Saturday, July 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መገጭ የመስኖ ግድብ ‹‹አሳፋሪ ፕሮጀክት ነው›› የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፍአለ (ዶ/ር)

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአማራ ክልላዊ መንግሥት በጎንደር ከተማ ዙሪያ በምትገኘው መገጭ ተብላ በምትጠራ መንደር ውስጥ የመንደሯን ስያሜ ይዞ በ2.4 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ወጪ የግንባታ ሥራው በ2001 ዓ.ም. የተጀመረው መገጭ የመስኖ ግድብ ዛሬም መጠናቀቅ አልቻለም።

የታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ሕዝብን የንፁህ ውኃ ችግር ለመፍታትና በጎንደር ከተማ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮችንም በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የታሰበው የመገጭ ግድብ ግንባታ በ2001 ዓ.ም. ሲጀመር አጠቃላይ ወጪው 2.4 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ተገምቶ ነበር። 

ነገር ግን የመገጭ ግድብ ለጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የውኃ ጥም ዛሬም ሊደርስ አልቻለም። የጎንደር ዙሪያ አርሶ አደሮችም ቃል የተገባላቸው የመስኖ ግብርና ህልም ሆኖባቸዋል።

የመገጭ ግድብ የግንባታ ውል ከተፈጸመበት ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ሦስት ጊዜ ምርጫ ተካሂዶ አገሪቱ በሦስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተመርታለች። በአማራ ክልል ደግሞ ስድስት ርዕሳነ መስተዳድሮች ተፈራርቀዋል፣ ግደቡ የሚገነባባት ጎንደር ከተማም እንዲሁ በስድስት ከንቲባዎች ተመርታለች።

በእነዚህ ወቅቶች በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ብዙ ነገሮች ተቀያይረዋል። ያልታሰቡት ሆነዋል። ያልተገመቱት ተደርገዋል። የመገጭ ግድብ የግንባታ ሥራ ሲጀመር ከሦስት እስከ አራት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ ግን የግድቡ ግንባታ መቼ እንደሚጠናቀቅ በእርግጠኝነት ማወቅ የሚችል የመንግሥት አካል የለም።

የመገጭ ግድብ እንቆቅልሽ ከአካባቢው ማኅበረሰብ አልፎ የአማራ ክልል መንግሥትንም በእጅጉ እያሳዘነ የሚገኝ ፕሮጀክት ሆኗል። 

የአማራ ክልልን በመወከል በፌዴራልና በአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑ የሕዝብ ተወካዮች በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም. ከወከላቸው ማኅበረሰብ ጋር በመወያየት ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ካቀረቧቸው የማኅበረሰቡ ችግሮች መካከል አንዱ የመገጭ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ጉዳይ ይገኝበታል። 

ከ14 ዓመት በኋላም ሊጠናቀቅ ስላልቻለው መገጭ መስኖ ግድብ በሕዝብ ተወካዮቹ አማካይነት የማኅበረሰቡ ቅሬታ የቀረበላቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ቅሬታ ስለቀረበበት ግድብ ማለት የቻሉት፣ ‹‹በጣም አሳፋሪ ፕሮጀክት ነው›› ብቻ ነበር። 

በፌዴራል መንግሥት አማካይነት ግንባታው የተጀመረው የመገጭ ግድብ 185 ሚሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውኃ የመያዝ አቅም እንደሚኖረው፣ የግድቡ ውኃ የሚተኛበት ሥፍራ ደግሞ ከ3 እስከ 5 ኪሎ ሜትር ስፋት እንደሚሸፍን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ግድቡ በሰከንድ 662 ሜትር ኩብ ትርፍ ውኃ ማስተንፈስ የሚችል ርዝመቱ 54 ሜትር የሆነ የትርፍ ውኃ ማስወገጃ አካል (spill way)፣ በሰከንድ 20 ሜትር ኩብ ውኃ መቀበልና መቆጣጠር የሚችል ቁመቱ 64.7 ሜትር የሆነ የውኃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ማማ (Intake tower)፣ የወገቡ ስፋት 2.5 ሜትር የሆነ በሰከንድ 40 ሜትር ኩብ ውኃ ወደ መስኖ መሬት ሊያደርስ የሚችል የመስኖ ቦይ ወይም ቱቦና የወገቡ ስፋት 1 ሜትር የሆነ የመጠጥ ውኃ ማስተላለፊያ ቱቦ (የሁለቱም ቱቦዎች ርዝመት 220 ሜትር) እንደሚኖሩት የፕሮጀክት ዲዛይን ያመለክታል።

በፕሮጀክት ዕቅዱ መሠረት በግድቡ የሚያርፈው 116 ሚሊዮን ሜትር ኩብ የሚሆነው ውኃ ለመስኖ አገልግሎት እንዲውል፣ የተቀረው 32 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ደግሞ ለጎንደር ከተማና ለጎንደር ዙሪያ መንደሮች የንፁሕ መጠጥ ውኃ አገልግሎት ለማቅረብ፣ ቀሪው 19 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ደግሞ በግድቡ እንደሚተኛ ታሳቢ ተደርጓል።

የፕሮጀክቱ ዓላማም ለአካባቢውና በመገጭ ወንዝ አዋሳኝ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ለመስኖ ልማት የሚሆን ውኃ በማቅረብ የክልሉን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ሲሆን፣ በዚህም ከ14, 000 እስከ 17,000 ሔክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታሳቢ ተደርጎ የተቀረጸ ፕሮጀክት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከመስኖ ልማቱ በተጨማሪ በጎንደር ከተማና ለዙሪያዋ ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውኃ ማቅረብ ሌላኛው ከፕሮጀክቱ የሚጠበቅ ውጤት ነበር። 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጎንደር ከተማ የውኃና ፍሳሽ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወርቅነህ አያል፣ በ2.5 ቢሊዮን ይሠራል የተባለው የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ከመጓተቱ ባለፈ በርካታ ቢሊዮን ብሮች ተጨምሮለትም ሊጠናቀቅ አለመቻሉን በአዘኔታ ተናግረዋል። ይህ ፕሮጀክት ሊጠናቀቅ ባለመቻሉም የጎንደርና አካባቢው ማኅበረሰብ ለከፍተኛ ችግር መዳረጉን ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በመጠጥ ውኃ ችግር ስቃይ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ የመገጭ ግድብ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሮ ቢሆን ኖሮ 30 በመቶ የሚሆነው የጎንደር ከተማ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ይፈታ ነበር ብለዋል።

አክለውም፣ ‹‹በጎንደርና አካባቢዋ ብዙ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የመገጭ መስኖ ግድብ አለ በሚል ዕሳቤም፣ ሌሎች ተጨማሪ ፕሮጀክቶች በአካባቢ እንዳይሠራ ማነቆ ሆኗል፤›› ብለዋል።

የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ችግርና የተቀመጡ መፍትሔዎችን እንዲሁም አሁን ያለበትን የግንባታ ደረጃ ለማወቅ፣ የመገጭ ግድብ ኘሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኤርሚያስ በጋሻው (ኢንጂነር) እንዲሁም የመገጭ ግድብ ግንባታ ተጠሪ ወርቅነህ አሰፋን (ኢንጂነር) ሪፖርተር ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

በተጨማሪም፣ የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር የመስኖ ግንባታና ክትትል ዴስክ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ሊከሳ፣ እንዲሁም የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብዙነህ ቶልቻ ጥያቄ ብናቀርብም ሪፖርተር ጋዜጣ ወደ ህትመት እስከሚገባበት ሰዓት ድረስ ምላሽ መስጠት አልቻሉም።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርቡ የሆኑ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ፣ የመገጭ ግድብ ግንባታ ከጅምሮ አንስቶ በበርካታ ችግሮች የተፈተነ ነው። ከእነዚህም መካከል፣ የበጀት እጥረት፣ የወሰን ማስከበር፣ የውጭ ምንዛሪ ችግር፣ የስሚንቶ እጥረትና ሌሎች ለግድቡ መዘግየት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው። 

በሌላ በኩል ደግሞ ግንባታው የሚከናወንበት ቦታ የመሬት ሁኔታ በቂ ጥናት ያልተደረገበት በመሆኑ በርካታ የግንባታና የኮንክሪት ሙሊት ሥራ ከተከናወነ በኋላ ግንባታው የከተናወነበት መሬት በመንሸራተቱ የመደርመስ አደጋ እንደገጠመው ምንጮቹ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ድጋሚ የፕሮጀክት ዲዛይን ክለሳ በማድረግ የመሬት መንሸራተት ችግሩን መፍትሔ ለመስጠት ጊዜ መውሰዱንና ፕሮጀክቱ ሲጀመር 2.4 ቢሊዮን ብር የተገመተው አጠቃላይ ወጪ አሁን ላይ በብዙ ዕጅ መጨመሩን ምንጮቹ ተናግረዋል። 

እንደ ምንጮቹ ገለጻ፣ ለግድቡ ግንባታ እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ ወጪ የተደረገውን ሳይጨምር ቀሪውን የግንባታ ሥራ ለማጠናቀቅ 6.4 ቢሊዮን ብር በጀት ተጠይቆ ተፈቅዷል። የበጀት ጭማሪው ሲፈቀድ ታሳቢ የተደረገው ፕሮጀክቱ በ2016 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ ቢሆንም ይህንን ማሳካት እንደማይቻል ከወዲሁ ታውቆ፣ በ2017 ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑንም ምንጮቹ አስረድተዋል።

ነገር ግን የግንባታ ሒደቱ አያያዝና አሁንም ድረስ ያልተፈቱ ችግሮች በመኖራቸው በ2017 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ብለው እንደማያምኑ ለፕሮጀክቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል።

የመገጭ ግድብን አሳፋሪ ፕሮጀክት ነው ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ለሕዝብ ተወካዮቹ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ ‹‹ፕሮጀክቱ በ2017 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ ዕቅድ ተይዟል ግንባታውን ስንመለከተው ግን የሚጠናቀቅ አይመስለንም፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች