Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን በዓመት እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር ያሳጣል ተባለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሴቶች ምንም እንኳን የኅብረተሰቡን ግማሽና ከዚያም በላይ ቁጥር እንደሚይዙ ቢታመንም እስካሁን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካው መስክ ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከወንዶች ጋር ሲነጻፀር ወደ ኋላ እንዲቀሩ አድርጓቸዋል እየተባለ ሲነገር ቆይቷል፡፡

በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ባደጉም ሆነ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ሴቶች ለኢኮኖሚ የሚያደርጉት አስተዋፅኦ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተለይም በኢትዮጵያ ሴቶችን በንግድ ሥራዎች ላይ ያላቸውን ስኬት ከወንዶች ጋር ሲወዳደር አመርቂ አይደለም የሚል ሐሳብ ይቀርባል፡፡ 

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከአሜሪካው ቫሳር ኮሌጅ፣ ከአቡዳቢው ኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልማት ጥናት ኮሌጅ ጋር በመተባበር የሥርዓተ ፆታ ትርፋማነት ልዩነትን እንዴት ማቀራረብ ይቻላል? በሚሉት ላይ በቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎ የተጠኑና ጉዳዩ ከዓለም አቀፍና እንዲሁም ከኢትዮጵያ አንፃር ምን ይመስላል የሚለውን የሚያሳዩ ዓለም አቀፍ የጥናት ውጤቶች ላይ ውይይት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ 

አደም ፈቶ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ተመራማሪ ሲሆኑ እርሳቸው ያጠኑት ጥናት የሥርዓተ-ፆታ ትርፋማነት አለመመጣጠን ወይም በወንዶችና በሴቶች ባለቤትነት በሚመሩ ንግዶች መካከል ትርፍ የማግኘት ዕድል ልዩነትን፣ በተለይም ከኢትዮጵያ አንፃር የዳሰሰ ነው፡፡ 

በዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ2018 የተሠራ የኑሮ ደረጃ ልኬት (ሊቪንግ ስታንዳርድ ሜዠርመንት) ጥናትን መሠረት በማድረግ 1,735 የሚሆኑ በሴቶችና በወንዶች ባለቤትነት የሚመሩ የንግድ ተቋማት በጥናቱ እንደተካተቱ የተገለጸ ሲሆን፣ የፆታ ናሙናው (ሳምፕሉም) በእኩል መጠን የተወሰደ ነው፡፡ 

ሴቶች ቤተሰብን ከድህነት ለማውጣት ትልቅ አቅም እንዳላቸው የጠቀሱት አደም (ዶ/ር)፣ ነገር ግን በሌላ ጎኑ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ ከወንዶች ጋር እኩል ባለመሆኑ ወይም እኩል ተሳትፎ ስለሌላቸው አገሪቱ ከሦስት እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ እንደምታጣ ይገልጻሉ፡፡ 

እንደ ኢኮኖሚ ተመራማሪው ገለጻ በኢትዮጵያ ያለው የሴቶች የንግድ ሥራ ባለቤትነት እንቅስቃሴ ጨቅላ የሚባል ሲሆን፣ ካላቸው ዓቅም ጋር ሲነፃፀርም በጣም የተራራቀ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ በቢዝነስ ባለቤትነት፣ በውሳኔ ሰጪነት እንዲሁም ከአካታችነት አንፃር ሲተያይ በኢትዮጵያ ያለው የሁለቱ ጾታዎች ደረጃ ያልተቀራረበ (ያልተመጣጠነ) የሚባል ነው፡፡ ይህም ከዕድገት፣ ልማት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ያለው ፈተና ብዙ ስለሆነ ነው፡፡

ለአብነትም የሚመለከታቸው አካላት በተለይም መንግሥት በትንንሽ የንግድ ሥራ ዘርፎች ለተሰማሩ ሴቶች በቂ ፋይናንስ አለማቅረባቸው፣ እንዲሁም የክህሎት፣ የሀብት፣ የከለላ ድጋፍ አለመኖሩ በጥናቱ ተገልጿል፡፡

በጥናቱ እንደተመላከተው፣ በኢትዮጵያ ወንዶችና ሴቶች የተለያዩ ቢዝነሶች ላይ በኃላፊነት ደረጃ ሲተያዩ እኩል ተሳትፎ የላቸውም፣ ውሳኔ በመስጠት ሒደት ውስጥ እኩል የሆነ የውሳኔ ሰጪነት አቅምም የላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ፣ ዓብይ ኢኮኖሚውን (ማክሮ ኢኮኖሚ) ጨምሮ ሲታይ ትልቅ ነገር እያጡ እንደሆነ አደም (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ 

በጥናታቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ በሴቶችና ወንዶች መካከል ሰፊ ልዩነት እንዲፈጠር ያደረገውን ምክንያትና ልዩነቱ ይኼን ሁሉ ዋጋ እንዴት ሊያስከፍል እንደቻለ ተመልክተዋል።

