Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየፆም ወራትና አንዳንድ ነገሮቻችን

የፆም ወራትና አንዳንድ ነገሮቻችን

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

እንዴት ሰነበታችሁ ውድ አንባቢያን፡፡ ባሳለፍናቸው ሳምንታት በአገራችን ቀደም ብሎ የክርስቲያኖች ዓብይ ፆም፣ ተከትሎም የእስልምና እምነት ተከታዮች ዋነኛው የረመዳን ፆም በመግባቱ አማኞች በፆም በፀሎት፣ በዕርቅና በመተሳሰብ መንፈስ ውስጥ እንዳሉ ጥርጥር የለውም፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የመንግሥትና የሕወሓት የሰላም ስምምነት ላይ መድረስና በአንፃራዊነት ግጭቶች ጋብ ማለታቸውም በበጎ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ያም ሆኖ የፖለቲካው ትኩሳት፣ የኑሮው ውድነትና በየአካባቢው በተለያዩ ምክንያቶች የዜጎች መፈናቀል ራስ ምታታችን ሙሉ በሙሉ እንዳይሽር ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ ለሁሉም የዕለቱ ጉዳያችን የተጠቀሱት ነገሮች ሳይሆኑ፣ አጿማቱና በሒደቱ የታዘብናቸው አንዳንድ ነገሮች ላይ ያተኩራል፡፡ በይዘቱ መቅለል ጭምር ዘና እያላችሁ እንደምታነቡት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የዓብይ ፆም ገብቶ አንድ ወር ገደማ ከተፆመ በኋላ የተቀደሰው ረመዳን  የሙስሊሞች የፆም ወር መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. መግባቱ ይታወሳል፡፡ በዚህም በአጠቃላይ የንግድና የገበያ ሁኔታው ላይ ከፍተኛ ድብታ ነው የተፈጠረው፡፡ አብዛኛው የንግዱ ማኅበረሰብና አንቀሳቃሹ የእምነቱ ተከታይ እንደ መሆኑ፣ የገንዘብ ዝውውሩም ሆነ ግብይቱ በዚያው ልክ መቀዛቀዙም አይቀሬ ነው።

በነገራችን ላይ ሙስሊሞች ወሩን በተመሳሳይ ሥነ ሥርዓትና ሃይማኖታዊ ደንብ መሠረት ነው የሚያከብሩት። ዋነኛ ይዘቱ ፆም (በዓረብኛ ሶም) ዘካና ሰደቃ (አሥራት/ችሮታ) ለድሆች መስጠት ሲሆን፣ የምሽት ረጅም ፀሎትና ስግደት (ተራዊህ)፣ ቁርዓን መቅራት (ማንበብ) ከሁሉም ዓይነት መጥፎ ድርጊትና ንግግር መራቅ ዋነኞቹ ናቸው።

ጠዋት ጎህ ከመቅደዱ በፊት ጀምሮ እስከ ፀሐይ ግባት በኋላ ድረስ ምንም ዓይነት ምግብ አይበላም፣ ውኃ አይጠጣም። ወደ ሆድ የሚገቡ ነገሮች በሙሉ የተከለከሉ ናቸው። በሙስሊሞች ዘንድ ፆም ከፈጣሪ በርካታ ትሩፋቶችን የሚያስገኝ ሲሆን፣ የረመዳን ፆም ደግሞ ትርፋቱ እጥፍ ድርብ መሆኑ ይታመናል። ሰላት (ስግደት) ማብዛትና ቁርዓንን አብዝቶ መቅራት (ማንበብ) የረመዳን ወር ዋነኛ ተልዕኮዎች ናቸው፡፡

የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዓብይ ፆምም በአማኞቹ ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው፣ ምዕመናን በፆም ብቻ ሳይሆን በማስቀደስ፣ በስግደትና ምፅዋት በመስጠት ፈጣሪያቸውን የሚያስታውሱበት ወቅት ነው፡፡ ወደ ፆሙ ማለቂያ ጊዜ ላይ ደግሞ ቀኑን ሙሉ መስገድና ቤተ ክርስቲያን እየተገኙ ፈጣሪን ማመሥገን ብቻ ሳይሆን፣ ከምግብና ከመጠጥ ለቀናት በመራቅ የአክፍልት ሥርዓት የሚከናወንበትም ነው፡፡ በወቅቱ ሁሉንም በሰላም ለዚያው እንዲያደርሰው ነው የምመኘው፡፡

የፆም ጊዜያት ነገር ከተነሳ አንዳንድ ገጠመኞቼን ላንሳ፡፡ በቅርቡ አንድ ግሮሰሪ ቁጭ ብለን ስንጨዋወት ዕድሜያቸው በግምት 70 ዓመት ገደማ የሚሆናቸው አዛውንት እንዲህ ሲሉ ጨዋታ ጀመሩ፡፡ ‹‹በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ በሁለት ወር ሁዳዴ የፆም ወቅት በመገናኛ ብዙኃን ዘፈን እንደማይቀርብ ታስተውላላችሁ?›› አሉ፡፡ ሌላኛው ጠና ያሉ ሰው ተጨማሪ አደረጉ፡፡ ‹‹አዎ! በደንብ እንጂ ዘፈን አይተላለፍም ነበር፡፡ በበገና፣ መዲናና ዘለሰኛ መንፈሳዊ ዜማዎች ብቻ ነበር የሚተላለፉት፤›› አሉ፡፡

ሌላኛው ቀጠሉ፣ ‹‹በሙዚቃ መሣሪያ ብቻ የተቀነባበሩ ክላሲካል ሙዚቃዎች ይተላለፉ እንደነበር ትዝ ይለኛል፤›› አሉ፡፡ ጨዋታውን መስማት እንጂ ትችት ማቅረብ አይሞከርም፡፡ ማለት በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበሩ ሙዚቃዎች ክላሲካል ናቸው? የለም ኢንስትሩመንታል ናቸው እያሉ ጨዋታ ማቆርፈድ ጥላቻ ያተርፋል፡፡

ይኼ ደግሞ እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ ይላል፣ ሁሉን ነገር የሚያውቀው እሱ ብቻ ይመስለዋል፣ ከእኔ በላይ ላሳር ይላል፣ ወዘተ. የሚባሉ ቅፅላዊ የጥላቻ ምላሾችን ያስገኛል፡፡ ስለዚህ ዝም ብሎ ከማዳመጥ የተሻለ አማራጭ የለም፡፡ አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰላችሁ? ወጣቶች ስለእግር ኳስ ያወራሉ፡፡ የአርሰናሉን ቴሪ ሄነሪ ጉብዝና የሚደግፉና የሚያጥላሉ ወጣቶች እርስ በርሳቸው እየተጯጯሁ ይነጋገራሉ፡፡

በዚህ ጊዜ አንድ ምሁር በወጣቶቹ ጨዋታ መሀለ ላይ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹… ዝም ብላችሁ ነው የምትንጫጩት የተጨዋቹን ስም እንኳን አስተካክላችሁ መጥራት አትችሉም፡፡ ቴሪ ሄነሪ አይባልም፣ ቴሪ ኦነሪ ነው የሚባለው፤›› አለ፡፡ ወጣቶቹ ተቃወሙ፣ ምሁሩ በእጁ የያዘውን የእንግሊዝኛ መጽሔት ገለጸና ‹‹ቴሪ ኦንሪ›› የሚለውን ጽሑፍ አሳያቸው፡፡

