የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ ነው፡፡ የፕሪቶሪያ ስምምነት ትግበራ መጀመርና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረቱ እንደ ወልቃይትና ራያ ያሉ በሁለቱ ክልሎች መካከል የይገባኛል ውዝግብ የፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት አመቺ ዕድሎች ተደርገው ቢታዩም፣ ከቃላት መወራወር በዘለለ ችግሩን ለመፍታት ተግባራዊ ዕርምጃዎች እስካሁን አልታዩም፡፡ በመሆኑም በይደር የቆዩት የወልቃይትና የራያ ጉዳዮች እንዴት መቋጫ ያገኛሉ የሚለው ጥያቄም አሁን ጎላ ብሎ እየተደመጠ ነው፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ባለፈው ሳምንት ዓርብ መጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ አስተዳደራቸው የቅድሚያ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አጨቃጫቂ ጉዳዮችን መፍታት አንደኛው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኤርትራ ሠራዊት፣ እንዲሁም የአማራ ኃይሎች ከትግራይ መውጣት ለሰላም ስምምነቱ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ መሆናቸውን ተናግረው ነበር፡፡
‹‹የአማራ ታጣቂዎች የእኛ ነው ብለው በጉልበት ከያዟቸው አካባቢዎች ምዕራብ ትግራይ፣ ፀለምትና ደቡብ ትግራይ አካባቢዎች የሚፈጽሙትን ግፍ የፌዴራል መንግሥቱ ማስቆም አለበት፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ የአማራም ሆነ የኤርትራ ኃይሎች ትግራይን ለቀው የመውጣታቸውን አስፈላጊነት አውስተዋል፡፡
‹‹የኤርትራ ሠራዊትም ሆነ የአማራ ታጣቂዎች የሚሠሩት ሰላሙን ወደኋላ እንዳይመልሰው ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ከጎረቤት ወንድማማችና እህትማማች ሕዝቦች ጋር ብዙ ተደማምተናል፡፡ ይህ ሊቀጥል አይገባም፡፡ ወደድንም ጠላንም ጎረቤት ሆነን ነው የምንኖረው፤›› ሲሉ የተደመጡት አቶ ጌታቸው፣ የአማራና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ወጥተው በአስቸኳይ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቦታቸው ካልተመለሱ የሰላም ትግበራው ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ተናግረው ነበር፡፡
አጨቃጫቂ የሆኑ ጉዳዮችን በሰላማዊ፣ በሕጋዊና በሕገ መንግሥታዊ መንገድ መፍታት አስፈላጊ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹እየከበደንም ቢሆን ሕገ መንግሥታዊ መንገድን መልመዱ የሚያዋጣ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የትግራይ ባለሥልጣናትን አቋም የተለያዩ የትግራይ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶችም ሲቀባበሉት ከርመዋል፡፡ የትግራይ ሉዓላዊ መሬት ካልተመለሰ የሰላም ትግበራ ብሎ ነገር የለም የሚሉ አስተያየቶች፣ የትግራይን አቋም በሚያንፀባርቁ ሚዲያዎችና ማኅበራዊ ዓምዶች ላይ ጎልተው ሲደመጡ ሰንብተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ወልቃይትና ራያ ሁለቱ ክልሎችን እያጨቃጨቁ ያሉ ጉዳዮች ሲሆኑ፣ የጥይት ጩኸት ዳግም ሳይሰማ እንዴት ዕልባት ያገኛሉ የሚለው ጥያቄ የተለያዩ ዓይነት ምላሾችን እያስተናገደ ነው የሚገኘው፡፡
