የክልል ልዩ ኃይሎች አወቃቀርና ሌሎች የሚስተዋሉ መሠረታዊ ጉድለቶች የአገር ደኅንነት ሥጋት በመሆናቸው የማስተካከያ ሥራ መጀመሩን አስታወቀው፣ ‹‹አንዱን ክልል አሳብጠን ሌላው ኃይል እንዲያጣ አናደርግምም በኢትዮጵያም አይሆንም››ሲሉ ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ ተናገሩ።
የክልል ልዩ ኃይሎች ላይ ከተስተዋሉት መሠረታዊ ጉድለቶች አንዱ አወቃቀራቸው ሕገ መንግሥታዊ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ለክልሎች የተፈቀደው መደበኛ ፖሊስ ብቻ መሆኑን የተናገሩት ጀኔራሉ፣ ‹‹አሁን ግን ክልሎች እንደ አገር ባዋቀሩት ልዩ ኃይል ከአሥራ አራት በላይ ሬንጀሮች (መለዮ ለባሾች) እየታዩና ለመለየትም አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
የክልል ልዩ ኃይሎች ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና የላቸውም መሆኑን፣ አወቃቀሩም ብሔርን መሠረት ያደረገ ከመሆኑም ሌላ፣ ኃይልና ፖለቲካ ተቆራኝቶ በአገሪቱ የፖለቲካ መፍቻ መንገድ መበላሸቱንና የአገሪቱ መከላከያ ኃይልን የሚገዳደሩ ጭምር መሆናቸውንም ምክትል ኢታማዦር ሹሙ ተናግረዋል።
“ለብሔሬ እሞታለሁ የሚል በመሆኑ አገራዊ አወቃቀርን ይሸረሽራል” ያሉት ጀኔራሉ፣ ‹‹ፖለቲከኛው በሐሳብ ማሸነፍ ሲያቅተው ሌላ በትር ያነሳል፣ (በትግራይ ክልል) ሦስት ዓመታት ሙሉ ጦርነት ውስጥ የቆየነው ፖለቲካና ኃይል ስለተገናኙ ነው፤›› ብለዋል።
ብሔርን መነሻ አድርጎ ሥልጣን የመያዝ ዕሳቤ አንዱ የአገሪቱ ወቅታዊ የፀጥታ ፈተና መሆኑን የገለጹት ጀኔራሉ፣ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር በመነጋገር ወደ ሕጋዊ መስመር ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ኦነግ ሸኔም ጋር ንግግር እንደተጀመረ ጠቁመው፣‹‹ኦነግ ሸኔ ወደ ንግግር የማይመጣ ከሆነ ልክ እናስገባዋለን›› ብለዋል።