- የፍትሕና የገንዘብ ሚኒስቴር ተቋማት የተሳተፉበት መፍትሔ ሰጪ ጥናት ተጠንቶ ተጠናቋል
- የጥብቅና ድርጅቶች የሒሳብ መዝገብ እንዲይዙ እንዳይደረግ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል
በሥራ ላይ ባለው የግብር አከፋፈል ሥርዓት ወይም ጠበቆችና የጥብቅና ድርጅቶች በየግላቸው የጥብቅና ፈቃድ ያላቸው በመሆኑ፣ ሁለቱም (ጠበቃውና ድርጅቱ) ግብር መክፈል እንዳለባቸው የሚደነግገው የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008፣ አግባብነት የሌለውና ከሕጉ አግባብ አንፃር አዋጁ ችግር ያለበት መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማኅበር፣ የገንዘብ ሚኒስቴርና የፍትሕ ሚኒስቴር በጋራ ባጠኑት ጥናት አስታወቁ፡፡
ተቋማቱ በጥናታቸው እንዳብራሩት፣ የጥብቅና ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/13 የሕግ ድርጅቶች ማቋቋምን ይፈቅዳል፡፡ ማንኛውም የጥብቅና ድርጅት ወይም ሸሪኮች የግብር አከፋፈል አግባብነት ባላቸው የሽርክና ማኅበር የተመለከቱ የግብር ሕጎችን የሚወስን ይሆናል፡፡ በመሆኑም የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 ‹‹ማንኛውም ድርጅት ደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋይ ሲሆን፣ ግብር የሚከፍልበትን ገቢ 30 በመቶ ግብር ይከፍላል›› እንደሚል ጥናቱ ያብራራል፡፡
የድርጅቱ ሸሪኮች በአዋጁ መሠረት ከትርፍ ክፍፍሉ ላይ አሥር በመቶ ግብር እንደሚከፍሉ ቢያስረዳም፣ የጥብቅና ድርጅት ሸሪኮች በየግላቸው የጥብቅና ፈቃድ ያላቸው በመሆኑ፣ የሚከፍሉት ግብር የትርፍ ክፍፍል ግብር ብቻ ይሁን ወይም ሌላ የግብር ግዴታ፣ አዋጁ በግልጽ ያስቀመጠው ድንጋጌ እንደሌለ ያብራራል፡፡
ጥናቱ እንደሚያስረዳው፣ የግብር አከፋፈልን በሚመለከት ጠበቃና የጥብቅና ድርጅት የሚሠሯቸው ሥራዎች አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ ሥራዎቹም ማማከርና የጥብቅ አገልግሎትን መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው፣ የግብር አከፋፈል ሥርዓቱም የተለየ መሆን እንደሌለበት በጥናቱ ተገልጿል፡፡ በዚህ ምክንያትም ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም የሚሰጠው አገልግሎት ከግለሰብ ጠበቃ የተለየ ባለመሆኑ፣ ከሕጉ አንፃር አዋጁ ችግር ያለበት መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል፡፡ አንድ ድርጅት በማኅበር ከተቋቋመና ሕጋዊ ሰውነት ካገኘ በኋላ፣ ‹‹በየግሉ ግብር ይክፈል›› ማለቱ አግባብ አለመሆኑንም አክሏል፡፡
‹‹ግብር ለየብቻ የሚከፈል ከሆነ ድርጅት ማቋቋም ጥቅሙ ምን ላይ ነው?›› በማለት የጠየቁት የጥናት ባለሙያዎቹ፣ ድርጅት ማቋቋም የሚፈልጉ በርካታ ጠበቆች ቢኖሩም፣ የሕጉ ግልጽ አለመሆን አርፈው እንዲቀመጡ እየተገደዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የፌዴራል ጥብቅና ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 ላይ እንደተደነገገው፣ ማንኛውም ጠበቃ ወይም ድርጅት ፈቃድ ለማደስ የግብር ክሊራንስ ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጠበቃ የግል ጥብቅና አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑንና የጥብቅና ድርጅትም ራሱን የቻለ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት መሆኑን አዋጁ ትርጉም እንደሰጠበት የሚያብራራው ጥናቱ፣ ይህ ሁለት የተለያዩ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው አካላት መሆናቸውን እንደሆነ ገልጿል፡፡
የጥብቅና ድርጅት ህልውና የሚኖረው በመሠረቱት አባላት ስምምነት በመሆኑ፣ ለሚገኘው የገቢ ግብር መክፈል ኃላፊነት የድርጅቱ መሆኑን በማብራራት፣ አባላቱ ከሚደርስባቸው የትርፍ ክፍያ ላይ አሥር በመቶ ቀንሶ በመያዝ፣ ለግብር ባለሥልጣኑ የማስገባት ኃላፊነት የድርጅቱ በመሆኑ፣ አባላቱ (ጠብቆች) በግላቸው ግብር መክፈል እንደማይጠበቅባቸው የጥናት ቡድኑ በጥናቱ አሳይቷል፡፡
በመሆኑም የድርጅቱ ክሊራንስ ለአባላቶች ጭምር (ለጠበቆቹ) እንደሚያገለግልና ፈቃዳቸውን ለማሳደስ በድጋሚ በግላቸው የግብር ክሊራንስ ሊጠይቁ እንደማይችሉ አክለው፣ ያ የማይሆን ከሆነ ‹‹በአንድ ገቢ ላይ ሁለተኛ ግብር መክፈልን (Double Taxation) እንደሚያስከትልና የገቢ ግብር ሕጉ ደግሞ ይህንን የማይፈቅድ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽንን በሚመለከት የጥናት ቡድኑ እንደገለጸው፣ ጠበቆች የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ለመጠቀም እንደማይገደዱ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር በሰርኩላር ቀሪ እንዲሆን መደረጉን ጠቁሞ፣ ለጠበቃና ለድርጅትም ተፈጻሚ የሚሆን መሆኑን ጥናቱ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
የሒሳብ መዝገብ አያያዝ የወጪ አመዘጋገብ ችግር እንዳይገጥመው ድርጅቶችም፣ እንደ ግለሰብ ጠበቆች ‹‹Progressive Taxation with Schedule›› መሆን እንዳለበትም የጥናት ቡድኑ ምክረ ሐሳብ አስቀምጧል፡፡
የጥናት ቡድኑ በዝርዝር ጥናቱ ባስቀመጠው መጠቁም (Recommendations) የደረጃ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች የሒሳብ መዝገብ መያዝ ግዴታ ቢሆንም፣ ጠበቆችና የጥብቅና ድርጅቶች ግን ከሥራው ልዩ ባህሪ አንፃር ወጪያቸው የሚመዘገብበት ሕግ ባለመኖሩ፣ የሒሳብ መዝገብ እንዲይዙ ሊገደዱ እንደማይገባ፣ ወይም የሥራ ባህርያቸው ልዩ መሆን ከግምት ገብቶ፣ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ መመርያ በልዩ ሁኔታ ሊወጣለት እንደሚገባ፣ በነጋዴ ላይ ለግብር አወሳሰን ግብዓት የሚሆኑ ፍሬ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የሕግ ማዕቀፎች ማሻሻያ፣ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባና ሌሎችንም ዝርዝር ምክረ ሐሳቦችንም የጥናት ቡድኑ አቅርቧል፡፡