አሽከርካሪዎች ሳያቋርጡ በተከታታይ ከአራት ሰዓታት በላይ ማሽከርከር እንደሌለባቸው የሚደነግግ አዲስ ደንብ ተረቆ፣ ለባለድርሻ አካላት ለውይይት ቀረበ፡፡
የአሽከርካሪዎች ለበርካታ ሰዓታት ማሽከርከርና ለድካም መጋለጥ ለአደጋ መንስዔ በመሆኑ፣ ይህንንም ለማሻሻል የተዘጋጀው ደንብ የአደጋ መንስዔዎችን በመቀነስ በኩል አስተዋጽኦ እንዲኖረው መዘጋጀቱም ተገልጿል፡፡
በመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ተረቆ በባለ ድርሻ አካላት ውይይት እየተደረገበት ያለው አዲሱ የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ፣ ከዚህ በፊት በ2003 ዓ.ም. ወጥቶ በ2009 ዓ.ም. ማሻሻያ ተደርጎበት የነበረውን ደንብ የሚሽር ነው፡፡ በውስጡም ከዚህ በፊት የነበሩ ድንጋጌዎችን አስተካክሎ ሌሎች በርካታ አዳዲስ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡
የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ኃላፊዎች ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በኢሊሌ ሆቴል ባካሄዱት ስብሰባ፣ በደንቡ ላይ የተደረጉትን ዋና ዋና ለውጦች በማስረዳት እንደ አዲስ ከመፅደቁ በፊትም አስተያየቶች ሲሰበሰቡ እንደነበር ተገልጿል፡፡
የአገልግሎቱ የሕግ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘሪሁን ጴጥሮስ፣ ለስብሰባው ተሳታፊዎች በደንቡ ላይ የተደረጉትን ለውጦችና አዳዲስ ድንጋጌዎችን በዝርዝር ገልጸዋል፡፡
አንደኛው እንደ አዲስ ድንጋጌ የገባው አሽከርካሪዎች በቀጥታ ከአራት ሰዓታት በላይ እንዳያሽከረክሩ የሚለው ሲሆን፣ የዚህን ድንጋጌ አስፈላጊነትም ለተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡
ኃላፊዎቹ ደንቡን በሚያዘጋጁበት ጊዜ በዚህኛው ድንጋጌ ላይ ብዙ ሐሳቦች ተለዋውጠው በመጨረሻ እንዲገባ መደረጉን የተናገሩት አቶ ዘሪሁን፣ አሽከርካሪዎች ለበርካታ ሰዓታት ካሽከረከሩ የድካም ስሜት ስለሚኖርና አደጋ ስለሚያደርሱ ዕረፍት ማግኘት ስላለባቸው ጥንቃቄ እንዲወስዱ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የትራፊክ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል ግልጽ ነው፤›› ብለው፣ ለረዥም ሰዓታት የማሽከርከርን ችግር የተናገሩት ሥራ አስፈጻሚው፣ አሽከርካሪዎች ከአራት ሰዓታት በላይ እንዳያሽከረክሩ ማለት ግን አስገዳጅ ሆኖ እንዳይቆጠር አሳስበዋል፡፡ ‹‹ለማስገንዘብ ያህል ነው›› ብለውም፣ አሽከርካሪዎችን በዚህኛው ድንጋጌ በሕግ ሊጠየቁ እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡
በደንቡ ላይ እንደ አዲስ ከተጨመሩት ድንጋጌዎች መካከል በሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች በከፍተኛ ድምፅ ሙዚቃ መክፈት፣ አሽከርካሪዎች መጠጥ በመጠጣትና ጫት በመቃም ወይም እያቆሙ አገልግሎት መስጠት እንደሌለባቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሕፃናት በተሽከርካሪ ውስጥ ይዘው የሚጓዙ ማናቸውም አሽከርካሪዎች፣ በተሽከርካሪዎች የኋላ መቀመጫ ላይ የሕፃናት ደኅንነት መጠበቂያ ቀበቶ ሊኖራቸው እንደሚገባም ደንቡ ያስገድዳል፡፡ የተሽከርካሪዎች ደኅንነት መጠበቂያ ቀበቶ መሥፈርት በአገልግሎቱም እንደሚወጣ ተጠቁሟል፡፡
በሌሊት የሚደረግ ጉዞን በሚመለከት ደንቡ እንደ አዲስ እንደሚደነግገው፣ የሕዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች በሌሊት በሚጓዙበት ወቅት አግባብነት ካለው አካል ሥምሪት ሳያገኙ መጓዝ እንደሌለባቸው ነው፡፡ ተሽከርካሪዎች የእግረኛ ማቋረጫ ቀለም ቅብ (ዜብራ) ከመድረሳቸው በፊት፣ ከማቋረጫው መስመር አንድ ሜትር ራቅ ብለው ማቆም እንዳለባቸውም በተጨማሪ ተደንግጓል፡፡
ከዚህ በፊት ተደንግጎ ነገር ግን በዚህኛው ደንብ የተሻረ ድንጋጌም እንዳለ አቶ ዘሪሁን የገለጹ ሲሆን፣ ድንጋጌውም የጭነት ተሽከርካሪዎች ሦስት የሆኑ መሥፈርቶችን አሟልተው የሚገኙ ከሆኑ ሕዝብ እንዲያመላልሱ ይፈቅድ የነበረው ነው፡፡
አገልግሎቱ ሲቋቋም 29 ከቅድመ አደጋ እስከ ድኅረ አደጋ ድረስ የሚሸፍኑ ሥልጣንና ተግባራትን እንደሚያከናውን የገለጹት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሮ ፈትያ ደድገባ፣ ካሉበት ኃላፊነቶች አንደኛው እነዚህ ሕግጋቶች ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹ዛሬ የምናደርገው የሕግ ማሻሻያ ሰነድ ዝግጅት አንዱ ከተሰጠን ሥልጣን ውስጥ ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ ፈትያ፣ አስተያየት እየሰበሰቡ ያሉት በሕጎች ላይ ዜጎች አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ለማድረግ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