Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሻይ ቅጠል ከሚያመርቱ ሦስት ድርጅቶች የሁለቱ ፈቃድ እንዲነጠቅ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሻይ ቅጠል አምርተው ኤክስፖርት ያላደረጉ ሁለት ድርጅቶች የንግድና የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲነጠቅ፣ የሚመለከታቸውን የመንግሥት ተቋማት በደብዳቤ መጠየቁን አስታወቀ፡፡

ሻይ ቅጠል ለማምረት ውል ፈጽመው ከሚሠሩ አርሶ አደሮች ውጪ፣ አምራች ድርጅቶች ሦስት ብቻ መሆናቸውን፣ ከእነሱም ውስጥ ሻይ ቅጠል በማምረት ኤክስፖርት የሚያደርጉት የኢትዮ አግሪ ሴፍት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አካል የሆኑት ጉመሮና ውሽውሽ እርሻ ልማት ድርጅቶች ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ኢስት አፍሪካ የተባለው ድርጀትና በጋምቤላ ክልል የማምረቻ መሬት ወስዶ እስካሁን ወደ ሥራ ያልገባው ቨርዳንታ፣ የሻይ ቅጠል ምርት ወደ ውጭ ለመላክ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የቡናና ሻይ ባለሥልጣንን የ2015 በጀት ዓመት የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በገመገሙበት መድረክ ላይ የተገኙት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር፣ ስለድርጅቶቹ አፈጻጸም ገለጻ አድርገዋል፡፡

አቶ ሻፊ፣ ሻይ ቅጠል በማምረት ኤክስፖርት የሚያደርጉት የኢትዮ አግሪ ሴፍት አካል የሆኑት ጉመሮና ውሽውሽ እርሻ ልማት ድርጅቶች ብቻ መሆናቸውን ተናግረው፣ ኢስት አፍሪካ የተባለው ድርጅት ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሻይ ቅጠል እያመረተ ቢሆንም እስከተያዘው ዓመት ኤክስፖርት እንዳላደረገ፣ እንዲሁም ቨርዳንታ የተባለው ድርጅት በጋምቤላ ክልል መሬት ወስዶ እስካሁን ድረስ ኤክስፖርት አለማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

ድርጅቶቹ ኤክስፖርት እንደማያደርጉና ከዚያ ይልቅ ምርታቸውን በአገር ውስጥ እያቀረቡ ስለሆነ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዕርምጃ እንዲወስዱ እንቅስቃሴ መጀመሩን ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ገልጸውላቸዋል፡፡

ድርጅቶቹ ያለባቸው ችግር ምን እንደሆነ ለማረጋጋጥ ጥረት መደረጉን የተናገሩት አቶ ሻፊ፣ በዋናነት ‹‹ገበያ እያፈላለግን ነው›› የሚል ምክንያት እንደሚያቀርቡና ፍላጎታቸው በአገር ውስጥ ገበያ የመሸጥ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በሁለቱ ድርጅቶች የንግድ ፈቃድና የኢንቨስትመንት ፈቃድ ላይ ተገቢውን ማስጠንቀቂያና ዕርምጃ እንዲወስዱ፣ በደብዳቤና በአካል በመቅረብ ንግግሮች መጀመራቸውን አቶ ሻፊ ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ከሻይና ከቅመማ ቅመም ኤክስፖርት ይገኛል የተባለው የውጭ ምንዛሪ ከታቀደው አንፃር በተለይ ከሻይ ምርት ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለአፈጻጸም ማነሱ ምክንያቱ ምንድነው የሚል ጥያቄ ከግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የሻይና የቅመማ ቅመም ኤክስፖርታችንን ከዓምና ዕቅዳችን አንፃር ስንመለከት ብዙም የሄደበት ሁኔታ የለም፡፡ ሆኖም በሚቀጥሉት ወራት በደንብ መሥራት የሚቻልበት ዕድል ይኖራል፤›› ሲሉ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹በእጃችን ያሉ የሻይ ምርቶች ወደ ውጪ ገበያ መቅረብ ስላለባቸው በየጊዜው በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር እየተነጋገርን፣ ወደ ውጭ እንዲልኩ ግፊት የማድረግና በጥራት እንዲያቀርቡ የማድረግ ሥራ በመሠራቱ የተሻለ ነገር መጥቷል፤›› ሲሉ አቶ ሻፊ አስረድተዋል፡፡

የሻይ ምርት ኤክስፖርት መቀነሱ ከምርትና ከምርታማነት ጋር የሚገናኝ እንደሆነ በመድረኩ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም በርካታ ችግሮች እንዳሉ ተጠቅሶ ከእነዚያም መካከል የማዳበሪያ አቅርቦት ማነስ አንዱ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በፋብሪካዎች ላይ ተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ ችግር እንደነበረ ያስታወሱት ሌላው ከባለሥልጣኑ የመጡ የሥራ ኃላፊ፣ በተለይም በጉመሮ አካባቢ በነበረ የበረዶ ክስተት በሰብል ላይ ጉዳት መድረሱንና ምርት መቀነሱን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በፀጥታ ችግር ምክንያት ምርት ለመሰብሰብ የሚፈለገው የሰው ኃይል ማግኘት ሳይቻል መቅረቱ ተጠቁሟል፡፡

ችግሩን ለመፍታት አንደኛው መፍትሔ ምርትና ምርታማናትን ማሳደግ መሆኑን፣ ለዚህም ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ እየተገባ ነው ተብሏል፡፡ ክልሎችም ኃላፊነት ወስደው እየሠሩበት እንደሆነ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

በዋናነት በሻይ ምርት ያለው የኢንቨስትመንት ውስንነት ተገልጾ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት እንደሚፈልግ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ገበያ ላይ ፍላጎትን የሚያሟላ ምርትና ምርታማነት ሊኖር ይገባል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች