- በኢትዮጵያ 200 ሺሕ ሰዎች የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል
በአማራ ክልል በከፍተኛ ሁኔታ እየተሠራጨ የሚገኘው ትራኮማ (የዓይን ማዘ) በሽታ እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የቀዶ ጥገና ሕክምና ካልተደረገላቸው 109 ሺሕ ሰዎች ዓይነ ሥውር እንደሚሆኑ የክልሉ የጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ሪፖርተር ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገራቸው በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ትኩረት የሚሹ በሽታዎች አስተባባሪ አቶ አዲሱ አበበ እንደገለጹት፣ በክልሉ 109 ሺሕ ሰዎች የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል፡፡ እስከ ሰኔ 2015 ዓ.ም. ሕክምናውን ካላገኙ ለዓይነ ሥውርነት ይጋለጣሉ፤›› ብለዋል፡፡
ትራኮማን ለማጥፋት ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ እየተደረገ ባለው ዘመቻ በክልሉ ከሚገኙ 166 ወረዳዎች መካከል ነፃ ማድረግ የተቻለው 59 ወረዳዎችን እንደሆነ የተናገሩት አቶ አዲሱ፣ ‹‹ቀሪዎቹ 107 ወረዳዎች ግን አሁንም የአፍላ ትራኮማ ሥርጭት ገና ከአምስት በመቶ በላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ ከሆነ፣ በሽታውን ለመከላከል በ107 ወረዳዎች የመድኃኒት ዕደላ እንደሚደረግ፣ ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በአካባቢ ሳይንስ የትምህርት ዓይነት የትራኮማ በሽታን መከላከያ መንገዶች በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ በማስገባት ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን፣ ሁሉም ሰዎች መፀዳጃ ቤት እንዲሠሩ ንቅናቄ ስለመጀመሩ፣ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለ750 ሺሕ ሰዎች የቀዶ ጥገና ሕክምና መሰጠቱ ተብራርቷል፡፡
እንደ ጤና ሚኒስቴር ከሆነ ከ200 ሺሕ በላይ ሰዎች የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል፡፡
የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና ያስፈለገው የዓይን ቆብ መታጠፍ ሊያስከትሉ ከሚችሉ ሃሩራማ በሽታዎች መካከል የሚጠቀሰውን፣ ትራኮማ በሽታ በኢትዮጵያ ማጥፋት ስላልተቻለ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የትራኮማ በሽታ ሥርጭቱ በሁሉም ክልሎች ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ የውኃ አቅርቦት በጣም አነስተኛ በሆነባቸው የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች የትራኮማ በሽታ በስፋት ተሠራጭቶ ነው የሚገኘው፤›› ሲሉ፣ በጤና ሚኒስቴር ትኩረት የሚሹ ሃሩራማ በሽታዎች ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ፍቅረ ሰይፈ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ትራኮማ በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች መሠራጨቱን የገለጹት አስተባባሪው፣ በሽታው በስፋት የሚገኝባቸውን ክልሎች ሲያስረዱ፣ ‹‹አማራ ክልል ከፍተኛውን ይይዛል፡፡ ሶማሌና አፋር ክልሎች ከሌሎቹ ጋር ሲነፃፀሩ የበሽታው ሥርጭት የተሻለ ነው፡፡ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጨምሮ በሌሎች ሁሉም ክልሎች የበሽታው ሥርጭት አለ፤›› ብለዋል፡፡
በበሽታው ተጠቅተው የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና ያልተደረገላቸው በኢትዮጵያ ምን ያህል ሰዎች እንደሚገኙ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ፍቅረ፣ ‹‹በፕሮግራም ደረጃ በተደረገው ሥሌት መሠረት አሁን 200 ሺሕ ያህል ሰዎች የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በአገር ደረጃ ሲታይ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች 70 በመቶ የሚሆነው የትራኮማ በሽታ ሥርጭት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ምን ያህል ሰዎች በትራኮማ በሽታ እንደተጠቁ ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ፍቅረ፣ ‹‹ቁጥሩን መግለጽ እንኳን ይከብዳል፡፡ የትራኮማ በሽታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በሽታው ኖሮባቸው ምልክቱ የማይታይባቸው በጣም ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ አሁን ተማሪዎችን ባለሙያ ትምህርት ቤት ሄዶ ካልመረመራቸው በስተቀር ለሕክምና የማይመጡበት አጋጣሚ አለ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በሽታው በባህሪው መጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው ምልክቶቹ የሚታዩት፤›› ያሉት አስተባባሪው፣ ስለዚህ ምን ያህል የትራኮማ ተጠቂዎች እንዳሉ ለማወቅ ትክክለኛ ቁጥር እንደማይኖር፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ ከ70 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝብ ለትራኮማ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ስለሚገኝ በበሽታው የመጠቃት ዕድሉ ሰፊ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁሉም ሰው በትራኮማ ተጠቅቷል ማለት ሳይሆን፣ ሊጠቃ ይችላል ብሎ ለማስቀመጥ የሚያስችል ማብራሪያ መሆኑን አክለዋል፡፡
የትራኮማ በሽታ በአማራ ክልል ከፍተኛ ሥርጭት እንዳለው፣ ሥርጭቱ ከ33 በመቶ በላይ እንደነበር፣ አሁን ግን ወደ 13 በመቶ ዝቅ ማድረግ እንደተቻለ፣ ምንም እንኳ የበሽታውን ሥርጭት 50 በመቶ መቀነስ ቢቻልም፣ በሚጠበቀው ልክ መቀነስ እንዳልተቻለና ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የውኃ አቅርቦትና የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ችግር መሆኑ ተብራርቷል፡፡
የትራኮማ በሽታን የማጥፋት ፕሮግራም ከተጀመረ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና እንደተደረገላቸው፣ በ186 ወረዳዎች የዓይን ቆብ መቀልበስ ችግር ጤና ችግር የማይሆንበት አጋጣሚ እንደተፈጠረ፣ በአሁኑ ወቅት በ295 ወረዳዎች አፍላ ትራኮማ ለማጥፋት ዝቅተኛውን የዓለም የጤና ድርጅት መሥፈርት በማሟላት 30 ሚሊዮን ለሚሆን ማኅበረሰብ ነፃ የመድኃኒት ዕደላ እንደተደረገ፣ ከ1‚400 በላይ የተቀናጀ የዓይን ጤና ባለሙያዎች በማሠልጠን የትራኮማ ሥርጭት ባለባቸው ወረዳዎች መመደብ እንደተቻለ፣ ይሁን እንጂ በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት እንዳልተቻለ፣ የዓይን ጤና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትና የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ዝቅተኛ እንደሆነ ጤና ሚኒስቴር ለሪፖርተር የላከው መረጃ ያሳያል፡፡