Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትመንግሥት ራሱ ለሕግ መገዛትን አውቆበታል ወይ?

መንግሥት ራሱ ለሕግ መገዛትን አውቆበታል ወይ?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ዴሞክራሲ የመላው ዓለም ‹‹ዜማ›› ነው፡፡ የአፍሪካ የዴሞክራሲ፣ የምርጫና የ(መልካም) አስተዳደር ቻርተርም ይህንኑ ያቀነቅናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ አንድ አሀዱ ብሎ የጀመረው፣ ‹‹ይህ ሕገ መንግሥት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ይደነግጋል›› ወይም ያስገድዳል ብሎ ነው፡፡ ፓርቲዎችም ከስያሜያቸው ጀምሮ ስለዴሞክራሲ ይናገራሉ፣ ለዴሞክራሲ ይታገላሉ፣ እንታገላለን ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለዴሞክራሲ የምር ትግል ከተጀመረ ቢያንስ ቢያንስ የካቲት 2016 ዓ.ም. ሲመጣ ግማሽ ምዕተ ዓመት ይሞላዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲን ስለማቋቋም፣ ወደ ዴሞክራሲ ስለመሸጋገር ብዙ ተብሏል፣ ብዙም ተከፍሎበታል፡፡

ዴሞክራሲ ማቋቋም ከአምባገነንነት ወጥቶ ወደ ዴሞክራሲ መግባትና ማለፍ ደግም ሰው ሰውን ከሚገዛበት ሥርዓት ሕግ ሰውን ወደሚገዛበት ሥርዓት ማለፍ፣ ሕግ፣ መንግሥትን ራሱን ወደሚገዛበት ሥርዓት መሸጋገር ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ለውጥ ለማምጣት፣ ይህንን የመሰለ ሽግግር ለማድረግ ደግሞ ዴሞክራሲ ነን፣ ዴሞክራሲ ሆነናል፣ ዴሞክራሲ አቋቁመናል፣ አውጀናል ማለት ውሸት መሆኑን፣ ከውሸትም በላይ ቅጥፈትና ሕዝብ ማታለልና ማጭበር መሆኑን፣ ብዙ ዋጋ ከመክፈል ጋር የተመዘገበ ያለፈው ሃምሳ ዓመት ታሪካችን በደም የመዘገበው ሀቅ ነው፡፡ ዴሞክራሲ በስምና በስያሜ እንደማይመጣ የደርግ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ፣ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ልምድ አስተምሮናል፡፡ ዴሞክራሲ በፓርቲዎች ስም ላይ በሚለጠፍ ቅጽል እንደማይገለጽ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፓርቲዎቻችን ታሪክና ልምድ ነግሮናል፡፡ ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ እንደማይደገስ የሕወሓት ልምድና ‹‹ድግሱ›› አስተምሮናል፡፡ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲ የማድረግ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ የመመሥረት ሥረ መሠረታዊ ቁምነገር ከየትኛውም ፓርቲ ወይም ቡድን ወገናዊነት ነፃ የሆነ የተቋማት ግንባታ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ትግል ችግር ያለውን ገዥ ቡድን ገርቶም ይሁን አውርዶ ከቡድን ይዞታነት፣ ተቀፅላነት ወይም የግል ባለቤትነት ነፃ የሆነ አገዛዝ የመገንባት ተቀዳሚ ተግባር ያለበት መሆኑን ጨርሶ አለመረዳት ነው፡፡ በአጠቃላይ የእስከ ዛሬ፣ ምናልባትም የእስከ ቅርብ ጊዜ ችግራችን የኢትዮጵያ መንግሥታዊ የሥልጣን መዋቅሮች ከአንድ ፓርቲ ወገናዊነት ተላቅቀው የተደራጁ ባለመሆናቸው ነው፡፡ ይልቁንም ጭራሹንም በፓርቲ መቃኘታቸው ትክክለኛና አስፈላጊ አድርጎ ከማዋቀርም ባለፈ፣ የሕዝቦችን ማኅበራዊ ህሊና ጭምር በፓርቲያዊ አስተሳሰብ መቆጣጠርን የአገር ትግል አድርጎ መያዝ የገዥዎች ተግባር ሆኖ መቆየቱ ነው፣ የችግራችን አናት ይኼ ነበር፡፡

- Advertisement -

ይህ ችግር ይህ ከፍተኛ ጉድለት አዲስ ሥልጣን ለሚይዘው ‹‹ገዥ›› ጭምር ግልጽ የሆነው (በግለሰብም ሆነ በፓርቲ ደረጃ)፣ በቅርቡ ከአምስት ዓመት በፊት በቅርብ ጊዜ እንደ ቀልድና እንደ ዋዛ የሰማነው (ወይም እንደ መርዶ የሰማነው) የተረዳነው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መሾምም ሆነ መመረጥ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩንም ቢሮና መኖሪያ ቤት መረከብ፣ የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ሥልጣን እንደማያጎናፅፍ በመራር ሁኔታ ስንረዳ ነው፡፡

