የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤትና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የተውጣጡ የጋራ የሰብዓዊ መብት መርማሪዎችን፣ በትግራይና ግጭት በተከሰተባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ሊያሰማራ ነው።
ለዚህም ሲባል መንግሥት ለተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ቢሮ ጥያቄ አቅርቦ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱን ለማወቅ ተችሏል። የሚሰማራው የጋራ ቡድን ትኩረት የሚያደርገው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ፣ የተፈጸሙ ጥሰቶችን ለመመርመር እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የጋራ የሰብዓዊ መብት መርማሪዎች በቅርቡ ለማሰማራት መታቀዱን አረጋግጠዋል።
‹‹በአሁኑ ወቅት ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ የሚከታተል የጋራ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ቡድን ለማሰማራት አቅደናል፤›› ሲሉ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የጋራ የሰብዓዊ መብቶች መርማሪ ቡድኑ ወደ ተባሉት አካባቢዎች መቼ እንደሚሰማራ አልገለጹም።
የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የጋራ የሰብዓዊ መብቶችን የሚከታተል የጋራ ቡድን በትግራይና ግጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎች እንደሚያሰማራ ጠቅሰው ነበር።
የፍትሕ ሚኒስትሩ አክለውም መንግሥት ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የሚያሟላ የሽግግር የፍትሕ ሥርዓት በመንደፍና በመተግበር ላይ ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ ለተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሐፈት ቤትና ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጥያቄ ማቅረቡን አስረድተዋል።
‹‹ይህ ጥያቄና እስካሁን የወሰድናቸው ዕርምጃዎች በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ለማሻሻል ያለንን ቁርጠኝነት፣ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥርዓት ጋር በመተባበር የሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥርዓት ጋር የመደጋገፍ መርህን ለማክበር ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል፤›› ብለዋል።
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ገለልተኛ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን በተቋቋመበት ዓላማ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ጠንከር ያለ ጥርጣሬና ተቃውሞ ቢኖረውም፣ ከገለልተኛ የባለሙያዎች ኮሚሽኑ ጋር የጋራ ትብብር ለመፍጠር ጥረት ማድረጉን የፍትሕ ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር።
ነገር ግን የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል የሆኑ የአፍሪካ አገሮች ተቃውመውት ጭምር የተቋቋመው ኮሚሽን የኢትዮጵያ መንግሥት ያደረጋቸውን ትብብር ጥረቶች ወደ ጎን በመተው፣ ፍሬያማ ባልሆነ ሕገወጥ መንገድ ለመቀጠል መምረጡንና ይህም መንግሥትን በጣም እንዳሳዘነ ተናግረዋል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ መንግሥት ከተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤትና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በቅርበት በመሥራት፣ ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።
የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን (ዶ/ር) ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ንግግር ካደረጉ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ፣ ኢትዮጵያን በተመለከተ ውይይት ያደረገው ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ላይ የተቋቋመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር የተሰጣቸውን ኃላፊነት በተመለከተ ገለጻ አድርገው ነበር።
በወቅቱ ባደረጉት ገለጻም ኮሚሽኑ ተልዕኮውን በአካል ተገኝቶ እንዳይወጣ የኢትዮጵያ መንግሥት ክልከላ ማድረጉን የተናገሩ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት የተፈጸሙ ጥሰቶችን ከርቀት ሆነው ለመመርመር መገደዳቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ክልከላውን እንዲያነሳ የጠየቁት ኮሚሽነሩ፣ ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድኑ ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጋር በተመባበር እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
በቅርቡ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳም በቅርቡ ባደረጉት ንግግር፣ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በዓለም አቀፍ ገለልተኛ አካል መጣራትና ተጠያቂነት መረጋገጥ እንዳለበት ሲናገሩ ተደምጠዋል።