Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልለዕይታ የበቁት ከውጭ የተመለሱ ብርቅዬ ቅርሶች

ለዕይታ የበቁት ከውጭ የተመለሱ ብርቅዬ ቅርሶች

ቀን:

በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመኖችና በተለያዩ አጋጣሚዎች ቅርሶች አንድም በዝርፊያ፣ አሊያም በስጦታም ሆነ በግዢ፣ ብራናዎችንም በማስገልበጥ ሲወጡ እንደነበር ይወሳል፡፡

አስከፊ የሚባለው ዝርፊያ የተፈጸመው በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመን በ1860 ዓ.ም. በመቅደላ አምባ ቤተመጻሕፍት ወመዘክር በእንግሊዞች አማካይነት የተፈጸመው ነው፡፡

በንጉሠ ነገሥቱ ቴዎድሮስ በተደራጀው ሙዚየም ውስጥ የተገኙና በእንግሊዝ ወታደሮች የተዘረፉትን የተለያዩ ውድ ቅርሶችን ለማስመለስ ከአፄ ዮሐንስ ጀምሮ (የክብረ ነገሥት የብራና መጽሐፍን አስመልሰዋል) ጥረት መደረጉና አሁንም መቀጠሉ ይታወቃል፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) ዘመንም ሆነ ከእሳቸው ንግሥና ቀጥለው በመጡት መንግሥታት ከፍተኛ ጥረት በተለያዩ ጊዜያት የተወሰኑ ቅርሶችና ንዋየ ቅድሳት (የቤተ ክርስቲያን ንዋዮች) መመለሳቸው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ቅርሶች በየጊዜው ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ርክክብ ሲደረግ ለአፍታ ከመታየት በቀር ኅብረተሰቡ በቋሚነትም ይሁን በጊዜያዊነት በዓውደ ርዕዮች እንዲመለከታቸው አለመደረጉ በየጊዜው የቅርስና ሙዚየም ባለሙያዎች ሲተቹት የነበረው ጉዳይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንትና የብሔራዊ ቅርሶች አስመላሽ ኮሚቴ አባል የሆኑት አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) በአንድ ወቅት እንደተናገሩት፣ ለተመለሱ ቅርሶች ራሱን የቻለ ሙዚየም ቢኖር ጥሩ፣ ባይቻል ግን ባሉት ሙዚየሞች ራሱን በቻለ ክፍል የተመለሱትን ቅርሶች ማስቀመጥና ማሳየት አለባቸው፡፡ ወጣቶችም ሆኑ ሌሎች ለመጎብኘት ሲመጡ፣ ስለ ቅርሱ ፋይዳና ከየት አገር እንደተመለሰ ለመረዳት ያስችላቸዋል፡፡

‹‹የማስመለስ ነገር ትርጉሙ ዝም ብሎ ቅርሱ ስለተመለሰ አይደለም፤ ታሪክን ሕያው ስለሚያደርግ ነው፡፡ የድሮውን ነገር አሁን ያለው እንዲማርበትና እንዲያስብ እንዲመራመርበት እንዲዝናናበት ለማድረግ ነው፡፡››

ይህን መሠረተ ሐሳብ የተገነዘበው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፣ ለመጀመርያ ጊዜ አዘጋጀሁት ያለውን ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የተመለሱ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ጊዜያዊ ዓውደ ርዕይን በሙዚየምና ተንቀሳቃሽ ቅርስ ልማት ዳይሬክቶሬቱ አማካይነት በባለሥልጣኑ ጋለሪ ለሕዝብ ዕይታ አቅርቧል፡፡ 

የኤግዚብሽን ዝግጅት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ናትናኤል ወንዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመቅደላ ጦርነት ወቅት ከተዘረፉ ቅርሶች መካከል የተወሰኑት፣ እንዲሁም በተለያየ ጊዜ በሕገወጥ መንገድ ተወስደው በአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች በተለይም በእንግሊዝ፣ ዴንማርክና ኔዘርላንድ ይገኙ የነበሩ ቅርሶች ተመልሰዋል፡፡ በጊዜያዊው ዓውደ ርዕይ ለዕይታ የበቁት ለአብነትም የአፄ ምኒልክ ጎራዴ፣ ከብር የተሠሩ የእጅ መስቀሎች፣ በአሠራሩ ልዩ የሆነ ከነሐስ የተሠራ መስቀል፣ አክሊል፣ ፅዋ፣ የገበታ ሥዕል፣ በብር ያጌጡ የቀንድ ዋንጫዎች፣ አሸንክታብ፣ የብራና መጻሕፍትና ሌሎችም ቅርሶች ይገኙበታል፡፡

እነዚህ ለብዙ ዓመታት በባዕዳን እጅ የነበሩ ቅርሶች ለኢትዮጵያ መንፈሳዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ዕሴቶች መጎልበት የሚኖራቸውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለትውልድ ጽኑ የሆኑ ማስታወሻዎችና ራስንንም ማያ መለያዎች መሆናቸውን በማመን፣ እንዲሁም ኅብረተሰቡ ለማንነቱና ለታሪኩ ቋሚና ዋቢ የሆኑት ታሪካዊ ቅርሶቹን በመንከባከብና በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለው ለማሳወቅ ዓውደ ርዕዩ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

‹‹ቅርሶቻችን ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉና ለዘላቂ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊና ተመሳሳይ ጥቅሞች እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ማበርከት እንዳለበት ለማስገንዘብ፣ አሁን ያለው ትውልድም በውጪ አገሮች ፍትሕ በጎደለው መልኩ ተወስደው የሚገኙ ቅርሶችን ለማስመለስ በተደራጀ መንገድ ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስተማሪያነት እንዲሆን ጊዜያዊ ዓውደ ርዕዩ ተዘጋጅቷል፤›› ብሏል ተቋሙ፡፡

በቅርስ ባለሙያዎች አገላለጽ፣ ቅርስ የአንድ ሕዝብ የዘመናት የኑሮ እንቅስቃሴ፣ የሥራና የፈጠራ ክንውን መዘክር እንደመሆኑ አንድ ሕዝብ ቅርስ አለው ሲባል ታሪክ አለው፣ ክብር አለው፣ ተደማጭነት እንዲያገኝ የሚያደርግ ማስረጃ አለው ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ለቅርስ የሚደረግ እንክብካቤና ጥበቃ በታሪክ መዘክርነት ለሚቀርብ ማስረጃ የሚደረግ ጥበቃ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ የአያሌ ባህላዊና ታሪካዊ፣ ተዳሳሽና የማይዳሰሱ፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ባለፀጋ ብትሆንም፣ ቅርሶቿ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ለጉዳትና ለአደጋ እየተጋለጡ መሆናቸውን የገለጸው ባለሥልጣኑ፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚገኙ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ላይ ስርቆት፣ ዘረፋና ሕገወጥ ዝውውር እየተፈጸመ፣ በአጭሩም የአገሪቱ የታሪክ ማኅደር ወደ ውጭ እየተጋዘ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ የማይካድ ነው ብሏል፡፡

እንደ ዩኔስኮ ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕገወጥ የባህላዊ ንብረት ዝውውር የሚፈጸምባቸው በርካታ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፣ አንዱ አለማወቅ ወይም አለመገንዘብ ሌላው በጥንታዊ ቅርስ አሰባሳቢ ደላሎች የሚፈጸም፣ ይህም ኢንተርኔትን ጨምሮ በጨረታ የሚሸጥበት ነው፡፡ በሌላ በኩልም በአገሮች ውስጥ ሆነ በአገሮች መካከል በሚደረጉ ጦርነቶች ለተንቀሳቃሽ ቅርሶች ዝርፊያ መንስዔዎች ናቸው፡፡

የአፄ ቴዎድሮስን መስዋዕትነት ተከትሎ በ1868 ዓ.ም. ከመቅደላ አምባ የተዘረፉት ቅርሶች በተለይ ከ500 በላይ የጽሑፍ ቅርሶች፣ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች፣ የንጉሣውያን የወርቅ ዘውዶችና ጌጣጌጦች፣ እንዲሁም አሥር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታቦታት በእንግሊዝ የተለያዩ ሙዚየሞች ከመገኘታቸው በተጨማሪም በርካታ ቅርሶች በግለሰብ እጅ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ዘረፋው እንዴት ነበር?

“የቴዎድሮስ አሟሟትና የመቅደላው ዘረፋ” በሚል ርዕስ ጥናት ያከናወኑት ግርማ ኪዳኔ፣ አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ሰኞ ሚያዝያ  6  ቀን 1860 ዓ.ም. ካጠፉ በኋላ የመቅደላ አምባን የወረሩት እንግሊዞች የፈጸሙትን ዝርፊያ በዝርዝር አቅርበውታል፡፡ እንዲህም አሉ፡-  

