Tuesday, September 26, 2023

የለውጡ ሐዲድና አምስቱ ዓመታት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር፣ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ሰላማዊ የመንግሥት ለውጥ በመደረጉና አዲሱ አስተዳደር በወሰዳቸው ፈጣን ዕርምጃዎች የተበረታቱ ዜጎች፣ በየአደባባይ ወጥተው ከለውጡ ጎን መቆማቸውን በድጋፍ ሠልፎች ሲያረጋግጡ  በስፋት ተስተውሏል፡፡

‹‹ለውጡን እንደግፍ ዴሞክራሲን እናበርታ›› በሚል መሪ ቃል ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ የተጠራው ታላቅ የድጋፍ ሰላማዊ ሠልፍ ደግሞ፣ ሕዝቡ በአገሪቱ ለመጣው ለውጥ የሰጠውን ከፍተኛ ድጋፍ በጉልህ ያንፀባረቀ ነበር፡፡ በዕለቱ የደረሰው የቦምብ ፍንዳታና የሰዎች ለጉዳት መዳረግ የሠልፉን ዓውድ የቀየረው ቢሆንም፣ የፖለቲካ ለውጡ በስሜት ፈንቅሎ ወደ አባባይ ለመደገፍ የወጣው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ መሆኑ ግን ማስታወሻ ጥሎ ያለፈ አጋጣሚ ነበር፡፡

በአንድ ወገን የሕዝቡ የረዥም ጊዜ የዴሞክራሲ ጥያቄ በለውጡ ምላሽ አገኘ ብለው ያመኑ በርካታ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል አምባገነናዊ ሥርዓት ያከተመበት የፖለቲካ ምዕራፍ ነው ብለው የወሰዱም ብዙ ነበሩ፡፡ ከሁሉም አቅጣጫ ለለውጡ ድጋፍና ሙገሳ በሚጎርፍበት በዚያ ወቅት ግን፣ ለውጡን በሩቁ በቀቢፀ ተስፋ የሚታዘቡ ወገኖች ተሠልፈው ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለውጡ መስመሩን ስቶ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊገባ ይችላል የሚል ጥርጣሬም ያሳደሩ ወገኖች ነበሩ፡፡

ከሁሉ በተለየ ደግሞ ለውጡን ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር በአግባቡ ማዋል ስለሚቻልበት ሁኔታና መስመሩን እንዳይስት፣ ከስሜታዊነት በፀዳ ሁኔታ ምክረ ሐሳባቸውን ለመለገስ የሞከሩት ወገኖችም መኖራቸው ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡

ለውጡ አገሪቱን ወዴት ለማሻገር እንዳሰበ ራሱን የቻለ ፍኖተ ካርታ እንዲበጅ የወተወቱ በርካታ ነበሩ፡፡ ለውጡን የሚመራው አስተዳደር ‹‹ኢትዮጵያ አዲሲቷ የለውጥ አድማስ›› በሚል ርዕስ ባለ አንድ ገጽ የዕቅድ ሰሌዳ ይፋ ማድረጉ፣ ልክ እንደ አንድ ትልቅ ፍኖተ ካርታ ነበር የተቆጠረው፡፡ አስተዳደሩ በ2011 እና በ2012 ዓ.ም. የማካሂዳቸው ብሎ ወደ 34 መርሐ ግብሮችን ይፋ ማድረጉ በአጭር ጊዜ ከወሰዳቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካሰጡት ዕርምጃዎች ጋር ተዳምረው፣ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ ለማሻገር ትክክለኛው አስተዳደር አስመስለውት ነበር፡፡

የለውጡ ከፍተኛ መሪዎች በመላ አገሪቱና ዳያስፖራው ባለበት ሥፍራ የተለያዩ መድረኮች ተገኝተው ስለዴሞክራሲያዊ ሽግግር የገቧቸው ቃሎች ደግሞ፣ በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ የተሳካለት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን ይሆናል የሚለውን እምነት በብዙዎች ዘንድ ያሳደረ ሊባል ይችላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማ ቀርበው የገቧቸው ቃሎችም መንግሥታቸው ከሕዝቡ ጋር ያሰረው እንደ አዲስ ማኅበራዊ ውል (Social Contract) መቆጠሩም ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡

