Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የእንቆቅልሻችን ብዛቱ!

ሰላም! ሰላም! እስላም ክርስቲያኑ ፆም ላይ ሆነው ለአገር ሲፀልዩ፣ አገር ሰላም አገር አማን እንዲሆን በየበኩላችን የሚፈለግብንን ብናበረክት መልካም ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንዳንዴ ወጣ ገባ እያልን ከቀልዱም ከቁምነገሩም ስንጋራና ስናጋራ፣ የአገር ሰላም ጉዳይ መቼም ቢሆን ሊረሳን አይገባም፡፡ እንዲህ ካልኩ እስቲ ወደ ወትሮው ትግላችን እናምራ፡፡ እንዴት ነው የከባድ ሚዛን ትግሉ? ኑሮን ማለቴ ነው። ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ከዓመታት በፊት የከባድ ሚዛን የቦክስ ውድድር የሚደረገው ብዙ እየቆየ ስለነበር፣ ዓለም ፍልሚያውን ለማየት የሚኖረው ጉጉት ላቅ ያለ ነበር። አሁንስ? አሁንማ ኑሯችን በራሱ ከባድ ሚዛን ሆኖ፣ መሸ ነጋ የሚያሳስበን እሱ ነው፡፡ የከባድ ሚዛን ቦክስ ተፋላሚዎችማ አንድም ለድልና ለዝና ብሎም ጠቀም ላለ ገንዘብ ነበር የሚፋለሙት። የእኛ አለ እንጂ ታግሎ ለሽንፈት፣ ሳይኖሩ ለመሞት። ኧረ ተውኝ እባካችሁ፡፡ በቃ ምን የለን ምን የለን፡፡ እንዲያው በባዶ ተስፋ ጥቂቶች ተሳክቶላቸው ሲኖሩ፣ አብዛኞቻችን ዕድሜን እንዲሁ ስንገፋ እንደ እነ አዛውንቱ ባሻዬ አርጅተንና ገርጅፈን ቁጭ። ያን ጊዜ ‘እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ፣ እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ’ ቢሉ ቢጮሁ፣ ‘ዋ!’ ብሎ መቅረት ይሆናል እንደ ሰማይ አሞራ። በእነ ጭልፊት ዘመን እነ አሞራ የዋህ ናቸው አትሉም!

ወይ ጉድ ዝም ብዬ በትካዜና በትችት ስንደረደር ዝም ትሉኛላችሁ? ‹‹ወንድሜ አንበርብር እንኳን እኛ የሦስተኛው ዓለም ሰዎች ተርፏቸዋል የተባሉትም እኮ እያማረሩ ነው…›› አለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ድንገት ደርሶ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ምንም እንኳ ዕውቀት ባያጥረው የገንዘብ እጥረት ግን ኩምሽሽ ያደርገዋል። ‹‹እኛ ስንዴ በትርፍ አምርተንም አያያዙን ባለማወቅ ወይም በስግብግብነት ላያችን ላይ ዋጋውን እየቆለልን ዳቦ ያምረናል፡፡ ምዕራባውያኑ በጥጋባቸው ምክንያት ደካማዋን ዩክሬን ከግዙፏ ሩሲያ ጋር አዋግተው፣ ዩክሬንያውያን ብቻ ሳይሆኑ መላ አውሮፓ በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ ነው፡፡ ተመልከት እንግዲህ ፈረንሣይ የጀመረው ነውጥ በጀርመን ቀጥሎ ከኑሮ ውድነቱ በተጨማሪ በኑክሌር ላለማለቅ ኔቶን በቃህ እያሉ እየጮሁ ነው…›› ሲለኝ፣ እነሱ እንዲህ የሆኑ የእኛ መጨረሻ ቢያስፈራኝ ልቤ ተረበሸ። ‹‹አንበርብር እኛ አያያዙን አላውቅበት ብለን ወይ ከታሪክ አንማር፣ ወይ ከሌሎች ጥፋት አንማር እንደ ዘመነ መሣፍንት ሰዎች በየቦታው ኬላ አቁመን መታወቂያ እንጠያየቃለን፡፡ ለረሃብ ማስታገሻ የሚሆነውን ምግባችንን አግተን ሕዝባችንን አሳሩን እናበላለን…›› ብሎ በወርቅና በሰም የተለበጠውን ቅኔ ለቀቀብኝ። ነገር ከተጀመረ እኮ ማቆሚያ የለውም!