ጥናቱ ሲደረግ ሴቶች ኃላፊ የሆኑባቸው መሥሪያ ቤቶች፣ ዕድሜያቸው፣ የትዳር ሁኔታና ሌሎችም ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮች ተጢነዋል፡፡ ሴቶች ያመረቱትን ዕቃ ወደ ገበያ ሄደው ይሸጣሉ ወይስ እዚያው ነው የሚሸጡት? ቢዝነሶቹ ፈቃድ አላቸው ወይስ የላቸውም? እንዲሁም ሌሎች የሚያጋጥሟቸው መሰናክሎችን ወስዶ በማጤን እነዚህ ጉዳዮች ልዩነት የሚፈጥሩ መሆናቸው ተረጋግጧል። በተጨማሪም ልዩነቶቹን የፈጠሩት ሁኔታዎች ተመዝነው በሁለቱ ፆታዎች መካከል ልዩነቶች እንዲኖሩ የበለጠ ጫና የሚያሳድሩት ተለይተዋል።

ጥናቱ እንዳመላከተው በርካቶቹ ሴቶች የያዟቸው ቢዝነሶች ፈቃድ እንደሌላቸው፣ መደበኛ ያልሆነ ዘርፍ ላይ እንደሚገኙ፣ አብዛኛውን ሀብት ተቆጣጥረው ያሉት ወንዶች ናቸው፡፡ በዕውቀት ደረጃ ሊሆን ይችላል ወይም ባላቸው የገንዘብ መጠን ሴቶች ለሀብት ያላቸው ተደራሽነት (አክሰስ) ዝቅተኛ መሆኑ ሌላኛው ተፅዕኖ መሆኑ ተገልጧል፡፡ 

በሴቶች ባለቤትነት የሚመሩት ድርጅቶች በዝቅተኛ ወጪ የሚሠሩ እንቅስቃሴዎች ላይ እንደሚሰማሩ ጥናቱ የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህም ሴቶቹ ከወንዶች ይልቅ ኃላፊነት (ሪስክ) የመውሰድ ተነሳሽነታቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ነው ተብሏል፡፡ 

በሴቶች ባለቤትነት የሚተዳደሩ ድርጅቶች አነስተኛ ትርፍ፣ አነስተኛ የሰው ኃይል፣ አነስተኛ የቆይታ ዘመን እንዲሁም ከሌሎቹ ጋር ሲነፃፀሩ የተለየ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያደርጓቸው ተፅዕኖ (ምክንያቶች) ከሚባሉት ውስጥ የዕውቀት፣ የክህሎት፣ የሥራ ልምድ እንዲሁም የውሳኔ ሰጪነት ዓቅም ማነስ ይገኙበታል፡፡

ለረዥም ሰዓታት በቤት ውስጥ ሥራ መጠመድ ምርታማነት ውጤታማነት የሚባለውን ጉዳይ ከመቀነሱ ውጪ በገቢና ትርፋማነት ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡

ወንዶች በተቆጣጠሯቸው ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ገብቶ ለመሥራት ሴቶች ያለቸው ዕድል አነስተኛ መሆኑ አንዱ የጥናቱ ግኝት ሲሆን፣ ዕኩል ባልሆነ ከባቢ የሚሠሩ በወንዶች የሚተዳደሩ ድርጅቶችና በሴቶች የሚተዳደሩ ድርጅቶች በሽያጭ፣ በትርፍ፣ በልምድ፣ በዕውቀት ሽግግር፣ በገበያ ትስስራቸው ላይ ልዩነት የሚፈጥር ጉዳይ መሆኑ እንዲሁ ተረጋግጧል፡፡

ምንም እንኳን በተለያዩ ፖሊሲዎች ላይ የሴቶችን ድጋፍና ተጠቃሚነት አስመልክቶ የተገለጹ የትኩረት አቅጣጫዎች ቢኖሩም፣ በተገቢው ልክ ዕውን ሆነው በሁለቱ ፆታዎች መካከል ያለውን ልዩነት ሲያጠቡ አልተስተዋለም፣ ምሁራን ዘወትር የሚያነሱት ሐሳብ ነው፡፡

በቁልፍ የኢኮኖሚ እንቀስቃሴዎች ላይ የሚስተዋሉት የፆታ አለመመጣጠን ጉዳዮች ሴቶች በኢኮኖሚ ያላቸውን ዕምቅ የኢኮኖሚ አቅም ዕውን እንዳይሆን መሰናክል ስለመሆኑም እንዲሁ ሲገለጽ ይሰማል፡፡

የኢኮኖሚ ተመራማሪው እንደሚሉት ባለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት መንግሥት የሴቶችን ትኩረት ለማግኘት ብሎ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በተዋረድ በሚወጡት ፖሊሲዎች ሴቶችን ትኩረት ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ 

በኢትዮጵያ ሴቶች እኩል የሆነ መብት እንዲኖራቸው በማድረግ፣ ተቋማት ጋር ሄደው ብድር እንዲያገኙ፣ በትምህርትና በሌሎችም እየተሞከረ ቢሆንም እስካሁን ያለው በወንዶችና ሴቶች መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው፡፡ በሚደረጉት ተከታታይ ጥረቶች ብዙ ውጤት አለመገኘቱና በሁለቱ ፆታዎች መካከል መጠነ ሰፊ የልዩነት ጉዳዮች እንዳሉ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡ 

