Monday, June 17, 2024

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው ስለ ለውጡ በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን እየተመለከቱ አገኟቸው]

 • እኔ ምልህ፣ ቴሌቪዥኖቹ በሙሉ የለውጡ ጉዞ አምስት ዓመት ሞላው የሚሉት ምኑን ነው? የምን ለውጥ ነው?
 • በቀላል አማርኛ አሁን ያሉት የለውጡ መሪ ወደ ሥልጣን የመጡበት አምስተኛ ዓመት ማለታቸው ነው።
 • አምስት ዓመት ሞላቸው እንዴ?
 • አዎ።
 • ታዲያ አምስት ዓመት ከሞላቸው ለምንድነው ሦስት ዓመት ይቀረኛል የሚሉት? ምርጫ ሊያራዝሙ አስበው ነው እንዴ?
 • እንደዚያ አይደለም።
 • እ?
 • የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት የእሳቸው አልነበረም።
 • እንዴት ማለት?
 • የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን ዘመን ነበር። ነገር ግን በፈቃዳቸው ሥልጣን በመልቀቃቸው የለውጡ መሪ ተተኩ። በምርጫ ከተመረጡ ደግሞ ሁለት ዓመታቸው ነው።
 • የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ለምንድነው ሥልጣን የለቀቁት?
 • ፈልገው ነው በፈቃዳቸው የለቀቁት።
 • በፍላጎትማ ሥልጣን አይለቀቅም።
 • ማንም አላስገደዳቸውም ስልሽ። ፈቅደው ነው የለቀቁት።
 • ባለፈው ፓርላማ ላይ ሥልጣን እንዴት እንደሚለቀቅ በብርጭቆ ሲያስረዱን አልነበር?
 • አዎ።
 • እንደዚያ እንዳይሆን የለቀቁት።
 • ማን?
 • የቀድሞው መሪ።
 • እንዴት?
 • ውኃ የሞላው ብርጭቆው ውስጥ እንትን ገብቶ።
 • ምን?
 • ድንጋይ!
 • በይ ሌላ ቦታ እንደዚህ እንዳትናሪ?
 • እንዴት?
 • ነገርኩሽ እንደዚህ ስትናገሪ እንዳልሰማሽ?
 • እንዴት? ምን ተናገርኩ?
 • ድንጋይ ለማለት የፈለግሽው ማንን ነው?
 • እኔ ምሳሌውን ደግሜ ተናገርኩ እንጂ፣ አንተ የሰጠኸውን ትርጉም አላልኩም። ጨርሶም አላሰብኩትም።
 • ይህንን የተናገርሽው ሌላ ቦታ ቢሆን ማንም ምክንያትሽን አይሰማም ነበር። አንጠልጥለው ነበር የሚወስዱሽ።
 • ወዴት?
 • ቃሊቲ ወይም ቂሊንጦ ነዋ። ይወረውሩሽ ነበር።
 • ምንም ሳላጠፋ? ያላልኩትን ተርጉሞ ማሰር ይቻላል አንዴ?
 • አይደለም ለአንቺ፣ ለእኔም ትተርፊኝ ነበር።
 • በዚህ ንግግር ለዚያውም በእናንተው በሰጣችሁት ትርጓሜ ቃሊቲ የሚያስወርድ ከሆነማ በተቃራኒው ይሆናል?!
 • ምኑ?
 • ለውጡን በማጽናት ፈተናዎችን መሻገር የምትሉት።
 • እንዴት ነው በተቃራኒው የሚሆነው?
 • ቦታው ተለዋውጠው።
 • ምኖቹ?
 • ለውጡና ፈተናው።
 • አልገባኝም?
 • ለውጡን በማጽናት ፈተናዎችን መሻገር አይደል ያላችሁት
 • እ?
 • ፈተናዎችን በማጽናት ለውጡን መሻገር ይሆናል ማለቴ ነው!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የመንግሥት ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ጋር ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የተመለከተ ቃለ መጠይቅ እያደረጉ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር የሰሜኑ ግጭት በኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ ያደረሰው መስተጓጎል ምን ያህል ነው።
 • በጣም የሚገርመው በግጭት ውስጥ ሆነን እንኳን የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እያደገ እንጂ መስተጓጎል አልገጠመውም።
 • እንዴት ሊሆን ቻለ? እስኪ ያብራሩልኝ?
 • ለምሳሌ ባለፉት ስምንት ወራት ሦስት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ተችሏል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ16 በመቶ ብልጫ አለው። ስለዚህ ዕድገት እንጂ ፍሰቱ አልተስተጓጎለም።
 • ለመሳብ ከተቻለው የውጭ ኢንቨስትመንት ውስጥ ምን ያህሉ ወደ ኢንቨስትመንት ገብቷል?
 • እሱ አሁን አይታወቅም።
 • ታዲያ እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል?
 • አብዛኞቹ ፅኑ ፍላጎት እንዳላቸው ማረጋገጥ ይቻላል።
 • ዓምናም ሆነ ዘንድሮ መሳብ ከተቻለው ውስጥ እስካሁን ወደ ኢንቨስትመንት የገቡ የሉም ማለት ነው? ወይስ መረጃው አልደረሰዎትም?
 • መረጃውን በቀጣይ የምናየው ይሆናል። ነገር ግን ፅኑ ፍላጎት እንዳላቸው እርግጠኛ መሆን ይቻላል።
 • ጥሩ። እስኪ ከአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ ረገድ ያለውን አፈጻጸም እንመልክት። በግጭቱ ምክንያት የገቢ አሰባሰቡ አልተደናቀፈም?
 • ይገርምሀል። በአገር ውስጥ የሚሰበሰበው ገቢ በየዓመቱ እስከ 20 በመቶ ዕድገት የሚመዘገብበት ነው። በአጠቃላይ በዚህ ረገድ ጥሩ ስኬት ነው ያለው።
 • የሚሰበሰበው ገቢ ከአጠቃላይ ጂዲፒው አንፃር ምን ያህል ነው?
 • በገቢ ረገድ ያለው ትልቅ ችግር ከጂዲፒ ጋር ያለው ጥምርታ ነው። ከዓመት ዓመት በማሽቆልቆል ላይ ነው።
 • አሁን ያለው የገቢና የጂዲፒ ጥምር ምጣኔ ምን ያህል ነው?
 • ከአምስት ዓመታት በፊት 11 በመቶ ነበር።
 • አሁን ያለውን ነው የጠየኩት?
 • የዘንድሮው የሚታወቀው በዓመቱ መጨረሻ ላይ ነው።
 • የስምንት ወሩን ማወቅ አይቻልም?
 • ይቻላል ግን ሙሉ ሥዕሉን የሚገልጸው ዓመቱ መጨረሻ ላይ የሚሰበሰበው ገቢ ሲታወቅ ነው።
 • እሺ ዓምና የነበረው ምጣኔ ምን ያህል ነበር?
 • ስምንት በመቶ ነበር።
 • የአፍሪካ አገሮች አማካይ ምጣኔ 18 በመቶ ነው። አሁን የነገሩኝ ቁጥር ግን በጣም ዝቅተኛ ነው። ኢኮኖሚው ቆሟል ወይም ገቢ እየተሰበሰበ አይደለም ማለት ነው?
 • የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን መዘንጋት የለብህም።
 • የሕዝብ ቁጥር መጨመር ከአገር ወሰጥ ገቢ መቀነስ ጋር ምን ያገናኘዋል?
 • ለምን አይገናኝም? ይገናኛል!

[ሚኒስትሩ ቃለ መጠይቁን ጨርሰው እንደወጡ ጋዜጠኛው ከአለቃው ስልክ ተደወለለት] 

 • እሱን ቃለ መጠይቅ አቆየው።
 • ለምን? ጥሩ ቃለመጠይቅ እኮ ነው።
 • የምልህን አድርግ። በተጨማሪም …
 • በተጨማሪ ምን?
 • የተጠራቀመ የዓመት ዕረፍት አለህ ተብሏል።
 • ስለዚህ?
 • ዕረፍት መውጣት አለብህ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን ቅሬታውንም አልሰማሁም። እንዴት? አልሰማሁማ? የምን ቅሬታ ቀርቦባቸው ነው? ሰሞኑን ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ውድና ቅንጡ አውሮፕላን ተከራይተዋል የሚል ቅሬታ...