Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በአዲስ አበባ የደራው ‹‹የቦንዳ ልብስ›› ገበያ

በሕብስት አበበ

በአዲስ አበባ ከተማ ገበያውን ካጥለቀለቁት ልብሶች  ውስጥ በተለምዶ ‹‹የቦንዳ ልብስ›› የሚባለው ከውጭ የሚገቡ የተለበሱ ጨርቆች ይገኝበታል፡፡ ‹‹የቦንዳ ልብስ›› ወደ አገር ውስጥ የሚገባው በተለያዩ መንገዶች ሲሆን፣ አንዱና ዋነኛው በድንበር በኩል በኮንትሮባንድ የሚገባው ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ከሚታወቁ ድንበር አካባቢዎች መካከል በሞያሌ፣ በድሬዳዋና በሌሎች የድንበር ከተሞች ከሚባሉት በተጨማሪ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል በተለያዩ ሁኔታዎች ሲገባ ይስተዋላል፡፡

በአየር መንገዱ የሚገቡ ለሁለተኛ ጊዜ የሚለበሱት ጨርቆች የሚገቡባቸው መንገዶች የተለያዩ ሲሆኑ አንደኛ ለዕርዳታ የሚገቡ በማስመሰል፣ ሌላኛው ደግሞ ይዞ የሚገባው ግለሰብ የራሱ አስመስሎ በማስገባት መሆኑ ይነገራል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ገበያውን ያጥለቀለቀው ‹‹የቦንዳ ልብስ›› ገበያ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ለዚህም ፍላጎት መጨመር የተለያዩ መንስዔዎች ቢኖሩትም አንዱና ዋነኛው ግን የምርቶች የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም።

ለሁለተኛ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉት የእነዚህ ልብሶች ዋጋ ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ በጥራት የተሻሉ ‹‹ብራንድ›› ወይም ተቀባይነት ባላቸው አምራቾች የተመረቱ ልብሶች ናቸው በሚል አመለካከት ተቀባይነት አግኝተዋል። ይህም በምግብ ፍጆታ ዕቃዎች ናላው የዞረ ማኅበረሰብ የልባሽ ጨርቆች ላይ ‹‹የቦንዳ ልብስ›› ገበያ መስፋፋት እፎይታን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ምንም እንኳን ለማኅበረሰቡ ከተለያዩ የኑሮ ውድነት ጫናዎች ያቀለለ ቢሆንም፣ የመንግሥትን የታክስ ገቢ የሚያሳጣ መሆኑ አልቀረም፡፡ በተጨማሪም፣ አዲስ ልብስና ጫማ የሚያስመጡ ንግዶች ገበያ ላይ ጫና መፍጠሩ የማይቀር ነው።

‹‹የቦንዳ ልብስ›› መሸጫ ሱቆች ልባሽ ጨርቆቹን ለማስገባት ከድንበር ላይ ኬላ ጀምሮ እጅ መንሻ ይሰጣሉ፡፡ ይህም በየዘርፉ ሕገወጥ የንግድ አሠራር ሰንሰለት መዘርጋቱን የሚያሳይ ሲሆን፣ ከቦንዳ ምርት በተጨማሪ ሌሎችም ምርቶች ለማስገባት ይህንኑ ሰንሰለት በመመልከት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ስልኮችና ሌሎች ኤልክትሮኒክ ዕቃዎች በዚሁ መንገድ የሚገቡ ናቸው፡፡

እነዚህ ዕቃዎች በተለይም የድንበር ከተሞች ማለትም ድሬዳዋ፣ ሞያሌ፣ መተማና ሌሎች ከተሞች ላይ የሚሸጡ ሸቀጦች መሀል ከተማ ከሚሸጠው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ 

ሞያሌ ከተማን ብንመለከት በኮንትባንድ የሚገቡ ልብሶችና ጫማዎች ዋጋቸው እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ በዚህ የንድግ ሥራ የተሰማሩ ነጋዴዎችም የከፈሉትን ከፍለው ወደ አዲስ አበባ የሚያስመጡ ሲሆን፣ በሥራቸው ውጤታማ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

በመንግሥት የሚደረገው ቁጥጥር የላላ መሆኑ ደግሞ ለነጋዴዎችና በዚህ ሥራ ለሚገቡ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል፡፡ የሕግ አተገባበር ክፍተት፣ የቁጥጥር ማነስ፣ በዘርፉ የሚዘዋወረው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ቁጥጥሩ የሚደረግባቸው የድንበር ኬላዎች ተቆጣጣሪዎች ጭምር በዚህ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ እንዲያውም በድንበር አካባቢ በኬላ ተቆጣጣሪነት የሚመደቡ ሰዎች ዕድለኛ እንደሆኑ ሁሉ ይነገራል፡፡ ምክንያቱም ከቦንዳ ልብስና ጫማዎች፣ ሕገወጥ ነዳጅ ዝውውር ግዳጅ፣ ኤሌክትሮኒክስና ሌሎችም የሚነግዱ ሰዎች በእጅ መንሻ ኪሳቸውን እንደሚያደልቡ ይነገራል፡፡ ይህ አሠራር በሕጋዊ መንገድ ልባሽ ጨርቆችን የሚሸጡ የማያበረታታ፣ ገበያቸውን የሚገዳደር መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ በሕጋዊ መንገድ ታክስና ሌሎች አስፈላጊ ሕግጋቶችን ተከትለው የሚነግዱትን የሚያደናቅፍ መሆኑ በዘርፉ የሚሠሩ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ በሁለቱ የገበያ ሁኔታዎች የሚገቡ ልብሶችን ዋጋቸው ሲነፃፀር እንኳ በሕጋዊ መንገድ የሚገባው ልብስ ዋጋው የማይቀመስ ሆኗል፡፡

‹‹የቦንዳ ልብስ›› የወንድ ሱሪ ከ1,000 ብርና በታች ይሸጣል፡፡ ባለቡቲኮች ደግሞ ያስገቡትን አዲስ የወንድ ሱሪ ከ1,800 ብርና ከዚያ በላይ ነው የሚሸጡት። በዚህ የዋጋ ልዩነት የሰፋ በመሆኑና የኑሮ ውድነቱ ተደምሮ የቦንዳ ልብስ በድጋሚ ለመግዛት የሚገደዱ ብዙዎች ሆነዋል፡፡ በዚህ ረገድ በተለይም በኮንትሮባንድ የሚገቡ ጫማዎች ከ1,500 ብር በታች የሚሸጡ ሲሆን፣ በሕጋዊ መንገድ ቀረጥ ተከፍሎባቸው የሚገቡት አዲስ ጫማዎች በአማካይ ከ3,500 ብር በላይ በሆነ ዋጋ ይሸጣሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በቦንዳ ሽያጭ የሚታወቁ ሥፍራዎች አሉ፡፡ ሃዲድ፣ 22 አካባቢ፣ ሳሪስ፣ ቄራ፣ ጨረታ፣ እሁድ ገበያ በዚህ ንግድ የሚታወቁ ሲሆኑ ከቅርብ ጊዜያት በኋላ ደግሞ የአቀራረብ ሥራዓታቸውን በማዘመን በተለያዩ ትልልቅ ሞሎች ላይ ጭምር ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡

በዚህ ሥራ  በአካል ከሚሸምቱ በተጨማሪ ነጋዴዎች የቴሌግራም፣ የፌስኩክ ቻናሎችን በመክፈት ብዙ ደንበኞችም በማፍራት በገበያቸውን አስፋፍተዋል፡፡ በዚህ ሥራ የተሰማሩ ዜጎች የቦንዳ ሽያጭ በኦንላይን ገበያ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ የነፃ ዴሊቨሪ (ገዥዎች ባሉበት ቦታ ሄደው በማድረስ ወይም በመሸጥ) ጭምር አገልግሎታቸውን በሰፊው የሚሠሩ ነጋዴዎች ቁጥር ትንሽ የሚባል አይደለም፡፡ በአብዛኛው የሚታወቀው ለሁለተኛ ጊዜ የሚለበሱ ልብሶች ብቻ ሳይሆኑ፣ ጫማ፣ ቦርሳ፣ ቀበቶ ጭምር ለገበያ (ለሽያጭ) ይቀርባሉ፡፡

መንግሥት ለሁለተኛ ጊዜ የሚለበሱ ጨርቆችን ከድንበር ጀምሮ ለመቆጣጠር ሥራዎች ቢሠራም ቁጥጥሩ ከአንገት በላይ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡

ለዚህም እንደ ማሳያ የሚያነሱት የቦንዳ ልብሶች በገፍ እንዲገባ ምክንያት የሆኑ ብዙ መንስዔዎች ይነገራሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ አገሪቱ ልባሽ ጨርቆች የማምረትና ለገበያ ማቅረብ ላይ ዝቅተኛ አፈጻጸም ስላላት ነው ይባላል፡፡

ለዚህም እንደ ማሳያ ከውጭ ልብስ ለማምረት የገቡ ባለሀብቶች  ጭምር ለአገር ውስጥ ፍጆቻ ሳይሆን ኢምፖርት ምርት ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ይነሳል፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ ዓለም አቀፍ ብራንድ መሆኑ የሚታወቀው ኤች ኤንድ ኤም የተለያዩ ልባሽ ጨርቆችን ቢያመርትም፣ ትኩረት ያደረገው የውጭ ገበያ ላይ በመሆኑ የአገሬው ሰው ለማግኘት የማይታሰብ ሆኖበታል፡፡ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ላይ የተሰማሩትም ቢሆኑ፣ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ብለው የሚቀርቡት የዋጋ ተመን የሚቀንስ አለመሆኑ ሌላኛው ችግር መሆኑ ሲነገር ይስተዋላል፡፡

በዚህና በሌሎች ዘርፎች ብዙ ችግሮች ምክንያት ዜጎች ከአዲስ ልብስ መግዛት ይልቅ ወደ ቦንዳ ልብስ እንዲያመዝኑ ምክንያት ነው፡፡ 

በዚህም በተለይም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዚህ ንግድ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የሚመጣውም ልባሽ ጨርቆች ኪሳቸውን የማይጎዳ ሆኖ ስላገኙት በአስቤዛ ለተራቆተው ኪሳቸው የልብስ ሸመታውን ከወደ ቦንዳ ተራ በመዝለቅ ለማካካስ ተገደዋል፡፡ 

 

ነገሩን ከሸማች አንፃር ለተመለከተው የኑሮ ውድነት ችግር የወለደው መፍትሔ አድርጎ ይገነዘበዋል። ለሸማቹም እፎይታ እንደሚሰጥ ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ከዘለቄታዊ የአገር ልማትና ዕድገት መመልከት የሚገባው መንግሥት እየደራ የሚገኘው ‹‹የቦንዳ ልብስ›› ገበያ የአገር ውስጥ አምራቾችን የሚያቀጭጭ፣ ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያዳክም መሆኑን ሊያጤን ይገባል። 

ጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኝ ‹‹የቦንዳ ልብስ›› ወይም ጫማ ገበያውን አጥለቀለቀው የአገር ውስጥ ጫማ አምራቾች ምን ሊሆኑ ነው? ራሳችንን በአገር ውስጥ ልብስ እንዴት ልንችል ነው? ብሎ ጥያቄውን ከወዲሁ ሊመልስ ይገባል።

 

 

 
     

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት