- ባለፉት 12 ዓመታት 182 ቢሊዮን ብር ለግድቡ ወጪ ተደርጓል
በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በመጪው ክረምት የሚካሄደው የውኃ ሙሌት፣ በግድቡ የሚተኛውን አጠቃላይ የውኃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እንደሚያደረሰው ምንጮች ገለጹ።
ባለፈው ዓመት የግድቡ የመካከለኛ ክፍል ግንባታ ከባህር ጠለል 600 ሜትር ከፍታ ላይ ደርሶ የውኃ ሙሌት የተከናወነ ሲሆን፣ ዘንድሮ ከየካቲት ወር ወጨረሻ አንስቶ የመካከለኛውን ክፍል ከፍታ 620 ሜትር ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ ነው።
በተቀመጠው ዕቀድ መሠረትም ካለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ሳምንት አንስቶ የመካከለኛው ክፍል የኮንክሪት ሙሌት የተጀመረ ሲሆን፣ ባለፉት 30 ቀናት ውስጥም የግድቡን የመካከለኛ ክፍል አምና ከነበረበት 600 ሜትር ከፍታ ወደ 610 ከፍ ማድረግ ተችሏል። በዚህ የግንባታ ፍጥነት ከተካሄደ ቀሪውን የከፍታ ደረጃ ያለ ችግር ክረምቱ ሳይገባ መፈጸም እንደሚቻል ምንጮቹ ጠቁመዋል።
በግድቡ ግራና ቀኝ የሚገኙት ክፍሎች የግንባታ ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ 633 ሜትር ላይ ለማድረስ ዕቅድ ተይዞ ግንባታዎቹ እየተከናወኑ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የእነዚህ ክፍሎች የግንባታ ከፍታ 625 ሜትር ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።
ባለፈው ዓመት ማለትም የግድቡ መካከለኛ ክፍል 600 ሜትር ላይ ከደረሰ በኋላ የተካሄደው ሙሌት የግድቡን የውኃ መጠን ወደ 22 ቢሊዮን ሜትር ኩብ እንዳደረሰው ይታወቃል።
የዘንድሮ የዝናብ ወቅት ከመድረሱ አስቀድሞ የግድቡን መካከለኛ ክፍል ወደ ሚፈለገው ከፍታ ማድረስ የሚቻል በመሆኑ፣ በዘንድሮው ክረምት የሚያዘው የውኃ መጠን በግድቡ የሚተኛውን አጠቃላይ የውኃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ አንደሚያደርሰው ምንጮቹ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ዘንድሮ የሚያዘው የውኃ መጠን ብቻውን ባለፉት ሦስት ዓመታት የተያዘውን የውኃ መጠን እንደሚያክል ይጠበቃል።
ባለፉት 12 ዓመታት ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ የወጣው አጠቃላይ ወጪ 181.2 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ አሁን ላይ 91 በመቶ ለማድረስ እንዳስቻለ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆራ (ኢንጂነር) ሰሞኑን ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሰጡት መረጃ ያመለክታል።
የኮንክሪት ሥራው ለብቻ ሲታይ ከ95 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፣ የሃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር ማለትም በግድቡ ውስጥ የሚቀበሩ የውኃ ማቀባበያ አሸንዳዎችና የእነዚህ በሮች ገጠማ ሥራ 76 በመቶ ላይ ይገኛል። የጄነሬተርና የተርባይኖች ተከላ ሥራ ደግሞ 67.5 በመቶ ደርሷል።
ቀሪ ሥራዎችን ጨርሶ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ደግሞ ተጨማሪ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
|
|