በጥናቱ ላይ ሀብት (ሪሶርስ) ከሰው ኃይል፣ ከመሬት፣ ከካፒታል፣ ከመሠረተ ልማት እንዲሁም ከማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንፃር የተመዘነ ሲሆን፣ ከላይ በተገለጹት ሦስት ጉዳዮች ላይ ሁሉ ሴቶች እጥረት እንዳለባቸው ታይቷል፡፡ 

ለአብነትም ሴቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ለመሸጥ ተፈላጊ የሆነውን ትስስር (ኔትወርክ) በመፍጠር ረገድ ያላቸው ውጤት አነስተኛ እንደሆነና በአጠቃላይ የቴክኖሎጂ ዕጦት ሴቶችን እየጎዳ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ 

በአንድ አገር ውስጥ የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ)፣ የሥራ ዕድል እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ሴቶች ያላቸው አበርክቶና ተፅዕኖ ለጥያቄ የማይቀርብና ዓብይ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በብዛት ሴቶች የሚያቋቋሟቸው ድርጅቶች ኢ-መደበኛና አነስተኛ የሆኑ፣ በትንሽ ካፒታል የሚዘወሩ፣ ያላቸውን የክህሎት አቅም የሚገድቡ ሆኖ ይገኛል ሲል ጥናቱ ያስረዳል፡፡

የሴቶች የባለቤትነት ድርሻ፣ የገቢ፣ የትርፍ፣ የደሞዝ እንዲሁም ሌሎች ነገሮች በአማካኝ ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የሚያሳይ ከባቢ የለም፡፡

የራስን ገቢ ከመፍጠር አኳያ የተደረገው ጥናት እንዳመለከተው ከወንዶች ይልቅ በሴቶች የሚመመሠረቱ ድርጅቶች ብድር እንደመነሻ ገቢ ይወስዳሉ፡፡ 

ከዚህም ባሻገር ሴቶች የመሰረቷቸው ቢዝነሶች የሀብት (ሪሶርስ) የማኅበራዊ ባህላዊ መሰናክሎች ሰላባ ሆነው ይገኛሉ፡፡

 

በሴቶች የሚመሩ ድርጅቶች የገበያ ችግር ሰለባ እንዲያጋጥማቸው ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ ብዙኃኑ የሚገኙት በመኖሪያቸው አካባቢ የሚሠሩ ስለሆኑ ነው፡፡በጥናቱ እንደታየው በወንዶች የሚተዳደሩ ድርጅቶችና በሴቶች የሚተዳደሩ ድርጅቶች የሚሠሩባቸው የሥራ አካባቢ በሽያጭ፣ በትርፍ፣ በዕውቀት ሽግግር የቢዝነስ ትስስር በመፍጠር ረገድ ሰፊ ልዩነት የሚፈጥር ሆኖ ተገኝቷል፡፡

አደም (ዶ/ር) በጥናታቸው እንዳሳዩት፣ ኢትዮጵያ ያዘጋጀቻቸው የሕግ ማዕቀፎች፣ ሕጎችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ስለ ሴቶች ያለውን ጉዳይ የተረዳ እስካልሆኑ ድረስ ተፈላጊውን ግብ ለማሳካት አይችሉም፡፡

የኢኮኖሚ ተመራማሪው ለሪፖርተር እንደገለፁት፣ በቀጣይ በተለያዩ ተቋማት የሚካሄዱ ቴክኖሎጂ ላይ የተሠረቱ ማዕቀፎች ሴቶችን በተለይ ማዕቀፍ ያደረገ መሆን አለበት፡፡ በሌላ በኩል አበዳሪ ድርጅቶች ለሴቶች የሚሰጥ አገልግሎት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ፣ ለሴቶች የሚሰጣቸው ብድርም አነስተኛ ወለድ ያለው፣ በረዥም ጊዜ የሚከፈል እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪ ሴቶች ሀብት የማሰባሰብ ግንዛቤያቸውንና ብቃታቸውን እንዲጨምሩ ሥልጠናዎች ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

በሌላ በኩል ገጠር አካባቢ ያሉ በሴቶች የሚንቀሳቀሱ የንግድ ሥራዎች ላይ መሠራት እንደሚገባው፣ የሥልጠና፣ የአቅም ግንባታና ሌሎች ጉዳዮች የሚሰጡት ከተማ ላይ እንደመሆኑ መጠን ወደ ገጠር አካባቢ በመሄድ እንዲሰጥ ማድረግ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን አደም (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡ 

በኢኮኖሚክስ አሶሴሽን አሰናጅነት በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የቀረቡት ጥናቶችን መሠረት አድርጎ በተካሄደው ውይይት ላይ እንደተመላከተው፣ ወደ 15 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የልማት ጥረት የሚጠፋው በፆታ አለመመጣጠን፣ ሁሉንም ሴቶች ወደ ልማት ባለማስገባት፣ ከሥነ ተዋልዶ ጋር በተያያዘ እንዲሁም ሴቶችን ገበያው ላይ ባለመሳተፍ ምክንያት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች