ ኑሮ ካጣ፣ ወደ አውሬነት ይቀየራል፤›› ካለው ምንም ያህል አይርቅም፡፡ ጠባብ የብሔር ፖለቲከኞች የኅብረተሰቡን የዘመናት መልካም እሴቶች እያጠፉ፣ ሀቅን በውሸት፣ ሥራን በቅጥፈት፣ ርህራሔን በጭካኔ፣ ማኅበራዊ ኑሮን በግለኝነት እንዲተኩ አድርገው ውጥንቅጡን አውጥተውታል፡፡

ለአገር ጥሩ ባህልና ሞራል ግንባታ ዋልታ የነበሩትን የሃይማኖት ተቋማት ሳይቀር በክለዋቸዋል፡፡ በአገራችን ፍቅርና ሰላም ሳይሆን፣ ቂምና በቀል፣ ጥላቻና ጥርጣሬ እየተስፋፋ ማኅበራዊ ኑሮም እየጠፋ፣ እሱም እንደ ፖለቲካ ባህሉ ሴራና መበላላት የሰፈነበት ከሆነ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የብሔር ፖለቲካ ባለፉት 30 ዓመታት የተከለው የዘረኝነት ሥርዓት፣ አገራችን ለዘመናት ያዘለቀቻቸውን ግሩም የሆኑ ማኅበራዊ ግንኙነታችን፣ አብሮ የመኖርና የአገራዊ ፍቅራችንን እሴቶች እያከሰመ፣ በሕዝቡ መሀል መከፋፈልንና እርስ በርስ መበላላትን እያጠናከረ፣ ኅብረተሰቡን ከሰው ልጅነት ወደክፉ አውሬነት እንዳወረደው ምንም አያጠራጥርም፡፡

አንዳንድ የዱር አውሬስ ከእኛ በተሻለ ሰላማዊ ማኅበራዊ ኑሮ ይኖራል፡፡ የሚያሳዝነው በእዚህ መርዘኛና ኋላ ቀር የብሔር ፖለቲካ ዘረኛ ሥርዓት ከባዱን ዋጋ እየከፈለ ያለው፣ ምንም ፖለቲካ የማያውቀው ምስኪኑ ሕዝብ ነው፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ትልቁን ድርሻ እየከፈለ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሕወሓት በቆሰቆሰው ጦርነት በትግራይ ብቻ እንኳን በወጣቱ ላይ የደረሰውን ዕልቂት ለመገመት ያዳግታል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ለማፋጀት በሚል እርኩስ ዓላማ ቀልቡን ወርሰው፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ዘምቶ የገዛ ወንድሞቹንና እህቶቹን፣ ሕፃናትን፣ ልጃገረዶችን፣ አሮጊቶችን፣ እናቶችንና አባቶችን ሳይቀር በአሰቃቂ ሁኔታ እንደ ክፉ አውሬ የበላቸውና እሱም በጦርነት የተበላው በእዚህ ጠባብ የብሔርና ዘረኝነት ፕሮፓጋንዳ ህሊናውን መርዘው አውሬ ስላደረጉት ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ ዙሪያ በወለጋ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአጣዬ፣ በጉጂ፣ በጋምቤላና በሌሎችም አካባቢዎች የደረሰው አስከፊ የሕዝብ ጭፍጨፋም ይኸው የጠባብና ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲካ የዘራው፣ አዕምሮን የሚበክል የዘረኝነት መርዝ ውጤት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

የጠባብ ብሔር ፖለቲካ አስተሳሰብ ዋናው ጉዳቱ ደግሞ ለአገር ግንባታ ትልቅ ፀር መሆኑ ነው፡፡ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ለእዚህ መርዘኛ አስተሳሰብ በአገራችን በቅሎ ማቆጥቆጥና ማደግ በዋነኝነት ሕወሓትና ኦነግ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ እነሱ በጋራ የተከሉት ሕገ መንግሥት ነው በአገራችን የግንባታ ጉዞ ላይ ትልቅ ጋሬጣ የተከለው፡፡ ሌላው ቢቀር “ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” በፈለጉበት ጊዜ ‹‹የመገንጠልንና ክልል የመመሥረትን›› መብት ያለ ገደብ በሕገ መንግሥቱ አንቀጾች (39 እና 47) የሰጧቸውን ብቻ መመልከቱ በቂ ነው፡፡ አገር በጋራ ለመገንባት የሚመኝ መንግሥት ይህን አያደርግም፡፡ የአንድ አገር ሕዝብ ቋንቋውን፣ ባህሉንና ታሪኩን በእኩል የመንከባከብና የማሳደግ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ድህነትን ለማጥፋትና ለማደግ ግን በጋራ ካልታገለ የትም አይደርስም፡፡ ሕዝብን በክልልና በብሔር በቋንቋ በማለያየት፣ በቂምና በቀል፣ በድንበርና በሀብት ዝርፊያ እርስ በርስ በማጋጨት፣ በጠባብ አዕምሮ የሌላውን ባህልና ቋንቋ በማስጠላትና የአገርን የጋራ ታሪክ በማፈራረስ፣ ሲፈልጉም ለመገንጠል በቋፍ ላይ ቆሞ በማሰላሰል አገር በአንድ ልብ ለመገንባትና ለማበልፀግ ምንም ጊዜ ቢሆን አይቻልም፡፡ የህልም ሩጫ ነው፡፡