ባለፈው ሳምንት መገባደጃ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፍአለ (ዶ/ር) ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደተናገሩት፣ ሁለቱ ክልሎች የሚያጨቃጭቋቸውን ጉዳዮች በሠለጠነ መንገድ መፍታት ይችላሉ፡፡
የአማራና የትግራይ ሕዝቦችን ወንድማማችነት በሰፊው ያወሱት ይልቃል (ዶ/ር)፣ ‹‹ትግራይ ክልል ከእኛ የሚጠይቀው ነገር ካለ በሰላም፣ በውይይት፣ ከዚያም ባለፈ በሕግ ለመፍታት እንችላለን፡፡ ይህን የሠለጠነ መንገድ ሁላችንም ተቀብለን መጠቀም አለብን፡፡ ምክንያቱም የሰላም ዋጋ ሊተመን የማይችል ነው፤›› ብለዋል፡፡
ይህ የርዕሰ መስተዳድሩ ንግግር ከሰሞኑ የአማራና የትግራይ ክልሎች ችግሮችን ተቀራርበው በመነጋገር ለመፍታት ጥረት ጀምረዋል የሚል ዜና ከመሰማቱ ጋር ተደራርቦ፣ የሁለቱ ክልሎች ቁርሾ ሰላማዊ መፍትሔ ያገኛል የሚለውን ተስፋ አጉልቶት ነው የሰነበተው፡፡
ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒው ችግሩ አሁንም ቢሆን የጥይት ጩኸት መነሻና የቀጣይ ዙር ጦርነት መቀስቀሻ ሊሆን እንደሚችል ሥጋትም እየተሰማ ነው፡፡
ይህን በተመለከተ የተጠየቁት የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት አቶ አብዩ በለው ግን፣ የሰላም ስምምነቱ ከሚለው በተቃራኒ የትግራይ ፖለቲከኞች ጉዳዩን እያቀረቡት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት አጨቃጫቂ ጉዳዮች በሕገ መንግሥቱ፣ በድርድርና በሽምግልና እንደሚፈቱ ተቀምጧል፡፡ የትግራይ ሉዓላዊ ግዛት የሚባል ነገር የለም፡፡ ስምምነቱ ውስጥም እንደዚያ የሚል ሐሳብም ሆነ ንግግር የለም፤›› ይላሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ ከሆነ፣ ሕወሓቶች በድርድሩ ወቅት የወልቃይትም ሆነ የራያ ጉዳይ እንዳይነሳ ፈልገው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የፌዴራል መንግሥቱ ተደራዳሪዎች ወልቃይትና ራያን የመሳሰሉ አጨቃጫቂ ጉዳዮች ካልተነሱ ድርድር እንደማይኖር በማሳወቃቸው ጉዳዩ መነሳቱን ይጠቅሳሉ፡፡ በድርድሩ ሒደትም አጨቃጫቂ የሆኑ ጉዳዮች በድርድር፣ በሽምግልናና በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይፈታሉ የሚል መግባባት ላይ መደረሱንና ይህም በስምምነት ሰነዱ ውስጥ መሥፈሩን ያክላሉ፡፡
ይሁን እንጂ አቶ አብዩ ሁሌም የግጭት መንገድ ይከተላሉ የሚሏቸው ሕወሓቶች፣ አክቲቪስቶቻቸውና ሚዲያዎቻቸው ‹‹የትግራይ ሉዓላዊ ግዛት ካልተመለሰ የሰላም ስምምነት ብሎ ነገር የለም›› የሚል ፕሮፓጋንዳ እየነዙ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ምዕራባውያኑም በማያውቁትና ባልገባቸው ጉዳይ የሕወሓትን መረጃ ብቻ መሠረት በማድረግ ምዕራብ ትግራይ እያሉ ይጮሃሉ፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከሰሞኑ የተናገሩትም ሆነ ምዕራባውያኑ የሚደጋግሙት፣ ‹‹Western Tigrya›› ወይም ምዕራብ ትግራይ የሚል የተደጋጋመ ሐሳብ ለአንድ ወገን ያደላ፣ የተዳፈነ ቁስልና ቁርሾ የሚቆሰቁስ በመሆኑ ሊታረም ይገባልም ይላሉ፡፡
ወልቃይትና ራያ የትግራይ ነው የሚል የሚዲያ ሙግት በማድረግ የሚታወቁት ታሪክ አዋቂው አቶ ተስፋ ኪሮስ በበኩላቸው፣ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ለትግራይ የተወሰነ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
