ኢትዮጵያን ጨምሮ 12 የአፍሪካ ከተማዎች ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለ የመሠረታዊ አቅርቦቶች ጥናት ሊደረግ መሆኑ ተነገረ፡፡
የአፍሪካ ከተሞች የምርምር ጥምረት ‹‹African Cities Research Consortium (ACRC)›› በኩል ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክት፣ ሦስት አንኳር ዋና ላይ ያተኮረ መሆኑን ‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› አስታውቋል፡፡
በ‹‹ዩናይትድ ኪንግደም›› (Foreign Common Wealth and Development Office -FCDO) በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ተጠቃሚ የሚሆኑት አሥራ ሁለት የአፍሪካ አገሮች፣ ለፕሮጀክቱ የሚሆነውን ጥናት የሚያደርጉት በራሳቸው ባለሙያ እንደሆነ፣ ዓርብ መጋቢት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል ከባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄደ ውይይት ላይ ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ መምህርና የምርምር ሥርፀት አስተባባሪ ኢዛና ዓምደ ወርቅ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ በሚደረገው የመጀመርያ ዙር ጥናት አሥር ተጨባጭ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡
በዚህ መሠረት ከሦስቱ ዋነኛ ነጥቦች በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድ፣ በውኃና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጥናቱ የሚያተኩር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በቀጣይ በሁለት ዙሮች የሚደረገው ጥናት የሚያተኩረው የወጣቶች አቅም ግንባታና የመኖሪያ ቤቶች ላይ እንደሆነ የተናገሩት አስተባባሪው፣ ‹‹በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥናት ሲደረግ በርካታ ዳሰሳዎች ይደረጋሉ፤›› ብለዋል፡፡
በተለይም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች የቤት አቅርቦትን ለማሻሻል ‹‹የሚደረጉ ጥረቶች ምንድን ናቸው? ያሉትስ ተግዳሮቶች ምን ይመስላሉ?›› የሚለውን ለመመለስ ጥናቱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
የአሥራ ሁለቱም የአፍሪካ አገሮች ጥናት ሲካሄድ አንድ ዓይነትና ተመሳሳይ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ሲሆን፣ የጥናት ምርምር ፕሮጀክቱ ተፈጻሚ የሚደረገው ለስድስት ዓመታት ያህል ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ለስድስት ዓመታት በሚቆየው ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ መሆኗን፣ በአሁኑ ወቅትም ፕሮጀክቱን በአዲስ አበባ ከተማ ተፈጻሚ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ኢዛና (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱንም ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቅ ያስታወቁት አስተባባሪው፣ ጥናቱ ሊያተኩርባቸው የተያዙ መነሻ ሐሳቦች ላይ የመንግሥት ፖሊሲ አውጪዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት፣ የከተማ አስተዳደሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሠረት በተለያዩ ጊዜያት መድረኮችን በመፍጠር ዋና በሆኑ ነጥቦች ላይ ውይይት የሚደረግ መሆኑን ገልጸው፣ የመጀመርያውን ዙር ጥናት በነሐሴ ወር ለመጨረስ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
የአፍሪካ አገሮች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታትና ዘላቂ የሆኑ መፍትሔዎችን ለማበጀት፣ እንዲህ ዓይነት ጥናት እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የጥናት ባለሙያ ተገኝ ገብረ እግዚአብሔር (ፕሮፌሰር) አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረገው ይህ ጥናት ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ቢያተኩርም፣ በሥሩ ግን ሰፊ እንቅስቃሴዎች ያቀፈ መሆኑን ተገኝ (ፕሮፌሰር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