ይህም ቢሆን ግን ለውጡ ሐዲዱን መሳት የለበትም የሚለው የፖለቲካ ልሂቃን ውትወታ ከዚሁ ጎን አብሮ ነው የዘለቀው፡፡

ለውጡ በተከሰተ በስድስተኛ ወሩ ሕዝቅኤል ጋቢሳ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹Managing Political Transition in Ethiopia: The Choice Factor›› በሚል ርዕስ ለውጡ በምን አግባብ መመራት እንዳለበት የራሳቸውን ምልከታ አጋርተው ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1990 የሶቪየት ኅብረት መበተን በኋላ በርካታ አገሮች የዴሞክራሲ ሽግግርን ቢሞክሩም የተሳካላቸው ግን ጥቂቶች ብቻ መሆናቸውን እንደ ምሳሌ ያነሱት ሕዝቅኤል (ፕሮፌሰር)፣ በዚህ መሰሉ ሒደት ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮችን አውስተው ነበር፡፡

‹‹የለውጥ ወይ የሽግግር ሒደት ውስጥ የገቡ አገሮች ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊያመሩ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ሁሉ፣ ከፊል አምባገነናዊና የለየለት አምባገነናዊ ሥርዓት ውስጥም ሊወድቁ ይችላሉ፤›› ሲሉ ሞግተዋል፡፡

በዚህ መሰሉ የሽግግር ሒደት የለውጡን ውጤታማነት ሊወስኑ የሚችሉ ነገሮችንም ፕሮፌሰሩ ያስቀምጣሉ፡፡ ‹‹በሽግግሩ ሒደት የሚሳተፉ የፖለቲካ ልሂቃን የሚጫወቱት አሉታዊ/አዎንታዊ ሚና፣ እንዲሁም ለውጡን የሚሾፍሩት መሪዎች ሚናና የተፎካካሪ ፖለቲካ ኃይሎች ሚና አወንታዊነትና አሉታዊነት የለውጡን ስኬት የሚበይን ነው፤›› በማለትም ገልጸዋል፡፡

ልክ እንደ ሌሎች ሁሉ በለውጡ ማግሥት ቀድመው ስለለውጡ መንገድ ምክረ ሐሳብ ከሰጡት አንዱ የሆኑት የአሁኑ የኢዜማ ፓርቲ መሪና የያኔው የግንቦት ሰባት መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሁለት ምክንያቶች ጥንቃቄ እንደሚሻ ተናግረው ነበር፡፡

‹‹ዓብይ (ዶ/ር) በቃላት ለማድረግ የሚፈልጓቸው ነገሮች እኛም ለማድረግ የምንፈልጋቸውና የታገልንላቸው ናቸው፡፡ እንዲሳካላቸው ከልብ መመኘት ብቻ ሳይሆን ልናግዛቸውም እንፈልጋለን፡፡ እኛ እነዚህን ውጤቶች ነው የምንሻው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመጣ የማገዝ እንጂ ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት ኖሮን አያውቅም፤›› ብለው ነበር፡፡

ፕሮፌሰሩ ሲቀጥሉም፣ ‹‹አሁን ያለው የፖለቲካ ኃይል አሠላለፍ እውነተኛ የዴሞክራሲ ለውጥ ካልሆነ ጥገናዊ ለውጥ ዕውን ይሆናል፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ጥገናዊ ለውጥ እያመሩ ላለመሆኑ ማረጋገጫ ማግኘት እንሻለን፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ይህን ካሉና ለውጡ ከተጀመረ እነሆ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ እስካሁን የለውጡን ጥገናዊ ለውጥነት ወይም የተሟላ ዴሞክራሲያዊነት አረጋግጠው መሆን አለመሆኑን ግን ምላሽ ሰጥተውበት አያውቁም፡፡

ለውጡ እንደ ተጀመረ ሰሞን የተወሰዱ ዕርምጃዎች በእርግጥ የብዙዎችን ተስፋ ያለመለሙ ነበሩ፡፡ ከፀረ ጥላቻ ንግግር አዋጅ መውጣት ጀምሮ አሳሪና አፋኝ የነበሩ አዋጆችን ለማሻሻልና ለመቀየር ብዙ ሥራ መታየቱ የመጀመሪያው የለውጡ ትሩፋት ተብሎ መገለጽ ይችላል፡፡ ከሕግ ማዕቀፍና ከፍትሕ ሥርዓቱ ማሻሻያዎች ጎን ለጎን ተቋማዊ ሪፎርሞች በየሴክተሩ ስለመካሄዳቸው በሰፊው ሲነገር ነበር፡፡ በመከላከያና በደኅንነት ተቋማት ተደረገ ከተባለው ሪፎርም በተጓዳኝ በትምህርት ዘርፉ መተግበሩ የተነገረው የትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ ፎኖተ ካርታ ለውጡ ያስገኛቸው ውጤቶች ሲባሉ ከርመዋል፡፡

የሚዲያዎች በነፃነት መንቀሳቀስ መፈቀድ፣ የታጠቁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሳይቀሩ ወደ አገር ገብተው ሁሉም ተቃዋሚዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ መፈቀዱ በለውጡ የተገኙ የዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት ውጤቶች ሲባል ነበር፡፡ በለውጡ ማግሥት ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ እናፀናለን የሚለው የለውጡ መንግሥት ቃል ያለ ብዙ ውጣ ውረድ ዕውን ይሆናል የሚለው ግምት ከፍተኛ ነበር፡፡ በሒደት ግን አገሪቱን ተደጋጋሚ ቀውሶች ያጋጥማት ጀመረ፡፡ በሌላ በኩልም ለውጡን ይመሩ፣ ይደግፉና ይከተሉ ከነበሩ ወገኖች ጥቂት የማይባሉ በየፌርማታው መውረድ ሲጀምሩ ለወጡ መስመሩን እየሳተ ነው የሚለው ሥጋት እየሰፋ መጣ፡፡

ለውጡ በመጣ በጥቂት ወራት ልዩነት ከኃላፊነታቸው በክብር የተሰናበቱት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ ‹‹በአገራችንም ሆነ በአኅጉራችን ያልተለመደው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለትውልድ ጠቃሚ በመሆኑ ጀምረነዋል፡፡ እኔም የታሪኩ አካል ስሆን ከግል ጥቅም ይልቅ የአገራዊና የሕዝብ ጥቅም መቅደም እንዳለበት ከግምት በማስገባት ነው፤›› ሲሉ የስንብት ንግግር አድርገው ነበር፡፡

በዚህ ረገድ ይታይ የነበረው የአመራር መተካካቱ፣ የመዋቅር ለውጡና የአመራር ሽግሽጉ ሁሉ በወቅቱ ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር መስመር ጠቃሚ ዕርምጃ ተብሎ ተገምቶም ነበር፡፡

እንደ ሌንጮ ባቲ ያሉ አንጋፋ የፖለቲካ ሰዎች ‹‹ኢትዮጵያን የምትደግፉ ሁሉ የለውጡ መሪዎችን ደግፉ›› ብለው እስኪናገሩ ድረስ፣ በጊዜው ከለውጡ ጎን መቆም ሁሉም የተቀበለው የስምምነት ውጤት ይመስል ነበር፡፡

‹‹ኃይሌ ፊዳ የደቡብና የአማራ ልሂቃንን ለመሰብሰብ ቢሳካለትም ኦሮሞን መሰብሰብ ግን አልቻለም፡፡ የእኛ ድርጅት ኦነግ ኦሮሞን በመሰብሰብ የተዋጣለት ቢሆንም ሌላውን ግን መሰብሰብ አልቻለም፡፡ ኦሮሞንም ሆነ ሌላውንም መብሰብ የቻሉት እነ ዓብይ (ዶ/ር) እና ለማ ናቸው፤›› በማለት ነበር የጊዜውን ለውጥ ሁሉም ወገን ከጎኑ ቆሞ እንዲደግፍ ሌንጮ የቀሰቀሱት፡፡