በእዚህ ረገድ አገራችንን በተለይ ባለፉት ዓመታት በብዙ ዕርቀት ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ ያስቀራት የብሔር ፖለቲካው እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም፡፡ የሚያሳዝነው በተከታታይ የሚመጡት የአገር መሪዎች፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በእዚህ የብሔር ፖለቲካ በመመረዛቸው፣ ይህን ሀቅ በሚገባ ለመረዳት አለመቻላቸው ነው፡፡ እስከ ዛሬ መፍትሔ ሊገኝለት ያልቻለውና አገራችንን ለዕድገቷ ብቻ ሳይሆን፣ ለህልውናዋም ፀር የሆነው ዋናው ኋላ ቀሩ ሕገ መንግሥት እንደሆነም አምነው መቀበል ያዳግታቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብዝኃነት መገለጫ የሆነችና ከ80 በላይ “ብሔር ብሔረሰቦች” የተለያየ ባህልና ቋንቋ ቢኖራቸውም፣ እንደ ዛሬው በብሔር ፖለቲከኞች ዘረኛ አጥር ሳይራራቁ፣ ለዘመናት ተከባብረውና ተፋቅረው፣ ተጋብተውና ተዋልደው በሰላም የኖሩባት የምታስቀና አገር እንደነበረች ዓለም ይመሰክርላታል፡፡ አልፎ አልፎ እንደ ቤተሰብ የእርስ በርስ ግጭት በመሀላቸው ቢፈጠርና የዕድገት እንከኖች ቢኖርባትም እንኳን፣ ሕዝቦቿ ይህንን ግሩም እሴታቸውን ለዘመናት ጨርሰው አልተውም ነበር፡፡

በዚህ ግሩም የአገር ቅርስና እሴት ላይ በመገንባት፣ የተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦችን ታሪክ፣ ቋንቋና ባህል እኩል ትኩረት እየሰጡ በማዳበር፣ የጋራ አገራቸውን ኢትዮጵያን በማፍቀር በአንድነት እንዲያድጉና እንዲበለፅጉ፣ ሚዛናዊና ዘመናዊ የሆነ ኅብረ ብሔራዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ሲገባ፣ በመከፋፈልና በመለያየት ተጠምደው አገራችንን ከሁሉም ወደኋላ በማስቀረት ለዜጎቿም ሰቆቃ እንድትሆን አደረጓት፡፡ ስለዚህ ዛሬ ዋናው አንገብጋቢ ጥያቄ እንዴት አድርጎ ነው ይህን ሥር የሰደደ በጠባብ ብሔር አስተሳሰብ ላይ የቆመ የዘረኝነት ሥርዓትና ኋላቀር የፖለቲካ ባህል መቀየርና አገራችንን ትክክለኛ አቅጣጫ ማስያዝ የሚቻለው የሚለው ነው፡፡ በእኔ ዕምነት ለእዚህ ዋና መፍትሔ፣ ከፋፋዩንና ኋላቀሩን የዘረኝነት ሥርዓት ሥር እንዲሰድ በማድረግ ቀጥ አድርጎ ያቆመውን ሕገ መንግሥት ማሻሻሉ ወይም መቀየሩ ምንም አማራጭ የለውም፡፡

  1. በብር ፖለቲካ የቆመው የኢትዮጵያ መንግሥት እንዴት ቢሻሻል ይሻላል?

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን ለማሻሻልም ሆነ ለመቀየር በአንደኛ ደረጃ ሕገ መንግሥቱ በ1987 ዓ.ም. ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ (ለ29 ዓመት ያህል) ያጋጠሙትን ትልልቅ ፈተናዎችን በመመርመርና የሌሎችን አገሮች ተሞክሮንም በማገናዘብ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረቱና ለአገራችን ይበጃሉ የሚባሉ ሐሳቦችን ለምክክር ለሕዝብ በማቅረብ ውሳኔ ላይ ለመድረስ መጣር ያስፈልጋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በመሠረቱ በርካታ ችግሮች ያሉት ይመስለኛል፡፡ ሁሉንም እዚህ ላይ ለመዘርዘር ቦታ አይበቃኝም፣ በቂ ሙያና አቅሙም የለኝም፡፡ ይሁን እንጂ የሕገ መንግሥቱ አንዱ ዋነኛ ችግር፣ በሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች ማለትም በሕግ አውጭው፣ ሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው መሀል ያሉት ኃላፊነቶችና የሥልጣን እርከኖች፣ ወይም የሥልጣን ክፍፍሉ (Separation of Powers) በሚገባ አለመገለጻቸውና መደብዘዛቸው፣ በመሀላቸውም በቂ ቁጥጥርና ሚዛናዊ አስተዳደር (Check and Balance) አለመኖሩ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡           

በእዚህ ረገድ ከየትም አገር በተሻለ ከአሜሪካ መንግሥት አወቃቀር ትልቅ ትምህርት ለማግኘት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ ከ230 ዓመታት በላይ በማስቆጠር ፀንቶ፣ ለረዥም ዕድሜ የቆየው የአሜሪካ ፌዴራል ሥርዓት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በርካታ የፖለቲካ ሊቃውንት እንደሚሉትም፣ ይህን ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ ሥርዓት ስኬታማ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱት ባህሪዎቹ በዋነኝነት፣ የሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች (ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ) ኃላፊነቶችና ሥልጣኖቻቸው በሕገ መንግሥቱ በሚገባ መለየታቸውና በመሀላቸውም የእርስ በርስ ቁጥጥሩና ሚዛናዊ አስተዳደሩ በሚገርም ሁኔታ በጥንቃቄ የታነፀ መሆኑ ሁልጊዜ ይጠቀሳል፡፡ እነዚህ ሦስት የመንግሥት ቅርንጫፎች፣ ምንም እንኳን የተለያየ ሥልጣን ቢኖራቸውና በመሀላቸው ቁጥጥር ቢኖርም፣ በአንፃሩ ሦስቱም እርስ በርሳቸው እንዲደጋገፉና በጋራ (በቲም) እንዲሠሩ ሆነው ነው በሕገ መንግሥቱ የተዋቀሩት፡፡ ይህ የመንግሥት አወቃቀር፣ አገሪቱ በየጊዜው ሊያጋጥሟት የሚችሉትን ፈተናዎች እየተቋቋመች በአንድነቷ ፀንታ እንድትቀጥል እየረዳ በስኬት በማሳለፍ፣ ሕገ መንግሥቱንም ትውልድና ታሪክ ተሻጋሪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

