በአባ ጌድዮን ዘደብረ ሊባኖስ
ይድረስ ለአገር መሪዎችና ፖለቲከኞች፣
ይድረስ ተምረናል ለምትሉ ምሁራን፣
ይድረስ ለአገር ሽማግሌዎች፣
ይድረስ ለሃይማኖት መሪዎች፣
ይድረስ ህሊና አለኝ ለምትሉ ባለህሊናዎች በሙሉ፣
ምነው አገሬ ካለፈ ታሪክ መማር አቃታት? ምነው አገሬ ከታሪክ ተምራ ሯሷን ማስከበር ተሳናት? ወዳጆቼ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ተወያይቶ ችግር መፍታት ባለመቻሉ ምክንያት በተከሰተው አስከፊ ጦርነት፣ ብዙኃን ደሃ እናቶችን ያለ ጧሪ ያለ ቀባሪ ያስቀረ ዕልቂት አስከተለ።
ከዚህ የአገራችን ክፉ ታሪክ መማር ባለመቻላችን ወርደን እርስ በእርስ ከሰሜኑ የአገራችን ክፍል ጋር ጦርነት በመጋጠማችን፣ የደሃን ልጅ ሙጥጥ አድርጎ የበላ ሌላ አስከፊ የጦርነት ታሪክ አሳለፍን። አሁንም ቢሆን የወልቃይትና የራያ አላማጣ ጉዳይ በሰላም እስካልተፈታና ዘላቂ ዕልባት እስካልተደረገበት የተዳፈነ እሳት ወይም ድንገት ሊፈነዳ የሚችል የተጠመደ ቦምብ ነው።
ችግሩ በዘላቂ መፍትሔ ዕልባት ሳያገኝና ጦርነቱ ሳይውል ሳያድር፣ እንዲሁም የወዳደቁት እንኳን በቅጡ ተለቅሞ አስከሬናቸው አፈር ሳይለብስ፣ ያለፈው አልበቃ ብሎን ሰሞኑን በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች መካከል ጎራ ለይቶ መተነኳኮስ ተጀምሯል። የጦርነት ነጋሪቱም ዕለቱን በሚያፈጥኑና ችግሩን በሚያባብሱ አሉታዊ ድርጊቶች ታጅቦ ሲጎሰም በዓይንም በጆሮም ይታያል፣ ይሰማል።
በሰሜኑ የአገራችን ክፍልም ነገሩ ሲጀመር በዚህ መልኩ ነበር። ሄዶ ሄዶ ወደ ጦርነት ሲገባ ያስከተለው መዘዝ የደሃን ልጅ ቅርጥፍ አድርጎ ከመብላት ባሻገር በብዙ ብድር የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ዶግ አመድ ሆነዋል። ቢያንስ ወደ ሰላሳ ዓመታት ወደ ኋላ የሚጎትት ኪሳራ በክልሎች ተመዝግቧል።
መንግሥት ካዝናው ተራቁቶ በውጭ ምንዛሪ ዕጦት የሕዝብ ኑሮ ተመሰቃቅሏል። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ተነስቶ መቃቃርና ማኅበራዊ ቀውስ ተፈጥሯል። በእርግጠኝነት ከዚህ አደጋ ለመውጣት በርካታ የጭንቅ ዓመታት ከፊት ተጋርጠዋል።
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከሰተው አደጋ መከራው እያናወዘን እንደ ጦስ ዶሮ በክፉ አዙሪት በኢኮኖሚ ችግር በጭንቅላታችን ተፈጥፍጠን የሚያነሳን የውጭ እጅ ለማግኝት በክፉ መቃተት ላይ በምንገኝበት በዚህ ክፉ ሰዓት፣ ዳግም ከማንወጣበት ሌላ ማጥ ለመዘፈቅ እየተንደረደርን እንገኛለን።
