በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን መዳወላቡ ወረዳ ዋሬ ቀበሌና በአጎራባች ስድስት ቀበሌዎች አለ የተባለው የዩራኒየምና የቶሪየም ማዕድናት ክምችት በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ቢነገርም፣ እስካሁን የከፋ አደጋ አለማስከተሉን በመግለጽ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
በቀድሞው የጨረራ መከላከል ባለሥልጣን፣ በኦሮሚያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን፣ በኦሮሚያ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን፣ በማዕድን ሚኒስቴርና በኦሮሚያ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት በተደረገ ጥናት፣ በሰዎችና በእንስሳት ላይ የዩራኒየምና የቶሪየም ክምችት አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ መታወቁን፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባወጣው የኦዲት ሪፖርት ገልጿል፡፡
የዋና ኦዲተር ሪፖርት እንደሚያሳው የቀድሞው የጨረራ ባለሥልጣን ወይም የአሁኑ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን የዩራኒየምና የቶሪየም ማዕድናት በሰዎች፣ በእንስሳትና በአካባቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጥሩ ከጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃዎችን በመውሰድና ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ስለጉዳዩ ጥናት አድርጎ መከናወን የነበረባቸውን ሥራዎችን አለማከናወኑን አስታውቋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ ስታንዳርድና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም የጨረራ አመንጭ ቁሶች ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥርን በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣንና የፈዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት አካሂዷል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ችግሩ ካለና ሕዝብ እየተጎዳ ከሆነ መፍትሔው ምን ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ጥላሁን እንደገለጹት፣ በኦሮሚያ መደወላቡ አካባቢ አለ የተባለው የዩራኒየምና የቶሪየም ክምችት በአካባቢና በኅብረተሰቡ ላይ አደጋ ሊያደርስ በሚችልበት ልክ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ክምችቱ አለ በተባለበት ቦታ ወካይ ናሙና በሦስት ዙር በመሰብሰብ ጥናትና ምርምር በማከናወን በተቋሙ ኃላፊዎች ተገምግሞ፣ በአካባቢም ላይ ሆነ በኅብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ጉዳት ሊያመጣ በሚችልበት ደረጃ አለመሆኑ መታወቁን ገልጸዋል፡፡ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ግን በኦዲት ሪፖርቱ ችግር አለ ብሏል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌታቸው በበኩላቸው ‹‹እውነት ነው ኅብረተሰባችን ተጎድቷል፡፡ የኬሚካልም፣ የባዮሎጂካልም ወይም የሌላ ዓይነት ጉዳት ሊሆን ስለሚችል ሁሉን አቀፍ ጥናት በማድረግና ነጥሎ በማየት መሠረታዊ መነሻውን ለማወቅ ከሌሎች ጋር በቅንጅት እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ከዚህ ቀደም ለቁጥጥር ሥራው አጋዥ የሆኑ ስድስት የምርመራና የተለያዩ የጥናት ሥራዎች ማከናወኑ ተገልጿል፡፡ ወደፊት ግን በቅንጅት ዘርዘር ያለ ጥናት የሚያስፈልገው መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
በማዕድን ፍለጋ ልማትና በዘርፉ በሚደረጉ የምርምር ሥራዎች ላይ የጨረራን ጉዳት ለመቀነስና ለመከላከል አስቀድሞ ከሚመለከተው አካል ጋር ማጥናት፣ እንዲሁም ዕቅድ በመያዝ መሳተፍ እንደነበረበት በኦዲት ሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
ባለሥልጣኑ የዩራኒየምና የቶሪየም ማዕድናት የጨረራ ይዘት ተፅዕኖ አለመፍጠሩን በተመለከተ የክሊኒካል ላቦራቶሪ ፍተሻ አለማድረጉን የዋና ኦዲተር ሪፖርት ያስረዳል፡፡ ዋና ኦዲተር ዋቢ ባደረገው የጥናት ውጤት በሁለት ቀበሌዎች በሚገኙ (ኦዳና እና ዋሬ) የማዕድን ቦታዎች ከተወሰዱ የአፈር ናሙናዎች የዩራኒየም፣ የቶሪየምና የፖታሺየም ክምችት በአካባቢው በኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል አስታውቆ፣ ከባለሥልጣኑ የተሰጠውን ምላሽ ለመቀበል እንደሚቸገር አክሎ አስረድቷል፡፡
በባሌ ዞን አለ የተባለው ዩራኒየምና የቶሪየም ክምችቶች በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ በኦዲት ግኝቱ ቢነገርም፣ ባለሥልጣኑ ያደረገው ጥናት ግን ጉዳት የለም ይላል፡፡