የአሜሪካን ሕገ መንግሥት ያነፁት የመጀመርያዎቹ አባቶች (“The Founders”) ብዙ ተጨንቀውና በሐሳብ ተፋጭተው ነው ይህን የመሰለ ጠንካራ የመንግሥት መዋቅር ሊዘረጉ የቻሉት፡፡ ይህም የሚያሳየው ለራሳቸው ሳይሆን፣ ምን ያህል ለመጭው ትውልድና ለአገራቸው ዜጎች መብትና ነፃነት የሚጨነቁ፣ የሚቆረቆሩና አርቆ አሳቢ እንደ ነበሩ ነው፡፡ ለዚህ የሕገ መንግሥቱና የፌዴሬሽኑ ከ230 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ረዥም ዕድሜ ራሱ በቂ ምስክር ነው፡፡ እርግጥ በእዚህ ረዥም ዕድሜው መሠረቱን ሳይለቅ 27 ጊዜ ማሻሻያ (Amendment) ተደርጎለታል፡፡

ይህንን ዕድሜ ጠገብና የረቀቀ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ለመረዳት ቢያግዝ በሚል አንድ ምሳሌ እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ፡፡ የሕግ አውጭው አካል (Congress) በሕዝብ በቀጥታ የሚመረጡ አባላት ያሉበት ሁለት ምክር ቤቶች አሉት፡፡ እነዚህም የሕዝብ ተወካዮችና የሕግ መወሰኛ (“ሴኔት”) ምክር ቤት ይባላሉ፡፡ አንድ ሕግ (Bill) ሲረቀቅ፣ ሁለቱም ምክር ቤቶች በየግላቸው መድረክ ተወያይተውና ተመካክረው፣ ልዩነቶቻቸውን ካጠበቡና በስምምነት ካፀደቁት በኋላ፣ ቀጥሎ ወደ አገሪቱ ከፍተኛው ሕግ አስፈጻሚ አካል ማለትም ወደ ፕሬዚዳንቱ እንዲፀድቅ ይልኩታል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከተስማማበት ያፀድቅና ይፈርምበታል፣ ከዚያም የአገሪቱ ሕግ ይሆናል፡፡

ካልተስማማበት ግን ከፈለገ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣኑ (Veto Power) ይሽርና ረቂቁን ወደ ምክር ቤቱ (Congress) ይመልሰዋል፡፡ ከእዚያ በኋላ ምክር ቤቱ ከፈለገ የፕሬዚዳንቱን ሥጋት ለማቃለል ሕጉን ያሻሽልና እንዲያፀድቀው እንደ ገና ወደ ፕሬዚዳንቱ መልሶ ይልከዋል፡፡ ካልሆነ ግን የፕሬዚዳንቱን ሐሳብ በመቀበል ሕጉን ማሻሻል ካልፈለገ፣ እሱም በሕገ መንግሥቱ ደንብ መሠረት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቱን ተጠቅሞ 2/3ኛ ድምፅ ካገኘ ሊያሳልፈው ይችላል፡፡ ያ ከሆነ ፕሬዚዳንቱ  ሕጉን አልቀበልም ሊል አይችልም፣ ረቂቁም የአገሪቱ ሕግ ይሆናል፡፡ 2/3ኛ ድምፅ ካላገኘ ግን ፕሬዚዳንቱ እንደሻረው ይቀራል፡፡

ሁለቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች ተስማምተውበት የአገሪቱ ሕግ ከሆነ በኋላ፣ ቀጥሎ ሦስተኛው የመንግሥት ቅርንጫፍ፣ ማለትም የአገሪቱ ፌዴራል ፍርድ ቤትም ሕጉን በመመርመር ካልመሰለው ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት ዕድል አለው፡፡ ፍርድ ቤቱ ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት ሥልጣን፣ አንድ የሆነ የመንግሥት አካል (ለምሳሌ ከሕግ አስፈጻሚው) ወይም የዜጎች መብት ጠባቂ የሆነ የሲቪክ ማኅበር፣ ይህ አዲስ ሕግ ሕገ መንግሥቱን ይፃረራል ካለና በፌዴራል ፍርድ ቤት ክስ ከመሠረተበት ብቻ ነው፡፡

ክሱም ካስፈለገ በይግባኝ እስከ ከፍተኛው የአገሪቱ ፍርድ ቤት (Supreme Court) ድረስ ሊሄድ ይችላል፡፡ ይህ አካል ያሳለፈውን ሕግ ማንም ሊሽርው አይችልም፡፡ የእዚህ ሦስተኛው የመንግሥት ቅርንጫፍ፣ የፍርድ ቤቱ ኃላፊነት በዋነኝነት በአገሪቱ የሚወጡት ሕጎች ሕገ መንግሥቱን የሚፃረሩ እንዳይሆኑ ነቅቶ መጠበቅ ነው፡፡ ዜጎችም ይህን ስለሚያውቁ ማናቸውም በአገሪቱ የሚወጣ ወይም የሚጣስ ሕግ፣ ሕገ መንግሥቱን ወይም የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚፃረር ከመሰላቸው በጠበቆቻቸው አማካይነት በፍርድ ቤት የመክሰስ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡

በእዚህ ዓይነት ሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን ሥልጣን በሚገባና በትክክል በመጠቀም፣ እርስ በርሳቸውም በቂ ቁጥጥር በማድረግና ተደጋግፎ በመሥራት፣ በሕገ መንግሥቱ የተጻፉትን የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ፣ ፍትሕ የሰፈነበት የፌዴራል ዴሞክራቲክ ሥርዓት በአገራቸው እንዲያድግ ተግተው ይሠራሉ፡፡ በነገራችን ላይ በክልሎች (States) ወይም ክልሎችና የፌዴራል መንግሥቱ መሀል ችግር ካለም፣ ፍርድ ቤቱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ክሱን የማየትና በጉዳዩ የመወሰን መብት አለው፡፡

በዚህ ዓይነት አገሪቱ በየጊዜው ያልጠበቀችው ትልቅ የውስጥ ወይም የፖለቲካ ቀውስና ፈተና ሲያጋጥማትም፣ ሕገ መንግሥቱን በመመርኮዝና መፍትሔ በመፈለግ፣ ችግሩን በመፍታት ለበርካታ ጊዜያት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በማድረግ ስኬታማ ውጤትን ለማግኘት ችላለች፡፡ ለምሳሌ ፕሬዚዳንት ኒክሰን ትልቅ ጥፋት ስላጠፋ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከኃላፊነቱ እንዲለቅ ተገዷል፡፡ ፕሬዚዳንት ክሊንተንም በሥልጣን ላይ እያለ የሥነ ምግባር ጉድለት በማሳየቱ በሕግ አውጭው አካል ተከሶ፣ በሕጉ መሠረት ክሱ (Impeachment) በሴኔት ታይቶ በድምፅ ብልጫ በነፃ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ዛሬ  ደግሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ትልቅ ጥፋት አጥፍተሃል ተብሎ በፌዴራል ፍርድ ቤት ተከሶ ጉዳዩ እየታየ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር ማለት እንዲህ ነው፡፡                                             

እንግዲህ ይህን ከላይ ያቀረብኩትን የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ተሞክሮ እንደ ትምህርት ለመውሰድ ብንሞክር፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትስ ችግሮቹን ለመፍታት በተለይም በሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች መሀል በቂና ግልጽ የሆነ የሥልጣን ክፍፍል፣ ቁጥጥርና ሚዛናዊ የሆነ አወቃቀር አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጥያቄ መርምሮ ለመመለስ የሚረዳ ይመስለኛል፡፡ በበኩሌ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎቹ መሀል በቂና ግልጽ የሆነ የሥልጣን ክፍፍል፣ የቁጥጥርና ሚዛናዊ አስተዳደር አለው ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ከተፈለገ ይህን አብሮ ማየቱ መልካም ነው የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ አንዱም በአገሪቱ ብዙ ችግር እየፈጠረ ያለው እሱ ይመስለኛል፡፡

በተለይም በሕግ አስፈጻሚው ገደብ የለሽ ሥልጣንና በሁለቱ ማለትም ሕግ አውጭውና ሕግ ተርጓሚው ደካማነት፣ ወይም በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ሥልጣን፣ ኃላፊነትና ግዴታቸውን በሚገባ ባለመጠቀማቸው የተነሳ፣ በሕገ መንግሥቱ የተጻፉት የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩና እየተረገጡ ነው፡፡ ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ ሥርዓት ሊገነባ ቀርቶ፣ አገራችን ጭራሽ ዛሬም ዕድል ብሎላት ወደ ተላመደችው የአምባገነንነት ሥርዓት ተመልሳ ለመግባት በፍጥነት ወደኋላ እየሄደች ያለች ይመስለኛል፡፡

ዛሬ ያለውን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የመዋቅር ችግር ለማሳየት፣ ለምሳሌ ያህል ጥቂቶቹን እንድገልጽ ይፈቀድልኝ፡፡ በአንቀጽ 72 (ቁ 2) ሕገ መንግሥቱ፣ “ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪዎች ናቸው ይላል፡፡ እንዲሁም በአንቀጽ 53 (ቁ 4) ‹‹የምክር ቤቱ አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው፣ ተገዥነታቸውም ሀ. ለሕገ መንግሥቱ ለ. ለሕዝቡ ሐ. ለህሊናቸው ብቻ ይሆናል፤›› ይላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህን ይበል እንጂ በተግባር እንደሚታየው ግን፣ የምክር ቤቱ አባላት አንዳንዴ ተገዥነታቸው (ተጠሪነታቸው) ለሕገ መንግሥቱና ለሕዝቡ ሳይሆን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይመስላል፡፡ ለእዚህ በርካታ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል፣ ቦታ ስለማይበቃን ግን በቅርቡ የሆነ አንድ አስገራሚ ክስተት ብቻ ልጥቀስ፡፡

ምክር ቤቱ ከዓመት በፊት ሕወሓትን “አሸባሪ” ነው ብሎ ወስኖ እንደነበር ሁላችንም እናስታውሳለን፡፡ ይሁን እንጂ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ (ለፓርላማውና ለሕዝብ በሚገባ ያልተብራራው) ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማውን አፈ ጉባዔ የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውን መርተው መቀሌ እንዲሄዱና “የአሸባሪውን” የሕወሓት ቡድን መሪዎች እንዲያነጋግሩ አዘዟቸው፡፡ አፈ ጉባዔውም በምክር ቤታቸው ያስወሰኑትን ውሳኔ ወደጎን ትተው፣ ምንም ሳይሳቀቁ መቀሌ ሚኒስትሮችን እየመሩ ሄደው ገና ስያሜው በፓርላማ ካልተሻረለት “ከሽብርተኛው ሕወሓት” መሪዎች ጋር አንገት ለአንገት እየተቃቀፉ፣ ፊታቸው በፈገግታ ፈክቶ፣ ናፍቆታቸውን ሲወጡና ሲወያዩ ውለው ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት አቀረቡ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ጉዱን በመገረም ተመለከተ፡፡ አፈ ጉባዔውን ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩን “ነውር ነው፣ ተው” ያላቸው ወይም የጠየቃቸው አካል ማንም አልነበረም፡፡ ሕዝቡም ምንም አቅም ስለሌለው በዝምታ በመገረምና በኃፍረት አለፈው፡፡

