በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በክረምት ወቅት ከዝናብ መክበድ ጋር ተያይዞ ለጎርፍ አደጋ የሚጋጠሉ ዜጎች ቁጥር ከፍ እንደሚል ይታመናል፡፡ በተለይም ወንዝ ዳር ጎጆ ቀልሰው የሚኖሩ ሰዎች ለአደጋው ይበልጥ ምቹ ለመሆናቸው ከሰሞኑ የታዩ አደጋዎች ማሳያ ናቸው፡፡
በመዲናዋ በክረምት ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ጎርፉ ዋና መንገድ ላይ ጭምር ስለሚተኛ ከፍተኛ ለሆነ የመንገድ መጨናነቅ ለመኪና አደጋ ማኅበረሰቡ ሲጋለጥ ተስተውሏል፡፡
የዝናብ መጠኑ በሚጨምርበት ወቅት የሚከተለው ጎርፍ በነዋሪዎች ቤት ውስጥ በመግባት የሕይወት፣ የአካል ጉዳት ብሎም የንብረት ውድመት ማስከተሉም የተለመደ ነው፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ሰላም ሠፈር ቀጣና አምስት አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ግርማ ብሩ ከባለቤታቸው ወ/ሮ ስንዱ ገበየሁ ጋር ጎጆ ቀልሰው መኖር ከጀመሩ ሃያ ዓመት አስቆጥረዋል፡፡
ከባለቤታቸው ሦስት ልጆችን ያፈሩት እኚህ አባት፣ የዛሬ ስምንት ወር ገደማ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ንብረታቸውን ሙሉ ለሙሉ ማጣታቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
በወቅቱ የጣለው ዝናብ ከፍተኛ በመሆኑ የአብዛኛው የአካባቢው ማኅበረሰብ ንብረት በጎርፍ እንደተወሰደ የሚናገሩት አቶ ግርማ፣ የእሳቸውን ቤት ጨምሮ አከራይተው የልጆቻቸውን የዕለት ተዕለት ጉርስ የሚሸፍኑበት አሥራ አንድ ቤቶች ድምጥማጣቸው እንደጠፋ ይገልጻሉ፡፡
በተለይ የእሳቸው ቤት ወንዝ ዳር መሆኑ ችግሩን ይበልጥ እንዳጎላውና የእንጨት ሥራዎችን የሚሠሩባቸው ማሽኖችን ጭምር በወቅቱ ጎርፉ እንደወሰደባቸው ያስረዳሉ፡፡
በወቅቱም በደረሰባቸው የጎርፍ አደጋ የተነሳ ሥፍራውን ለቀው ከእነ ልጆቻቸው ዘመድ ቤት መግባታቸውንና አሁንም ቢሆን በአካባቢው ነዋሪ ድጋፍ ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት ተሠርቶላቸው እየኖሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከሰሞኑም የጣለው ዝናብ ምንም ዓይነት የጎርፍ አደጋ ባያስከትልም መጪው ክረምት ግን ሥጋት እንዳደረባቸው የሚናገሩት አቶ ግርማ፣ 20 ዓመት ሙሉ እዚያው አካባቢ ከማኅበረሰቡ ጋር በፍቅር ሲኖሩ እንደዚህ ዓይነት አደጋ አጋጥሟቸው እንደማያውቅ አስታውሰዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ልጅ ይዞ እንዲህ ዓይነት አደጋ ሲደርስ ችግሩን ከባድ እንዳደረገው፣ አሁን ካሉበት ሥፍራ ለቀው ቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይቀላቀሉም ቤተሰቦቻቸውም በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ሌላ ቦታ እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት ሥራ እንደሌላቸውና የልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ቀርቶ የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን ከባድ እንደሆነባቸው ያስረዳሉ፡፡
አካባቢው ቁልቁለታማ በመሆኑ ለጎርፍ ለመጋለጥ ምቹ እንደሆነ፣ ወረዳውም ሆነ የሚመለከተው አካል ችግሩን በመረዳት የወንዝ ዳርቻውን መገንባት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ በተደጋጋሚ ወንዙ እንዲገነባና ድልድይ እንዲሠራለት የአካባቢው ማኅበረሰብ ለወረዳው ጥያቄ ማቅረቡን፣ ይሁን እንጂ እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ አለመሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
አብዛኛው በወንዝ ዳር የሚኖሩ ሰዎች መሄጃ አጥተው እንጂ፣ ለመኖር ተመችቷቸው እንዳልሆነ መንግሥትም ይህንን በመረዳት ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
እዚያው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ፈቲያ ከማል እንደገለጹት፣ የዛሬ ስምንት ወር ገደማ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ አብዛኛው የአካባቢ ነዋሪ ንብረቱን አጥቷል፡፡ የጎርፍ አደጋው ሲከሰት ሦስት ልጆቻቸውን ይዘው መሸሻቸውን፣ የቤታቸውን ንብረት አንድም ሳይቀር ጎርፍ ይዞት እንደሄደ ይናገራሉ፡፡ ችግሩም ሲከሰት እንደ አጋጣሚ ሆኖ የእሳቸው ቤት መትረፉንና ንብረታቸውን ብቻ ጠራርጎ እንደወሰደባቸው ለሪፖተር አስረድተዋል፡፡
በተለይ ልጅ ይዞ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲደርስ ነገሩን ከባድ ያደርገዋል የሚሉት ወ/ሮ ፈቲያ፣ ይህንንም በመረዳት መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ይላሉ፡፡ በተለይ መጪው ጊዜ ክረምት በመሆኑ አብዛኛው የአካባቢው ነዋሪ ሥጋት ውስጥ መውደቁን፣ ሰሞኑንም የጣለው ዝናብ በከፊልም ቢሆን ቤታቸው ውስጥ እንደገባ ይገልጻሉ፡፡
ከዚህ በፊት ወረዳው የወንዝ ዳርቻውን የይድረስ ይድረስ መገንባቱን ሆኖም፣ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በመፍረሱ የአካባቢው ማኅበረሰብ ሥጋት ውስጥ መውደቁን ጠቁመዋል፡፡
ወንዙ የማንንም ቤት ሳይነካ በቀጥታ እንዲሄድ ወረዳው እንዲገነባላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ጥያቄ ቢቀርቡም፣ ምላሽ አለመሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ከወረዳ 13 ወደ ወረዳ ዘጠኝ የሚያሻግረው መንገድ አንድ ድልድይ መሆኑን፣ ያንንም ድልድይ ጎርፍ ስለወሰደው አብዛኛው ሰው ውኃ ውስጥ ገብቶ እንደሚሻገር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በዚህም የተነሳ ተማሪዎች ችግር ውስጥ መውደቃቸውን፣ ይህንንም በመረዳት መንግሥት ጊዜያዊ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የማኅበረሰቡን ጥያቄ በፍጥነት እንዲመልስ ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የቀጣና አራት አገው ሠፈር ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አሚና ከድር በበኩላቸው፣ ከዚህ በፊት በተከታታይ ሦስት ዓመታት በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ንብረታቸውን ማጣታቸውን፣ ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው ጎጆ ቀልሰው መኖር ከጀመሩ 14 ዓመታት ያስቆጠሩት እኚህ እናት፣ ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር ሰቀቀን ውስጥ እየወደቁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በተለይ በክረምት ወቅት የሚዘንበው ዝናብ ከፍተኛ መሆኑን፣ የእሳቸው ቤትም ለጎርፍ አደጋ ለመጋለጥ ትንሽ ነገር እንደሚበቃው ያስረዳሉ፡፡ በየዓመቱ የጎርፍ አደጋ የሚከሰትበትን ቦታ በመለየትና በመገንባት ከፍተኛ የሆነ ወጪ ቢያወጡም፣ ከአደጋው ግን ሊተርፉ አለመቻላቸው ችግሩን አጉልቶታል ይላሉ፡፡ ከዚህ በፊትም በተከተሰው የጎርፍ አደጋ ልጃቸውን ይዘው ከቤት መውጣታቸውንና ከዘመድ መጠጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከተለያየ ቦታ ተጠራቅሞ የሚመጣው ውኃ የእሳቸውን ደጅ ረግጦ ስለሚያልፍ ለጎርፍ አደጋ ለመጋለጥ ምቹ መሆኑን፣ ከዚህ ቀደምም የቤት ዕቃዎቻቸውንና ቤታቸውን ጎርፍ አፍርሶባቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በተደጋጋሚ መንግሥት ጋ ቢሄዱም፣ ምንም ዓይነት መፍትሔ አለማግኘታቸውንም ያክላሉ፡፡ በተለይ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ውስጥ ራሱን ለማትረፍ ሲል ቦይ በማውጣት ውኃውን ወደ ሌላ መስመር እንዲሄድ የሚያደርጉ ሰዎች በመኖራቸው፣ ችግሩ የከፋ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በእሳት አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን የቦሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብቴ አማረ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቦሌና በየካ ክፍለ ከተማ የሚገኙ 25 ቦታዎች የመሬት መንሸራተት እንዲሁም ለጎርፍ አደጋ ታጋላጭ ናቸው፡፡
ከተለዩት ቦታዎች ውስጥ ሊፈናቀሉ ወይም ችግር ሊደርስባቸው የሚችሉ ዜጎችን ቁጥር መለየታቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ እነዚህን ከችግሩ ለመታደግ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተለይ የተጋላጭነት ስፋቱና እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ እኩልና ተመጣጣኝ አለመሆኑ፣ ችግሩን እንዳባባሰውና በዚህም የተነሳ ተቋሙ ትልቅ ፈተና ውስጥ እንደገባ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ፣ ወረዳ 11፣ ወረዳ ሰባት፣ ወረዳ 13፣ ወረዳ 12 ሲሆኑ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት፣ ወረዳ አራት፣ ወረዳ ዘጠኝ፣ ወረዳ 10፣ ወረዳ 11 ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን አቶ ሀብቴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስትና ወረዳ አራት ኅብረተሰቡን የማንሳት ሥራ መሠራቱን፣ ይህም ትልቅ ዕፎይታን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡
ከከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ አብዛኛው ማኅበረሰብ ወንዝ ዳር ድረስ ሄደው እንደሚሠፍሩና የችግሩም ገፈት ቀማሽ እንደሚሆኑ አብራርተዋል፡፡
አብዛኛው ለጎርፍ አደጋም ሆነ ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች ላይ ጥናት መደረጉን፣ ተቋሙ ከየአካባቢው ወረዳ ጋር ቅንጅት በመፍጠር ወጥ የሆነ አሠራር እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መንገድ የወንዝ ዳርቻን ተከትለው የሚሠፍሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ሥጋት ተጋላጭ ስለሆኑ፣ ሁሉንም በሚባል መልኩ ለማንሳት መመርያ መፅደቁን የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ዋና ኮሚሽነር አቶ ፍሥሐ ጋረደው ተናግረዋል፡፡
በተለይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው የወንዝ ዳርቻ በርካታ ሰዎች በሕገወጥ መንገድ መሥፈራቸውን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ግለሰቦቹ ለከፍተኛ ጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን አውቀው፣ ከቦታው እንዲነሱ አሳስበዋል፡፡ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ተመሳሳይ ችግር መኖሩንም ተናግረዋል፡፡
የአደጋ ሥጋቱን ለመቀነስ በማንኛውም በሕገወጥ መንገድ የተሠሩ ቤቶችን ማፍረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ በሕጋዊ መንገድ ሠፍረው ነገር ግን ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጊዜያዊ መጠለያ እየተዘጋጀላቸው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ከሰሞኑ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በደረሰው የጎርፍ አደጋ አራት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