Saturday, July 20, 2024

ቅራኔዎች እንዲረግቡ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

አገር በሕግና በሥርዓት ልትመራ የምትችለው ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል እንደሆኑ የሚያረጋግጥ አሠራር ሲኖር ነው፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ ከአገር መሪ ጀምሮ እስከ እያንዳንዱ ዜጋ ድረስ፣ ለሕግና ለሥርዓት መኖር የሚፈለግባቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን በነፃነት፣ በእኩልነትና በፍትሕ የምታኖራቸው አገር እንድትኖራቸው የሚያስችል ሥርዓት መታነፅ አለበት፡፡ ይህ ሥርዓት መታነፅ የሚችለው ሁሉንም ዜጎች አካታችና አሳታፊ ዓውድ ሲኖር ነው፡፡ መንግሥት አሠራሩ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ ዜጎችም መብታቸውን ብቻ ሳይሆን ግዴታቸውን ጭምር በሚገባ መወጣት አለባቸው፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት ሲጎድለውና ተጠያቂነት ሳይኖርበት ሲቀር፣ ለማመን የሚከብዱ ሕገወጥ ድርጊቶች ይንሰራፋሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መቃቃር ይፈጠራል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በበርካታ ጉዳዮች ቅራኔዎች ከመጠን በላይ እየተስፋፉ ነው፡፡ ከመለስተኛ ግጭቶች እስከ አውዳሚ ጦርነቶች ያስተናገደች አገር አንፃራዊ ሰላም ልታገኝ ነው ተብሎ ተስፋ ሲደረግ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ አደገኛ አዝማሚያዎች ብዙዎችን ሥጋት ውስጥ እየከተቱ ነው፡፡

ሕግና ሥርዓት ሲከበር ከሕገወጥነት ይልቅ ሕጋዊነት የበላይ ይሆናል፡፡ የመንግሥት ሹማምንትና ሠራተኞች ሕግ አክብረው ሲሠሩ ለሌሎችም አርዓያ መሆን ይችላሉ፡፡ ሕጋዊነት ወደ ጎን እየተገፋ ሕገወጥነት ሲስፋፋ ሥርዓተ አልበኝነት ይንሰራፋል፡፡ መንግሥት ውስጡን ሲያፀዳ ውሳኔዎቹም ሆኑ ዕርምጃዎቹ ተቀባይነት ይኖራቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የኃላፊነት መርህ እየተጣሰ ከፍተኛ የአገር ሀብት መውደሙ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች ማለትም ሕግ አውጭው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው እርስ በርስ ቁጥጥር እየተደራረጉና ሚዛናቸውን እየጠበቁ መሥራት ከቻሉ ሕግ ማስከበር አያቅትም፡፡ የአስፈጻሚው ጡንቻ እየበረታ ሕግ አውጭውና ሕግ ተርጓሚው አቅመ ቢስ ሲሆኑ፣ የአገር ሀብት መጫወቻ ከመሆኑ በተጨማሪ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይጨፈለቃሉ፡፡ በአገር አንጡራ ሀብት እንዳሻቸው የሚፈነጩና ሥልጣናቸውን ከመጠን በላይ የሚባልጉበት የሚበዙት፣ በሕግ መጠየቅ ያለባቸው ዝም እየተባሉ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ሲንሰራፋ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለበርካታ ቅራኔዎች መፈጠር ሰበብ እየሆኑ ያሉ ችግሮችን ፈር አስይዞ፣ አገርን ከገባችባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ ማውጣት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡

የዴሞክራሲ ተቋማት በመባል የሚታወቁት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም ከነበሩበት አፈና ውስጥ ወጥተው በርካታ መልካም ተግባራት እያከናወኑ ነው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ተቋማትን ይዞ በሚገባ መንቀሳቀስ ከተቻለ ሕጋዊና ሰላማዊ ተግባራትን ማከናወን አያቅትም፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ የሲቪክና የሙያ ማኅበራትን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን፣ የፍትሕ አካላትን፣ የዳያስፖራ አደረጃጀቶችንና ሌሎች አካላትን አጋዥ በማድረግ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ፍትሕና እኩልነት የሚያሰፍን ምኅዳር መፍጠር ይቻላል፡፡ በተጨማሪም በዕውቀታቸው፣ በሥራ ልምዳቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሠገኑ ዜጎችን ተሳትፎ ማከል ሲቻል ደግሞ ከሚታሰበው በላይ አስደናቂ ውጤት ይገኛል፡፡ ለአገራቸው ተጨባጭ የሆነ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉ ወገኖች ገለል ሲደረጉ፣ ከአገራቸው ላይ የሚነጥቁ ዘራፊዎችና ፍትሕ ነፋጊዎች እየበዙ ሰላምና መረጋጋት ይጠፋል፡፡ ብቃት ያላቸው ወገኖች የዳር ተመልካች ተደርገው ብቃት አልባዎች ሕዝብ እያጉላሉ ያስለቅሳሉ፡፡ በበርካታ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እየተስተዋለ ያለው ይህ ነው፡፡

ሕግና ሥርዓት በተሟላ ሁኔታ ለማስፈን የሚቻለው ለሕግ የበላይነት ክብር ሲሰጥ ነው፡፡ ሁሉም የመንግሥት ተሿሚዎችና መዋቅሮች ሥራቸውን በሕጉ መሠረት ብቻ እያከናወኑ መሆናቸው በተጨባጭ የሚረጋገጠው፣ ለብልሹ አሠራሮች የሚያጋልጡ ድርጊቶችና ዝንባሌዎች ሲወገዱ ነው፡፡ እነዚህን እንከኖች ለማስወገድ ደግሞ ሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች እየተናበቡና ሚዛናቸውን እየጠበቁ መሥራታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ሕግ አውው አካል በሕገ መንግሥቱ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለማከናወን የሚያስችል ቁመና መያዝ፣ አስፈጻሚው በሕግ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስችሉ ብቁ ሹማምንትና መዋቅሮች ማግኘት፣ እንዲሁም የሕግ ተርጓሚው አካል ደግሞ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት መሥራት መቻል ይጠቀሳሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ይህ የሦስቱ አካላት በነፃነት ኃላፊነትን የመወጣት ተግባር፣ ሕገወጥ ድርጊቶችን ከመከላከል በተጨማሪ አምባገነንነት እንዳይንሰራፋ ያግዛል፡፡ እንዲሁም የገዥው ፓርቲና የመንግሥት ሚና እንዳይደበላለቅና አላስፈላጊ ትርምስ እንዳይኖር ይረዳል፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖርበት ከማስቻሉም በላይ፣ ዜጎች በመንግሥት ላይ የሚኖራቸው እምነት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ የሚያደርጉ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር የመንግሥት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ለግብር ከፋዩ ሕዝብ ስለማይሰጡ፣ በየቦታው ምሬት ማዳመጥ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ከመሠረታዊ አገልግሎቶች ጀምሮ እስከ ፍትሕ ተቋማት ድረስ ብዙዎች እሮሮ ያሰማሉ፡፡ በወረዳ ወይም በቀበሌ የነዋሪነት መታወቂያ ወይም ሌሎች አስተዳደራዊ አገልግሎቶች ለማግኘት የሚስተዋለው መጉላላት በቃላት የሚገለጽ አይደለም፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ በየደረሱበት ጉቦ የሚጠየቁ ዜጎች ከአቅማቸው በላይ እየሆነባቸው ነው፡፡ ከመሬትና ተያያዥ ንብረቶች ጋር ጉዳይ ያለባቸው ዜጎች ለወራት አንድ ጉዳይ ማስፈጸም ሲያቅታቸው፣ ጉቦ የሚሰጡ ግን ያሉበት ቦታ ድረስ ጉዳያቸው ተፈጽሞ ይመጣላቸዋል፡፡ ከኃላፊ እስከ ታችኛው ሠራተኛ ድረስ በጉዳይ አስፈጻሚ ካልሆነ በስተቀር አገልግሎት የማይገኝባቸው ወረዳዎችና ክፍላተ ከተሞች ተበራክተዋል፡፡ ባለጉዳዮች በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ አቤት ሲሉ ግን አዳማጭ የላቸውም፡፡ ሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች እየተናበቡ፣  ከዴሞክራቲክ ተቋማት የሚገኙ ግብዓቶችን እየተቀበሉ፣ ከሌሎች ለአገር ከሚያስቡ ወገኖች መረጃዎችን እያሰባሰቡ ኃላፊነታቸውን ቢወጡ ግን ሕገወጥነት ሕዝብ ላይ አይፈነጭም ነበር፡፡

ኢትዮጵያን በየዕለቱ ከሚያጋጥሟት የፖለቲካ ልዩነት ከሚፈጥራቸው ንትርኮችና ሽኩቻዎች በላይ፣ ለሕዝብ ዘላቂ ሰላምና ለአገር ህልውና የሚጠቅሙ ጉዳዮች እየተዘነጉ ነው፡፡ ለአንድ አገር ልማት፣ መልካም አስተዳደርና ፍትሕ ከምንም ነገር በፊት የሚቀድሙ ናቸው፡፡ ልማት ሲኖር ዜጎች በተለያዩ መስኮች በመሰማራት ከድህነት ለመውጣት ብቻ ሳይሆን፣ አስተማማኝ የሆነ ዕድገት ለማስመዝገብ መልካም ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡፡ መልካም አስተዳደር ሲኖር የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ከመከበሩም በላይ፣ ሁሉንም መሠረታዊ አገልግሎቶች በእኩልነት ለመጠቀም የሚያስችል ዕድል ያገኛሉ፡፡ ፍትሕ መስፈን ያለበት ብዙኃን በጥቂት ጉልበተኞች እንዳይሰቃዩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው እንዲረጋገጥ ነው፡፡ የብዙኃኑ ሕዝብ ጥያቄ ልማት፣ መልካም አስተዳደርና ፍትሕ ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹ አሁንም ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በመልካም አስተዳደርና በፍትሕ ዕጦት የሚሰቃዩ ወገኖች አሁንም በከፍተኛ ምሬት ድምፃቸውን እያሰሙ ነው፡፡ ቅራኔዎች እንዲረግቡ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...

የዘንድሮ ነገር!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ካዛንቺስ፡፡ ከእንጦጦ በኩል ቁልቁል እያስገመገመ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...