ያስ ይሁን እሺ፣ ምናልባት ቀላል ነው ሊባልና በመገረም ሊታለፍ ይችላል፡፡ ከእዚያ በባሰ የሚያሳዝነው የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሕዝብ የተመረጡ ሆነው እያለ፣ የሕግ አውጭው የፀጥታና የደኅንነት አካላት በሕዝብ ላይ ብዙ ግፍ ሲሠሩና መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት መጠበቅ አቅቶት ምስኪኑ ሕዝብ ሲጨፈጨፍና ሲፈናቀል እያዩ፣ ለዓመታት ምንም ስቅጥጥ ሳይላቸው መቅረቱ ያሳዝናል፡፡ ለምሳሌ በወለጋ በተደጋጋሚ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎች ሲታረዱና ከቀዬአቸው ሲፈናቀሉ፣ ሌላው ቀርቶ በፓርላማ ስብሰባ ላይ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ይደረግ ተብሎ ሲጠየቁ እንኳን አልፈቀዱም፡፡ ለሕዝቡስ ይቅር እሺ ሕገ መንግሥቱ እንደሚለው ምኑ ላይ ነው ታዲያ “ለህሊናቸው ተገዥ” የሆኑት? ይህን ጉድ እየታዘበ በማዘን፣ የመረጣቸውና ሥልጣን የሰጣቸው ሕዝብ ቢያንስ በሆዱ “ህሊና የላቸውም” ቢላቸው ምንም አያስገርምም፡፡ እሺ ያም ይቅር በዙሪያቸው በአዲስ አበባ ዜጎች በዘራቸው እየተመረጡ ቤታቸው በላያቸው ላይ እየፈረሰባቸው በረሃ ሲጣሉ፣ ለአውሬ ሲዳረጉ፣ ሲደበደቡና ሲገደሉ እነሱም ሆነ የአዲስ አበባ ምክር ቤት፣ የፍትሕ ሥርዓቱም ምንም ደንታ አልሰጣቸውም፡፡ ለጊዜውም ቢሆን የመንግሥትን ሰብዓዊ መብት ጥሰት አስቁሞ ሁኔታውን መመርመር አልፈለጉም፡፡ የሕግ አስፈጻሚው አካልም ተው የሚለው ስለሌለ ግፍ መፈጸሙን ቀጥሏል፡፡  

 በአንቀጽ 55 ተራ ቁጥር 16 ሕገ መንግሥቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹በማንኛውም ክልል ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማስቆም ሳይችል ሲቀር፣ በራሱ አነሳሽነትና ያለ ክልሉ ፈቃድ ተገቢውን ዕርምጃ እንዲወስድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ጥያቄ ያቀርባል፣ በተደረሰበት ውሳኔ መሠረትም ለክልሉ ምክር ቤት ውሳኔ ይሰጣል፤›› ይላል፡፡ እኔ እንደሚገባኝ ከሆነ ምክር ቤቱ ይህን ኃላፊነቱንም እስከ ዛሬ አልተወጣም፡፡ በተጨማሪ በእዚህ አንቀጽ (55) ቁጥር 18 ላይ ሕገ መንግሥቱ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ለሕግ አስፈጻሚው አካል በተሰጠ ማንኛውም ሥልጣን ላይ የምክር ቤቱ አባላት በ1/3ኛ ድምፅ ሲጠየቁ ምክር ቤቱ ይወያያል፣ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ የመመካከርና አስፈላጊ መስሎ የታየውን ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አለው፤›› ይላል እርግጥ ምን ዓይነት “ዕርምጃ” ነው የሚወስደው የሚለው ባይብራራም፣ ምክር ቤቱ ግን ይህን ሥልጣኑንም እስከ ዛሬ አልተጠቀመበትም፡፡ ይህም ለአስፈጻሚ አካሉ ሕገ መንግሥቱን ያለ ገደብ መጣሱንና በሕዝብ ላይ ግፍ መሥራቱን እንዲቀጥልበት የልብ ልብ የሰጠው ይመስላል፡፡

በነገራችን ላይ በአንቀጽ 50 ተራ ቁጥር 3 ‹‹የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፣ ተጠሪነቱም ለአገሪቱ ሕዝብ ነው፤›› ይላል ሕገ መንግሥቱ፡፡ ምስኪኑ ሕዝብ ፈርዶበት በምን ሥልጣኑ ነው ምክር ቤቱን ሊቆጣጠረው የሚችለው? አምስት ዓመት ቆይቶ በምርጫ? ወይስ በሦስተኛው ከፍትሕ ሥርዓቱ መዋቅር ጋር በተገናኘው ሌላ የመንግሥት ቅርንጫፍ በ“ፌዴራል ምክር ቤቱ”? በእሱማ እንዳይቆጣጠረው አይችልም፡፡

የፌዴራል ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ የተወካዮች ምክር ቤትንም ሆነ ሕግ አስፈጻሚውን አካል የመቆጣጠር ሥልጣን አልተሰጠውም፡፡ አባላቱ የሚመረጡትም በሕዝቡ ሳይሆን በክልል ምክር ቤቶች ነው፡፡ እርግጥ ‹‹የክልሉ ምክር ቤት ከፈለገ በሕዝብ ሊያስመርጣቸው፤›› ይችላል ይላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ፣ (ከፈለገ!) እስኪ እግዜር ያሳያችሁ አሁን እውነት እንደዚህ የብሔር ፖለቲካ አምባገነንነት በገነነበት አገር፣ የክልል ምክር ቤቱ የፌዴራል ምክር ቤቱን ተወካዮች በሕዝብ የሚያስመርጥ ይመስላችኋል? ከዚያስ ይልቅ ምናለበት የፌዴራል ምክር ቤቱ ወኪሎች በቀጥታ በሕዝብ ይመረጣሉ ቢል ኖሮ ሕገ መንግሥቱ፣ እሱ ትንሽ ይሻል ነበር፡፡

በነገራችን ላይ የክልሎች ሕገ መንግሥት ደግሞ ራሱን የቻለ ሌላ የአገሪቱ አንድነት ጠንቅ ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም፡፡ እሱን እዚህ ላይ ለመዘርዘር ያዳግታል፡፡ ሌላው የሚገርመው፣ የተወካዮች ምክር ቤት የሚያወጣውን ሕግ ለቁጥጥር እንዲያመች የሚመረምርና ድምፅ የሚሰጥበት ሌላ የመንግሥት አካል አለመኖሩ ነው፡፡ የፌዴራል ምክር ቤቱም አይችልም፡፡ ረቂቁ በተወካዮች ምክር ቤት በድምፅ ብልጫ ከፀደቀ በኋላ በቀጥታ ለፕሬዚዳንቱ ለፊርማ ይላክና ከእዚያ በኋላ የአገሪቱ ሕግ ይሆናል፡፡ ሁለቱ ምክር ቤቶች በጣምራ የሚሠሩትም ኃላፊነት በሚገባ አልተብራራም፡፡ 

ይህን ብለን እስኪ አሁን ደግሞ ወደ ሦስተኛው የመንግሥት ቅርንጫፍ ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ ትኩረት እናድርግ፡፡ ይህማ በእኔ እምነት ጭራሽ የተጠላለፈና የተወሳሰበ፣ ለመረዳትም የሚያስቸግር ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የፍትሕ ሥርዓቱን ከሚያስከብሩት ከላይ የተጠቀሰው የመንግሥት ቅርንጫፍ የፌዴራል ምክር ቤቱ አንዱ ሲሆን፣ በዋነኝነት ግን ዳኞች ናቸው፡፡ ዳኞች በፌዴራልና በክልል ደረጃ የተዋቀሩ ሲሆኑ፣ ‹‹የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የበላይና የመጨረሻ ዳኝነት ሥልጣን ይኖረዋል፤›› ይላል ሕገ መንግሥቱ (አንቀጽ 80 ቁ 1)። ይሁን እንጂ የፌዴራል ምክር ቤቱ ደግሞ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን አለው ይላል (አንቀጽ 62 ቁ 1)፡፡ የሕገ መንግሥታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሳም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ያገኛል ይላል ሕገ መንግሥቱ (አንቀጽ 83 ቁ 1)። እዚህ ላይ በሁለቱ አካላት መሀል (በፌዴራል ምክር ቤቱና በዳኞች ወይም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሀል) የኃላፊነት “ግጭት” አያስነሳም ወይ የሚል ጥያቄ ቢያስነሳ ምንም አያስገርምም፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፣ ለፌዴራል ምክር ቤቱ ተጠሪ የሆነ (ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሳይሆን) ሌላ ተጨማሪ ወይም ደጋፊ ሥልጣን ያለው አካልም አለ፡፡ ይህ አካል ‹‹የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ›› ይባላል፡፡ ችግሩ የፌዴራል ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥቱን በሚመለከት ጉዳይ ውሳኔ የሚሰጠው፣ በቅድሚያ በዚህ በሥሩ ባለው አካል ተጣርቶ ከቀረበለት በኋላ ነው (አንቀጽ 84 ይመልከቱ)፡፡ ይህ “ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ” ከፈለገ ጉዳዩን (ክሱን) መርምሮ “ሕገ መንግሥትን አይመለከትም” ብሎ ወደ ፌዴራል ምክር ቤቱ ሳይልክ ሊጥለውም ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አሥራ አንድ አባላት ያሉት የዚህ “የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ” ሰብሳቢ ነው እንጂ፣ በግሉ (ወይም ከሌሎች ዳኞች ጋር ሆኖ) የመወሰን ሥልጣን የለውም፡፡ እንግዲህ ዜጎች ፍትሕ ለማግኘት መሄድ ያለባቸውን ውጣ ውረድ በእዚህ “ቢሮክራሲ” ብቻ ለመገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡

በእኔ እምነት እነዚህ የአንድ የመንግሥት ቅርንጫፍ (የፍትሕ) አካል የሆኑት ሁለቱ (ማለትም የፌዴራል ምክር ቤቱ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱና ዳኞች) በሥልጣን ሊጋጩ የሚችሉበትና በመሀሉ ሕዝቡ ቀልጣፋ ፍትሕ በማጣት ሊንገላታና ሊሰቃይ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ይመስለኛል፡፡ በእዚህ አወቃቀር በተለይም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ወይም ዳኞች የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች በተግባር ለማዋል የሚያስፈጽመውን አካል፣ ማለትም ሕግ አስፈጻሚውን ለመቆጣጠርም ቀላል አይሆንም፡፡ ምናልባት ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ብዬ የምገምትው፣ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤቶች የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች እየጣሱ ፖሊሶች ዜጎችን በእስር ቤት በማቆየት የሚያሰቃዩበት አንዱ ዘዴ ነው፡፡

ይህ መጥፎ ልምድ በግልጽ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር ቢሆንም፣ አሁን ባለው የፍትሕ ሥርዓት “ለፌዴራል ምክር ቤቱ ጉባዔ” ቀርቦና ተጣርቶ፣ ለዚያውም ካለፈ “ለፌዴራል ምክር ቤት” ቀርቦ ከተሳካ፣ ሕግ አስፈጻሚውን በሕጉ መሠረት ይህን “በሥልጣን የመባለግ” ልምዱን (Power Abuse) ለአንዴም ለመጨረሻም ለማስቆም ምን ያህል አዳጋች አቀበት እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡ በእኔ እምነት ምናልባት በየእርከኑ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ የተዘረጋ “የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቶች” (Constitutional Courts) መዋቅር ቢኖር፣ ይህ ችግር ሊቃለልና ዜጎችም ቀልጣፋ ፍትሕ ሊያገኙ ይችሉ ነበር፡፡ 