“እንደ እንግሊዝ ጦር አዛዦች አባባል ተልዕኳቸውን የእንግሊዝ እስረኞችን ለማስፈታት ነበር፡፡ ከዚህ የተልዕኮ ሽፋን በስተጀርባ ግን ዓላማቸውን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ታሪካዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸውን ቅርሶች ለመዝረፍ ጭምር መሆኑ የሚያጠያይቅ አይሆንም፡፡ ሪቻርድ ሆምስ የተባለው የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ከእንግሊዝ ጦር ጋር አብሮ እንዲመጣ መደረጉ ለዚህ የዘረፋ ተግባር መከሰት እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡

“የመጀመርያው ዘረፋ ቡድን ያተኮረው በሟቹ ንጉሥ ሬሳ ላይ ነበር፡፡ የአንገት መስቀልና የጣት ቀለበታቸውን፣ ሸሚዛቸውንና ሽጉጣቸውን ከመዝረፋቸውም ባሻገር ሹሩባቸውን ሳይቀር ሸልተው የወሰዱ ለመሆኑ በታሪክ መዛግብት መረዳት ይቻላል፡፡

“ሁለተኛው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው የቤተ መንግሥት ሕንፃ በመድፈር ነበር፡፡ ንጉሡ በሕይወታቸው ሳሉ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ለማቋቋም የሰበሰቧቸውን እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ መጻሕፍትን እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የብሔራዊ ቤተ መዛግብት መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ አያሌ የመንግሥት ሰነዶችንና የተለያዩ መረጃዎችን ሳይቀሩ ዘርፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶችና ማኅተም፣ በተለይም ክብረ ነገሥት የተባለው ታላቁ መጽሐፍ ይገኙባቸዋል፡፡ ቀጥለውም ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ማዕድ ቤት ውስጥ በመግባት ሃያ እንሥራ የሚሆን የተጠመቀ ጠጅና የእህል አረቄ ዘርፈው ከመጠን በላይ ሰክረው ነበር፡፡ ከዘረፏቸው ቅርሶች ይልቅ ጥፋት ያደረሱባቸው አመዝነው ታይተዋል፡፡ ብዙ ቅርሶች ጥለዋል፣ ሰባብረዋል፣ መጻሕፍትንም ቀዳደዋል፣ አልባሳትንም ሸረካክተዋል፡፡

“የሦስተኛው የዘረፋ ቡድን ከወሰዳቸው መካከል ከወርቅ የተሠራ የአቡነ ሰላማ አክሊል ወይም ዘውድ ጫማና ቀበቶ፣ ከወርቅ የተሠሩ ሁለት ጽዋዎች፣ ከወርቅ የተሠራ በአንገት ላይ የሚጠልቅ የአፄ ቴዎድሮስ የሰሎሞን ኒሻን እንዲሁም ንጉሡ ሲነግሡ ለብሰውት የነበረው የማዕረግ ልብስ ይገኙባቸዋል፡፡

“አራተኛው ቡድን በዘረፋቸው መካከል የተለያዩ ጋሻዎች፣ ከእነዚህ ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ ጋሻ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የሚገመተውና የፊታውራሪ ገብርዬ ጋሻ፣ ልዩ ልዩ ጦሮችና ጎራዴዎች፣ ያሸበረቁ የፈረስ ዕቃዎች፣ በተጨማሪም የቴዎድሮስ እስረኞች የታሰሩበት የእግር ብረት ይገኙበታል፡፡

“አምስተኛውና የመጨረሻው የዘረፋ ቡድን ያተኮረው አፄ ቴዎድሮስ በየአገሩ ሲዘዋወሩ ያርፉበት በነበረው ድንኳናቸውና ይጠጡበት በነበረው ዋንጫቸው፣ የማንነቱ  ባልታወቀ የፈረስ ልባብ ላይ ነበረ፡፡ ወታደሮቹ በዚህ ሳይገቱ የደረሱበትን በማሰስና እያንዳንዱ ቤት ውስጥ በመግባት ተመሳሳይ ዘረፋ ከማካሄዳቸውም ባሻገር ከተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች የተገኙትን መንፈሳዊ ሥዕሎችና እንዲሁም ቁጥራቸው አሥር የሚደርሱ ታቦቶችን ሳይቀሩ ወስደዋል፡፡ በአጠቃላይ ከንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ጀምሮ በአነስተኛ ጎጆ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ሳይቀሩ ተዘርፈዋል፡፡

