በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከኦሮሚያ ክልል ገርባ ምርጫ ጣቢያ የብልፅግና ፓርቲን በመወከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት፣ እንዲሁም ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዚዳንትነት የመሩት ጫላ ዋታ ደረሰ (ዶ/ር) ያለ መከሰስ መብት ተነስቶ የወንጀል ምርመራ ተጀመረ፡፡
የቀድሞው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ያለ መከሰስ መብት የተነጠቁት፣ ዩኒቨርሲቲውን ሲያስተዳድሩ በነበሩበት ወቅት በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትና በገንዘብ ሚኒስቴር በተደረገ የኦዲት ምርመራ በተገኘባቸው የኦዲት ክፍተት መሆኑ ተገልጿል፡፡ በግለሰቡ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ምርመራ በመጀመሩ ነው ተብሏል፡፡
የፓርላማው የሕግና የፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ ትናንት ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደ 13ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ መሠረት፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በፓርላማ አባሉ ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ላይ የቀረበውን ያለ መከሰስ መብት ይነሳ ጥያቄ ሲመረምር መቆየቱን አስረድተዋል፡፡
ወ/ሮ እፀገነት እንዳብራሩት፣ በ2008 ዓ.ም. በፀደቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስፈጻሚ የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 15 ንዑስ አንቀጽ አንድ መሠረት ቋሚ ኮሚቴው የቀረበውን ያለ መከሰስ መብት መርምሮ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁን አስታውሰዋል፡፡
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጫላ (ዶ/ር) የመንግሥት ግዥ ሕግ ከሚፈቅደው አሠራር ውጪ፣ የውስጥ ገቢ ማስገኛ በሚል ቢኤችዩ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ የተባለ አማካሪ ድርጅት በማቋቋምና በራሳቸው በፕሬዚዳንቱ ስም ንግድ ፈቃድ በማውጣት፣ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተለያዩ የግንባታ ሥራዎች የማካሄድ አገልግሎት እንዲሰጥ የቀጥታ ግዥ ውል መፈጸማቸውን የቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳብ ያመለክታል፡፡
በተጨማሪ ለአማካሪ ድርጅቱና አማካሪ ድርጅቱ ላፀደቃቸው ተቋራጮች ክፍያዎችን በመፈጸም በመንግሥት ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ለማጣራት በተደረገው የወንጀል ምርመራ፣ ከ195 ሚሊዮን በላይ ብር የሚያወጡ የግንባታ ሥራዎች ለዘጠኝ ተቋራጮች ከመንግሥት የግዥ አዋጅና አፈጻጸም መመርያ ውጪ በቀጥታ እንዲፈጸም ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለመሠረተ ልማት ግንባታ የተፈቀደለትን የካፒታል በጀት አላግባብ በመጠቀም የግዥ ሕግ ደንብ ባልተከተለ መንገድ ዋጋቸው 116 ሚሊዮን ብር የሆኑ 14 ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን በተቋራጩ ስም ግዥ መፈጸሙን፣ እንዲሁም የተገዙት ተሽከርካሪዎች ግን በግል ተቋራጮች ስም የተመዘገቡ መሆናቸው ተብራርቷል፡፡
በሌላ በኩል ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎቹ የተገዙበት ዋጋ እጅግ የተጋነነ መሆኑን፣ ለአብነትም አንድ ባለ ሁለት ተከፋች ጋቢና ያለው ፒክአፒ መኪና ከአስመጪ ድርጅቱ በ3.3 ሚሊዮን ብር ተገዝቶ ዩኒቨርሲቲው በ6.1 ሚሊዮን ብር እንደተረከበው ተደርጎ መመዝገቡ ተገልጿል፡፡
አሥራ አራቱ ተሽከርካሪዎች በዩኒቨርሲቲው ሀብት ቢገዙም ባለቤትነታቸው የሥራ ተቋራጩ እንዲሆኑ አድርገዋል የተባሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የተሰጣቸውን የመንግሥት ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ለራሳቸው የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና አማካሪ ድርጅት በሌለበት በተቋሙ የግንባታ ጽሕፈት ቤት የፀደቀ የክፍያ የምስክር ወረቀቶች መሠረት፣ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ለተቋራጭ እንዲከፈል በማድረግ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በነበሩት ጫላ (ዶ/ር) እና ቢኤችዩ በተሰኘው ድርጅት ላይ የተደረገው የሀብት ምርመራ እንደሚያሳየው፣ ድርጅቱን የሚያንቀሳቅሱት ሥራ አስኪያጅና የቦርድ ዳይሬክተር እሳቸው ናቸው ተብሏል፡፡ በዚህም ድርጅቱ በገባው ውል መሠረት ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ከዩኒቨርሲቲው የባንክ ሒሳብ ተቀንሶ ገቢ እንደተደረገለት ተገልጿል፡፡
በጫላ (ዶ/ር) ባለቤት ወ/ሮ ፀሐይ ኃይሉ ስም 72 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ባለሦስት ወለል ሕንፃ በአሥር ሚሊዮን ብር የተገዛ መሆኑን፣ ሕንፃው የተገዛውና ክፍያው የተፈጸመው ቢዳሩ ኮንስትራክሽን ከተሰኘ ድርጅት አራት ሚሊዮን ብር፣ አቶ ተስፋሁን ሌንጀቡ 3.3 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ቦኩ ኢታንሰ ከተሰኙ ግለሰብ 2.5 ሚሊዮን ብር በጫላ (ዶ/ር) ባለቤት ስም በተከፈተ የባንክ ቁጥር ገቢ መደረጉ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡ በዚህም ለሕንፃ ግንባታ አሥር ሚሊዮን ብር ወጪ ያደረጉት ግለሰቦች ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ጋር የጥቅም ትስስር እንዳላቸው በውሳኔ ሐሳቡ ተገልጿል፡፡
ጫላ (ዶ/ር) በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አንድ ሙሉ ክፍያው የተፈጸመ ቤት በልጃቸው ስም መኖሩን፣ እንዲሁም በራሳቸው ስም የአንድ ሚሊዮን ብር አክሲዮን መገኘቱ ከፍትሕ ሚኒስቴር ለቋሚ ኮሚቴው መቅረቡ ተጠቁሟል፡፡
በመሆኑም ቋሚ ኮሚቴው የቀረበለትን ያለ መከሰስ መብት ጥያቄ መሠረት በማድረግ ባደረገው ውይይት፣ የአባሉ ያለ መከሰስ መብትን ለማንሳት በቂ አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል ገርባ የምርጫ ክልል የብልፅግና ፓርቲን ወክለው ፓርላማ የገቡት ጫላ (ዶ/ር)፣ የቋሚ ኮሚቴውን የውሳኔ ሐሳብ ተከትሎ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በኦዲት ሪፖርቱ መሠረት በተካሄደው ምርመራ ቢኤችዩ ኮንሰልታንሲ እንደተባለው የግል ሳይሆን፣ የዩኒቨርሲቲው ድርጅት ነው ብለዋል፡፡ ይህ ድርጅት በአዋጅ 1152/2011 እና በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ 476 መሠረት ተደራጅቶ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ ተገዙ የተባሉት ተሽከርካሪዎች በፕሮጀክት ማዕቀፍ የተገዙ እንጂ በዩኒቨርሲቲው ቀጥታ ግዥ የተገዙ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ቀጥታ ግዥ ተብለው የተጠቀሱትም በ2012 ዓ.ም. አጋማሽ እና በ2013 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተማሪዎች ተመልሰው ትምህርታቸውን ባለው መሠረት ልማት መቀጠል ባለመቻላቸው ወቅት ተገንብተው ያልተጠናቀቁ ሕንፃዎች በመኖራቸው፣ ሕንፃዎቹን በማጠናቀቅ ተማሪዎቹ ርቀታቸውን ጠብቀው ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ለማድረግ የተደረጉ የቀጥታ ግዥ ናቸው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በግል የተነሱት ጉዳዮች ከሥራው ጋር ግንኙነት የላቸውም ያሉት ጫላ (ዶ/ር)፣ በዩኒቨርሲቲው በተቋሙ በነበሩበት ወቅት የነበረው ተቋማዊ ሁኔታ ፈታኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ፈታኙን ሁኔታ ለመቀየር በከፍተኛ ሁኔታ ሲሠሩ እንደነበር፣ ነገር ግን በዚህ መሀል ግድፈቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ሒደት ተቋሙን ከአካባቢው ጋር በማስተሳስርና በውስጥም በውጪም ግቢውን በማስዋብ በርካታ ሥራ ሲሠሩ እንደነበር ጠቅሰው፣ ነገር ግን ይህ ሁኔታ ያልተመቻቸውና ጥላቻ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ ብለዋል፡፡
ጫላ (ዶ/ር) አክለውም አገር በቀል ዕውቀቶች በትምህርት ውስጥ ተካተው እንዲያደርጉ፣ የገዳ ሥርዓት በትምህርት እንዲካተት ጥረት ሲያደርጉ መቆታቸውን፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥም አገር በቀል የፍትሕ ሥርዓት እንዲካተት ሲደረግ ይህንን ያልፈለጉ አካላት ጫና ሲያደርጉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡-
ከምክር ቤት አባላት መካከል ሕግ መከበር ቢኖርበትም ያለ መከሰስ መብታቸው የተነሳባቸው አባል ጉዳይ መታየት አለበት በማለት አስተያየት የሰጡ ነበሩ፡፡
በ2014 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካይነት በተካሄደ የባለድርሻ አካላት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ በዓቃቤ ሕግ ምርመራ በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የኦዲት ክፍተት እንደተስተዋላባቸው አስታውቆ ነበር፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎቹ መካካል ቡሌ ሆራ፣ አርባ ምንጭ፣ ሐዋሳ፣ ወልዲያ፣ መቱ፣ ደብረ ታቦር፣ ዲላና ዋቻሞ ይገኙበታል፡፡
በመጋቢት 2014 ዓ.ም. የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲን በተመለከተ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባጠናቀረው የ2013 ዓ.ም. ባለ 40 ገጽ የኦዲት ሪፖርት፣ በዩኒቨርሲቲው አሠራር ላይ በርካታ የኦዲት ክፍተቶች እንደተስተዋሉበት ገልጾ ነበር፡፡
የኦዲት ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በትምህርት ላይ ላሉ መምህራን ያላግባብ 788 ሺሕ ብር አበል መክፈሉን፣ ከተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅት መሰብሰብ የነበረበት 63 ሚሊዮን ብር አለመሰብሰቡን፣ በ24 ሚሊዮን ብር ከአዋጅና ከመመርያ ውጪ ግዥ አከናውኗልና የመሳሰሉት በርካታ የሕግ ጥሰቶች ተጠቅሰውበታል፡፡
በጫላ (ዶ/ር) ያለ መከሰስ መብት ላይ ከተገኙት 248 የምክር ቤት አባላት መካከል 247 እንዲነሳ ድምፅ ሲሰጡ፣ ጫላ (ዶ/ር) ግን ድምፀ ተዓቅቦ በማድረግ ውሳኔው በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