Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አስመሳዮች!

የዛሬ ጉዞ ከፈረንሣይ ለጋሲዮን ወደ ጊዮርጊስ ነው። ሥሌቱን የማንደርስበት፣ ክፍልፋዩን ቆጥረን የማንጨርሰው፣ አሻራው ከባድ የሆነ የሰው ልጆች የውጣ ውረድ መድረክ ይኼው ጎዳና ነው። እግረኛው፣ ባለአውቶሞቢሉ፣ አውቶብስና ታክሲ ተጠቃሚው የሚያጣድፍ እያጣደፈው በወጣችለት ፀሐይ በበራለት የንጋት ብርሃን ነግዶ ለማትረፍ፣ ዘርቶ ለማጨድ ይጓዛል። ጉዞው ቀልብ አያውቅም። ስንክሳሩ ተራኪን ያደክማል። ታክሲ መሳፈሪያው አካባቢ የሚታየው ትርምስ የሰውን ልጅ የዕለት ተዕለት ውጣ ውረድ የሚተርክ ይመስላል። እያንዳንዱ ሰው በገዛ ራሱ የሕይወት መስመር ታቅዶ የሚጠብቀው፣ ተጀምሮ ያላላቀ አጀንዳ ባለቤት ነው። ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ አቅጣጫ ይዞ እየሄደ እየመሰለው አቅጣጫው የጠፋበት ብዛቱ ነው። የሚጠሉትን እንደሚያፈቅሩት አምነው፣ የሚሹትን እንደሚንቁት ቆጥረው የግፊያውን ሠልፍ ያደመቁት ነፍሶች ጥቂት አይደሉም። ከቶ ምን ቃል ይኼን ቅስም የሚሰብር ትዕይንት ይገልጻል? ጥቂት ከፈት ብለው ብርሃናቸው በሚታይ ጥርሶች ጀርባ ጥቁር የሐዘን ጭስ ይንበለበላል። የሆነውን ከመሆን አልፎ ሕዝበ አዳም ራስን ፈልጎ የማግኘት ማስተዋል ፍፁም ርቆታል። ይህን መሰል አብረክራኪ እውነት ጎዳናው ላይ ያፏጫል። ቀና ብለው በሚራመዱ ሰዎች ውስጥ የጎበጠ ማንነት ድንቅር እያለ ዕይታን ያጥበረብራል። የዘመኑ ትዕይንት ነው!

‹‹ምድሪቱ ቂሟ ከማን ጋር እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም…›› ይላል አንድ አልፎ ሂያጅ። ስብራት የሚጠግን ጊዜ ተፈጥሮ መንፈስ የሚያድስ ብሔራዊ መግባባትን የሚያሰፍን የሕዝብ የበላይነት ያልናፈቀው የለም። ደመኝነትን ታሪክ የሚያደርግ ተግባር ያልናፈቀው ማግኘት ያዳግታል። ከመጋቢው መንገድ እስከ አውራ ጎዳናው መሀል ተዘርሮ ፀሐይ የሚሞቅ ሀቅ ይህ ነው። ‹‹ሞልቷል ሳበው!›› አለ ወያላው  ዘሎ  እየገባ። ‹‹ምን ይሞላል ብለህ ነው የዚህ ዓለም ነገር?›› ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ አዛውንት ናቸው። ‹‹አይዞን አንድ ቀን አገራችንም እንደ ታክሲው መሙላቷ አይቀርም፡፡ አገር ባትሞላ ሲኦልና ገነት ቀድመው ሞልተው ይገላግሉናል…›› አላቸው። ‹‹ምን? ምን? ሆ…ሆ… ስቴዲየም መሰሉህ እንዴ እንዲህ እንደምታስበው ጢም ብለው የሚሞሉት? መጀመሪያ እስኪ አገራችን ሙሉ ትሁን። ይቀልዳል እንዴ ይኼ? እንኳን ዓለም ሞባይላችንስ መቼ ደህና የአየር ሰዓት ሞላ? እንፍቃለን የለም፣ ኪሳችን ባዶ። ሆዳችን ባዶ፣ ኔትወርኩ ባዶ። እኮ ኢትዮጵያ ናት የምትሞላው?›› አሉት አንዴ በመስኮቱ አሻግረው ወደ ውጭ እየተመለከቱ፣ አንዴ ደግሞ ወደወያላው ዞረው ዓይን ዓይኑን እያዩ። ‹‹ታዲያ ምን ተሻለ ይላሉ?›› አላቸው ሾፌራችን። የወያላውን ተግባቢነት ለመንጠቅ ይመስላል። ፈጠን ማለቱ ነው!