በእዚህ ሁሉ የሕገ መንግሥት እንከን መሀል የሕግ አስፈጻሚው አካል (መከላከያን፣ ደኅንነትንና ፖሊስን የሚቆጣጠረው) መረን የለቀቀ ሥልጣን ተሰጥቶት፣ በማናአለብኝነትና በዕብሪት ተሞልቶ፣ የሕዝብ ተውካዮች ምክር ቤቱም አሁን ባለው ሕገ መንግሥት የተሰጠውን ውስን የመቆጣጠር ሥልጣን እንኳን ለመጠቀም ወኔና አቅም ስለተሳነው፣ በአገሪቱና በሕዝብ ላይ ብዙ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ እግዜርን ካልፈራ በቀር ገና ብዙ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ለጭቁኑ ሕዝብ ድምፅ ሊሆኑ የሚችሉትን እንደ ነፃ ሚዲያ ያሉትንም እያፈነ፣ የሲቪክ ማኅበራትን ለምሳሌ “የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና” “ዕንባ ጠባቂ” የሚባሉትን በሕገ መንግሥቱ የተፈቀዱትንም ተቋማት እያኮላሸ የአምባገነንነት ሥርዓት በመገንባት ላይ ያለ ይመስላል፡፡

ይህ አካሄዱ በአገሪቱ በብሔር ፖለቲካና በዘረኝነት የተደገፈውን ሥርዓትም እንኳን ለመግታት ይቅርና ይበልጥ እንዲያድግና እንዲጠናከር እያደረገው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየጊዜው፣ “ተቋም እየገነባን ነው” ይበሉ እንጂ ሕግ አስፈጻሚው አካል “ሕዝባዊ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ተቋሞችን” እየቦረቦረና እየናደ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ፣ ከጠባብ ብሔርተኞች ጋር በመተጋገዝ ሕገ መንግሥቱም እንዳይሻሻል ወይም እንዳይቀየር በግልጽ እንቅፋት እየሆነ ነው፡፡

ያም ሆነ ይህ ከላይ እንደተጠቀሰው ከተቻለ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ወይም ለመቀየር መፈተሽ ካለባቸው ዋና ዋና ባህሪዎች አንዱ፣ የመንግሥቱ አወቃቀር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች መሀል ግልጽ የሆነ የሥልጣን ክፍፍልና (Separation of Powers) ጠንካራ የቁጥጥርና ሚዛናዊ አስተዳደር (Check and Balance) ሥርዓት እንዲኖረው ቢደረግ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበርና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ብዙ ይረዳል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በእዚህ ረገድ የአሜሪካን ሕገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የሌሎችንም አገሮች ተሞክሮ፣ ለምሳሌ የደቡብ አፍሪካንና የናይጄሪያን ማየቱም ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከእነሱና ከሌሎችም ተሞክሮ በመቅሰም ለአገራችን የሚበጅ ትክክለኛ ሕገ መንግሥት መቅረፅ ይቻል ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

እርግጥ ዛሬ በአገራችን የተዘረጋው የፖለቲካና የመንግሥት ሥርዓት ፓርላሜንታዊ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ከሕገ መንግሥቱ መሻሻል ጋር አያይዞ የትኛው ሥርዓት ለአገራችን ይበጃል? ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዚዳንታዊ? የሚለውንም ጥያቄ አብሮ ማየቱ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ሁለቱም ሥርዓቶች የራሳቸው የሆነ ጠንካራና ደካማ ጎኖች አሏቸው፡፡ ሆኖም በእኔ እምነት በተለይም በብሔር ፖለቲካ ሰበብ ዛሬ በአገራችን ሥር ሰዶና ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የዘረኝነት ሥርዓት ለማስቆም፣ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የተሻለ አማራጭ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ በሽግግሩ ጉዞ መንገራገጭ ሊኖር ይችላል፣ እሱ ያለ ነው፡፡ በመጨረሻ ግን ሕገ መንግሥቱ ቢሻሻል ወይም ቢቀየርና ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ቢገነባ፣ ዘንቦ ተባርቆ ለአገራችን የፖለቲካ ሕይወት ጥሩ ቀን ይወጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

የፕሬዚዳንትነት ሥርዓት ይሻላል የምልበትን ምክንያቶች በሚቀጥለው ጽሑፌ (በክፍል አራት) ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ በዚያውም እግረ መንገዴን በብሔር ላይ የቆመውንና ውስብስቡን “የፌዴራል አወቃቀር፣” እንዲሁም “የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀቱን” ሥርዓትም እንዴት አብሮ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አማራጭ ሐሳቦችን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ እስከዚያ ግን ዋናው ማሳሰብ የምወደው ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል አሁንም የአገራዊ ምክክሩ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡                      

  1. ራዊ ምክክሩ ለምን ያስፈልጋል? እንዲሳካስ ምን መደረግ አለበት?

ባለፉት 50 ዓመታት አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ቀውሶችንና ችግሮችን አሳልፋለች፡፡ ለእዚህም አንዱ ዋና መንስዔ በተለይም “የፖለቲካ ልሂቃኑ” ልዩነታቸውን በሰላም በመፍታት ፋንታ፣ በሁለቱም ወገን ያሉት የመንግሥት ሥልጣን የያዙትም ሆነ ሊይዙ የሚፈልጉት በጉልበት ለማሸነፍ ሲሞክሩ፣ ሕዝቡን በተለይም ወጣቱን በየጊዜው በጦርነት እየማገዱ አገራችን ወድማለች፡፡ ስለዚህ ካለፈው ታሪካችን ተምረን፣ የአገራችንን ውስብስብ የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት በሰላማዊ መንገድ “አገራዊ ምክክር” ማድረጉ አማራጭ የለውም ብዬ አምናለሁ፡፡

ችግሩ አገራዊ ምክክሩን ለማካሄድ አሁን ያለው የአገራችን ሁኔታ አመቺ ይሆናል ወይ የሚለው ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ደጋግሞ ቢመጣ አያስገርምም፡፡ ግን ሁለተኛው ከባድ ጥያቄ ደግሞ ሌላ ምን አማራጭ አለን ታዲያ የሚለው ነው፡፡ በእኔ እምነት ሁለቱንም ለመመለስ በቅድሚያ ወደድንም ጠላንም ያለውን መንግሥት ተባባሪነት፣ ቅንነትና ቆራጥነት ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪ ግን ኢትዮጵያን አፍቃሪ የሆኑ ዜጎች በሙሉ አገራቸውን ለማዳን በጋራ መነሳት አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ብሔራዊ ምክክሩ እንዲካሄድና እንዲሳካም በቁርጠኝነት ተደራጅተው በሰላማዊ ትግል መታገል ይኖርባቸዋል፡፡ መረዳት ያለብን በርካቶች ጽንፈኛና ጠባብ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ አገራዊ ምክክሩን ከልባቸው አይፈልጉትም፡፡ ሕገ መንግሥቱም እንዲሻሻል ወይም እንዲቀየር አይፈልጉም፣ ለምን ቢሉ ጥቅማቸው ይነካልና፡፡ 

ስለዚህ አገራቸውን ማዳን የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን በትግላቸው ማተኮር ያለባቸው ሕገ መንግሥቱን ለመቀየር እንዲተባበሩ፣ በመንግሥት ላይ ጠንካራ ተፅዕኖ ለማሳደር መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በቅድሚያ ግን አሁን ባለው ሕገ መንግሥትም ኃላፊነቱንና ግዴታውን ተቀብሎ በማክበር፣ በሕዝቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዲያቆምና ሕግንም ማክበርና ማስከበር እንዳለበት ደጋግመው ማሳሰብና ማስገደድ ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች በነፃነት የመናገር፣ የመጻፍና የመሰብሰብ መብታቸው ሳይከበር፣ የሕዝብ ድምፅ የሆኑትን ጋዘጠኞችም እያፈኑ በመውሰድ መደብደብና ማሰቃየት ሳይቆም፣ በሕግ የተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለ ሥጋት መሰብሰብና እንደ ልባቸው በየትኞቹም የአገሪቱ ክልሎች እየተዘዋወሩ ሐሳባቸውንና ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ ማስረዳት ካልቻሉ፣ ስኬታማና እውነተኛ አገራዊ ምክክር ለማድረግ አይቻልም፡፡

በተጨማሪ አገሪቱ ሰላም አጥታ በውጥረት ላይ እያለች ስኬታማ አገራዊ ምክክር ማድረግ ቀላል አይደለም፡፡ በርካቶች መንግሥት የዜጎችን መብት ለመጠበቅና የአገራችንንም ፀጥታ፣ ሰላምና አንድነት ለማስከበር ከልቡ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ስለሌለው፣ አገራዊ ምክክሩ አይደረግም ወይም አይሠራም፣ ቢደረግም ለይስሙላ እንጂ ስኬታማ አይሆንም ብለው ያምናሉ፡፡ እርግጥ ይህ አደጋ እንዳለ ይሰማኛል፣ ሆኖም ሁኔታዎች እንዲቀየሩ በጋራ ተባብሮ ኃይልን አሰባስቦ በሰላማዊ ትግል መታገል እንጂ ተስፋ መቁረጡ ለውጥ አያመጣም፡፡ 

ሌላ የተሻለ አማራጭ መንገድም የለንም፣ ደም መፋሰሱ ይበቃናል፡፡ ሰላም ሲጠፋ ዋና የሚጎዳው ምስኪኑ ሕዝብ ነው፡፡ ኋላቀሩ ሕገ መንግሥትና በዘረኝነት ላይ የቆመው “የፌዴራል ሥርዓት” በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ በሕዝብ ምክክር፣ ፍላጎትና ድምፅ ካልተሻሻለ ወይም ካልተቀየረ፣ አገራችን ምንጊዜም ቢሆን ዘላቂ ሰላም አታገኝም፡፡ ሕዝባችንም ነፃነትና ፍትሕ ሊያገኝና ከድህነት ሊላቀቅ አይችልም፡፡ ያ ብቻ አይደለም አገራችን ለህልውናዋ ያሠጋታል፡፡ ለእዚህ ነው ተባብሮ ሰላማዊ ትግል የሚያስፈልገው፡፡ መደራጀት ነው የሚጎድለው እንጂ ኢትዮጵያን አፍቃሪ የሆነው ሕዝባዊ ኃይል ከዘረኞች፣ ከጽንፈኞችና ከጠባብ ብሔርተኞች እጅግ አድርጎ ይበልጣል፡፡

በሚቀጥለው ጽሑፌ (በክፍል አራት) ውስብስቡ ‹‹በብሔር ላይ የቆመው ዘረኛው ሥርዓት፣ የፓርቲና የክልል ፌዴራል መዋቅሩ›› እንዴት ሊሻሻል ይችላል? በሚለው ሐሳቤን ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ እስከዚያ በሰላም ያገናኘን!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ! ለአገራችን ሰላም ያውርድልን!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ‹‹በአገር ፍቅር ጉዞ›› መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው aberlie03@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...