‹‹የጎርፍና የድርቅ ጉዳይ እያለ ለዚህ ምላሽ የለኝም››
የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት
ከዓረብ አገሮች ከስደት ለተመለሱ መጠለያ ለብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ቤታቸውን ያከራዩ ግለሰቦች፣ ክፍያ እየተፈጸመላቸው አለመሆኑንና በቤቶቻቸው ላይ ውድመት ቢደርስም ኮሚሽኑ የማደስ ግዴታውን አለመወጣቱን ተናገሩ፡፡
በርካታ ስደተኞችን ከሳዑዲ ዓረቢያና ከሌሎች የዓረብ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የማስመጣቱ ሒደት በተጀመረበት ወቅት በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የግለሰቦችን ቤቶች በመከራየት ሲያስጠልል የቆየው ኮሚሽኑ፣ ኪራይ ባለመክፈሉና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ አከራዮች ቅሬታቸውን እያቀረቡ ነው፡፡
ከአከራዮቹ አንደኛው የሆኑት ሰርካለም ገብረ ክርስቶስ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጉርድ ሾላ አካባቢ የሚገኝ ቤታቸውን ለኮሚሽኑ ለሁለት ዓመታታ ያህል ማከራየታቸውን፣ ነገር ግን የስድስት ወራት ሒሳብ ካለመክፈሉም በላይ ከስደት ተመላሾቹ በቤቱ በቆዩበት ወቅት ያወደሟቸውን ንብረቶች ባለማደሱ ግዴታውን እንዳልተወጣ አስረድተዋል፡፡
በአንድ ጊዜ ከ200 እስከ 300 የሚደርሱ ከስደት ተመላሾች አንድ ሺሕ ካሬ ላይ ባረፈ ግቢያቸውና ባለሦስት ፎቅ በሆነው ቤታቸው መጠለላቸውን የተናገሩት ሰርካለም (ዶ/ር)፣ በወር 185 ሺሕ ብር ሒሳብ ውል ገብተው ለሁለት ዓመታት እንዳከራዩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ በየሦስት ወሩ ክፍያ እንዲፈጽም ቢስማማም፣ ባለፉት ስድስት ወራት ክፍያ ባለመፈጸሙ ውላቸውን ለማቋረጥ እንደተገደዱ ተናግረዋል፡፡
‹‹በኮሚሽኑ ድክመት ንብረታችን ውድመት ደርሶበታል፤›› ያሉት አከራዩ፣ 1.2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት እንደወደመባቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ለኪራይ ክፍያ እየተጨቃጨቅን ነበር የስድስት ወራት እስኪቀርባቸው ድረስ ሲከፍሉን የነበሩት፤›› ያሉት ሰርካለም (ዶ/ር)፣ ሲሉም አክለዋል፡፡ ‹‹ኮሚሽኑ ቤቱን በየጊዜው ቢያስጠግነው እንዲህ ዓይነት ውድመት አይገጥመውም ነበር፤›› ሲሉ የወደሙ ንብረቶችን አለመተካቱን በተመለከተ አስረድተዋል፡፡
ሌላው ሪፖርተር ያነጋገራቸው አከራይ ወ/ሮ አሰገደች በቀለ፣ እሳቸውም ኮሚሽኑ በውላቸው መሠረት የኪራይ ክፍያና የዕድሳት ወጪ ሳይፈጸምላቸው ስደተኞቹ እንደወጡ ገልጸዋል፡፡ በሰሚት አካባቢ በ126 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ባለ ስድስት ፎቅ ማከራየታቸውን የተናገሩት ወ/ሮ አሰገደች፣ በኪራይ ውሉ መሠረት በየወሩ 145 ሺሕ ብር ክፍያ መፈጸም ነበረበት ብለዋል፡፡ ‹‹ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር እስከ ዘንድሮ ጥቅምት ወር ድረስ ያለው ክፍያ ተቆርጦ ነው የተከፈለው፤›› ያሉት አከራይዋ፣ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም. መጀመርያ ላይ ውላቸው ከመቋረጡ በፊት የነበሩ ክፍያዎች እንዳልተፈጸሙ ተናግረዋል፡፡
‹‹ኪራዩ ካለቀ በኋላ አንድ ወር የዕድሳት ጊዜ ይኖራል የሚል ነበር ውላችን፣ ነገር ግን እስካሁን ዕድሳትም አልተጀመረም፤›› ያሉት ወ/ሮ አሰገደች፣ የኮሚሽኑን ኃላፊዎች ለማነጋገር ያደረጉት ጥረትም አለመሳካቱን አስረድተዋል፡፡ የእሳቸው ቤትም ከ200 እስከ 300 የስደት ተመላሾች ይጠለሉበት እንደነበር፣ ለአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት ደግሞ ኮሚሽኑ ዕድሳት ማድረግ እያለበት እንዳላደረገ ገልጸዋል፡፡ ቤታቸውም ከ600 ሺሕ ብር በላይ የሚሆን ውድመት እንደደረሰበት አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ ዓረቢያ የማስመለስ ሒደቱ መጠናቀቁን፣ ከመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ 131 ሺሕ ዜጎች መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ኮሚሽኑ በዚህ ሳምንት ማሳወቃቸው የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ የማስመለስ ሒደት 493 ሚሊዮን ብር ከመንግሥት፣ እንዲሁም 50 ሚሊዮን ብር ደግሞ በአጋር አካላት ትብብር ለክፍያ መዋሉም ተገልጾ ነበር፡፡
ሪፖርተር የሌሎችንም ተጨማሪ አከራዮች ቅሬታ ከሰማ በኋላ የኮሚሽኑን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴን ለማነጋገርና መልስ ለማግኘት ባደረገው ጥረት፣ ‹‹እንደ ማንኛውም ቦታ ገንዘቡ ምናልባት ሊዘገይ ይችላል፤›› ያሉት አቶ ደበበ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ፍላጎት እንደሌላቸው ተናግረው፣ ‹‹የጎርፍና የድርቅ ጉዳዮች እያሉ፣ ለዚህ ቅሬታ መልስ አልሰጥም፤›› በማለት እያነጋገራቸው ያለውን ዘጋቢ በመሳደብ ስልክ ዘግተውበታል፡፡