‹‹ጉዳዩ የዘገየው ጊዜያዊ አስተዳደር እስኪመሠረት እንጂ ወደ ትግራይ ይመለሳሉ፡፡ አጨቃጫቂ ጉዳዮች በሕገ መንግሥቱ ይፈታሉ ተብሏል፡፡ በፌዴራልና በትግራይ ሕገ መንግሥትም ይፈታ ቢባል የወልቃይትና የራያ ባለቤትነት ለትግራይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የአማራ ክልል በሰሜን በኩል ወሰኑ ትግራይ እንጂ የኤርትራና የሱዳን ድንበሮች አይደሉም፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡
አቶ ተስፋ እንደሚናገሩት፣ ሁለቱ ክልሎች ከተስማሙ በመግባባት ችግሩን መፍታት ይችላሉ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገብቶበት ሕዝበ ውሳኔ (Referendum) እንደሚደረግ ግልጽ መሆኑን ያክላሉ፡፡
እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ በወልቃይት ራያ ጉዳይ ላይ ያለውን ውጥረት ለመፍታት ምን ታስቦ እንደሆነ ከመንግሥት ወገን የተለየ ፍንጭ እስካሁን አልተሰማም ነው የሚባለው፡፡ የፈዴራል መንግሥቱ ጉዳዩን በምን ሊዳኘው እንዳሰበ ከመገመት ውጪ፣ የተረጋገጠ መረጃ ሲሰጥ አልታየም የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ ጉዳዩ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል በሪፈረንደም ዕልባት ያግኝ፣ ወይም በሁለቱ ክልሎች ንግግር ይፈታ የሚሉ የመፍትሔ ነጥቦች የተጨበጠ ውሳኔ ሲሰጥባቸው አልተሰማም፡፡
ይህ አለመታወቁ ደግሞ እንደሚያሳስባቸው ነው አንዳንድ ወገኖች የሚናገሩት፡፡ በወልቃይት ጉዳይ ተሟጋችና ማኅበራዊ አንቂ የሆኑት አቶ አስፋው አብረሃ የፌዴራል መንግሥቱ ሐሳብ ምን እንደሆነ አለመታወቁ፣ ‹‹የሁላችንም ጥያቄ ነው፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡
‹‹የሚያጋጩ ቦታዎች ይቆያሉ ተባለ እንጂ አቶ ጌታቸው እንደተናገሩት ለትግራይ ይመለሳሉ የሚባል ነገር በስምምነቱ ላይ የለም፡፡ ስምምነቱ የደበቀው ነገር ካለ ወይ ነገሩ ድብብቆሽ አለመሆኑ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ በተጨባጭ በሰነዱ ከሰፈረ ግን ወልቃይትም ሆነ ራያ ለትግራይ ይመለሳሉ የሚል የለም፤›› ይላሉ፡፡
የወልቃይትና የራያ ጉዳይ የጥይት ጩኸት ሳይሰማና ተጨማሪ ግጭት ሳይከተል እንዲፈታ የሚመኙ በርካታ ቢሆኑም፣ ችግሩ ግጭት ሊያስከትል ይችላል የሚል ሥጋት የሚያነሱም በርካታ ናቸው፡፡ ከግራም ከቀኝም ወልቃይት ካልተመለሰ/ከተመለሰ ሰላም የለም የሚለው ሙግትና ውዝግብ በበዛበት በዚህ ወቅት፣ የፌዴራል መንግሥት ለጉዳዩ ቀዝቃዛ አፀፋ ነው የሰጠው የሚል አቋም ከአንዳንዶች ይንፀባረቃል፡፡
ከአንድ ወር ቀደም ብሎ በፕሪቶሪያ ስለተካሄደው የሰላም ስምምነት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጻ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪና የመንግሥት ዋና ተደራዳሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ ስለዚሁ ጉዳይ የተናገሩት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡
‹‹በፕሪቶሪያው ስምምነት በሕወሓት በኩል ስለምዕራብ ትግራይ ምንም አልተነሳም፡፡ ለእኛ የገረመን ሕወሓት ይህን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ አለማንሳቱ ነበር፤›› ያሉት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ሕወሓት ጦርነት ያደረገበትን ነገር መተው እንደገረማቸው ተናግረው ነበር፡፡
የመንግሥት ዋና ተዳራዳሪው ሲቀጥሉም፣ ‹‹ተቃውሞ ያልተነሳበት ጉዳይ ተቀባይነት እንዳገኘ ይቆጠራል የሚል ነበር የእኛ አቋም፡፡ ክርክር ቢደረግ አንድ ነገር ነው፣ ነገር ግን ክርክር ባለመደረጉ ያለውን ‹ዲፋክቶ› እንደተቀበሉት ይቆጠራል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
ሬድዋን (አምባሳደር) ዲፋክቶን በተመለከተ፣ ‹‹አጨቃጫቂው አካባቢ በእነሱ እጅ ከሌለና ተቃውሞ ካላነሱበት ያለውን ዲፋክቶ ከሕግና ከፖለቲካ አንፃር እንደ መቀበል ይቆጠራል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በድርድሩ መገባደጃ ግን አንዳንድ ‹‹ዘላቂ ነገሮች›› በእኛ በኩል ተፈጠሩ ሲሉ ያስታወሱት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ይህን ጊዜ የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ ካልተፈታ የሚል አጀንዳ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
‹‹በስተመጨረሻ ግን ከድርድሩ ብዙ ነገር ስለተገኘ በዚህ ምክንያት ከምናፈርሰው የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ከውስጥም ከውጭም የመጠበቅ ኃላፊነት የፌዴራል መንግሥቱ በመሆኑ፣ መከላከያ በእነዚህ ቦታዎች ይቆያል የሚል ነጥብ ላይ ተደረሰ፤›› ሲሉም ዋና ተደራዳሪው ገልጸው ነበር፡፡ ሬድዋን (አምባሳደር) በዚህ ገለጻቸው የወልቃይትና የሌሎች አጨቃጫቂ መሬቶች ጉዳይ በሕገ መንግሥታዊ አግባብ ይፈታሉ የሚል መግባባት ላይ መደረሱን ነው ያሰመሩበት፡፡
መንግሥትና ሕወሓት የተግባቡበት ስምምነት ይህ ከሆነ ታዲያ ወልቃይት ይመለስ ወይም ‹‹ስታተስኮ›› ይጠበቅ የሚለው ሙግት ዛሬ በምን መነሻ ይራገባል የሚለው ጥያቄ ብዙ የሚያነጋግር ይመስላል፡፡ የወልቃይትና የራያ አካባቢዎች ለትግራይ የመመለሳቸው ጉዳይ በስምምነቱ የተረጋገጠና የስምምነቱ ትግበራ ቀጣይ ዕርምጃ ተደርጎ እየቀረበ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢ አለመሆኑን የሚናገሩ ወገኖች ጉዳዩ በሕገ መንግሥታዊ አግባብ በተባለው መሠረት እንዲፈታ በተቃራኒው እየጠየቁ ይገኛል፡፡
አቶ ተስፋ ኪሮስ እንደሚናገሩት፣ የአጨቃጫቂ ጉዳዮች ስታተስኮ ይመለሳል ወይም ለትግራይ እንደሚመለስም እርግጥ ሆኗል፡፡ ‹‹የፌደራል መንግሥቱ ከአማራ ኃይሎች ጋር በቀጥታ ከመላተም ይልቅ የፖለቲካ ሥራ መሥራት ስላለበት፣ መዘግየቱን ራሳቸው አቶ ጌታቸው ከዚህ ቀደም አረጋግጠዋል፡፡ ጊዜ ቢወስድም ስታተስኮው ይጠበቃል፤›› ሲሉ በእርግጠኝነት ስሜት ተናግረዋል፡፡
አቶ አስፋው አብረሃ ግን፣ ‹‹የትግራይ ግዛት ካልተመለሰ ሰላም የሚባል ነገር የለም፡፡ የሕወሓት ኃይሎች ቢሉም በሕገ መንግሥቱ ይፈታል ከሚለው ማዕቀፍ መውጣት አይችሉም፤›› ሲሉ ነው የሚናገሩት፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳም ቢሆኑ ይህንን መናገራቸውን የሚያስታውሱት አቶ አስፋው፣ ነገር ግን መልሰው ‹‹እየከበደንም ቢሆን የሕገ መንግሥቱን መፍትሔ መቀበል አለብን፤›› የሚል ነጥብ ማንሳታቸውን ያስረዳሉ፡፡
ሕወሓቶች በተለይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፖለቲካ ድጋፍ ከውስጥም ከውጭም ለመሰብሰብ በሚል አጨቃጫቂ ቦታዎች ለትግራይ ይመለሳሉ የሚል የሐሰት ዘመቻ መክፈቱን የሚጠቅሱት አቶ አብዩ በበኩላቸው፣ ጉዳዩ በዚህ መሰል አካሄድ እንደማይፈታ ይናገራሉ፡፡
‹‹ሰላም መቅደም አለበት፣ ነገር ግን ሰላም መመሥረት ያለበት እውነት ላይ በመቆም ነው፡፡ የወልቃይትም ሆነ የራያ ጉዳይ የሚፈታው በተመሳሳይ በእውነት ላይ በመቆም ነው፤›› ሲሉ ነው አቶ አብዩ ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት፡፡