ይህንን በመሰለ አጋጣሚ ምክንያት የመንግሥት አውታራትን ገለልተኛ አድርገው የማነፅ ቀዳሚ ሥራ ሳያከናውኑ ሥልጣን መያዝ፣ ሥልጣን ያዝኩ ማለት እንደማይቻል ተረዳን፡፡ ገለልተኛ ተቋማትን ወደ መገንባት ተግባር የገባነው ከዚህ በኋላና በዚህ አማካይነት ነው፡፡ ያም ሆነ፣ ይህ አደራ የሁሉም ፓርቲዎችና ታጋዮች የጋራ መግባቢያና መገናኛ አልሆነም፡፡

ወደ ሰሞነኛ ጉዳያችን ስለ‹‹የሰላም ስምምነቱ ትሩፋት››፣ እውነትም ስለየሰላም ስምምነት አፈጻጸም ‹‹ሪፖርት›› መነጋገሪያ ስለሆነው ብቻ ሳይሆን፣ መነጋገሪያ መሆኑ ራሱ ስላነጋገረው፣ የሕወሓት ከአሸባሪነት ስያሜ የመሰረዝ ጉዳይ፣ ስለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አቋቋም ነገር፣ ይህ ሁሉ ፓርላማ ውስጥ ስለተስተናገደበት ሁኔታና አያያዥ ከማንሳታችን በፊት፣ ከፍ ሲል ጠቆም ያደረግሁትንና እጅግ በጣም ጎልቶና ደምቆ ሊነገር የሚገባውን ሁሉም ፓርቲዎች ሊስማሙበት፣ ሊታገሉለትና ሊዋደቁለት ስለሚገባ አንድ መነሻ ጉዳይ ላንሳ፡፡ የተለያዩ  ፓርቲዎች አሉ ማለት እርስ በርሳቸው ተወዳዳሪ ናቸው ማለት ነው፡፡ የሚወዳደሩትም ለሥልጣን ነው፡፡ የተለያዩ ፓርቲዎች፣ እርስ በርስ ‹‹የሚፋጁ››፣ የሚፋለሙ ፓርቲዎች ግን ፍልሚያቸውንና ትግላቸውን አንድ ብለው ለመጀመር፣ መጀመርያ መቀመጫቸውን ማደላደል አለባቸው፡፡ የቡድኖች ወይም የፓርቲዎች መንግሥታዊ ገዥነት ከነፃና ከትክክኛ ምርጫ የሚመነጭበት አዲስ ምዕራፍ ይከፈት ማለት፣ የድምፅ ብልጫ አግኝቶ ፍላጎትን ውሳኔ ማድረግ የሚያስችል የጨዋታ ሕግ እንዲኖር ለማድረግ፣ የመንግሥት ዓምዶች ገለልተኛ ሆነው መታነፅ አለባቸው፡፡ ይህንን ሥራና የአገር አደራ ዋናው ግዳጁ ያደረገውን ለውጥ ከቅልበሳ ማዳን መጀመርያ የሁሉም ሥራ የሁሉም ወገኖች አደራ መሆን አለበት፡፡

ለውጡን ከቅልበሳ ማዳን ላይ ግን የአገር ህልውናን መከላከልን የመሰለ ከፍተኛ ግዳጅ ተደርቦ መጣ፡፡ ቀላል አልነበረም እንጂ እነዚህ ሁለት የእናት አገር ጥሪዎች በመንግሥት ዙሪያ ከፍተኛና ዓድዋን የሚያስታውስ ሕዝባዊ ርብርብ ፈጠሩ፡፡ ለውጡን ከቅልበሳ የማዳን ጉዳይ፣ ይህንንም ለማሳካት ገለልተኛ ተቋማትን የመገንባት ሥራ ማንም ወለም ዘለም የማይልበት የአገር አደራ ይሆን ዘንድ፣ እዚህ ላይ ተደርቦ የመጣውን ጦርነት ማሸነፍ ግድ ነበር፡፡ ወደ እዚያ ያደረሰን ዝርዝሩ ብዙ ቢሆንም፣ ጦርነቱን በጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አማካይነት አሳረግን፡፡ በዚህ በያዝነው የመጋቢት (18 እስከ 24) አራተኛ ሳምንት መጨረሻ ላይ፣ አምስት ወር የሞላው የሰላም ስምምነት ጦርነቱን ከማቆም በላይ ዋነኛውንና ራሱ ጦርነት የተነሳበትን የለውጡን ሥራ አጧጡፎና እንደ ገና አስጀምሮ ማስኬድ የሚያስችል ጅምር ነው፣ ወይም ነበር፡፡    

የሰሜኑ ጦርነት ዋናው ጉዳያችን ሆኖ ብዙ ካስከፈለን በኋላና ከዋናው ለውጡን የማካሄድ የገለልተኛ ተቋማት ግንባታ ሥራ ከማከናወን ዋናው አደራ እያስተጓጎለና እያዘናጋ ካስጀመረን በኋላ፣ ዋናው ጉዳያችን የሆነው ጦርነት መፍትሔ አገኘ ብለን አንፃራዊ፣ የዕፎይታና የእሰይታ ስሜት ውስጥ ገባን ስንል፣ ያለፉት አራትና አምስት ወራት የሰላም ስምምነቱን አፈጻጸም ሪፖርት የምናደምጥበትና የምንገመግምበት (በዚህም ላይ የግምገማችን ውጤት የምንገልጽበት፣ የምናሳውቅበት፣ የእዚህንም ምላሽና ማብራሪያ ኃላፊነት ከሚሰማው የመንግሥት የሥልጣን አካላት መልሰን የምናገኝበት፣ ወዘተ) መሆኑ ቀርቶ፣ ባልተጠበቁ ዱብ ዕዳዎችና ዝም ብለው እየወረዱ በሚወድቁብን የብራ መብረቆች የምንታመስበት፣ የመመሳቀል አደጋ ውስጥ የገባንበት ጊዜ መጣ፡፡ እነዚህን ባለፉት አራትና አምስት ወራት እየተዘረገፉ፣ ዝርክርካችንን እያወጡ ያስቸገሩንን የችግሮች ዓይነትና ዝርዝር ከሚዲያዎቻችን በተለይም የ‹‹ሕዝብ ሚዲያ›› ከሚባሉ መዋዕለ ዜና ይልቅ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መደበኛ ሥራ ሪፖርቶች ዘግበውልናል፣ መዝግበውልናል፡፡ ጦርነቱም የገዛ ራሳችንን ዝርክርክነት ያሰናከለውን ተቋም የመገንባት ሥራ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ላይ እስካሁን ገና አለማፈሩን የሚነግረንና የሚያፅናናን ሁሉንም ያላዳረሰና ያልዘለቀ፣ እርስ በርስም ያላቆላለፈና ያላስተሳሰረ ተቋማዊ ዋስትናም ያላገኘ ግንባታ ሁልጊዜም መተማመኛ ሊሆነን እንደማይችል ጭምር ነው፡፡ በነገራችን ላይ በተለይም በዚህ በምንነጋገርበት ጦርነት አበቃ፣ አንፃራዊ የዕፎይታና የእሰይታ ጊዜ ውስጥ ገባን በምንልበት ወቅት ውስጥ እየተዘረገፉ ያስቸገሩን፣ ጉዳዮቻችን እያወጡ፣ ያሳጡንና ያጋለጡንን ችግሮች ዘገባና ዝርዝር የምንሰማው ከውጭ የሰብዓዊ መብት ‹‹ተቆርቋሪ›› ተቋማትና አገሮች ሳይሆን ከአገራችን ለዚያውም ከመንግሥታዊ ኢሰመኮ ነው፡፡ ለመዘርዝር ሳይሆን ለምሳሌ ያህል ለመጥቀስ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አኳያ የክልል ባንዲራና መዝሙር ነገር የሕገወጥነት ባህርይ በድፍረትና በዝርዝር ከእነ መፍትሔው ሪፖርትና ይፋ ሲደረግ የሰማነው፣ የባጃጆች ጉዳይ ችግርና መፍትሔ የተነገረው የለውጡ ዋና ይዘት የሆነው ተቋማትን ገለልተኛ አድርጎ የማነፅ ሥራ በአንፃራዊነት በተሳካበት በኢሰመኮ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ‹‹ቁጣ››ውን ጭምር ገልጾ የዘረዘራቸው የሕግ አስከባሪ አካላትን ሕገወጥ ተግባራት (ከዚያ የመነጩና የተጋቡ የግል ተቋማት ማለትም የአከራዮች የአገልግሎት ሰጪዎችን ‹‹ነውሮች››) በዝርዝር፣ በልክና በመልኩ የሰማነው እንደ ልማዳችን ከከሳሽ ከአቤት ባይ ብቻ ሳይሆን (ለዚያውም የእነሱን አቤቱታ የሚያስተጋባ ከተገኘ) ገለልተኛ አድርጎ የማዋቀር ሥራ ከተሠራበት የመንግሥት ተቋም ነው፡፡ ልብ ይደረግልኝ፣ ይህን ሁሉ ምሳሌ አድርጌ መግለጽ የጀመርኩት በነገራችን ላይ ብዬ ነው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ያስመዘገብናቸው ድሎች ግን ዘላቂ ዋስትና የሚኖራቸውና የምንኖርበት ሥርዓት የስም ጌጥ፣ የተውሶ ልብስ ይልቅ፣ የውስጥ ባህርይ እንዲሆኑ የጀመርነውና በመከላከያ፣ ከዴሞክራሲ ተቋማት መካከል በሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ በአንፃራዊነት የተሳካው ገለልተኛ አድርጎ የመገንባት ሥራ የአገር ዋና አደራ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል መረባረቢያ ሲሆን ነው፣ ሆኖም ሲቀጥል ነው፣ ዋናው ሥራችን ሲሆን ነው፡፡