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች መካከል ግጭቱ ብሶ ወደ ጦርነት ከተገባ እመኑኝ እንዳለፉት ችግሮች በቀላሉ ማገገም አይደለም ተመልሶ አገር መሆን የማይታሰብ ይሆናል። በጭራሽ አሸናፊ የሌለውና በቀላሉ የማይቋጭ መሆኑን ለመገመት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው። ምናልባት ከዚህ ዕልቂት ዕድለኛ ሆነህ ከተረፍክ ቀና ስትል የምታየው ሰላም አስከባሪ በሚል ስም በገዛ አገርህ ከዚህ አትለፍ የሚል ቋንቋው የማይሰማ ወይ ነጭ ወይ ጥቁር ወታደር ነው።
በእርግጥ በአገራችን ከእኔ የሚሻሉ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪዎችና ሽማግሌዎች፣ እንዲሁም በሳልና አገር ወዳድ ፖለቲከኞች፣ ብሎም ለህሊናችሁ የምትኖሩ አርቆ አስተዋዮች እንዳላችሁ ጥርጥር የለኝም። ቢያንስ ያለፈው ተሞክሮም ቢሆን የአሁኑ ዳር ዳር ነገሮች ያለ መከሰት ዕድላቸው ተመናምኖ ባለበት በዚህ ሰዓት፣ ዝምታው አገራችን ዓይናችን እያየ ትውደም ብሎ እንደ መስማማት የሚቆጠር መሆኑን ቢያንስ ከሁለቱም ክልሎች ምሁራን፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት መሪዎችና ከባለ ህሊናዎች የሚሰወራቸው ነው ብሎ መገመት ይከብዳል።
ወገኔ ዝምታው እስከ መቼ ነው? መንግሥት ከሁሉም የበለጠ ኃላፊነት ስለተሸከመ እባክህ ይህ ድርጊት አገር ያጠፋል፣ እባክህ ይህ አካሄድ አገር ይጎዳል ብሎ መጋፈጥ፣ ፊት ለፊት መሞገትና ከአባባሽ ድርጊቶች እንዲመለስ የማድረግ ኃላፊነት የእኛ አይደለምን? ወገኖቼ አሁን እንደ ልብ መንግሥትን የምንሳደበው ቢያንስ ተረጋግተን ቁጭ ያልንበት ሥፍራ ስላለን ነው። ነገር ግን በዚሁ መልኩ መቀጠል የምንችል ይመስላችኋል? የተሳሳተውን ተው የሚል እንዴት ጠፋ? የሚሰማስ አካል እንዴት ጠፋ?!
እባካችሁ የሚመለከታችሁ አካላት የጦርነት ነጋሪት መጎሰሙ አገር ያሳጣል እንጂ አይገነባም። ስለዚህ እባካችሁ ስለእግዚአብሔር ብላችሁ ዳግም የንፁኃን ደም አይፍሰስ። እስካሁን የፈሰሰው ብቻ ለአገራችን የመርገም እንጂ የበረከት አይደለም።
እባካችሁ የተማርን ነን ባዮች ምሁራን፣ እባካችሁ የአገር ሽማግሌዎች ነን ባዮች፣ እባካችሁ የሃይማኖት መሪዎች ነን ባዮች፣ እባካችሁ ባለመልካም ህሊና የሆናችሁ ፖለቲከኞችና አገር ወዳድ ዜጎች “የጨው ገደል ሲናድ ብልጥ ያለቅሳል ሞኝ ይስቃል” ነውና የተራራቁትን አቀራርቡ።
በእርግጥ ችግር መፍታት፣ ማቀራረብም ይሁን ማስማማት ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ዋጋም እንደሚያስከፍል አውቃለሁ። ነገር ግን እስካሁን ኢትዮጵያ እዚህ የደረሰችው ብዙ ዋጋ ተከፍሎ ነው። ዋጋውን የከፈሉት ደግሞ የደሃ ልጆች ደም ገብረው ነው። አሁን እንኳ ተራው የእናንተ ይሁንና እስኪ ዋጋ ክፈሉ።
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት ሥላሴ የሥነ መለኮት ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