Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየክልል ልዩ ኃይልን ‹‹መልሶ ማደራጀት›› በሚል ለማፍረስ የሚደረገው ሒደት እንዳሳሰባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች...

የክልል ልዩ ኃይልን ‹‹መልሶ ማደራጀት›› በሚል ለማፍረስ የሚደረገው ሒደት እንዳሳሰባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ

ቀን:

  • ‹‹ልዩ ኃይልን መልሶ ማደራጀት የሚካሄደው በሁሉም ክልሎች ነው››

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት

የክልል ልዩ ኃይሎችን አደረጃጀት ‹‹መልሶ ማደራጀት በሚል›› የማፍረሱ ዕርምጃ በአንዳንድ አካባቢዎች ተቃውሞ ማስነሳቱን ጠቁመው፣ እነሱንም እያሳሰባቸው መሆኑን አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡ ተቃውሞው ወደ ግጭት እንዳያመራ ሥጋት እንዳደረባቸውና እያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ‹‹የልዩ ኃይሎችን መልሶ ማደራጀት›› በሁሉም ክልሎች የሚካሄድ እንጂ አንድን ክልል ብቻ የለየ አለመሆኑን ተናግሯል፡፡

የልዩ ኃይል መፍረስ ጉዳይ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተቃውሞ እንደገጠመው ተነግሯል፡፡ ወልዲያ አካባቢ ተቃውሞ ካጋጠማቸው አካባቢዎች አንዱ ሲሆን፣ በሌሎች አካባቢዎችም ‹‹አማራውን ሆነ ብሎ ራሱን እንዳይከላከል ትጥቅ ለማስፈታት የታቀደ ሴራ ነው፤›› በሚል ተቃውሞዎች መነሳታቸው ታውቋል፡፡

ዓርብ መጋቢት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ስለጉዳዩ መግለጫ የሰጠው የፌዴራል መንግሥት ‹‹በአንዳንድ አካባቢዎች በመረጃ እጥረት የተነሳና ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀቱን ሥራ በአግባቡ ባለመረዳት ችግሮች አጋጥመዋል፤›› ሲል ተናግሯል፡፡

‹‹መንግሥት በቂ ጥናትና ዝግጅት አድርጎበት የተጀመረ ነው›› የተባለው የክልል ልዩ ኃልሎችን ወደ መከላከያና መደበኛ ፖሊስ የማዘዋወሩ ሥራ በሁሉም ወገን መግባባት የሚከናወን ነው ብሏል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ የክልል ልዩ ኃይል አባላቱ ወደመከላከያ ወይም ወደ መደበኛ ፀጥታ ኃይል መመለስ ካልፈለጉ ወደ መደበኛ ሕይወት የመመለስ አማራጭ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ወደ ሲቪል ሕይወት የመመለስ ፍላጎት ላላቸው አስፈላጊው መቋቋሚያና ድጋፍ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

መንግሥት የልዩ ኃይል መልሶ ማቋቋም አማራ ክልልን ብቻ የለየ አይደለም ቢልም፣ ክልሉ የተለየ የፀጥታ ሥጋት አለበት ያሉ ኃይሎች ግን ተቃውሟቸውን እያቀረቡ ነው፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ ዕርምጃውን እንደሚቃወም ተናግሯል፡፡ የአማራ ክልል መስተዳድር የልዩ ኃይሉን እንዳይበትን የጠየቀው አብን፣ አማራ የሕልውና አደጋ የተጋረጠበት መሆኑን ነው የተናገረው፡፡ በመሆኑም ‹‹የጋራ መግባባትና መተማመን ላይ ሳይደረስ›› የልዩ ኃይሉ መፍረስ እንደሌለበት አብራርቷል፡፡

በተመሳሳይ በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ዕርምጃውን ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው ብሎታል፡፡ የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ሕጋዊ የፀጥታ መዋቅር የማስገባት ዕርምጃን እንደሚደግፍና ከዚህ ቀደም ሲጠይቀው የነበረው መሆኑን የገለጸው ኢዜማ፣ ነገር ግን ዕርምጃውን በጥድፊያ ማከናወን አደገኛ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

ኢዜማ በመግለጫው ሕወሓት በአማራ ክልል ቁጥጥር ሥር ያሉ አካባቢዎችን አስመልሳለሁ በሚልበት ወቅት፣ የአማራ ልዩ ኃይልን ማፍረሱ ከፀጥታ አኳያ ሥጋት እንደሚፈጥር አመልክቷል፡፡

በሳምንቱ መገባደጃ ላይ መግለጫ የሰጠው ኅብር ኢትዮጵያ ፓርቲም፣ በአገሪቱ መግባባትና የጋራ ራዕይ ሳይፈጠር የልዩ ኃይል ማፍረስ ዕርምጃ መውሰድ የፀጥታ ሥጋት የሚፈጥር ነው ብሏል፡፡ ልዩ ኃይልን የማፈረስ እንቅስቃሴ በአገሪቱ ያለውን አለመተማመንን የበለጠ ያሰፋል ብሎታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...