Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምበኬንያ ሲካሄድ የነበረው የተቃውሞ ሠልፍ ለጊዜው ተቋረጠ

በኬንያ ሲካሄድ የነበረው የተቃውሞ ሠልፍ ለጊዜው ተቋረጠ

ቀን:

የኬንያ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ በዚህ ሳምንት ጠርተውት የነበረውን የተቃውሞ ሠልፍ መሠረዛቸውን አስታውቀዋል፡፡

‹‹በኬንያ የኑሮ ውድነቱ ጣራ ነክቷል፣ በ2022 የተደረገው ምርጫ ተጭበርብሯል›› በሚል ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ለሦስት ጊዜያት ተቃውሞ ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ተቃውሞ ለመጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዞለት ነበር፡፡   

በጎዳና የሚደረጉ ተቃውሞ ሠልፎች ቀርተው፣ አጀንዳዎች በውይይት እንዲፈቱ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎም፣ ሚስተር ኦዲንጋ ለአራተኛ ጊዜ የጠሩትን የተቃውሞ ሠልፍ መሠረዛቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

- Advertisement -

ኦዲንጋ በየሳምንቱ ሰኞና ሐሙስ እንዲካሄድ በጠሩት ተቃውሞ ሠልፍ፣ ቀድሞ በተደረጉት ሦስት የተቃውሞ ሠልፎች ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ400 በላይ ሰዎች ተጎድተዋል፣ ንብረቶች ወድመዋል፣ የንግድ ተቋማትም ተዘርፈዋል፡፡

ሚስተር ኦዲንጋ እንዳሉት፣ ለአራተኛ ቀን ሊካሄድ የነበረውን የተቃውሞ ሠልፍ የሰረዙት፣ ፕሬዚዳንት ሩቶ፣ በምርጫ አካሄድ ላይ ነበሩ የተባሉ ችግሮችን ለማየት ሁለቱ ወገኖች የተስማሙበት ኮሚቴ እንዲዋቀር ከስምምነት በመድረሳቸው ነው፡፡

የ2022 ምርጫ ተጭበርብሯል ሲሉ ክስ የመሠረቱትና የተረቱት ኦዲንጋ፣ ‹‹የሩቶ የውይይት ጥሪ አዎንታዊ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የሚደረገው ውይይት ውጤት የማያመጣ ከሆነ ተቃውሞ የመጥራት መብታቸው የተጠበቀ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኦዲንጋ የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን ላይ ሪፎርም እንዲደረግ ሲጠይቁ የከረሙ ሲሆን፣ በሚዋቀረው ኮሚሽንም የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች እንዳይገቡ ማረጋገጫ እንዲሰጥና ከሁለቱም ወገኖች የተውጣጡ የፓርላማ ተወካዮች በባለሙያዎች ተደግፈው እንዲሠሩ መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከ2022 ምርጫ መጭበርበር ጎን ለጎን የኑሮ ውድነትን ያነሱት ኦዲንጋ፣ የሩቶ መንግሥት ድጎማዎችን ማንሳቱን ይኮንናሉ፡፡

‹‹ኑሮ በተወደደ ጊዜ ጫናውን ለማቃለል ድጎማ ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ያሉት ኦዲንጋ፣ የሩቶ መንግሥት በነዳጅ፣ የኬንያ ሕዝብ መሠረታዊ ምግብ በሆነው በበቆሎና በኤሌክትሪክ የነበሩ ድጎማዎችን ማንሳቱ የኑሮ ውድነትን ማባባሱን ተናግረዋል፡፡

በኑሮ ውድነትና ዓምና ተጭበርብሯል በተባለ የምርጫ ሒደት የተነሳው ተቃውሞ፣ ኬንያንና ጎረቤት አገሮቿን የከፋ ቀውስ ውስጥ ሊከታት ይችላል የሚል ሥጋትን ደቅኗል፡፡

ይህንን ተከትሎም የአገሪቱ የሃይማኖት ተቋማት፣ መንግሥትና ተቃዋሚው ፓርቲ ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱና እ.ኤ.አ. በ2007 ተደርጎ በነበረው ምርጫ በተቀሰቀሰ ግጭት፣ 1,200 ሰዎች የሞቱበትን ዓይነት ችግር እንዳይደገም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሩቶ ለሕዝባቸው በሰጡት መግለጫ፣ ኦዲንጋ ችግሩን ከጎዳና ይልቅ በፓርላማ ሥርዓት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኬንያውያን ሰላማዊና ለሕግ ተገዥ እንዲሆኑ በመግለጽም፣ ‹‹ወንድሜ ራይላ ኦዲንጋ የተቃውሞ ሠልፍህን ጥሪ ሰርዘው፣ አገራችንን ወደፊት ለማራመድ ዕድሉን እንጠቀምበት፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እኛ እህቶቻችንንና ወንድሞቻችንን ለኬንያውያን ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ማሳተፍ እንፈልጋለን፡፡ ይህ ችግሮችን ለማየትና ለመፍታት ያስችላል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በኬንያ የታየው አለመረጋጋት ዓለም አቀፍ ዕይታን የሳበ ሲሆን፣ አሜሪካና እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች አገሮችም በኬንያ መረጋጋት እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት በበኩሉ፣ በኬንያ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ መተኮሱን፣ ውኃ መጠቀሙን፣ ማምለኪያ ቦታዎች፣ የንግድ ተቋማትና ሌሎች ንብረቶች መቃጠላቸውን ጠቅሶ ተፃራሪ ወገኖች ሰላም እንዲያሰፍኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የተቃውሞ ሠልፍ መጠራት ከጀመረበት ካለፉት 15 ቀናት ወዲህ በ20 ጋዜጠኞች ላይ ጥቃት መድረሱን በኬንያ በጋዜጠኝነት ዘርፍ የሚሠሩ ማኅበራት ሲያሳውቁ፣ መንግሥት ጋዜጠኞች ዒላማ እንዳልተደረጉ ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...