‹‹ሥራ መልቀቅ መብት ነው›› የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ
ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ ተብለው ተተኪዎች የተሾሙላቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም የሁለቱም ፍርድ ቤቶች ምክትል ፕሬዚዳንቶች ከሥራ መልቀቅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ አስነሳ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ብርሃነ መስቀል ዋጋሪ፣ እንዲሁም ምክትል ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ ተናኜ ጥላሁን በፈቃዳቸው ሥራ መልቀቃቸው ተነግሮ ተተኪዎች ተሹመዋል፡፡
ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነት በፈቃዳቸው በለቀቁት አቶ ብርሃነ መስቀል ምትክ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የነበሩትና ከዓመታት በፊት ለቀው በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ይሠሩ የነበሩት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ ፕሬዚዳንት፣ ወ/ሮ ዛህራ ኡመር ዓሊ ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ተመርጠው፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ለፓርላማው ዕጩ ሆነው ከቀረቡ በኋላ ሹመታቸው በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡
በተመሳሳይ በጥር 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትላቸው በፈቃዳቸው የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው ተገልጾ በምትካቸው ዋናና ዋክትል ፕሬዚዳንቶች መሾማቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ለፓርላማ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች በፈቃዳቸው ለቀዋል ተብሎ ምትክ ከመሾም ለምን ለቀቁ የሚለው ጉዳይ መመርመር እንዳለበት፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባልና የምክር ቤቱ አማካሪ ኮሚቴ አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ጠይቀዋል፡፡
‹‹ይህ ከዳኝነት ነፃነት ጋር የሚያያዝ ጉዳይ የለውም ወይ? ምናልባት አስፈጻሚው አካል በዳኞች ነፃነት ውስጥ ጣልቃ እየገባ ስለሆነ ሊሆን አይችልም ወይ? መርምረነዋል ወይ? ይህ በደንብ እንዲታይ እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዳኝነት ነፃነትን የሚጋፋ ነገር እየተስተዋለ በመሆኑ ጉዳዩ ከዚህ ጋር ይተሳስራል የሚል እምነት ስላለኝ ነው፤›› ያሉት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ ‹‹ለምሳሌ የፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች በፖሊስ ያለ መፈጸም ሁኔታ አለ፡፡ ይህ ችግር በውሳኔያቸው ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ አሳድሯል?›› ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በመሆኑም ይህንን ጉዳይ የሕግና የፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ሊዘረጋ ከሚፈለገው የነፃ ዳኝነት ሥርዓት ጋር ያለው አንድምታ ምንድነው የሚለውን፣ እንዲሁም ከጣልቃ ገብነት ጋር መያያዝና አለመያያዙን ሪፖርት ሊቀርብ ይገባ ነበር ብለዋል፡፡
አንድ የምክር ቤት አባል በሰጡት አስተያየት፣ የተሾሙት ዳኞች በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት እንዲከበር እንዲሠሩና ለውጥ እንዲመጣ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ፍትሕ በገንዘብ በሚገዛበት በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ፍትሕ የለም ፍትሕ አጥተናል እያለ ነው፡፡ ገንዘብ ያለው በገንዘብ እየገዛ፣ ገንዘብ የሌለው ግን እየተንከራተተ ነው፡፡ ለኅብረተሰቡ ፍትሕ የምታመጡ እንድትሆኑ አደራ፤›› ብለዋል፡፡
ለጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት አሰያየም በፌዴራል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የሚታይ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ሥራ መልቀቅ መብት ነው፤›› ብለዋል፡፡
በሁለቱም ዳኞች ሹመት ላይ በእያንዳንዳቸው ላይ ሁለት ድምፀ ተዓቅቦ ቢቀርብም፣ የውሳኔ ሐሳቡ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡
የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 መሠረት ዳኞች የጡረታ ዕድሜያቸው ከመድረሱ በፊት በሦስት ምክንያቶች ከሥራ ሊሰናበቱ እንደሚችሉ ገልጸው እነሱም በዲሲፕሊን ቅጣት፣ በጤና መታወክ፣ ወይም በፈቃዳቸው በሚለው ሕግ መሠረት ሊለቁ እንደሚችሉ ቢናገሩም፣ ፕሬዚዳንቶቹ ግን በየትኛው ምክንያት እንደተነሱ አልገለጹም፡፡