እናም ጨዋታም አይደል የያዝነው? ያለፈውን ከማሞገስ የያዙትን ከማክፋፋት ምንም እንደማይገኝ የማውቀው እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ‹‹ወደፊት›› ብዬ ወደ ሥራዬ ተሰማርቻለሁ። ዘመኑን አመነውም አላመነውም፣ መንግሥትን አማረርነውም አሞገስነውም ቀኑና ሌሊቱ መምሸት መንጋቱን መቼ ይተዋል? እንዲያው ነው እባካችሁ፡፡ ታዳያላችሁ አንድ የሚከራየው ቤት ማግኘት የተቸገረ ሰው አላስቆም አላስቀምጥ ብሎኝ እንከራተታለሁ። ይገርማችኋል አሁን ይኼ ቤት አጥቶ እረፍት አሳጣኝ የምላችሁ ሰው የተከራየውን ቤት ለቆ እንዲወጣ፣ ድርስ እርጉዝ ልጃቸውን እያሳዩት ተማፅኖ ያቀረቡለት አከራዩን ላለማስቀየም ሲል ቤት ፈልግልኝ ያለኝ በቀደም ዕለት ነው። ‹‹ምንስ ቢሆን ይህ ሰው በዚህ በችግር ጊዜ ሰበብ እየተፈጠረ ከኖረበት ቤት ይባረራል?›› ስላቸው ባሻዬን፣ ‹‹ወይ አንተ ድሮና ዘንድሮ አንድ መሰለህ? ድሮ የሰው መድኃኒቱ ሰው ነበር፡፡ የአሁኑን ግን ምን እነግርሃለሁ አንበርብር? ያለ ገንዘብ ሰው ዘመድ አላውቅ ብሏል እኮ…›› አሉኝ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ፊታቸውን ሸፍኖት። እነሆ ይኼን ያህል ዘመን ያስቆጠረ የሰው ልጅ የሥልጣኔ ሩጫ መጨረሻው በአፍቅሮተ ንዋይ ግብግብ ሊቋጭ ያሰፈሰፈ ይመስላል። ‹‹ትዝታ ታማኝ ነው ወረትን አያውቅም፣ እንደ ሰው ለገንዘብ ቦታውን አይለቅም…›› እየተባለ እስከ መቼ ሰው በሰው ትዝታ ይዘልቅ እንደሆን እንጃ። ‹‹እኔ አላማረኝም አዲስ ነገር በዝቷል፣ በኪስህ ተማመን ጎበዝ ፍቅር ጠፍቷል…›› ያለው ሙዚቀኛ ትዝ ሲለኝ ደግሞ ግራ ይገባኝ ይጀምራል። ስንቱ ግራ አጋብቶን እንደምንዘልቀውም ራሱ ግራ ይጋባል!

 ታዲያ ቤት ፍለጋ ላይ ታች ስል ጉድ ቆጠራ የተሰማራሁ ይመስል የማላየውና የማላጤነው ነገር አልነበረኝም። ቤት ፍለጋዬ ያተኮረው ኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ ነው። ባለአንድ መኝታ ሦስተኛ ፎቅ ላይ አለ ብለውኝ ለማየት እየወጣሁ ሁለተኛው ደረጃ ላይ ስደርስ፣ ‹‹እንጀራ ሙሉውንና በቁርጥ እንሸጣለን…›› የሚል ጽሑፍ አነበብኩ (መቼም አንዴ ጉድ አይጣችሁ የተባልን እኮ ነን)፡፡ አብሮኝ የነበረውን ሰው፣ ‹‹ምንድነው ይኼ?›› አልኩት እያየሁት እንደማያይ ሆኜ። ‹‹እንጀራ ተቆርጦ ይሸጣል ማለት ነው?›› ስለው፣ ‹‹ያውም አንዱ እንጀራ ስድስት ቦታ ተቆርጦ ነዋ…›› ብሎ ሊያሾፍብኝ ቃጣው። የብልፅግናው መንግሥታችን ያላየው (ምናልባት እያየ እንዳላየ የሆነበት) ጉድ ትላላችሁ ከዚህ በላይ ምን አለ? ታዲያ እኔም አፌ አያርፍ ምን ስል ጠየቅኩ መሰላችሁ? ‹‹እውነት ብልፅግና ዝም አለ?›› ብለው፣ ‹‹ምን ይላል ይኼ ሰው? መንግሥት የሚባለው ማን ሆነና?›› ብሎ ያ አብሮኝ ደረጃ የሚወጣው ሰው ተበሳጨብኝ። ‹‹ወዳጄ እዚህ ለምሳሌ ነጭ ወይም ሰርገኛ የጤፍ እንጀራ ነው የሚሸጠው፡፡ ወጣ ብለህ ጉራንጉሩ ውስጥ ብትገባ ደግሞ ከትንሽ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ወይም ሌላ እህል የተቀየጠ ዓይነ ሰፋፊ ወፍራም እንጀራ በሽ ነው…›› ሲለኝ ጥያቄና መልሳችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሄድ በራሴ ጊዜ አቆምኩት። አገር ምድሩ ለይቶለታል አይደል እንዴ ጎበዝ!

ጉድና ጉዳ ጉዱን እዚህና እዚያ ስባክን እያየሁ ከአንደኛው ጉዳይ ወደ ሌላው እዘላለሁ። በፊት ደህና ምግብ ቤት ገብቶ ዘና ብሎ ምሳውን ይበላ የነበረ ሁሉ ቁልቁል ተዘቅዝቆ፣ በቃሪያና በሽንኩርት ያበደ ዳቦ በድንች (እርጥብ ይሉታል) መንገድ ዳር ተሰባስቦ መብላት ከጀመረ መሰንበቱን ብዙዎች ታውቃላችሁ፡፡ ‹‹አንበርብር ይህም ወደፊት ብርቅ መሆኑ አይቀርም…›› ያለኝን ደላላ ወዳጄን ገርምሜ ወደ ሥራዬ አመራሁ፡፡ በድለላ ሙያ ከተሰማራችሁ ‹‹ያልተገላበጠ ያራል›› የሚሉት አባባል በደንብ እንደሚሠራ ታረጋግጣላችሁ። ዳሩ የዘመኑ ሰው እንዲህ ያለውን የሥራ ማነቃቂያ አባባል የሚሞክረው አጉል አጉል ቦታ ሆኗል። ‹‹እስኪ አስቡት ሕዝብ ለማገልገል ተሹሞ እንደ መዥገር የሰው ደም ሲመጥ፣ የትውልድ አርዓያና ተምሳሌት ለመሆን በቃል ኪዳን ታስሮ ትዳር መሥርቶ ሲያበቃ፣ ከአንዷ ወደ ሌላዋ ሲገለባበጥና ተነካክቶ ሲያነካካ ዝም ሲባል አይጨንቅም?›› ስል የሰማኝ አንድ ወዳጄ፣ ‹‹በጣም እንጂ፣ ደግነቱ በቤተሰብና በትዳር ላይ ያለውን የሞራል ዝቅጠት ለመታደግ ራሱን የቻለ ‘ፀረ ወዲያ ወዲህ’ የሚባል ኮሚሽን ያስፈልጋል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ግን ከምንም ነገር በላይ ታስቦበት የምግብ ሚኒስቴር ቢቋቋም እላለሁ፡፡ ምግብ እንዲህ እንደ አልማዝ ተወዶብን ከምግብ በላይ ሌላው ሚኒስቴር ትርፍ ነገር ነው…›› ሲለኝ አስደነቀኝ። ጎበዝ አቤት እንበል እንዴ!

እናም ስዘዋወር ያገኘሁት ሥራ ያው የቤት ሽያጭ ድለላ ሆነ። ምን ይደረግ ቤት በሌለበት አገር ቤት ፈላጊው በዝቶ እኮ ነው። ቤቱን ለመሸጥ የቀረበውን ዋጋ ስሰማ ሄጄ ለማየት ጓጓሁ። የተባለውን ቤት ሄጄ ሳየው የተጠሩት ሚሊዮን ብሮች ያንሱታል እስክል ድረስ አስገራሚ ነበር። ወዲያው የማገኘውን ኮሚሽን ሳሰላው ያቁነጠኝጠኝ ጀመር። ገዥ ይገኛል ብዬ ካሰላሁት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሁለት ደንበኞች ሲገጥሙኝ ግን ድንግጥ አልኩላችሁ። ምን አስደነገጠህ አትሉኝም? በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ልክ፣ ሚሊዮን ምንም የማይመስለው የኅብረተሰብ ክፍል መበራከቱ ነዋ። ‹‹ካፒታሊዝም ይሏል ይኼ ነው…›› የሚለው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስላቅና ምፀት አዘል አባባል ጆሮዬ ላይ ደወለ። ይኼኔ አንዱ ነገረኛ ሰማኝ መሰል፣ ‹‹ታዲያስ፣ ዕድገት የለም ትላላችሁ ግን ይኼው ሚሊዮን በግለሰብ ደረጃ አስቆጠርናችሁ…›› ብሎ ገላመጠኝ። ምን ትሉታላችሁ? የነገረኛው ሰው ንግግር ደንበኛዬ ጆሮ ጥልቅ ስላለ፣ ‹‹ምንድነው የሚለው?›› ብሎ ጠየቀኝ። እኔም የተናገረውን ስደግምለት፣ ‹‹ተወው እባክህ ‘ሞኝና ወረቀት ያስያዙትን መቼ ይለቅና?›› ብሎ ተረተበት። ወዲያውም መሄዳችን ስለነበር የመኪናውን ጋቢና በር ከፈተልኝ። ሚሊዮን መቁጠር የተጀመረው በልፋት ነው ወይስ በአቋራጭ? አቋራጩ በዝቶ ሚሊዮኖች ለዳቦ ሲሠለፉ፣ ጥቂቶች ሚሊየነር ሆኑ፡፡ መጥኔ በሉ ማለት አሁን ነው!

 ሳናስበው የጀመርነውን የጭውውት ቀዳዳ እያሰፋን መጓዝ ጀመርን። ትንሽ እንደሄድን ጨዋታችንን አቁመን በስሱ ተከፍቶ ወደ የምንሰማው ‹‹ኤፍኤም›› ሬዲዮ ሁለታችንም ጆሯችን ቀሰርን። ጋዜጠኛው እየደጋገመ የእንግሊዝ ንጉሣውያን ቤተሰብና የአዲሱን ንጉሥ ሥርዓተ ንግሥ በተመለተ በመገረም ይተነትናል፡፡ ደንበኛዬ በጣም ተናዶ፣ ‹‹እሺ እንደ ዜና ይወራ ግድ የለም። ትንታኔ ውስጥ ለመግባት እኛ ምን አገባን? ምናለበት መንግሥት ቀልዶ ባያስቀልድብን?›› አለ። ‹‹እንዴት?›› አልኩት ጥቂት ላናግረው። ቀልብ በጠፋበት ዘመን ከቀልቡ ሆኖ የሚያወራ ሰው ጥቂት በመሆኑ፣ በሰማው ነገር እጅግ ተቆርቁሮ ሳየው ከልቡ መሆኑ ስለገባኝ። ‹‹እንዴት?