‹‹የዘመኑ ሰው በውድድር ስም የማይነጣጠቀው ነገር የለም…›› ይላል ከጎኔ። ‹‹ምን ይሻላል? ጊዜን ከዚህ የበለጠ ለመታዘብ ዕድሜ መለመን፣ አበቃ። ምንም የሚሻል ነገር የለም። ደግሞ በዚህ ጊዜ ምኑን ትቼ ምኑን እተወዋለሁ ልጄ። እንዲያው በአጠቃላይ ፖለቲከኛን አምኖ ለጥ ብሎ መተኛት አያስፈልግም። እኛም እኮ አልሰማ ብለን እንጂ ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም ተብለናል…›› ሲሉት ሾፌራችን በሳቅ አውካካ። ‹‹ሰላም ሰፍኖ ሁላችንም በእኩልነት የምንኖርበት ሥርዓት እንዲገነባ የሚያግዝ ቢያንስ መፍትሔ የለዎትም?›› ቢላቸው አጠገባቸው የተቀመጠ ወጣት እሳቸውም በተራቸው ሳቃቸውን ለቀቁት። ‹‹አንተ? ተወኝ ስል አትሰማም እንዴ? አንተስ ብትሆን አርፈህ ውሎህን ጨራርሰህ በሰላም ወደ ቤትህ ብትገባ አይሻልም? ነው ወይስ የበቀደሙ የፓርላማ ውሎ ራስህን አዙሮታል? ምነው አንተን ባደረገኝ እንዳልል አንተም ብሶብሃል…›› እያሉ አሽሟጠጡት። ወጣቱ ግራ ተጋብቶ አፍሮ ዝም አለ። ወያላው ነገሩን እንደገና አንስቶ፣ ‹‹‘ፋዘር’ ታዲያ ነገራችን ሁሉ መቆራረጥ በበዛበት ዘመንና ምድር ላይ ለመኖር ምን ዕድሜ አስለመንዎ?›› አላቸው። ‹‹ታዲያ በብሔር ተደራጅቼ መሬት ልለምንህ ኖሯል? ያውም አፍጣጭና ገላማጭ የበዛበት መሬት? ኧረ እባካችሁ ተውኝ ብያለሁ ዛሬ። ነው ምክክር አላችሁ እኔን አናግራችሁ ጥርስ ውስጥ ለማስገባት?›› ብለው የቁጣ መሳይ ገጽታ ሲያሳዩ፣ ‹‹ይቅርታ ‘ፋዘር’ አስቆጣሁዎት መሰለኝ?›› ብሎ ሳይጨርስ በድጋሚ፣ ‹‹ወይድ ቀጣፊ፣ ወትሮም ተደራጅተሽ ስታበቂ ሰውን ክፉ ለማናገር እሳት መጫር ሙያ መስሎሻል አዳሜ? ቆይ ግድ የለም…›› ብለው ፈገግታቸውን ብልጭ አደረጉ። እንዲያ ነው እንጂ ብልጠት!

ጉዟችን ቀጥሏል። በብዛት ከተደረደሩ ጥቅሶች መሀል አንዷን አስተውሎ ያነበበ ወጣት መናገር ጀመረ። ‘ፍጥነት ዕድሜን ያሳጥራል እንጂ ጊዜን አይቆጥብም’ ትላለች። ገርሞት ፈገግ እንዳለ፣ ‹‹እኔ እኮ የማይገባኝ አሁን ይኼ ጥቅስ ለእኛ ነው መለጠፍ ያለበት? ወይስ ለሾፌሩ?›› ብሎ ጠየቀ። ‹‹ኧረ ተወኝ ወንድሜ…›› ይላል አጠገቡ የተቀመጠው ተሳፋሪ በሰለቸ ድምፀት። ወያላው ይገላምጠዋል። ለካ አላየነው ኖሮ እንጂ ጫቱን ደበቅ አድርጎ እያኘከ ነው። ‹‹ወይ ይኼ ምርቃና? ስንቱን አጀገነው? ስንቱን አከሰረው? ስንቱን ሚኒስትር፣ ስንቱን ካርል ማርክስ፣ ስንቱን መንገድ ቀያሽ፣ ስንቱን ቀዶ ጠጋኝ አደረገው? ስንቱን ተንታኝ፣ ስንቱን ነፈዝ አድርጎ አንገዋለለው…›› ይላል ይኼን የሚያስተውል ሸበቶ ጎልማሳ። ከጎኑ ያለው ተቀብሎ፣ ‹‹ስንቱን እንዳይሆን አድርጎ አስቀረው ብለህ ጨምርበት እስቲ። ስንቱ ትዳሩን ፈታ፣ ስንቱ ጥርሱ ሟሟ፣ ስንቱ መልኩ ጠፋ፣ ስንቱ ሙዱ ከፋ አትልም?›› ሲለው ወያላው ብግን ብሎ እንዳልሰማ ሆኗል። የሚስቅ ይስቃል። በዚህ መሀል አንድ ኮስታራ ወጣት፣ ‹‹አሁንማ ፖለቲካው ሠፈር ምርቃና በዝቶ ነው መሰል የምንሰማው ሁሉ አገር አስጥሎ ያስጠፋል…›› እያለ ተንገፈገፈ፡፡ እውነቱን ሳይሆን አይቀርም!

ወዲያው የዋናው ርዕሰ ጉዳይ ጨዋታ ተመልሶ ተነሳ። ወጣቱ፣ ‹‹በጣም እኮ ነው የሚገርመው። ‘ብልሹ አሠራርን በማስወገድ ጠንካራ የልማት ኃይል እንፍጠር’ ተብሎ የሚለጠፈው ለእኛ። ‘ለሙስና እጅ አንሰጥም’ ተብሎ የሚለጠፈው ለእኛ። መቼ ይሆን ሁሉም የራሱን ጉድፍ ማጥራት የሚጀምረው?›› ይላል። አሁንም አጠገቡ የተቀመጠው፣ ‹‹ወንድሜ ድረቅ ቢልህ፣ ልፋ ቢልህ ነው፣ ሰሚ ያለ መስሎሃል?›› ይለዋል፡፡ ‹‹ወሬ… ወሬ… ኧረ ወሬ ጠላሁ…›› ሲል ወያላው እንደ መወናጨፍ ይቃጣዋል። ‹‹የመጣ የሄደው ዝም ብሎ ሲቀደድ አንተ ምን አለብህ መከራ የማየው እኔ…›› ብሎ ሾፌሩን ይተነኩሰዋል።  ሾፌሩ ግራ እንደ መጋባት እያለ፣ ‹‹ታዲያ ወሬን መደምሰስ ነዋ። ሰውስ ምን ያድርግ? መሥራት ካልቻለ፣ ደህና ምግብ መብላት ካልቻለ፣ ቢያንስ ማውራት መቻል የለበትም?›› ይለዋል በስፖኪዮ እያየው። ‹‹እውነት ነው፣ ስናወራ ነው ውስጣችን ያለው ብሶት ተንፈስ የሚለው…›› አዛውንቱ ቅድም የጀመሯትን ሽሙጥ ቀጠሉ። በዚህ መሀል ነበር አንዱ፣ ‹‹አይ እማማ ኢትዮጵያ፣ እስከ መቼ ይሆን የሞት ክብረወሰን ሰባሪ ሆነሽ የምትኖሪው?›› ብሎ የፓርላማውን እንካ ሰላንቲያ አስታኮ ብዙ ነበር የተናገረው። ብቻ ለብቻ አንሳፈር ነገር ተደራርበንም አልተረፍን!

ወያላችን ከደም ፍላቱ ቀዝቀዝ ብሎ ሒሳብ እየተቀበለ መልስ ይሰጣል። መጨረሻ ወንበር ከሁለት ሴት ጓደኞቻቸው ጋር የተሰየሙ ወጣቶች ድንገት ወሬ ጀምረዋል። ‹‹ወንድሜ እዚህ አገር ስንዝር ለመራመድ ግንብ ማፍረስ እንደሚጠበቅብህ አልነግርህም። ወረዳ የለ ክፍለ ከተማ፣ ፖሊስ ጣቢያ የለ ፍርድ ቤት፣ ማዘጋጃ የለ ቤተ መንግሥት እኛን ማገልገል ሳይሆን ዓላማቸው የሚመስለው እኛ እንድናገለግላቸው ነው። ማን ወዶ ይሰንፋል? ማን መማር ይጠላል? ማን ማትረፍ አይፈልግም? ግን ሁሉንም እንዳይሆን የሚያደርገው ይኼ እንደ ጥቁር ድመት ጨለማ ውስጥ የተደበቀ ፖለቲካ ነው። እና በዚህ መሀል እኔ ለአገሬ ምን አደረግኩላት ብዬ ላስብ ወይስ እንዴት ብዬ በልቼ ልደር?›› ሲል ያኛው ብዙም ሊከራከረው አልፈለገም። ‹‹በልቶ ለማደር ማሰብ እንደ አስተዋጽኦ ይቆጠር ይሆን?›› ይላል ያ ኮስታራ ወጣት። ይህንን ሲል ሰምቶት ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመ ጎልማሳ፣ ‹‹ምን ይታወቃል የኑሮ ውድነቱ እኮ አቅላችንን እያሳተን ነው፡፡ የአገር ነገር ሲነሳ ሁሌም  ቢሆን ምሳጤ አይጠፋም። ሁሉም በየራሱ ህሊና ጅረት ይሆናል። ግራ ቀኝ እያየ አንዳንዴም ፊት ለፊት፣ ብቻ በዝምታ ያስባል። ኑሮ እንዲህ እንደሚታክተን አዕምሮን ማሰብ ቢታክተው አገራችን የዕብዶች መናኸሪያ መሆኗ አይቀርም ነበር…›› አለው። ምኑ ከምኑ እንደሚገናኝ ሳይገባን ጎልማሳውን በጥርጣሬ ተመልክተን ደስ እንዲለው አንገታችንን በአዎንታ ነቀነቅን። ‹‹አይ አንቺ አገር መቼ ይሆን በልቶ ማደር ልጆችሽን በሐሳብ አዙሪት እየናጠ መድፋቱን የሚተዋቸው?›› እያሉ  አዛውንቱ ለብቻቸው ሲያጉተመትሙ፣ መጨረሻ ወንበር የተሰየሙት ወጣቶች ባልሰማ ሌላ ወሬ አውርተው ያሽካካሉ። አለመደማመጥ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። መጨረሻ ወንበር የተሰየሙት ሴቶች የጓደኞቻቸው ደርሶ ኮስታራ መሆንና የጠነከረ ወሬ መጀመር እያስገረማቸው ይጠይቃሉ። ‹‹አንተ ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ አገሬ ኑሮዬ የምትል ኮስታራ የሆንከው? አርፈህ አበልህን እየበላህ አትኖርም እንዴ?›› ብላ አንደኛዋ ከት ብላ ስትስቅ ሌላዋ ተቀብላ፣ ‹‹ኧረ በፈጠራችሁ እንዲህ ስታወሩ አንዴ ቪዲዮ አንስቼ ፌስቡክ ላይ ሼር ላድርጋችሁ ፕሊስ? ኦ ለካ የፌስቡክ ዕገዳ ተጥሎብናል። ወይኔ ግን ደስ ሲሉ እነዚህ ውብ አገር ወዳዶች…›› እያለች ማላገጧን ቀጠለች። ይኼኔ ከወንዶቹ አንዱ በአንበለጥም ዘዬ፣ ‹‹መቼም እንደ አንቺ በዓመት አንዴ ታላቁ ሩጫ ከመሮጥ ቢረባም ባይረባም ስለአገር ስለኑሮ ማውራት ይሻላል..›› አለ። ‹‹ውይ… ውይ… የሩጫውንስ ነገር አታንሳብኝ። በቀደም ሲያቀብጠኝ በአለቀ ሰዓት ልሩጥ ብዬ ሁለት ቀን ልተኛ?›› ብላ ወደ አንዱ ወዳጇ ደረት ልጥፍ ስትል፣ ‹‹እዚህ አገር እኮ ያስቸገራችሁት እናንተና እናንተን መሳዮች ናችሁ…›› አላት ያኛው። ‹‹እነ ማን?›› ስትል የወዲህኛው ተቀብሎ፣ ‹‹ሳታሟሙቁ የምትሮጡት፣ ሳትንደረደሩ የምትዘሉት፣ ሳትሮጡ ‘አሸንፈናል’፣ ‘ተሸንፋችኋል’ እያላችሁ በሜዳሊያ የምትጣሉት ናችኋ?›› ብሎ ተሳፋሪዎችን ፈገግ አሰኛቸው። ወያላው ‘መጨረሻ’ ብሎ በሩን ከፈተው። ኮስታራው ወጣት በፍጥነት ወርዶ እየተራመደ፣ ‹‹ከላይ እስከ ታች የበዛው አስመሳይ ነው፣ አስመሳይ ሁሉ…›› ሲል ድምፁ ያስተጋባ ነበር፡፡  መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት