Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ያለንበትን ጊዜ ከብዙ ነገሮች ጋር እያስተያየሁ ከራሴ ጋር ስነጋገር ከወራት በፊት የገጠመኝ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ በአንደኛው እሑድ አራት ኪሎ ከሚገኙ የዘመኑ ካፌዎች በአንዱ በረንዳ ላይ ሆኜ ቡና እየጠጣሁ ጋዜጣ እያነበብኩ ነበር፡፡ እዚህ አካባቢ ከመጣሁ ስለቆየሁ ነው መሰል በረንዳው በሰው ተሞልቶ ሁሉም ከቢጤው ጋር ሲያወጋ ለእኔ አዲስ ክስተት ነበር፡፡ ከዓመታት በፊት ይህን የመሰለ ድባብ ቢኖርም፣ የአሁኑ ግን በጣም ደስ ይላል፡፡

ይህን እያሰብኩ ሳለ ከበስተጀርባዬ ያለው ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠች አንዲት ውብ ሴት ዘመናዊውን አይፎን ስልክ ጆሮዋ ላይ ለጥፋ ዝግ ባለ ድምፅ እያወራች ነበር፡፡ ውበቷ ማርኮኝ ነው መሰል ወንበሬን 45 ዲግሪ አዙሬው በስላች ከፊት ለፊቷ ገጭ አልኩ፡፡ ከውበቷ በላይ ላይዋ ላይ ኢንቨስት የተደረጉት ጌጣጌጥ፣ አልባሳት፣ መጫሚያ፣ ቦርሳና ስልኳ ልዩ ሞገስ ሰጥተዋታል፡፡ ጠረጴዛው ላይ ያስቀመጠችው የቢኤም ደብልዩ ቁልፍ ደግሞ ዓይን ያጥበረብራል፡፡

ሁለመናዬን ስቼ ፈዝዤ እያየሁዋት ሳለሁ ሁለት አካላቸው በስፖርት የፈረጠመ የሚመስሉ ጎልማሶች በአንገታቸው ሰላምታ እየሰጧት ሲቀመጡ አንገቴን ሰበር አደረግኩ፡፡ የስልክ ንግግሯን እስከምትጨርስ የሚጠባበቁት ጎልማሶች አይፎን ስልኮቻቸውንና የዘመናዊ መኪና ቁልፎቻቸውን ጠረጴዛው ላይ ሲመድቡ ሳይ ይህችን ውብ ሴት እንደማልመጥናት ወዲያው ገባኝ፡፡ የእኔ ሐሳብ የስልክ ንግግሯን ስትጨርስ በተለመደው የአራዳ ልጅ አቀራረብና ባለኝ የመቀላጠፍ ተሰጥኦዬ ልቀርባት ነበር፡፡ አሁን የተረዳሁት ነገር ቢኖር ከከባድ ሚዛን ጋር መወዳደር አለመቻሌን ነው፡፡ ወር ሙሉ ለፍቼ ከሃያ ሺሕ ብር በላይ የማላገኝ ሰው አቅሜን ማወቅ ይኖርብኛል፡፡ ለማንኛውም ወደ ገጠመኜ ልመልሳችሁ፡፡

ያቺ ውብ ወይዘሮ የስልክ ወሬዋን ጨርሳ ጠረጴዛ ከተጋሩዋት ሰዎች ጋር ከልብ በመነጨ ፈገግታ እየተሳሳመች ሰላምታ ከተለዋወጠች በኋላ አስተናጋጅ ቀርቦ ትዕዛዝ ተቀብሎ ሄደ፡፡ ሴትየዋ ውኃ፣ ሁለቱ ጎልማሶች ደግሞ ማኪያቶ ይዘው ሦስቱም ለጊዜው በራሳቸው ሐሳብ ውስጥ ሰጠሙ፡፡ በዚህ መሀል ዝግ ባለ ድምፅ የተገናኙበትን ጉዳይ ማውራት ሲጀምሩ፣ ድንገት አንድ አባባል ጆሮዬ ውስጥ ጥልቅ አለ፡፡ ሴትየዋ፣ ‹‹ይኼ ፈጽሞ ሊያሳስባችሁ አይገባም፡፡ ጉዳዩን ያለ ምንም ሥጋት ሐሙስ ምሽት ላይ እጨርሰዋለሁ፡፡ ለዚህም ከአስተማማኝ ሰው መተማመኛ አግኝቻለሁ…›› ስትል ሰማኋት፡፡ ሰዎቹ ሕገወጦች ካልሆኑ በስተቀር የሥራ ጉዳይ ከሆነ ‹‹ሥጋት አይግባችሁ›› የሚለው አባባል ግራ አጋባኝ፡፡

