በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተከዳሄደው ጦርነት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ከፍተኛ ዕልቂትና ውድመት ከማድረሱም በላይ፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለው ጉዳት እንደ ዋዛ የሚረሳ አይደለም፡፡ በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ግፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ጦርነቱ ለዘለቄታው እንዲቋጭ የሰላም ስምምነት ቢፈረምም፣ በስምምነቱ መሠረትም ለሰላም ሒደቱ የሚረዱ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ቢባልም፣ ሰላሙን የበለጠ ለማፅናት ሲባል ሕወሓት ከአሸባሪነት መዝገብ ስሙ እንዲፋቅ በፓርላማ በአብላጫ ድምፅ ቢወሰንም፣ ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት ናቸው ተብለው ክስ የተመሠረተባቸው ክሳቸው ቢነሳምና የታሰሩት ጭምር ቢፈቱም አሁንም ብዙ የሚቀሩ ተግባራት አሉ፡፡ በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል በወልቃይትና በራያ ግዛቶች ምክንያት ያለው ፍጥጫ አንዱና ዋነኛው ሲሆን፣ አፋርን ጨምሮ የሦስቱ ክልሎች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን መልሶ የማስቀጠሉ ጉዳይ ሌላው ተግባር ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ተግባራት በሰከነ መንገድ ለማስኬድ ግን፣ የሰላምን ተስፋ የሚያዳፍኑ ድርጊቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡ ከፈረሱ ጋሪው እየቀደመ ታጥቦ ጭቃ መሆን እንዳይከተል ይታሰብበት፡፡
ሰሞኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሹማምንት ወደ መሀል አገር በመምጣት፣ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተው ተመልሰዋል፡፡ ክልሉን መልሶ ማቋቋምና የካሳ ክፍያና የበጀት በፍጥነት መለቀቅ፣ የእስረኞች መፈታትና የይገባኛል ግዛቶችን የማስመለስና የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ውይይት የተደረጉባቸው ጉዳዮች እንደነበሩ ተሰምቷል፡፡ ቀደም ሲል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የአማራና የትግራይ ክልሎች ሕዝቦች ወንድማማቾች መሆናቸውን፣ አውዳሚው ጦርነትም በምንም ዓይነት ሁኔታ መነሳት እንዳልነበረበትና ያሉትን ችግሮች በመነጋገር መፍታት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱም መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ብቻ ሳይሆን አፋርንም ጨምሮ ሰላም የማስፈን ሒደቱን ማጠናከር ተገቢ ነው፡፡ እንዲሁም ሰላሙ አስተማማኝና ዘላቂ እንዲሆን ደግሞ፣ እከሌ ከእከሌ ሳይባል ሁሉም ኢትዮጵያውያን ዕገዛ እንዲያደርጉ ዕድሉን መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሒደት አንዱን የማቅረብና ሌላውን የመግፋት አባዜ ተወግዶ፣ ሰላምን የማስፈን እንቅስቃሴው ከሴረኝነት ይፅዳ፡፡ ሰላም የማስፈን ሒደቱ በሴራ ፖለቲካ ሲበከል ከተለመደው የጥፋት አዙሪት ውስጥ መውጣት አይቻልም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን እንኳንስ በሰሜን በመላዋ ኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ፣ ሙሉ ትኩረት ወደ ልማት እንዲሆን ፍላጎታቸው ነው፡፡ ይህ ፍላጎት ዕውን መሆን የሚችለው ግን የሚመለከታቸው የመንግሥትና የፓርቲ ባለሥልጣናት፣ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ፖለቲከኞችና ደጋፊዎቻቸው፣ ምሁራንና ልሂቃን፣ የእምነት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራት ተወካዮችና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሙሉ በኃላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት የሚፈለግባቸውን ለማበርከት ዝግጁ ሲሆኑ ነው፡፡ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ አመራሮች በማናለብኝነት እንደፈለጉ እንዳይወስኑ፣ ፖለቲከኞች ሥልጣንና የሚያስገኘውን ጥቅም ብቻ ከአገር በማስበለጥ እንዳሻቸው እንዳይሆኑ፣ እንዲሁም ሌሎች ወገኖች የአገርን ጉዳይ ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም በማሳነስ እንዳይመለከቱ እርስ በርስ መናበብ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ነገሮች ፈራቸውን እየሳቱ ያሉት ለሕጋዊና ለሰላማዊ ተግባራት ትኩረት በመነፈጉ ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ለኃላፊነትና ለተጠያቂነት መርህ የሰጡት ትኩረት እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ፣ ለሰላም መስፈን ጠንቅ የሆኑ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡
አገርን በቅጡ የማስተዳደር ኃላፊነት የተጣለበት መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ የሕዝቡን ውሎና አዳር መከታተል፣ ሰላሙንና ደኅንነቱን ማስጠበቅ፣ ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መከላከል፣ ለኑሮውና ለጤናው አደገኛ የሆኑ ጎጂ ድርጊቶችን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡ ዜጎችን ያለ አድልኦና ያለ ማግለል የሚያገለግል መንግሥት ዙሪያውን ጩኸት አይሰማበትም፡፡ ነገር ግን በማንነታቸው ምክንያት በጅምላ የተጨፈጨፉ፣ የተዘረፉና የተፈናቀሉ፣ ጎጆአቸው የፈረሰባቸውና ሕይወታቸው ሲዖል የሆነባቸው ዜጎች እሪታ ከአድማስ እስከ አድማስ እያስተጋባ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ እየተፈጸመ ያለው መጠነ ሰፊ ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ተብሎ፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና በሌሎች አካላት ጭምር መግለጫ እየወጣበት ነው፡፡ ዜጎችን ጎጆአቸውን በጅምላ እያፈረሱ ሜዳ ላይ መጣል ሰላም እንዳይሰፍን ከፍተኛ ሥጋት ከመፍጠሩም በላይ፣ እንዲህ ዓይነትና ሌሎች መሰል ተግዳሮቶች ሲበዙ ቀውሱን ያባብሳሉ፡፡ ሕግ በማስከበር ሽፋን በቂም በቀል ፖለቲካ የተለበጡ ክፋቶች ማቆሚያ ከሌላቸው፣ ከሚታሰበው የሰላም ተስፋ ይልቅ ሌላ ዙር ጥፋትና ውድመት እንደሚከተል ማሰብ ይገባል፡፡
በአገር ደረጃ ለሰላም መስፈን እንቅፋት እየሆኑ ካሉ ችግሮች መካከል አንደኛው የሐሰተኛ መረጃ መብዛት ነው፡፡ በዚህ ድርጊት ላይ የሚሳተፉ አካላት ቅራኔያቸው በየዕለቱ እየጨመረ በመሆኑ፣ ያለ ምንም ኃፍረትና ይሉኝታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሐሰተኛ መረጃ መፈብረክ የተለመደ ድርጊታቸው ሆኗል፡፡ በቀጥታ ሥርጭት ጭምር የሚተላለፉ ንግግሮችም ሆኑ የተቀረፁ መልዕክቶች ሳይቀሩ፣ ከዓውዳቸው ውጪ የሆነ ገጽታ እየተላበሱ ለሰላም መስፈን እንቅፋት እንዲሆኑ እየተደረጉ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ አሳፋሪ ድርጊት ውስጥ የተሰማሩት ደግሞ ገዥውን ፓርቲ የሚደግፉና በተቃራኒ የቆሙ ናቸው፡፡ መረጃ የማጥራት ተግባር የሚያከናውኑ ሌሎች ወገኖች ቢኖሩም፣ እነሱ ራሳቸው ከምን ፍላጎት አኳያ ተግባራቸውን እንደሚያከናውኑ ግልጽ ባለመሆኑ ተዓማኒነታቸው አስተማማኝ ሊሆን አልቻለም፡፡ በግራና በቀኝ በሚለቀቁ የተዛቡ መረጃዎች ሳቢያ ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅ፣ ከመነጋገር ይልቅ መገፋፋት እየበረታ ለሰላም ያለው ተስፋ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ብዙኃኑ ሕዝብ በኑሮ ውድነትና በሰላም ዕጦት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይህንን አሳዛኝ ገጽታ መለወጥ አለመቻል ዋጋ ያስከፍላል፡፡
ኢትዮጵያ ከበርካታ ዓመታት ፍዳና ጭቆና በኋላ የዛሬ አምስት ዓመት ለየት ባለ ሁኔታ አዲስ የለውጥ ንፋስ ቢነፍስባትም፣ አምስቱ ዓመታት በጅምራቸው ጊዜ ያሳዩት ተስፋና ተከትለው የመጡት አስመራሪ የመከራ ቋቶች ግን ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ይፈጥራሉ፡፡ ለሰላም፣ ለእኩልነት፣ ለፍትሕ፣ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና በነፃነት ለመኖር የሚረዱ መልካም ጅምሮች የታዩባቸው አምስቱ ዓመታት፣ ለማሰብ የሚከብዱ እጅግ በጣም አደገኛ ክፋቶችና ጥፋቶች የተፈጸሙባቸው በመሆናቸው ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ፈውስ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ለሰላም፣ አብሮ ለመኖር፣ ለሕግ የበላይነት መከበርና ለሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮች ተባባሪ የሆነ ኩሩና አስተዋይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ እያደር ከድጡ ወደ ማጡ መጓዟ ያሳዝናል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በውጭ ኃይሎች ግፊትና ጫና በሰላም ለመቋጨት የተደረገውን ጥረት ሩቡን ያህል፣ በሌሎች አካባቢዎች ቢሞከር ውጤቱ ቀና እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላም ተጠምቷልና፡፡ አሁንም መንግሥትን ጨምሮ የአገር ጉዳይ የሚመለከታችሁ በሙሉ፣ ለአስተማማኝ ሰላም መስፈን ቁርጠኝነታችሁን በተግባር አሳዩ፡፡ የሰላምን ተስፋ የሚያዳፍኑ ድርጊቶችንም አስቡባቸው!