Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሐሰተኛ መታወቂያ ሥርጭት በተሳተፉ አመራሮችና ተባባሪዎቻቸው ላይ ዕርምጃ መወሰዱ ተገለጸ

በሐሰተኛ መታወቂያ ሥርጭት በተሳተፉ አመራሮችና ተባባሪዎቻቸው ላይ ዕርምጃ መወሰዱ ተገለጸ

ቀን:

አራት አመራሮቹ በሐሰተኛ የመታወቂያ ሥርጭት መሳተፋቸውን፣ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ (የቀድሞው የአዲስ አበበ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ) አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው አራት አመራሮቹ በሐሰተኛ ሰነድ እጃቸው እንዳለበት ማረጋገጡን ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. የተገለጸው ኤጀንሲው፣ እያደረገው ባለው ሪፎርም አገልግሎት መስጠት ተቋርጦ ከተጀመረ በኋላ በተደረገው ክትትል፣ በተለይ በሕገወጥነትና ሐሰተኛ ማስረጃ ሥርጭት ተሠማርተው የተገኙ አካላትን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

የኤጀንሲው አራት አመራሮች በሐሰተኛ ሰነድ ሥርጭት ተሰማርተው መገኘታቸውን የገለጹት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ዓለማየሁ ናቸው፡፡

‹‹የሐሰተኛ ሰነድ ሥርጭት ለኤጀንሲው ከባድ ፈተና ሆኗል፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹በአመራርነት እያገለገሉ ያሉና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አራት አመራሮች ከመረጃ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከአመራሮቹ በተጨማሪ በኤጀንሲው የሚገኙ ስምንት የቡድን መሪዎች፣ 51 ባለሙያዎችና አራት ደላሎች በሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እንደተሳተፉ፣ 86 ሐሰተኛ ሰነድ ይዘው የተገኙ ባለጉዳዮችን ጨምሮ በአጠቃላይ 153 ሰዎች ተጠያቂ መደረጋቸውም ተገልጿል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ‹‹ይህንን በዝርዝር ስንመለከተው በየክፍለ ከተማው ተጠያቂ ሆነው የተገኙት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ 15፣ በልደታ አምስት፣ በቦሌ ዘጠኝ፣ በአራዳ አራት፣ በጉለሌ ሰባት፣ በንፋስ ስልክ አራት፣ በለ ሚኩራ 14፣ በአቃቂ ሁለት፣ በየካ አራት፣ በአዲስ ከተማ ሦስት፣ በኮልፌ ቀራኒዮ አራት፣ በአጠቃላይ 71 ሰዎች ተለይተዋል፤›› ብለዋል፡፡

ከማስረጃ አኳያ ማብራሪያ ሲሰጡም 79 የሚሆኑ ሐሰተኛ ማስረጃዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደተቻለ አቶ ዮናስ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እነዚህ ሐሰተኛ ሰነዶች ዝግጅታቸውን ስንመለከት ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ ያለው ጉዳይ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ከዚህም ባሻገር ላልተገቡ ወይም ኢትዮጵያዊ ላልሆኑ ሰዎች ሰነድ መስጠት፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ለማይገባቸው ሰዎች የነዋሪነት መታወቂያ መስጠት ተጠቃሽ ናቸው፤›› ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው የተነገረው በኤጀንሲ ከተቀመጠው የአሠራር ሥርዓት ውጪ ሰነዶችን የመጠቀም ዝንባሌ እንዳለ፣ አገልግሎትን በገንዘብ የመሸጥ ሙከራ ያደረጉ ባለሙያዎችን ተጠያቂ ስለመደረጋቸው ነው፡፡

‹‹እጅ ከፍንጅ የያዝናቸው ሰዎች አሉ፤›› ያሉት አቶ ዮናስ፣ ‹‹በድምሩ 153 ሰዎች በቁጥጥር ሥር  እንዲውሉ ስናደርግ፣ ያለው ችግር ከዚህ የከፋ እንደሚሆን ታሳቢ በማድረግ፣ በደረሰን ጥቆማ በእኛ አሠራር ሥርዓት ውስጥ ተጠያቂ ልናደርጋቸው በምንችለው ደረጃ ክትትል አድርገን የያዝናቸው ናቸው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹የተቋማችን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ አሁን ካለበት አኳያ ስንመለከት፣ በከተማ ውስጥ ያለው የሐሰተኛ ሰነድ ሥርጭት እጅግ በጣም እየከፋ ነው፡፡ የፓስፖርት አገልግሎት ፍላጎት ከመጠን ያለፈና ከፍ ያለ መሆን እኛ ዘንድ የሐሰተኛ ሰነድ ተጋላጭነት የከፋ እንዲሆን አድርጎታል፤›› ብለዋል፡፡

ኅብረተሰቡ የፓስፖርት ፍላጎቱ የጨመረው በትክክለኛነት ከአገር ወደ አገር ለመዘዋወር ብቻ ሳይሆን፣ ፓስፖርቱን ወስዶ ለማስቀመጥም ጭምር መሆኑን በተደረገው ዳሰሳ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

እንደ ገለጻው ከሆነ፣ የተለያዩ የውጭ አገር ዜጎችም የኢትዮጵያ ፓስፖርት ይዘው በማዕከል ደረጃ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

‹‹የእኛን ሰነዶች አስመስሎ መሥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈተና እየሆነ ነው የመጣው፡፡ አስመስሎ ለመሥራት የሚደረገው ጥረትም ከፍተኛ ነው፤›› ያሉት አቶ ዮናስ፣ ‹‹ከዚህ ቀደም በአንድም በሌላም መንገድ በደላሎች እጅ የገቡ ሰነዶችም መኖራቸውን አረጋግጠናል፤›› ብለዋል፡፡

በጦርነት ቀጣና የነበሩ የክልል የወሳኝ ኩነት መዋቅር የነበሩ ሰርተፊኬቶችም በነበረው ችግር ባልተገቡ ሰዎች እጅ እንዲሠራጩ የተደረገበት አጋጣሚ እንዳለም፣ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጋር በመሆን ተምግሟል ብለዋል፡፡

ከኤሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ወደ ኤጀንሲ የሚላኩ ሰነዶችን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ዮናስ፣ ‹‹ላለፉት ሦስት ሳምንታት  35 ሰነዶች እንዲጣሩ ወደ እኛ ተልከው፣ ከእነዚህ መካከል 29 ሰነዶች ሐሰተኛ መሆናቸውን አረገግጠናል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር አሁን እያጣሯቸውና በእጃቸው ላይ የሚገኙ 91 የሚሆኑ ሰነዶች እንዳሉ፣ ከእዚህም ውስጥ ትክክኛ ያልሆኑ ከኤጀንሲው ያልወጡ ማስረጃዎች እየተደረገ ባለው ማጣራት እየተለዩ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ 104 ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎትን ጨምሮ የልደት፣ የጋብቻና ሌሎች የወሳኝ ኩነት አገልግሎቶች እየተሰጡ ቢሆንም፣ በቀሪዎቹ 14 ወረዳዎች ግን አገልግሎቱ የሚሰጠው በማንዋል መሆኑን ተነግሯል፡፡

እንደ ገለጻው ከሆነ፣ በከተማ አስተዳደሩ ሥር የሚገኙ ቀሪዎቹ በ14 ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የዲጂታል አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉት መሠረተ ልማት ስለሌላቸው ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ሲሠራ በነበረው መሠረት የቴክኖሎጂ ዝርጋታ እንደተጠናቀቀ፣ ከዚህ በኋላም በ14 ወረዳዎች የወረቀት አገልግሎቱ ሙሉ ለሙሉ ቀርቶ የዲጂታል አገልግሎት እንደሚዘረጋ ተገልጿል፡፡

ከወረቀት ንክኪ በመውጣት የወሳኝ የኩነት አገልግሎት ለመስጠት በተደረገው ጥረት በ104 ወረዳዎች 470 ሺሕ ነዋሪዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት የዲጂታል አገልግሎት ማግኘታቸው ተጠቁሟል፡፡

የዲጂታል አገልግሎቶችን ሙሉ ለሙሉ ለማዳረስ እየተሠራ ቢሆንም፣ ሪፎርሙ ከተጀመረ ከጥቅምት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ከኤጀንሲው ውስጥም ሆነ ከኤጀንሲው ውጪ ባሉ አካላት በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ ነው ተብሏል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ የአሠራር ሥርዓቱን በሪፎርም የማሻሻል፣ በየዕለቱ የሚሰጠው የወሳኝ የኩነት አገልግሎቶችን ኦዲት የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑም  ተብራርቷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ከሚገኙ 1.7 ሚሊዮን ነዋሪዎች መካከል 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑት የዲጂታል መታወቂያ እንዳላቸውም ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...