ይኼኔ ወጣቶቹ ተቹት፣ ‘ሚዲያዎቻችን ቴሪ ሄነሪ ብለው ነው የሚጠሩት፣ እነሱም አያውቁም ማለትህ ነው አንተ? ከጋዜጠኞቹ የበለጠ ታውቃለህ? ጉረኛ ዘለዓለም እኔነኝ አዋቂ ትላለህ፣ ሰው ትንቃለህ፣ አንተን ብሎ አዋቂ ድንቄም ምሁር…’ እያሉ ወረዱበት፡፡ ሰውየው ይኼ ይገጥመኛል ብሎ አላሰበም ነበርና በጣም ደነገጠ፡፡ እንደ ውርደት ቆጥሮ አፍሮ ነው መሰለኝ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከዚያ ግሮሰሪ ቀረ፡፡

ይኼው እስከ ዛሬ ብቅ ሲል ዓይቼው አላውቅም፡፡ መጀመርያ ነገር ባልተጋበዘበት ጨዋታ መሀል ጣልቃ መግባቱ፣ ሁለተኛ ነገር የወጣቶቹን ዋነኛ ትኩረት አለመረዳቱ፣ ሦስተኛ ነገር ለእሱ ትችት የወጣቶቹ ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል አለመገመቱ፣ ወጣቶቹም ቢሆኑ የሰውዬውን እርምት ቢቀበሉ፣ ባይቀበሉ እንኳ ችላ ብለው ወደ ራሳቸው ጨዋታ አለመመለሳቸው የሚገርም አጋጣሚ ነበር፡፡

የአንዳንድ ግሮሰሪ ጓደኛማማቾች አንዱ ችግር ይኼ ነው፡፡ መስማት እንጂ ለማረም ወይም ለማስተካከል መሞከር ምላሹ ደስ አይልም፡፡ እኛም በመሣሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ ‹‹ክላሲካል ይባላል›› ሲሉ ዝምብለን አድምጠናል፡፡ በክላሲካልና በኢንስትሩመንታል የሙዚቃ ዓይነቶች (ሥርዓቶች) መካከል ስላለው ልዩነት የሚነግረን አንባቢ ቢኖር፣ እንደሚሆን አድርጌ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆኔን በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ፡፡

በነገራችን ላይ አሁን አሁን የደከመውና በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የነበረው የበገና፣ የመዲናና የዘለሰኛ (በሙስሊሙም ፆም ቢሆን መንዙማ) በፆም ወራት የሚተላለፉበት ልምድ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት አሠራር ቢኖር መልካም ነበር፡፡ በሃይማኖት ሰበብም ሆነ በሌላ ማንኛውም ምክንያት ዓለማዊ ዘፈን ሳንሰማ የምንውልበት ጊዜ የሚያስፈልገን ይመስለኛል፡፡ ዘወትር አሸሼ ገዳሜ ማለትም ይሰለቻል፡፡

በአገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ አዳዲሶቹ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ብሔራዊ ሬዲዮና ኤፍኤሞች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያውሉት ለሙዚቃ ማስተላለፊያነት ነው፡፡ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ምግብ የሆኑ የበገና ሙዚቃዎች ቢበዙ ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ይኼ እንኳ ባይሆን ከዓለማዊ ሙዚቃ ሥርጭት ነፃ የሆኑ ቀናት (Music Free Days) ወይም ሙዚቃ የማይተላለፍባቸው ቀናት እንዲኖሩ ማድረግ ይቻላል፡፡

በሌላ አማራጭ ደግሞ ቀኑን መወሰን እንኳ ባይቻል ሙዚቃ የሌለባቸው ቻናሎች እንዲኖሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ቻናሎች ካሉ በአንደኛው ቻናል ሙዚቃ የማይተላለፍበት ዕለት እንዲኖር ቢደረግስ? በብዙ አገሮች ማስታወቂያ የማይተላለፍባቸው ቀናት (Advertising Free Days) አሉ፡፡

ማስታወቂያ የማይተላለፍባቸው ቻናሎች ያሏቸው አገሮችም አሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሙዚቃ ነፃ የሆኑ ቀናት ወይም ቻናሎች እንዲኖሩ በማድረግ አሠራር ላይ ማሰብ ይቻላል፡፡ አሁን አሁን የቻናሎች ቁጥር እንዲጨምር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የቻናሎች መብዛት ጥቅምም ጉዳምትም አለው፡፡

ዋነኛው ጉዳት ቻናል ሲበዛ (በተለይ በቴሌቪዥን) ተመልካቹ ሪሞት ኮንትሮሉን ይዞ ይቀመጥና እንደ ዜና፣ ትንታኔ፣ የሚዲያ ዳሰሳ፣ የከፍተኛ ባለሥልጣናትና የሥራ ኃላፊዎች መግለጫዎች ወይም ብሔራዊ ፋይዳ ያላቸው ጠንከር ያሉ ዝግጅቶች በሚተላለፉበት ሰዓት ቻናሉን በመቀየር እንደ ኳስ ጨዋታ፣ ሙዚቃ፣ ቴአትር፣ የውጭ ፊልሞች ወዳሉበት ጣቢያ በማዞር ለአዝናኝ ፕሮግራሞች ቅድሚያ ዝንባሌ ይሰጣል፡፡

በካናዳ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው አንድ ጣቢያ ብቻ በነበረ ጊዜ፣ ዜና የሚያዳምጠው ሕዝብ ብዛት ሁለት ጣቢያ (ቻናል) ከሆነበት ጊዜ እጅግ የበለጠ እንደነበር ተረጋግጧል፡፡ የቻናል ብዛት በጨመረ ቁጥር ብሔራዊ ፋይዳ ያላቸውን ዝግጅቶች የሚያዳምጠው ሕዝብ ቁጥር በጣም ቀንሶ የተገኘበት ጥናት አለ፡፡

ስለዚህ እንደ ዜና የመሪዎች ንግግር፣ ብሔራዊ መግለጫዎች፣ የምርጫ ሒደቶችና የመሳሰሉት ፕሮግራሞች በሚኖሩ ጊዜ በሁሉም ቻናሎች በተመሳሳይ ሰዓት እንዲተላለፉ የሚደረግበትን አሠራር ከወዲሁ አስቦ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ የሙዚቃና የዳንስ ዝግጅቶች የሚተላለፉባቸው የቴሌቪዥን ሰዓቶች ቢቀንስ ጡትና ዕምብርት የበዛበትን ትዕይንት ከማየት ለመቆጠብ ይረዳል፡፡

ልጆቻችን ያዩትን ነገር ልቅም አድርገው ይይዛሉ፡፡ ከቴሌቪዥኑ ጋር አብረው ይዘፍናሉ፡፡ መቀመጫን የሚያወዛውዙ ጭፈራዎችን ሲለማመዱ ይውላሉ፡፡ ለትምህርታቸው ጥናት የሚሰጡት ትኩረትና ጊዜ ያጥራቸዋል፡፡ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ያሉ የሠፈር ልጆች ብትጠይቁዋቸው የከፍተኛ ባለሥልጣኖቻችንን ስሞች አያውቁም፡፡

በቴሌቪዥን አንድ ሚኒስትር ቀርበው በታዩበት ወቅት እኚህ ሰው ማን ናቸው? ኃላፊነታቸውስ ምንድነው? ተብለው ሲጠየቁ እንደማያውቋቸው ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በቂ ስታትስቲክስ ነው ለማለት ግን አይቻልም፡፡ ሁሉም ሰው ከሕፃን እስከ አዋቂ፣ በከተማም ሆነ በገጠር ሕዝቡ አንድም ሳይቀር የሚያውቃቸው ግፋ ቢል ዓብይ አህመድን ብቻ ነው፡፡ ይኼ ደስ ይላል፡፡