ይህንን ጦርነት የቀለለበትን የተቋም ግንባታ ሥራ አደራችንን ለብቻውና በአንድነት እንድናከናውን ደግሞ በተለይም ባለፉት አምስት ወራት ድንገት እየተዘረገፉ ያመሱንና ያመሳቀሉን ችግሮች የገዛ ራሳቸው ባህርያዊ ጥፋትና ክፋት ሳያንስ በመንግሥት ዙሪያ ተሰባስቦ የኖረውን፣ በአገር ውስጥም በውጭ አገርም ከፍ ያለና እጅግ በጣም አስደናቂ ትጋትና ውጤት ያስመዘገበውን ድጋፍ መበታተን፣ ቢያንስ ቢያንስ መከፋፈል ችለዋል፡፡ ይህንን ችግር መርምሮ፣ በሽታችንን አውቆ፣ መፍትሔውንና መድኃኒቱን መፈለግ የሁሉም ባላገር፣ ዜጋና ሕዝብ ግዴታ ነው፡፡ የመንግሥት የመሪነት ሚናም መተኪያም ሌላ አማራጭም የለውም፡፡ መንግሥት በዚህ ረገድ በሽታችን፣ ሕመማችን ምንድነው አለ? እውነተኛው በሽታችንን አወቀ ወይ? ምንስ መላ መታ? ምን ዓይነት መፍትሔስ ዘየደ? ይህ ራሱ አስቸጋሪ ጥያቄ ነው፡፡

የመንግሥት የሥልጣን አካላት በአጠቃላይ በየደረጃው የሚገኙ የሕግ አስከባሪነት ሥራና ተግባር የተሰጣቸው ልዩ ልዩ ክፍሎች በየፊናቸው የሚወስዷቸው በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ድርጊቶችም ሆኑ አዳዲስ ተግባራት እየተደራረቡ የ‹‹ዘመቻ›› ሥራም ሆነው ሲከሰቱ፣ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለውና የመንግሥትን ፖሊሲ የሚቆጣጠረው ለውጡንም የጦርነቱንም ጥረትና ትጋት (ርብርብ) የሚመራው የመንግሥት ባልቦላ ምልክት ሳያሳይ፣ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ዝም ብሎ ቀጠለ፡፡ ከፍ ሲል የጠቀስናቸው ኢሰመኮና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚያወጡት ሪፖርትና መግለጫ እንኳን አልከነክን፣ አልቆረቁር ብሎ የመንግሥት ዝምታ አገር አደነቆረ (እርግጥ ነው መንግሥት በዚህ ጊዜ ውስጥ በደርግ ጊዜ፣ በኢሕአዴግም ዘመን እንደለመድነው፣ በተለይም በኢሕአዴግ ዘመን ሲባል እንሰማ እንደነበረው ዓይነት የዚህ ዓይነት ሪፖርት መስማት የጀመራችሁት፣ እንዲህ ያለ ምርጫ ቦርድ፣ እንዲህ ያለ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያያችሁም በእኔ ጊዜ ነው፣ በእኔ ምክንያት ነው፣ ዕድሜ ለእኔ በሉ አላለም!!)፡፡

ዝም ብሎ ማሰር ቀረ አላልንም ወይ? ሳናጣራ አናስርም ያልነውን መፈጸም ምን ከለከለን? ብሎ ለሕዝብ ምላሽ የሚሰጥ የመንግሥት ልሳን ጠፋ፡፡ እከሌ የሚባል ሰው ጠፋ፣ ተሰወረ ሲባል፣ ተጥሎ ተሰውሮ ‹‹ተገኘ ተብሎ ሲወራና የሆነ ተቋም መሥሪያ ቤት የሥራ ቦታና ንብረት ተሰብሮ፣ ተከፍቶ፣ ተዘርፎ ተገኘ ሲባል፣ ወዘተ እንዴት አድርጎ ይህ በመንግሥት፣ በፖሊስ አገር ይፈጸማል? የሚል የመንግሥት፣ የፖሊስ የበላይ ጠፋ፡፡ ከዛሬ ነገ ለውጡና ሽግግሩ አምጦ የወለደውና ነገር ግን የሆነ ቦታ አልከስኩሶ ያስቀመጠው ‹‹The back stops here›› (ማለትም ይህማ ስህተት ብቻ ሳይሆን ጥፋት ነው፣ መፈጸም የለበትም፣ አልነበረበትም፡፡ ማንም ፈጸመው፣ ማንም አጠፋው ዞሮ ዞሮ ኃላፊነቱና ተጠያቂነቱ የእኔ ነው) የሚል ድምፅ ጠፋ፡፡ ከዛሬ ነገ ከአሁን አሁን እንዲህ ያለ ምላሽ እንዲህ ያለ ድምፅ ከከንቲባው ጽሕፈት ቤት፣ ከአዲስ አበባና ከፌዴራል ፖሊስ አዛዦች፣ አለዚያም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት፣ ከየክልል መስተዳድሮች ጽሕፈት ቤት ጭምር ብቅ ይላል ብለን ጠበቅን፡፡ ለውጡና ሽግግሩ እንዲህ ያለ ‹‹ባህል›› ለአንደበት ወግ ያህል እንኳን አላሰማን ብሎ፣ ሳያሰማን ቀርቶ አሳፈረን፡፡

