Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአዲስ አበባ ተሽከርካሪዎች ሕጋዊ የቴክኒክ ምርመራ እንደማያደርጉ ተገለጸ

ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአዲስ አበባ ተሽከርካሪዎች ሕጋዊ የቴክኒክ ምርመራ እንደማያደርጉ ተገለጸ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ከ650 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች ውስጥ፣ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ እንደማያደርጉ ተገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰሌዳ ቁጥር ያላቸው ከ650 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እንደሚሰጡ፣ ከእነዚህ ውስጥ 330 ሺሕ ያህሉ ብቻ የቴክኒክ ምርመራ በማድረግ ቦሎ መውሰዳቸውን የተናገሩት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍሬው ደምሴ ናቸው፡፡

ወደፊት ሙሉ በሙሉ ወደ ሕጋዊነት ይመጣሉ ተብሎ ባይጠበቅም፣ 450 ሺሕ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች በየዓመቱ የቴክኒክ ምርመራ በማድረግ ቦሎ እንዲወስዱ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ ሳያደርጉ የሚቆዩ ተሽከርካሪዎች ቢኖሩም፣ በሚቀጥለው ዓመት ሊመጡ ስለሚችሉ ከእነ ቅጣቱ ክፍያ ይፈጽማሉ ተብሏል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ27 ሺሕ በላይ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች የተመዘገቡ መሆናቸውን፣ ለ29,300 ተሽከርካሪዎች ሰሌዳ መስጠቱን አቶ ፍሬው ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ከ30 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ ማከናወናቸውን አክለዋል፡፡

የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚታዩበት መሆኑን ገልጸው፣ ሕገወጥ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ሰርተፊኬት ከተፈቀደው ኮታ በላይ መመርመር እንዲሁም ተሽከርካሪን በወቅቱ የቴክኒክ ብቃትን አለማረጋገጥ ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ፈታኝ ሆነው መቆየታቸው ተናግረዋል፡፡

ሕጋዊ ከሆኑ ተቋማት በትክክል ምርመራ አድርገው የወጡ ተሽከርካሪዎች ምን ያህል ናቸው የሚለውን መረጃ በቀላሉ የሚገኝበት ሁኔታ ባለመኖሩ፣ ለመረጃ አያያዝ ተቸግረው መቆየታቸውን አቶ ፍሬው አስረድተዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ እነዚህንና ሌሎችን የአሽከርካሪና የተሽከርካሪ አሠራሮች ላይ ያለውን ችግር ሊፈታ ይችላል የተባለ መተግበሪያ ሲስተም፣ ቴዎስ ቴክኖሎጂ የተሰኘ ድርጅት ይፋ አድርጓል፡፡

መተግበሪያው ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ነው ይፋ የተደረገው፡፡ ቴዎስ ቴክኖሎጂ ይፋ ያደረገው አዲስ ቴክኖሎጂ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ያደረጉና ያላደረጉትን የሚለይ፣ ሐሰተኛ የቴክኒክ ምርመራን የሚያጋልጥ፣ የተሽከርካሪን የነዳጅ አጠቃቀም በዓይነት የሚለይ፣ መረጃን ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ቋት በቀጥታ የሚልክ ነው ሲሉ የቴዎስ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ አጥናፉ በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

ተቆጣጣሪ አካላት ተሽከርካሪው ዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ ማድረግና አለማድረጉን በቀላሉ በእጅ ስልካቸው፣ የተሽከርካሪውን የሰሌዳ ቁጥር በተዘጋጀው አፕሊኬሽን በማስገባት መለየት እንደሚችሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል፡፡

ከአሁን በፊት ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቢሆንም፣ ከዚህ በኋላ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ሲስተሙን በመጠቀም ሁሉም ወደ ሕጋዊ መንገድ ሊገቡ እንደሚችሉ አክለዋል፡፡

ቴክኖሎጂውን በዋናነት የሚቆጣጠረውና የሚያስተዳድረው የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ነው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...