ምክንያቱም በጀርመን አገር ሔልሙት ኮል በነበሩበት ጊዜ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳረጋገጠው፣ በጀርመን በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተደረገው ጥናት ከ80 ፐርሰንት በላይ የሆኑት ተማሪዎች የአገራቸውን መሪ (ቻንስለር) ስም አያውቁም፡፡ የእግር ኳሱን ጀግና የፍራንዝ ቤከን ባወርን ስም ግን ሁሉም ጀርመናዊ ያውቃል፡፡ ከፍላጎት በላይ የሆነው የሙዚቃ አቅርቦታችን በተማሪዎቻችን አጠቃላይ ዕውቀትና በትምህርት አቀባበል ብቃታቸው ላይ ያስከተለው ጎጂ ወይም ገንቢ አስተዋጽኦ ስለመኖር አለመኖሩ፣ የሚመለከታቸው አካላት ጥናት ቢያደርጉ ሳይጠቅም አይቀርም፡፡

ወደ ጨዋታችን ስንመለስ የፋሲካ በዓልን እንዴት እንደምናከብርና የኑሮ ጣጣን ነገር ስናብሰለስል፣ ከተሰባሰብነው መካከል ሌላኛው ዕድሜ ጠገብ አዛውንት የአፄ ኃይለ ሥላሴን ዘመን አስተዳደር ካመሠገኑ በኋላ፣ ‹‹ያኔማ በኃይሌ ጊዜ ከትንሳዔ እስከ ዳግማዊ ትንሳዔ ድረስ ሳምንቱን ሙሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ዝግ ነበር፣ ሥራ የለም፡፡ ነጋዴ ብቻ ንግዱን ያካሂዳል እንጂ የመንግሥት ሠራተኛ ሥራ አይገባም ነበር፡፡ ማዕዶት ነው…›› የሚል ጨዋታ አመጡ፡፡

እንዲህ እንደነበር ያላወቅን ወይም ልብ ያላልን ሁሉ ተገረምን፣ ተደነቅን፡፡ አንዱ ሐሳቡን አቀረበ፣ ‹‹እኔ ግን ይህን አልደግፍም… ሳምንት ሙሉ ሥራ ባይገባ የሚጎዳው የመንግሥት ሠራተኛው ነው፣ ጊዜውን የት ያሳልፋል? የወር ገቢያችንን ለፋሲካ አውለናል፣ ደግሞ ሳምንት ሙሉ ሥራ ከሌለ እየዞርን ስንጠጣ መክረማችን ነው፡፡ ኪስ ከማራገፍ ሌላ ጥቅም ያለው አይመስለኝም፡፡ በዚህ ላይ አሁን የምንገኝበት ኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት የሚያላውስ አለመሆኑ ይታወቃል፡፡

‹‹የዛሬዎቹ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ሥራና ኃላፊነት እንዲኖራቸው ተደርገው የተደራጁ ናቸው፡፡ አገልግሎት ፈላጊዎች መስተናገድ አለባቸው፡፡ ኢንቨስተሮች ሀብታቸውን ለልማት ለማዋል ሳምንት ሙሉ ሠራተኛው እስኪገባ ድረስ መቆየት የለባቸውም፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ የመብራት፣ የውኃ፣ የስልክ መሥሪያ ቤቶችና የጤና ተቋማት ሳምንት ሙሉ ተዘግተው እንዲከርሙ ማድረግ ተገቢነት የለውም፤›› ሲል ለጨዋታው ሙቀት ሰጠ፡፡

ለሁሉም አሁን የምንገኝበት ሁኔታ በመርህ ደረጃም ቢሆን የሃይማኖት እኩልነትና የእምነት ነፃነት በሕገ መንግሥት ደረጃ የተረጋገጠበት ነውና ሁሉም ያሻውን የማድረግ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ የሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች ዋነኛ የፆም ጊዜዎች ተገጣጠሙና ጥቂት ለማለት ወደድኩ እንጂ፣ በእምንት ጉዳይ ይኼ ይደረግ ይኼ ይከልከል የማለት መብቱም ፍላጎቱም እንደሌለኝ አውቃለሁ፡፡ ለሁለቱም ሃይማኖት ተከታዮች መልካም በዓልና የፆም መፍቻ ጊዜ እንዲመጣልንም እመኛለሁ፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...