- የኢትዮጵያ ችግሮች ከመንግሥት አቅም በላይ ሆነዋል ሲል አቋም ይዟል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኦሮሚያ መወገን እያሳዩ እንደሆነና በሚያደርጉት ንግግርና ድርጊቶችም አቋማቸው ‹‹በወገንተኘነት ነው›› ሲሉ፣ የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅብር ኢትዮጵያ) አመራሮች ወቀሳ አቀረቡ፡፡
‹‹ወደ መጡበት አካባቢ የማዘመም ሁኔታ አሳይተዋል›› ብለው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) የወቀሱት የፓርቲው አመራሮች፣ ድርጊቶቻቸውና ንግግሮቻቸው ‹‹የመጡበት አካባቢን መሠረት የማድረግ ነገር በግልጽ ይታይባቸዋል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው በአዚማን ሆቴል ሐሙስ መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. መግለጫ በሰጠበት ወቅት የጥናትና ምርምር ምክትል ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር)፣‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ አሠላለፋቸውን ወደ [ኦሮሚያ] እያደረጉ እንደሆነ አሳይተዋል፤›› ብለዋል፡፡
ምክትል ሊቀመንበሩ በማስቀጠልም የመንግሥት ኃላፊዎች በግልጽ አቋማቸውን ባያሳዩም፣ መንግሥት በአማራ ክልል ትጥቅ የማስፈታት ሒደትን እየታዘቡ እንደሆነና ይህም ‹‹አለመተማመንን በእጅጉ ያሳድገዋል›› ብለዋል፡፡
‹‹ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት እንዲሸረሽርና ፍትሕና ነፃነት በእጁ እንዳያደርግ የሚገፋፋ አደገኛ አቋም›› እንደሆነ ፓርቲያቸው እንደሚያምን ይልቃል (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ሕዝብን ወክሎ ሁሉንም ነገሮች ማከናወን እንዳለበት፣ ካልሆነም ‹‹አንደኛውን ወክሎ ሌላኛውን መግፋት ዓይነት ጨዋታ›› እንደማያስፈልግ አክለዋል፡፡
የፓርቲውን መግለጫ በንባብ ያሰሙት ሊቀመንበሩ አቶ ግርማ በቀለ፣ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስብስብ እየሆኑ እንደመጡ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲያቸውም እነዚህ ችግሮችም ከመንግሥትና ከገዥው ፓርቲ አቅም በላይ ሆነዋል የሚል አቋም በፓርቲያቸው እንደተያዘ ገልጸዋል፡፡
በኢኮኖሚ፣ በደኅንነትና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ‹‹በእጅጉ አሳሳቢ›› ደረጃ ላይ እንደሆነ ‹‹የአደባባይ ሚስጥር›› መሆኑን የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ ፓርቲያቸው ችግሮቹን ለመቅረፍ የጋራ መግባባት ላይ መደረስ እንዳለበት ምክረ ሐሳቡ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ኅብር ኢትዮጵያ በመግለጫው በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥት የተፈረመውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚደግፈው፣ ነገር ግን ‹‹ግልጽነት የጎደለው ነው›› ሲልም ገልጾታል፡፡
ይህንን የሰላም ሒደት ‹‹ግልጽነት ጎድሎታል›› ሲሉ የተናገሩት ምክትል ሊቀመንበሩ ይልቃል (ኢንጂነር)፣‹‹ኢትዮጵያችን የአፍሪካ ዩክሬይን›› ሳትሆን መፍትሔ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