በመንግሥት ዙሪያ የተሰባሰበውና የተከማቸው የሕዝብ ድጋፍ እየተበተነ፣ እየሳሳና ምናልባትም በአንፃሩ ከመንግሥት በተቃራኒ እየተሠለፈ መምጣቱ በሚያሳስበን እኔን በመሰሉ ሰዎችና ወገኖች ሥሌት፣ መንግሥት ከብዙ ጊዜ ዝምታ ከረዥም ጊዜ የግብር ይውጣ ‹‹የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን›› ቴአትር በኋላ፣ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የሽግግር ጊዜ ፈተናዎች የገጠማትን ተግዳሮቶች መርምሬያለሁ፣ ለዚህም የትግል ሥልት ቀይሻለሁ ያለው ገና አሁን መጋቢት ወር ላይ (የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. መግለጫ ይመለከቷል) ነው፡፡

በመግለጫው መሠረት ከፍ ሲል በዚህ ጽሑፍ ያመላከትኩት የአገር በሽታ ምርመራ ሥራ ተከናውኗል፣ ሕመማችን ምን እንደሆነ ታውቋል፡፡ ‹‹መድኃኒቱም ታዟል››፡፡ አገራችንን ያጋጠሟት ፈተናዎች በዋናነት ከአምስት ነገሮች የመጡ መሆናቸውን ይገልጽና እነዚህንም ይዘረዝራል፣ ከእነዚህ ከ‹‹ሌብነት›› (ሙስና) የኑሮ ውድነት፣ የታሪክ ዕዳ ጋር ከተዘረዘሩት መካከል ወይም አንዱ ‹‹ነፃነትን ለማስተዳደር አለመቻል›› ፈተና ነው፡፡ እውነት ነው የማይናቅ ችግር ነው፡፡ የምንገኝበት ጊዜ (ለዚያውም የማይናቅ ክብደት ያላቸው ሰዎች ተቀልብሷል ድሮ ቀርቷል ይሉታል) የሽግግር ጊዜ የምንለው ሕገ መንግሥቱን ካሰነካከለ ፍጥርጥር ሕገ መንግሥቱንና በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን የመብትና የነፃነት፣ እንዲሁም የመንግሥት አወቃቀር ድንጋጌዎች አፍታትቶ ወደሚያሠራና ተግባራዊ ወደሚያደርግ ፍጥርጥር የመሸጋገር ጉዞና ሥራ ያለበት ምዕራፍ በመሆኑ ነው፡፡ ዴሞክራሲን ለማቋቋም የሚያስችል ለውጦች ውስጥ ገብተናል ብለን ነው፡፡ ከእነዚህ ለውጦች መካከል ዋናውና የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ትግል ጎዶሎ ሆኖ የኖረው ገለልተኛ ተቋማትን የማቋቋም ሥራ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ፣ ከዚያም በፊት በነበሩ የአገር የበላይ ሕጎች ሲዘረዘሩ የኖሩት የመብትና የነፃነት ድንጋጌዎች ይዘቶችን ከገዥዎች መልካም ፈቃድ ውጪና ከእርጥባን በዘለለ፣ እንዲሁም ከጉልበተኛ ጥቃት ነፃ በሆነ ደረጃ መኖር ያልቻልነው ተቋሞቻችንን ነፃና ገለልተኛ አድርገን ማቋቋም ባለመቻላችን ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ሥራና መሠረት ያለው፣ እንዲሁም የሕዝብ ድጋፍና ጥበቃ (ከሕዝብ እምነት ግንዛቤና ንቃት ጋር) ካላገኘ፣ አውታራት የገዥው ፓርቲ አሻንጉሊት በአንፃሩና በአፀፋውም ደግሞ የተቃውሞ እልህ መውጫ ይሆናሉ፡፡ ይህንን ለመጀመር፣ የተጀመረውን ተቋማትን ገለልተኛ አድርጎ የመቅረፅን ሥራ የማያጠራጥር፣ ቢያንስ ቢያንስ የማያስተማማ ለማድረግ ፓርቲና መንግሥትን የማለያየት፣ የማቆራረጥ ሥራ አሁን አገራችን ውስጥ እንደሚታየው ተጎልቶ የሚታይ፣ ሐውልት ሆኖ ተገትሮ የቀረ መሆን የለበትም፡፡ መግለጫው ውስጥ የምናየው፣ መንግሥትን ሲያደናቅፈው፣ ከዚያም በላይ ጠልፎ ሊጥለው፣ ሲያስፈራራው የምናየው በዚህ ረገድ የጎደለው ሥራ አንዱ ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱን በሌሎችም ከዚያ ቀደም በነበሩ የበላይ ሕጎች፣ አሁንም ሥራ ላይ ባሉ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር፣ ወዘተ ሕጎች የተዘረዘሩ የመብትና የነፃነት ድንጋጌዎች ዛሬም ገና ተቋማዊ ዋስትና አላገኙም፡፡ ብዙ ችግር፣ ተቃውሞና የጦርነት ጥቃት ጭምር ባጋጠመው በዚህ የለውጥና የሽግግር ጊዜ ውስጥ ደጋግመን የምናነሳቸውን (ደጋግመን ከማንሳታችንና ከ‹‹ኩራታች››ን የተነሳ ሰው ምናልባትም ከለውጡ ይልቅ፣ በእኛ በለውጡ አፍቃሪዎች/አድናቂዎች ላይ ተናዶና ተበሳጭቶ ‹‹አንዲት ጥርስ ቢኖራት በዘነዘና ተነቀሰችው›› ብሎ እንዲተረትባቸው አድርገን ይሆን ብዬ እፈራለሁ) የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የምርጫ ቦርድን የመሳሰሉት ተቋማት ላይ ለውጥ መጥቷል፡፡ ይህንን የመሰለ ለውጥ ግን በተገለጹት ተቋማት ላይ ብቻ የተወሰነ፣ በእነሱም ላይ ቢሆን ከውጭ የተርከፈከፈ ሽቶ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የትኞቹም የመንግሥት አውታራት ከሕዝብ ሥልጣንና ከሕግ በቀር ለማንም ቡድን መጠቀሚያ የማይሆኑበት ባህርይ እስኪጎናፀፍ ድረስ፣ ገዥው መንግሥትም በፓርቲውና በመንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት አውቆ አጥብቆ እስኪገዛ ድረስ፣ መንግሥት ከእነ ዛፍ ቅርንጫፉ፣ ከእነ ባለሥልጣናቱ በሕዝብ ወይም በሕግ ሥልጣን ሥር ማደር፣ ለሕግ መገዛቱ ዕውን እስኪሆን ድረስ የማጥለቁ ሒደት መቀጠል፣ ወደ የማይቀለስበት ደረጃና ከፍታ ድረስ መዝለቅ አለበት፡፡  አሁን የምናያቸው በመብቶቻችን የመገልገል ሻል ያለው ነፃነት በዋነኛነትና በአብዛኛው ጥርነፋውና አፈናው በመነሳቱና በመላላቱ ምክንያት የምናጣጥማቸው እንጂ ሥርዓታዊ መሠረትና ዋስትና የተጎናፀፉ አይደሉም፡፡