ሕወሓት በመስከረም 2011 ዓ.ም. በመቀሌ ባደረገው 13ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ፣ ‹‹አገራችን አሁንም አደጋ ላይ ስላለች የትግራይ ሕዝብ የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ ይቀጥል›› የሚል መግለጫ አውጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ በለውጡ የመጀመሪያ ሰሞናት ለውጡን የሚደግፉ  አቋሞችን ልክ እንደ ሌሎች ከማንፀባረቅ ወደኋላ ሲል አልታየም ነበር፡፡

ሕወሓት ለመጨረሻ ጊዜ በተካፈለበት የሐዋሳው የኢሕአዴግ ጉባዔ ላይ የጉባዔው የአቋም መግለጫዎች ተብለው የተንፀባረቁ ነጥቦች፣ የሕወሓትን የጊዜውን አቋም የሚያመላክቱ እንደሆኑ ይነገራል፡፡

‹‹በአገራችን ሕዝቦች አነሳሽነትና በኢሕአዴግ መሪነት አገራችን ወደ ተስፋ ሰጪ የለውጥ ምዕራፍ ገብታለች፡፡ ይህ የለውጥ ምዕራፍ የፈነጠቀው የተስፋ ብርሃን በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ መነቃቃትን ከመፍጠሩም ባሻገር ለዘመናት ተኮራርፈው የዘለቁ ወገኖች እንዲታረቁ፣ የታሰሩ እንዲፈቱና የተለያዩ እንዲገናኙ በማድረግ ብሔራዊ መግባባት ከፍ እንዲል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ በጉባዔያችን ታይቷል፤›› በማለት የገለጸው ኢሕአዴግ፣ ‹‹ለውጡ ሕዝባዊ፣ ሕገ መንግሥታዊና ኢሕአዴጋዊ መሆኑን በመተማመን እንዳይቀለበስ የየራሳችንን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት ተስማምተናል፤›› በማለት ነበር የጋራ አቋም ያንፀባረቀው፡፡

ሕወሓት የነበረበት ኢሕአዴግ ያን ጊዜ ይህን ይበል እንጂ በሒደት ግን በለውጡ መዘዝ ከብልፅግና ጋር ወደ ግጭት ማምራታቸውን፣ በጦርነቱ ዋዜማና ከዚያም ወዲህ ሲናገር ተደምጧል፡፡ ለውጡ መስመሩን ስቷል ያለው ሕወሓት ብዙም ሳይሰነብት ብልፅግናን አልቀላቀልም ብሎ ራሱን ማግለሉ፣ አገሪቱ አሁን ለምትገኝበት ምዕራፍ መነሻ ሆኖ ሲቀርብም ይታያል፡፡

በለውጡ ሰሞን የታዩ የሪፎርም ጅምሮች በሒደት መቀዛቀዝ ሲጀምሩ ለውጡን በሚመለከት የሚነሱ የፖለቲካ ውዝግቦችና አለመግባባቶች እየበረከቱ ሄዱ፡፡ ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው፣ ‹‹እንኳን ምርጫ ልናካሂድ ሕዝብ መቁጠር አልቻልንም፡፡ የሚመጣው ምርጫ መከራና ዕዳ ነው ይዞ የሚመጣው በእኛ ዕምነት፤›› ሲሉ እንደተናገሩት ሁሉ፣ ብዙ ውዝግቦች ታልፎ ብሔራዊ ምርጫ ቢካሄድም የአገሪቱን ፀጥታ ሁኔታ አለመለወጡ በሒደት ታይቷል፡፡

‹‹A Clash of Nationalism and the Remaking of the Ethiopian State: The Political Economy of Ethiopian Transition›› በሚል ርዕስ በ2014 ዓ.ም. የቀረበ አንድ ሪፖርት፣ ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ በርካታ ለውጦች ተከስተዋል ይላል፡፡ ‹‹አዳዲስ ሹመቶችና አዳዲስ መዋቅሮች በሲቪል ሰርቪሱ ተካሂዷል፡፡ ያለፈው መንግሥት ባለሥልጣናትን ለመተካት ጥረት ተደርጓል፡፡ በሀብት አስተዳደርና በተቋማት አሠራር ከተደረጉ ለውጦች በተጨማሪ፣ ክልሎች በፌደራል መንግሥቱ ያላቸው ሚናም እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ መንግሥት በለውጡ ማግሥት የወሰዳቸው የለውጥ ዕርምጃዎች በርካታ ከመሆናቸው አንፃር በጥንቃቄ መፈተሽና መለካት ይኖርባቸዋል፡፡ በአገሪቱ የመጡ ለውጦችን በአግባቡ መፈተሽና ማወቁ ደግሞ፣ ለቀጣዩ የአገር ልማትና ጉዞ ወሳኝ ዕርምጃም ነው፤›› በማለት ሪፖርቱ ያብራራል፡፡

ዛሬ ግን ከዚህ ይልቅ ለውጡን በሚመለከት የሚራመዱ አቋሞች ፍፁም የተራራቁና ሊቀራረቡም የማይችሉ ነው የሚመስለው፡፡ በመንግሥት በኩል ለውጡ አገሪቱን በዕርምጃዎቹ በብዙ መንገዶች ተጠቃሚ ስለማድረጉ ጎላ ያለ ሐሳብ ይንፀባረቃል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው በቆሙ ወገኖች ዘንድ ግን ለውጡ ነውጥ ነው የወለደው የሚል ሙግት ይነሳል፡፡

መጋቢት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ለውጡ የተመዘገበበት አምስተኛ ዓመት ከሰሞኑ ሲታሰብ፣ በመንግሥት በኩል በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸው ሲነገር ነበር፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ችግሮችን በመቅረፍ ግንባታውን ማፋጠን ስለመቻሉ በስኬት ተነስቷል፡፡ በጅምር የቀሩ ፕሮጀክቶችን ከዳር ማድረስ፣ ሰላምና ፀጥታን ማረጋገጥ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የተቋማት ግንባታን ዕውን ማድረግ፣ የዴሞክራሲ ልምምዶችን ማጠናከር የሚሉ የለውጡ ዓመታትን ስኬቶች መንግሥት በሰፊው ሲያቀርብ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒ የቆሙ ወገኖች የብልፅግና መንግሥት ለውጡን በተገቢው መንገድ አልመራውም፣ ለሕዝቡ የገባቸውን ቃሎችም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ውጪ በአግባቡ አልፈጸመም ሲሉ ይተቻሉ፡፡

ከሁለት ዓመት ቀደም ብሎ ‹‹The War in Tigray is a Result of Ethiopia’s Mismanaged Transition›› በሚል ሰፊ ሀተታው የአገራዊ ለውጡን መስመር መሳት በሰፊው የተቸው ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ በቅርቡ ባቀረበው፣ ‹‹ያለንበት ሁኔታና ቀጣዩ የትግል ምዕራፍ›› በሚለው ጽሑፍ ይህንኑ ሐሳቡን አጠናክሮታል፡፡ አቶ ጃዋር በዚህ ጽሑፉ ባለፉት አምስት ዓመታት አገሪቱን ያስተዳደረው ‹‹አገዛዝ ዴሞክራሲን መገንባት አልቻለም፡፡ እንዲሁም በኦሮሞ ስም አምባገነናዊነትን ለመፍጠር ይፈልጋል፤›› በማለት ነው በጠንካራ ቃላት የተቸው፡፡

 ይህን መሰል ጠንካራ ትችት ቢቀርብም በለውጡ የመጀመሪያ ወቅቶች እጅግ በርካታ አዎንታዊ ለውጦች በአገሪቱ መፈጠራቸውና ለውጡም በተረጋጋ መስመር ላይ ሲጓዝ ነበር የሚሉ አስታራቂ መላምቶችም ጎልተው ይሰማሉ፡፡ ከእነዚህ ወገኖች እንደሚደመጠው ደግሞ፣ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የዛሬ አምስት ዓመት ወደ ነበረችበት የለውጥ ሐዲድ መመለስ ነው የሚለው ሐሳብ አስታራቂ ይመስላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -