በምርት መሰብሰቢያ ወቅት በቂ የፋይናንስ ድጋፍ አለመገኘትን ጨምሮ የኤክስፖርት ምርት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ያጋጠመው የፀጥታ ችግር፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የውጭ ግብይት ድርሻ አፈጻጸምን ዝቅ ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡ ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ የኅብረት ሥራ ኮሚሽን የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም፣ ለፓርላማው የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲቀርብ ነው፡፡
በበጀት ዓመቱ የስምንት ወራት ኅብረት ሥራ ማኅበራት 28 ሺሕ ቶን የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ወደ ውጭ ልከው፣ 131.2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ቢታቀድም፣ ነገር ግን በ14 ማኅበራት 5,110 ቶን የሚጠጋ ምርት ወደ ውጭ ተልኮ 36.3 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መገኘቱ ተገልጿል፡፡
ለአብነትም በስምንት ወራቱ በኅብረት ሥራ ዩኒየኖች የተላከው ቡና ከሦስት በመቶ እንዳልበለጠ፣ ይህም የሆነው የቡና ግዥ ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑና ከዓለም አቀፍ ዋጋ ጋር መወዳደር ባለመቻሉ ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙመድ፣ በስምንት ወራት የኅብረት ሥራ ማኅበራት የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በመላክ የነበራቸው የውጭ ግብይት ድርሻ ከታቀደው ዕቅድ 18 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኤክስፖርት ምርቶች በሚባሉት ቡናና ቦሎቄ ላይ ያጋጠመው የውጭ ዋጋ መቀዛቀዝ፣ በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ያለው የቡና ዋጋ ከፍተኛ መሆን የማኅበሩ አባላት ምርቱን ለማኅበራት ከመስጠት ይልቅ ለደላላ መሸጥን እንደ አማራጭ በመውሰዳቸው፣ ለአፈጻጸሙ ዝቅ ማለት ተጠቃሾቹ ምክንያቶች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል በምርት መሰብሰቢያ ወቅት በቂ የፋይናንስ ድጋፍ አለመገኘቱ፣ የመጋዘን ችግር፣ እንዲሁም ቦሎቄና ሰሊጥ አምራች በሆኑት የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች (ትግራይና አማራ ክልሎች) በነበረው የፀጥታ ችግር በቂ ምርት እንዳልተሰበሰበ፣ በተመሳሳይ በወለጋ አካባቢም ተመሳሳይ ችግር በማጋጠሙ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ አፈጻጸም ዝቅ ማለቱን አቶ አብዲ የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
በተያያዘም የኅብረት ሥራ ማኅበራት የአገር ውስጥ ግብይት አፈጻጸም ድርሻቸው በማሳደግ በዓመቱ ከአጠቃላይ ግብይት 28 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው ኮሚሽኑ ያቀደ መሆኑንና ይህም የሰብል ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬና እንስሳት ማቅረብን የሚያካትት ነው ተብሏል፡፡
በስምንት ወራቱ ውስጥ 1.8 ሚሊዮን ቶን አጠቃላይ ምርቶችን በኅብረት ሥራ ማኅበራት ለማቅረብ ታቅዶ 1.2 ሚሊዮን ቶን መቅረቡ ታውቋል፡፡
‹‹የኅብረት ሥራ ማኅበራት የአገር ውስጥ ግብይት በማሳደግ በኩል አፈጻጸማችን በሚፈለገው ልክ አይደለም፤›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ከገበያ ምርቶች ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተወዳዳሪ መሆን አለመቻላቸው ዋነኛው ችግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጤፍ፣ በስንዴና በመሳሰሉት የግብርና ምርቶች ላይ የሚፈለገውን ምርት መሰብሰብ አለመቻሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያት ከሆኑት ውስጥ የሕገወጥ ንግድና የደላሎች ጣልቃ ገብነት ዋነኛው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የገዥዎች መበራከት (ሕጋዊ ሆነው ሰፊ የምርት ግዥ የሚፈጽሙ) ከምርት እጥረት ባሻገር የመግዣ ዋጋ እንዲንርና ምርት የመሸሸግ ድርጊቶች እንዲበራከቱ ማድረጉን አቶ አብዲ አስታውቀዋል፡፡ ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚፈለገውን ምርት በጊዜው ይዘው በመጋዘናቸው እንዳያስቀምጡ ችግር እንደገጠማቸው አክለዋል፡፡
በሌላ በኩል የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራ በቁጠባም ሆነ በብድር ሥርጭት በስምንት ወራቱ ውስጥ አመርቂ ውጤት እንዳስመዘገቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን የገንዘብ ቁጠባና ብድር ማኅበራቱን ወደ ትልልቅ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ከማሳደግ ባሻገር በየክልሉ ያላቸው ተደራሽነት እንዲሰፋ ይገባል ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ 25 ሚሊዮን አባላት ያሏቸው አምስት ክልላዊ ፌዴሬሽኖች፣ ከ395 በላይ የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች፣ እንዲሁም 105 ሺሕ ያህል መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ይገኛሉ፡፡