ይህንን በመሰለ ከባቢ አየር ውስጥ በሚኖርና በሚካሄድ ለውጥና ሽግግር ውስጥ ወደማያውቁት ዴሞክራሲ ሲያመሩ ለምሳሌ የንግግር ነፃነትን ከመብት መነካት ጋር ማሳከር ሳያውቁት ፈተና ሊያሳይ ይችላል፡፡ ከፖለቲካ ገለልተኛ በሆነ/ወይም ገለልተኛ ነው በሚባል ሙያዊ ኃላፊነት ውስጥ የፖለቲካ ፍትፈታ ውስጥ መግባት ያጋጥማል፡፡ በኅብረተሰቡም በመንግሥት እንቅስቃሴ ውስጥም ከዴሞክራሲያዊነትና ከሕገ መንግሥታዊነት ያፈነገጡ ከዚህ ጋር የሚጣሉ ተግባራት መኖራቸውም ላያስገርም ይችላል፡፡ የአገራችን ሁኔታ ግን ‹‹ያለ አዋቂ ሳሚ›› ጥፋትና ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ለውጡ፣ መንግሥት፣ አገሪቱ ራሷ ውጭ አገር ድረስ የተዘረጋ (ወይስ ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ የተቀዳ?) ደመኛ ጠላቶች አሉባቸው፡፡ ይህን በመሰለ ዓውድ ውስጥ የብልፅግና ፓርቲ ‹‹በሽታ ምርመራ›› ውጤት ከፈተናችን መካከል አንዱ ‹‹ነፃነትን ለማስተዳደር አለመቻል›› ነው መባሉ በጣም አንድ ዓይና ብቻ ሳይሆን፣ ሲበዛ ድንባዣም ነው፡፡ የፓርቲው የበሽታ ምርመራ ውጤት ነፃነት ማስተዳደር ካለመቻል ጋር አብሮ የሚኖረውን፣ የዚህ አጣማጅ አቻ ሆኖ ብቻ ሳይሆን ለብቻውና ነፃ ወጥቶ፣ ነፃነቱን አውጆ፣ በመንግሥት ሥልጣንና ባለሥልጣናት ማናህሎኝነትና ማን ያዘኛል ባይነት አገር ማፍረስ ደረጃ የደረሰውን ከሕግ በላይ የመሆን ዋና ሕመም ማየት አልቻለም፡፡ ጽሑፌን ስጀምር አስረግጬ የገለጽኩት ይመስለኛል፡፡ ዴሞክራሲ እገነባለሁ ማለት ሕግ መንግሥትን ራሱን፣ ሕግ ፓርላማውን ራሱን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የክልል መስተዳድሮችንና የከተማ አስተዳደሮችን ከእነ ፕሬዚዳንቶቻቸውና ከእነ ከንቲባዎቻቸው ይገዛል ማለት ነው፡፡ ማለት ጭምር ነው አላልኩም፡፡ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ መንግሥትንና ባለሥልጣኖቻቸውን ከሕግ በታች ማድረግ የለውና የሽግግሩ ዋና ዓላማና ግብ ነው፡፡

ለሕግ መገዛትን፣ ወደ እዚህ የ‹‹ማያውቁት›› አገር የሚደረግ ጉዞን እናውቀዋለን ወይ? አውቀንበታል ወይ? ብሎ መጠየቅ አንዳንድ ጠቋሚ ነገሮችን ሲያመላክተን አይቻለሁ፡፡ ለውጡን የሚመራው መንግሥትና የሥልጣን አካላቱ በሙሉ ከእነ መላው ባለሥልጣናቱና ሠራተኞች በሙሉ በሕግ ለመገዛት፣ በሕግ ሥር ለማደር ከመሃላ፣ ከቁርጠኝነት፣ ከመፈጠም በላይ ተግባሩ የሚታይ የአኗኗር ለውጥ ማድረግ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ይህ ለውጥ ሕዝብን መፍራትና ማፈርን፣ ሕግን ማክበር፣ በተቻለ መጠንና በሕግ የተወሰነውን ያህል በሕዝብ ድምፅ በግልጽ አሠራር፣ በሚዲያ፣ በጋዜጠኛና በሕዝብ ንቁ ተመልካችነት ውስጥ መኖርን ይጠይቃል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 9(2) ላይ ማንኛውም ዜጋ የመንግሥት [የሥልጣን] አካላት የፖለቲካ ድርጅቶች ሌሎች ማኅበራት፣ እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው ይላል፡፡ የለውጡን የሽግግሩ ዋና ግብ ይህ ውሸት ሆኖ ከኖረበት እውነት ሆኖ፣ ተጨባች ሆኖ ወደ የሚታይበት ሻል ያለ ሕይወት መሸጋገር ማለት ነው፡፡

ይህንን የጉዞ ፈር አድርገን ይዘናዋል ወይ? እዚያ ፈር ውስጥ መግባት ተደፍሯል ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች አፍ ሞልቶ ለመናገር ብዙ ‹‹የሚያጋልጡን›› እና ተቃራኒውን ‹‹የሚመሰክሩብን›› አሉ፡፡ ለምሳሌ የመንግሥትንና የባለሥልጣናቱን የአኗኗር ለውጥ ያሳያሉ፣ ይመሰክራሉ ካልናቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ግልጽ አሠራር ነው፡፡ የአሠራር ግልጽነት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህንን በአንቀጽ 12 ይደነግጋል፡፡ ለውጡና ሽግግሩ የአሠራር ግልጽነትን የጉዞ ፈሩ አድርጎ ይዞታል ወይ? እዚያ ፈር ውስጥ መግባት የሚያስችል ድፍረትስ የለወጥ መሪዎች አግኝተዋል ወይ የሚለው ጥያቄያችን የሚያገኘው መልስ የመንግሥትን ጥረትና ትጋት በአብዛኛው እጀ ሰባራ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የመንግሥት ወዳጅ፣ የመንግሥት ደጋፊ ትችት ነው፡፡ ምሳሌውን በአጭሩ ብቻ ገለጥለጥ አድርጎ ለማሳየት የሰላም ስምምነቱ አንድ ዋና ጉዳይ የሆነውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጉዳይን እንመልከት፡፡ ስምምነቱ ስለዚህ ጉዳይ የሚውል በስምምነቱ አንቀጽ 10 (1) የተወሰነውን ነው፡፡ የዚህ አንቀጽ የመጨረሻ ዓረፍተ ነገር፣ ‹‹The establishment of an inclusive interim regional administration will be settled through political dialogue between the Parties.›› ይላል፡፡ በአጭሩ አማርኛ አካታች የሆነ ጊዜያዊ የክልል አስተዳደር የማቋቋም ነገር/ጉዳይ በሁለቱ ወገኖች መካከል በሚደረግ የፖለቲካ ውይይት አማካይነት ይወሰናል ማለት ነው፡፡ ‹‹The Parties›› ማለት በስምምነቱ መግቢያ መጨረሻ ፓራግራፍ ላይ መንግሥትና ሕወሓት መሆኑ በትርጉም መወሰኑን በጭራሽ አላውቅም የሚሉ፣ ‹‹Parties›› ብሎ አጻጻፉ በስምምነቱ አጠቃላይ አካል በሙሉ በካፒታል ሌተር የመጻፍ ትርጉምና አንድምታ የተሳናቸውና የሳታቸው ‹‹Parties›› ማለት የፖለቲካ ድርጅቶች ማለት ነው ብለው ይተረጉሙታል፡፡

ስምምነቱ ግን የሚደነግገው መንግሥትና ሕወሓት ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት የሚቋቋሙበትን ጉዳይ/ሁኔታ ይወስናሉ ብሎ ነው፡፡ መላው ትግራይ ውስጥ ይህ መንግሥት ስለሚቋቋምበት ሁኔታና አሠራር ሁሉም አፍ ሆኖ ሲናገር፣ እዚህ የተቀረው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰማው ከዚያ ተንጠባጥቦ፣ ተቆርጦ፣ ተቀጥሎ፣ የሚሰማውን ያህል ብቻ ነው፡፡ እኔን የመሳሰሉ፣ እንደ እኔ ያሉ መንግሥትን ተማምነው የዚህን ወሬ ‹‹ክደው›› እና ‹‹አስተባብለው›› የኖሩ ሁሉ ቢያንስ ቢያንስ በዚህ ጉዳይ ረገድ፣ ‹‹የሌለኝን ሁሉ አለኝ ስል ከርሜ›› እያሉ እያንጎራጎሩ መንግሥትን መጠርጠር የጀመሩት አንቶኒ ብሊንከን የአገራቸውን የ2022 የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ይፋ በተደረገበት ዕለት፣ የአቶ ጌታቸው ረዳን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ሆኖ መሾም ‹‹አረጋግጠው›› በተናገሩበት ወቅት ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ ማርች 20 (መጋቢት 11 ቀን 2015 ድረስ) ኦፊሲያል ኢትዮጵያ ምንም አታውቅም፣ ምንም ነገር አልተናገረችም፡፡ መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ከጠቃላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የወጣ መግለጫ፣

‹‹የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 14/2/ለ መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፣ እንዲሁም በኢፌዴሪ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ለዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ግጭትን ለማቆም በፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ በተደረገው የሰላም ስምምነት አንቀጽ 10 (1) መሠረት አካታች ጊዚያዊ አስተዳደር ማቋቋም በማስፈለጉ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ‹‹የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ደንብን› አፅድቋል፡፡

‹‹በዚሁ ደንብ አንቀጽ 3(2) መሠረት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው ሾመዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ውክልና የሚያረጋግጥና አካታች የሆነ አስተዳደር በማዋቀር የክልሉን አስፈጻሚ አካል የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፤›› ብሎ ነገረን፡፡

ሌላው ሌላው ገመናችንን እንተወውና በዚህ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ ከተገለጹት ውስጥ አንድ ነገር ብቻ መዝዘን እናውጣ፡፡ ‹‹…የሚኒስትሮች ምክር ቤት መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ ‹‹የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ደንብ›ን አፅድቋል፤›› ይላል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕግ የማውጣትን የመሰለ ይፋዊ የአደባባይ ሥራ ሲሠራ እንኳን ሌላ ቢቀር እንደሌላው ጊዜ መጋቢት 9 ቀን ምሽት ላይ ዜና ሆኖ አልሰማንም፡፡ ዛሬም ድረስ ‹‹የትግራይ ክልል አካታች ጊዚያዊ አስተዳደር ደንብን›› ይዘት አናውቅም፡፡ ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ስለመውጣቱም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የወጣው ደንብ፣ ወይም በጣም በጣም ሕግ ለማክበር፣ ሕግ ለሚለው ሁሉ ለመገዛት ወጣ የተባለው ደንብ (ደንቡን ወጣ ለማለት በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ መውጣቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋልና) የያዘውን መልክና ልክ፣ እንዲሁም ይዘቱ ላይ ለመድረስ የተከናወነውን የመንግሥት ሥራ የአፈጻጸም ሪፖርትማ ለሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 (1) ባዳና እንግዳ ነው፡፡ የ‹‹ጊዜያዊ አስተዳደሩን›› የማቋቋም ሒደትን በሚመለከት ረገድ የዚያኛው ወግ (Party) ጩኸትም አደንቋሪ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ዝምታ ደግሞ ይበልጥ አደንቋሪና ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይዞ የሚማስን ነው፡፡ የፓርላማው የመጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ውሎ ይህንን ሳይጠይቀውና ሳያነሳው ማለፉ ደግሞ የሚገርምና የሚደንቅ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥም ነው ባለ ጉዳይ፣

‹‹ለዚህ፣ በዚህ አይደል ሰው የሚተማማ፣

ሞተችልህ አሉኝ ሕመሟን ሳልሰማ›› ብሎ ሙሾ የሚያወርደው፡፡

ይህንን ሁሉ እያልኩም አሁንም ገና ተስፋ አልቆረጥኩም፡፡ ሰው እንደፈለገው ሰውን ከሚገዛበት ሥርዓት፣ ሕግ ሰውን ወደ የሚገዛበት፣ ሕግ መንግሥትንና ባለሥልጣናቱን ወደሚገዛበት ወደ የሚያሰርጉበት/ሥርዓት ዕውን እንዲሆን፣ በተለይም የመንግሥቱ ከፍተኛ አመራር በተግባሩም፣ በአርዓያነቱም፣ የአነጋገሩም የጥፋት ምሳሌ መፅዳት ብቻ ሳይሆን፣ አደባባይ ወጥተው የራሳቸውንም ሆነ  የባልደረቦቻቸውን፣ የሠራተኞቻቸውን የሕግ ጥሰትና አልዳኝም ባይነት ማጋለጥና መቆጣት አለባቸው፡፡ ሳይጠየቁ መቅረትን በዚህ ደረጃ መልመድና ማለማመድ ካልጀመሩ የሚሠራ፣ በትክክል የሚሠራ ‹‹ፋንክሽኒንግ›› የመንግሥት አውታር ግንባታችን     ነገር ወሬና ውሸት ሆኖ ይቀራል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...