አንገቴን የያዝኩት ጋዜጣ ላይ ደፍቼ የሚነጋገሩትን በጥንቃቄ ማዳመጤን ቀጥያለሁ፡፡ ይህች ቆንጆ ሴት ለእኔ እንደማትሆን የበለጠ እየረጋገጥኩኝ ወሬያቸውን እየሰማሁ ነው፡፡ አንደኛው ግራና ቀኝ ገልመጥ ብሎ፣ ‹‹ግን እኔን የሚያሠጋኝ የዚያ የቀልቃላ ሰው ወከባ ነው፡፡ እሱ እዚያም እዚህም እየረገጠ እንዳያስበላን ነው የምፈራው…›› ሲል፣ ውቢት ወይዘሮ፣ ‹‹አይዞህ እሱም አደብ ገዝቷል፣ እነዚያ የሚያስፈሩትም በገንዘብ ተይዘዋል…›› እያለች ማብራሪያ ስትሰጥ ሁለቱ ጎልማሶች ፈገግ አሉ፡፡

በዚህ መሀል የሴትየዋ ስልክ ጮሆ መነጋገር ስትጀምር ሁለቱ ጎልማሶች ስለሚያገኙት ጥቅም በዝቅተኛ ድምፅ እየተነጋገሩ በጠረጴዛው ሥር ተጨባበጡ፡፡ ሴትየዋ የስልክ ንግግሯን ጨርሳ በመጠኑ በሚሰማ ድምፅ፣ ‹‹አብሽር ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኗል የቀረን ብራችንን መቁጠር ብቻ ነው…›› ብላ የመኪናዋን ቁልፍ ከጠረጴዛው ላይ አንስታ ተሰናብታቸው በፍጥነት ሄደች፡፡ በዚያ ቁመቷ ላይ የሚያረገርገው ዳሌዋ የካፌው በረንዳ ላይ የነበሩትን ሰዎች በሙሉ ማለት ይቻላል እንደ ማግኔት ስቦ ነበር፡፡

ሁለቱ ስፖርተኛ መሳይ ጎልማሶች ቢል አስመጥተው ክፍያቸውን ከፈጸሙ በኋላ አንደኛው፣ ‹‹ግን ይህችን ሴት ታምናታለህ? ማለቴ አንተ በጣም ስለምታውቃት አስተማማኝ ናት?›› ሲለው ሌላኛው ደግሞ፣ ‹‹ከማስተማመን በላይ ሌላ ቃል ቢኖር ኖሮ እሷን ነው የሚገልጸው፡፡ እሷ እኮ ከፈለገች ከሰይጣን ጋርም ቢሆን ከመደራደር ወደኋላ አትልም፡፡ ከቢሮ ጸሐፊነት ተነስታ የተተኮሰችው እኮ ቀልጣፋ በመሆኑዋ ነው፡፡ በዚያ ላይ የማትገባበትና የማታውቀው የለም…›› እያለ ዝናዋን ካበው፡፡ ንግግራቸውን ሲያበቁ በመጡበት ሁኔታ ተነስተው ሄዱ፡፡

እኔም ጉዳዩ ውስብስብ ሆኖብኝ ስለምን እንደሚያወሩ በግልጽ ባይገባኝም፣ ከሰዎቹ አነጋገር የተረዳሁት ከሕገወጥ ነገር ጋር የተያያዘ ሥራ ውስጥ መሰማራታቸውን ነው፡፡ ግን ምን ይሆን እያልኩ ባስብም ሊገለጽልኝ አልቻለም፡፡ ለነገሩ ግብር ማጭበርበር፣ ኮንትሮባንድ፣ መሬት በሕገወጥ መንገድ መውረር፣ ሕገወጥ ግንባታን ሕጋዊ ማድረግ፣ በሰነዶችና በቼኮች ማጭበርበርና የመሳሰሉ ወንጀሎች በደሩበት በዚህ ጊዜ ብዙ ወንጀሎች ይፈጸማሉ፡፡ ወንጀሎቹን የሚፈጽሙ ደግሞ እነሱ በአቋራጭ ይክበሩ እንጂ፣ በአገር ላይ ስለሚያደርሱት ጥፋት ደንታ የላቸውም፡፡

እንደ ዘበት ስለሚሊዮን ብሮች `ቢዝነስ` ሲያወሩ የነበሩት እነዚያ ሰዎች በርኩሰት የተሞላው ሙስና የሚባል የሌብነት ልማድ ካዳሚዎች ናቸው? አገሪቱን ሽባ አድርገው ዜጎችን እሳት የሆነ ኑሮ ውስጥ የሚማግዱት አጅሬዎች ናቸው? በእኛ ሚሊዮኖች ጉስቁልና የደለቡት እነዚህ የማይጠግቡ ጅቦች ናቸው? ዙሪያችንን ከሞራልና ከሥነ ምግባራዊ እሴቶች ያፈነገጡ አደገኞች ከበውናል፡፡ ትናንትናና ከትናንት በስቲያ ምንም ያልነበራቸው ምስኪኖች፣ ዛሬ መሬት መርገጥ እስኪፀየፉ ድረስ የሚንቀባረሩት ለካ እንዲህ ኖሯል? ይብላኝ ለእኛ፣ ይብላኝ ለአገራችን፡፡ 

(ቶማስ ተክሉ፣ ከአዲሱ ገበያ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...