Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየፖለቲካ ልዩነት አያግደውም የተባለ የወጣቶች ምክር ቤት መመሥረት

የፖለቲካ ልዩነት አያግደውም የተባለ የወጣቶች ምክር ቤት መመሥረት

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በኢትዮጵያ ካለው የሕዝብ ቁጥር 40 ሚሊዮን ያህሉ ወጣት የኅብረተሰብ ክፍል እንደሆነ ቢነገርም፣ ወጣቶች በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ይልቁንስ በሚደርስባቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በሥራ አጥነትና በሌሎችም ምክንያቶች ከአገራቸው ለመውጣት የሚፍጨረጨሩ ናቸው፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም ወጣቶች ተሰባስበው ስለቀጣዩም ሆነ ስላለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበት የተጠናከረ መድረክም ሆነ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወክለው ስለራሳቸው የሚወስኑበት አሠራርም የለም፡፡

በመሆኑም የወጣቶችን መብትና ጥያቄ ለማሟላትና ለመመለስ መንግሥት እየሠራባቸው ካሉት ተግባራት መካከል፣ ወጣቶች ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጥተው ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ማስቻል እንደሚገኝበት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ይገልጻል፡፡

ሚኒስቴሩ በ2013 ዓ.ም. ሊቋቋም የነበረው የወጣቶች ምክር ቤት፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሲገፋ ቆይቶ መጋቢት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ሲሆን እንዳስታወቀው፣ የተመሠረተው ምክር ቤት ወጣቶች ሐሳባቸውን በአደባባይ የሚገልፁበት መሆኑን ጠቁሟል፡፡

‹‹የወጣቶች ምክር ቤት ለወጣቶች ድምፅ›› በሚል መሪ ቃል በይፋ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት፣ ወጣቶች ሐሳባቸውን የሚገልጹበት በአደባባይ፣ የሚከራከሩበትና የዴሞክራሲ ሒደት ውስጥ በመግባት የሚሳተፉበት ነው ተብሏል፡፡

ዓላማውም ወጣቶች በአገር አቀፍና በማኅበረሰብ ልማት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ የአመራር ክህሎትና ዕድሎችን እንዲያገኙና በሁሉም የማኅበረሰብ ዕርከኖች የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቶች ላይ ተሳትፏቸውን ማስተዋወቅ እንዲችሉ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ ወጣቶች ካላቸው ዕምቅ ዕውቀትና ክህሎች አንፃር ለአገር ዕድገት የሚኖራቸው አበርክቶ እጅግ ከፍተኛ  በመሆኑ፣ ወጣቶች ፍላጎታቸውን መሠረት ባደረጉ የተለያዩ አደረጃጀቶች ተደራጅተው መብትና ጥቅማቸውን ማስከበር እንዲችሉ ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል ብለዋል፡፡

ወጣቶችን ለማብቃት፣ የአመራርና የውሳኔ ሰጪነት አቅማቸውን ለማሳደግ፣ ለወጣቱ ድምፅ የሚሆን የወጣቶችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብቶችንና ጥቅሞችን ለማስከበርና ከአኅጉርና ዓለም አቀፍ ምክር ቤቶች ጋር ጠንካራ ቅንጅቶችን ለመፍጠር የኢትዮጵያ ወጣቶችን የሚወክል አደረጃጀት መፍጠር ያስፈልግ ነበር ያሉት ሚኒስትሯ፣ በዚህም መሠረት በ1996 ዓ.ም. የወጣውን ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲና የወጣት አደረጃጀቶች ያሉበትን አሁናዊ ቁመና ለመረዳት የዳሰሳ ጥናት መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

በተገኘው ምክረ ሐሳብ መሠረትና የሌሎች አገር ተሞክሮዎችን በመውሰድ፣ አሁን ካለው የወጣቶችን ቁጥርና ፍላጎት ሊመጥን የሚችል አገር አቀፍ አደረጃጀት መመሥረት እንደሚገባ በመረዳት፣ አገር አቀፍ የወጣቶች ምክር ቤት እንዲመሠረት ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን አክለዋል፡፡

‹‹የወጣቶች ምክር ቤት መቋቋሙ አንድ ዕርምጃ እንጂ፣ በራሱ ብቻውን የመጨረሻ ግብ ሊሆን አይችልም፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ምክር ቤቱ በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስና የተቋቋመበትን ዓላማ እንዲያሳካ መንግሥት የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

አዲስ የተቋቋመው የወጣቶች ምክር ቤት በስፋት እየታየ ያለውን የወጣቶችን ችግር ከመንግሥትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለመፍታት የላቀ ሚና አለው ሲልም የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወጣት ፉዓድ ገና ተናግሯል፡፡

‹‹የወጣትነት ዕድሜ በትክክል ሥራ ላይ ሲውል ከራስ አልፎ ለአገር የሚጠቅም በመሆኑ፣ በሁሉም መስክ የጋራ አሻራዎቻችንን እያኖርን ለመጓዝ ተዘጋጅተናል፤›› ብሏል፡፡  

‹‹በምክር ቤት ደረጃ ባለመደራጀታችን የወጣቶች ፍላጎት ሁለንተናዊ ተሳትፎና ጥቅም ሳይከበር ቆይቷል፤›› ያለው ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተወክሎ የመጣውና የምክር ቤቱ አባል ወጣት ሙሐመድ ኑር ነው፡፡

150 መቀመጫዎች ያለው ምክር ቤቱ፣ 15 የሥራ አፈጻሚዎች፣ ፕሬዚዳንትና ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ያሉት መሆኑን ተናግሯል፡፡ እንደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወጣቶች፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት የሰላምና ፀጥታ ችግሮች በስፋት ይታያሉ ያለው ወጣት ሙሐመድ፣ እነዚህንና ሌሎች የወጣቶችን ተግዳሮቶች ለመፍታት ጠንክረው እንደሚሠሩ አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ምክር ቤት የትግራይ ክልልን በመወከል የተሳተፉ ወጣቶች አለመኖራቸው ተመልክቷል፡፡ ምንም እንኳን ነገሮች ባለመመቻቸታቸው ከትግራይ ክልል የተወከሉ ወጣቶች ባይገኙም፣ በምክር ቤቱ 12 መቀመጫዎች ያሉት መሆኑን የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሙና አህመድ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ቢኖራቸውም፣ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ቢሆኑም፣ የምክር ቤት አባል ከመሆን እንደማያግዳቸው ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ወደ ምክር ቤቱ ከገቡ በኋላ የወጣቶችን ድምፅና የምክር ቤቱን ሐሳብ ማንፀባረቅ ይኖባቸዋል ተብሏል፡፡

ለአብነት የኢዜማ አባል የሆነ ወጣት በአባልነት መሳተፉን አውስተው፣ ወጣቱ ወደ ምክር ቤቱ ሲመጣ የኢዜማን ሐሳብ ሳይሆን የወጣቶችን አጀንዳ በማምጣት ከወጣቶች ጋር በጋራ መምከር እንዳለበት ወ/ሮ ሙና ተናግረዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...