“ምንም እንኳ ጄኔራል ናፒየር ባዘዘው መሠረት በመቅደላ ተሰብስበው የነበሩት ሁሉ ቅርሶች ለጨረታ ቀርበው ነበር በማለት ለማስመሰል ተሞከረ እንጂ፣ አንዳንድ ባለ ሀብቶች በተለይም ሲቪሎችና ኦፊሰሮች ራሱ ጄኔራል ናፒየር ሳይቀር ቀደም ብለው ጨረታው በይፋ ከመጀመሩ በፊት ለየራሳቸው ያከማቿቸው ቅርሶች በብዛት እንደነበሩ ድርጊቱ ካለፈ በኋላ ሊታወቅ ችሏል፡፡ ለምሳሌ ለጨረታው ካልቀረቡት ቅርሶች መካከል የአፄ ቴዎድሮስ ዘውዶች፣ የክብርና የማዕረግ ልብሶቻቸው፣ በሺሕ የሚቆጠሩ የብራና መጽሐፎችና የቴዎድሮስ ማኅተም፣ የአቡነ ሰላማ የወርቅ አክሊል፣ በብር ያሸበረቀ ጋሻ፣ በክብረ በዓል ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል የቴዎድሮስ ከበሮና የመሳሰሉት ከሌሎች ንብረቶች ጋር ከመቅደላ ቤተ ክርስቲያን አጥር ግቢ በነበሩት ጎጆዎች ወስጥ ታምቀው እንደነበር ይነገራል፡፡

“በተለይም ከአቡነ ሰላማ መቃብር ላይ ተፈጽሞ የነበረውን የስርቆት ወንጀል አስመልክቶ ሲናገር ‹በጣም ከሚያስገርመውና ከሚያሳዝነው ነገር ሁሉ ከእስረኞቹ መካከል አንዱ ከስድስት ወር በፊት ተቀብረው የነበሩት ከአቡነ ሰላማ መቃብር ድረስ በመሄድ መቃብሩን አውጥቶና ሰብሮ ብዙ ሺሕ ዶላር ሊያወጣ የሚችል ከአልማዝ የተሠራ መስቀላቸውን ከአንገታቸው ላይ መንጭቆ መውሰዱ የቱን ያህል የተረገመ ሰይጣን እንደነበር ነው ሲል በዝርዝር አስቀምጦታል፡፡

“የአቡነ ሰላማን ከወርቅ የተሠራ አክሊልና የቁርባን ጽዋ ከአንድ ጦር ሜዳ ላይ ከዋለ ወታደር የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ ሆልምስ በአራት የእንግሊዝ ፓውንድ ብቻ ገዝቶት እንደነበር ቀደም ሲል ተጠቅሷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እንግሊዞች ድል አገኘን ብለው ወደ አገራቸው እንደተመለሱ የተጠቀሱትን ሁለት ቅርሶች ሪቻርድ ሆልምስ ከኮሎኔል ፍሬዘር፣ ከኮሎኔል ሚልወርድና ከኮሎኔል ካሜሩን ጋር ለብሪትሽ ሙዚየም በሁለት ሺሕ የእንግሊዝ ፓውንድ እንዲሸጥላቸው እ.ኤ.አ. ጁላይ 1 ቀን 1868 አቅርበውት እንደነበር የደብዳቤ ወረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

“በሽያጭም ሆነ በስጦታ መተላለፋቸው ለጊዜው ባይታወቅም በአሁኑ ጊዜ ከመቅደላ የተወሰዱት ቅርሶች በእንግሊዝ አገር ሙዚየሞች ውስጥ ባመጧቸው ሰዎች ስም ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ በጻፈው  ፕሬስተር ጆን ተብሎ በሚጠራው መጽሐፍ መጨረሻ ላይ ተርጓሚዎቹና አዘጋጆቹ ሀንቲንግፎርድና ቤክንግሃም እንደጠቀሱት በብሪትሽ ሙዚየም ውስጥ “ሆልምስ ኮሌክሽን” እየተባሉ የሚጠሩ አሥር ታቦቶች ከመኖራቸውም  በላይ ብዛታቸው ከአንድ ሺሕ በላይ የሚደርስ የኢትዮጵያ የእጅ ጽሑፍ መጽሐፎች በተጠቀሰው ሙዚየም ውስጥ ተደርድረው ይታያሉ፡፡

ከ155 ዓመታት በፊት የተዘረፉትን ቅርሶች ለማስመለስ ባለፉት መንግሥታት ከተደረጉት ጥረቶች ባሻገር “አፍሮሜት” የሚባለው የመቅደላ ቅርስ አስመላሽ ተቋም የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ጥቂት ቅርሶች መመለሳቸውም አይዘነጋም፡፡

የአፍሮሜት ድምፅ ከጠፋ በኋላ ከቅርብ ዓመት ወዲህ ብሔራዊ የቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...