›› አለኝ ዞር ብሎ ዓይቶኝ። ‹‹ስንት ለአገር የሚጠቅሙ ርዕሰ ጉዳዮችን እያነሳ የኅብረተሰብ ንቃተ ህሊና ከማጎልበት ይልቅ፣ ፋይዳ ቢስ ዘገባዎች ጊዜና ኢነርጂ እያቃጠሉ የሚዘግቡትን ዝም ማለቱ ነዋ። ስንት ቁም ነገር ማውራት በሚገባን ሰዓት፣ ስንት ልንነጋገርባቸው የሚገቡን ጉዳዮች እያሉ ሕዝቡን በኳስ ተጫዋቾች የጫማ ቁጥርና የከንፈር ወዳጆች፣ በፊልም ተዋናዮች የአልጋ ልብስ ቀለም ሲያደነቁሩ መዋል አለባቸው? መንግሥትስ ከሕዝብ በሚሰበስበው በጀት በሚያስተዳድረው የሬዲዮ ጣቢያ ዝም ብሎ ማለፍ ይገባዋል? ኧረ ተወኝ እባክህ…›› አለኝ በረጅሙ ተንስፍሶ። ‹‹ወንድሜ መርጦ ማዳመጥ የእኛ ፈንታ እንጂ፣ ይህንን ዘግቡ ያንን አትዘግቡ በማለት በንዴት መወራጨት ትክክል አይደለም…›› አልኩ እኔም በልቤ። በአፌ ተናግሬ ደንበኛዬን ማስቀየም አልፈለግኩም፡፡ ትችትና አስተያየት እንካ ሰላንቲያ በሚያስነሱበት አገር ወደ ውስጥ ተናግሮና ወደ ውስጥ ተንፍሶ እንዴት ይኖራል ግን? እንዴትም!

እንሰነባበት እስኪ። ሥራዬን ጨራርሼ በነጋታው ኮሚሽኔን ለመቀበል ቀጠሮ ይዤ ሳበቃ ወደ ቤቴ ገሰገስኩ። ሠፈር ስደርስ ካፊያ ቢጤ መጣል ጀምሯል። ሁሉም ባገኘው መጠለያ ሽጉጥ ሲል አሻፈረኝ ብዬ እኔ ወደ ቤቴ ሮጥኩ። ልክ በሩን ከፍቼ ስገባ ባሻዬና ማንጠግቦሽ ተቀምጠው ወግ ይዘዋል። ‹‹ባሻዬ? ምን እግር ጣለዎት?›› አልኳቸው በካፊያ የረሰረሰ ካፖርቴን እያወለቅኩ። ‹‹ካፊያ ሲይዘኝ ልጄ ቤት ላባራው ብዬ ነዋ…›› አሉኝ የአባትነት ፈገግታቸው በቅንነት ፊታቸውን እያበራው። በደስታ ፈገግ እያልኩ ከጎናቸው ስቀመጥ፣ ‹‹ሰሞኑን ከባድ ዝናብ ይጥላል ብሎ ሬዲዮ ሲናገር ሰምቻለሁ። ጠንቀቅ ብላችሁ ነቅታችሁ ተኙ። መቼም ከላይ ትዕዛዝ ከመጣ መመለስ ባይቻልም መጠንቀቅ አይከፋም…›› ብለው ማንጠግቦሽን እያዩ ሲናገሩ፣ ስለተፈጥሮ አደጋ እንደሚያወሩ ገብቶኛል። ‹‹አዬ ባሻዬ፣ በምናችን ልንችለው አምላክ እንዲህ ያለውን ነገር በእኛ ላይ እንዲሆን ይፈቅዳል?›› ብላቸው፣ ‹‹ኧረ እውነትህን ነው። በዚህ በኩል ሌባው፣ በዚያ ቀማኛውና ምቀኛው፣ እልፍ ስትል የሰው መብት የሚጋፋውና ፍትሕ የሚያዛባው፣ ወደ ማዶ የአመለካከትና የአስተሳሰብ መወላገድ እያሠቃዩን መቼ አገገምን? ጭራሽ የተፈጥሮ አደጋ ተጨምሮበትማ ስንቱን እንችላለን?›› አሉኝ። የንግግራቸውን እንቆቅልሽ መፍታት አላቃተኝም። ከመፈክር በላይ አልራመድ ያለው ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት፣ መልካም አስተዳደር፣ ፍትሕ፣ ነፃነት፣ ወዘተ ረሃብ ነው ያናገራቸው፡፡ የተናገሩት ግን ውስጤ ቀርቷል። የእንቆቅልሻችን ብዛቱ ይደንቃል፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት