Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

በመኖሪያ አካባቢያችን እጅግ በጣም የተከበሩ ትልቅ ሰው በቅርቡ ከዚህ ዓለም በመለየታቸው ሐዘን ላይ ከረምን፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚ የሆነ ሰው ሲሞት ሐዘኑ ምሬት ይፈጥራል፡፡ የሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ነፍሱን ይማረውና ‹‹ሞት እንኳ ጨክኖ ወስዶ ከሚያስቀረው ምናለ ደጋጉን ዳግመኛ ቢፈጥረው…›› የሚለው ዘመን ተሻጋሪ ዘፈኑ በዚህ ጊዜ ጎልቶ ይታወሳል፡፡ እኚህ በአካባቢያችን ተወዳዳሪ የሌለው ሰብዕና የነበራቸው ሟች መምህራችን፣ መካሪያችን፣ አስታራቂያችንና ለክፉ ጊዜ ደራሻችን ነበሩ፡፡ ከ1979 ዓ.ም. ጀምሮ የመሠረትነውን ዕድራችንን በሊቀመንበርነት እስከ ዕለተ ሞታቸው ከመምራታቸውም በላይ ታታሪነትን፣ አርዓያነትን፣ ታማኝነትንና ክብርን እንድንማርበት አድርገውናል፡፡ ከሐሜት፣ ከአሉባልታና ከከንቱ ወሬ ርቀን ልጆቻችንን በመልካም ሥነ ምግባር እንድናሳድግና ኑሯችንን እንድናሻሽል በእጅጉ ረድተውናል፡፡

ካለፈው ታኅሳስ ወር ወዲህ ለሞት ያበቃቸው ሕመም አልጋ ላይ ቢጥላቸውም፣ የአካባቢያችን ሰዎች ከአዳር በስተቀር ዘወትር እሳቸውን ስናስታምም ነበርን፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ እኚህን የትልቅ ሰብዕና መገለጫ የሆኑ መምህራችንን ውለታ በእዚህ እንኳን እንመልስ በሚል ነበር፡፡ እሳቸው ከእኛ የሚፈልጉት አንዳችም ዕርዳታ ባለመኖሩ የእኛ ተግባር ሕመሙ እንዳይሰማቸው አብረን መዋልና ማምሸት ነው፡፡ ይህንንም በፈረቃ ተወጥተነዋል፡፡ በዚህ ጊዜ እሳቸው እኛን ስለአገር፣ ወገንና በአጠቃላይ ስለሰው ልጆች ፍቅር እያስተማሩን በሰላም ይህችን ምድር በ70 ዓመታቸው ተሰናበቱ፡፡

ሕልፈታቸው ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ ከሕፃን እስከ አዋቂ ለእኚህ አንጋፋ አባታችን አንብተዋል፡፡ ቤተሰብና ባዕድን መለየት እስኪያቅት ድረስ ሐዘኑን በጋራ ተወጣነው፡፡ አስከሬናቸውን በወጉና በሥርዓቱ መሠረት ለግብዓተ መሬት አብቅተን አንድ ሳምንት ሐዘን ተቀመጥን፡፡ እኚህን የመሰሉ ታላቅ ሰው ጥለውልን ያለፉት ሰብዓዊነት እኛ ወዳጆቻቸውን በጥልቅ ስላስተሳሰረን ከቤተሰቦቻቸውና ከዘመዶቻቸው ጋር ሆነን በታላቅ አርምሞ አሰብናቸው፡፡

በዕውቀት ዘርፍ አንድ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት ከያዛቸው ድርሳናት የበለጠ የመጠቁ ባለፀጋ ናቸው፡፡ በቋንቋ፣ በታሪክ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሕክምና፣ በባህል፣ ወዘተ. ዕውቀቶች አካብተዋል፡፡ ከሕፃኑ ጋር ሕፃን፣ ከወጣቱ ጋር ወጣት፣ ከጎልማሳው ጋር ጎልማሳ፣ ከአዛውንቱ ጋር አዛውንት የመሆን ችሎታቸው ተደናቂ ነበር፡፡ ያላነበቡትና የማያውቁት የዕውቀት ዘርፍ የለም ማለት ይቻላል፡፡ እሳቸው ሁሉንም ነገር ነበሩ ቢባል የተጋነነ አይደለም፡፡

ሐዘን ላይ ተቀምጠን ከድሮ ጀምሮ የሚያውቋቸው ሰው ከደሴ ይመጣሉ፡፡ እንደ ደንቡ አልቅሰው ካስለቀሱን በኋላ ተረጋግተን ጨዋታ እንጀምራለን፡፡ እኚህ ከደሴ የመጡ ሰው ጨዋታ አዋቂና የሚገርም የማስታወስ ችሎታ ስለነበራቸው ስለእኚህ የተከበሩ ሰው እንዲህ ይነግሩን ጀመር፡፡

‹‹ያኔ ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ተመርቀን በአጋጣሚ ሁለታችንም አዲስ አበባ ተመደብን፡፡ በአንድ ጊዜ የትምህርት ቤት መምህራን፣ ሠራተኞችና ተማሪዎች የዘመድ ያህል ቀረቡት፡፡ ለቸገራቸው ካለው ላይ ይሰጣል፡፡ ባይኖረው እንኳ ተበድሮም ይሰጣል፡፡ የደከመ ተማሪን በዕረፍት ጊዜው ሳይቀር እያስጠና ለውጤት ያበቃል፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የተለያዩ የስፖርት ውድድሮችን አስጀምሮ ግቢውን ነፍስ ዘራበት፡፡ የስካውት፣ የበጎ አድራጎት፣ የእርሻና የሥነ ጽሑፍ ክበባት መሥርቶ ትምህርት ቤቱን ዝነኛ አደረገው፡፡ በእሱ ታዋቂነትና ተደናቂ እንቅስቃሴ የቀኑ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ጠርተውት ቀደም ቀደም ማለቱን እንዲያቆም ካልሆነ እንደሚያሰናብቱት ሲነግሩት፣ ‘ይቅርታ ጌታዬ በእዚህ ደስ በሚል ተግባር ሊኮሩና ደስ ሊልዎት ይገባል እንጂ ለምን ይበሳጫሉ? እኔ እኮ ነገ ስኮላርሺፕ አግኝቼ እሄዳለሁ፡፡ እርስዎ ግን ሥራውን የራስዎ አድርገው ይምሩን ያኔ ውጤቱን ያዩታል፤’ ሲላቸው ደነገጡ፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ እሳቸውም ያለሱ አልሆንላቸው ይል ጀመር …›› እያሉ ሲነግሩን አስገረሙን፡፡

እኚህ ትልቅ ሰው አሜሪካ ሄደው ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተምረው ሲመለሱ ደርግ አብዮቱን ቀልብሶ ሥልጣኑ ላይ ጉብ ብሏል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ተመድበው ሥርዓተ ትምህርት መምርያ ውስጥ ሲሠሩ በነበረው ሁኔታ ያዝኑና በወቅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለነበሩ ሰው ምክር ያቀርባሉ፡፡ እኚህ የደሴ ሰው እንደነገሩን ወታደር አገር መጠበቅ እንጂ መምራት የለበትም፡፡ ስለዚህ ይህንን ሐሳብ ለወታደሮቹ አቅርበው አገሪቱን ከደም መፋሰስ እንዲታደጉ ይጠይቁዋቸዋል፡፡ ይህን ሐሳብ ባቀረቡ በሁለተኛው ቀን በወታደሮች ተወስደው ማዕከላዊ ምርመራ ይታሰራሉ፡፡ እዚያ ሲገረፉና ሲሰቃዩ ከከረሙ በኋላ ዳኛ ፊት ሳይቀርቡ አሥር ዓመት ተፈርዶባቸው ወደ ከርቸሌ ይላካሉ፡፡ ከርቸሌ ገብተው በወቅቱ በተከፈተው ትምህርት ቤት ውስጥ ለሰባት ዓመት ያስተምራሉ፡፡ እሳቸው ያስተማሩዋቸው በርካቶች ዛሬ ባለዶክትሬት ዲግሪ ናቸው አሉን፡፡

‹‹ለመሆኑ በዚህ ሁኔታ ምን ይሰማቸው ነበር?›› በማለት እኔ ለደሴው ሰው ጥያቄ አቀረብኩላቸው፡፡ ‹‹ምን ይሰማዋል ብለህ ነው? እሱ እንደሆን አንድም ቀን እንዲህ ሆንኩኝ ብሎ አያውቅም፡፡ ሰባት ዓመት ከርቸሌ እስራቱን ጠጥቶ ሲወጣ ምን እንዳለ ታውቃላችሁ? ‘እነዚያ ለነፃነት የታገሉ ወጣቶች በጭካኔ በየፈፋው ተገድለው ተጥለው መላ አገሪቷ ሐዘን ላይ ወድቃ የእኔ ጉዳይማ የሽርሽር ያህል ነው’ ብሎ አሾፈብን፤›› አሉን፡፡

አዎ! እሳቸው ሁሌም ያሳስባቸው የነበረው የአገሪቷና የሕዝቧ ዕጣ ፈንታ እንጂ የራሳቸው ጉዳይ አልነበረም፡፡ ‹‹እኔ እንዲህ አድርጌ፣ እኛ እንዲህ አድርገን፣ እኔ… እኛ…›› የሚባለውን የግልና የቡድን ፉከራ ወይም ሽለላ ሲሰሙ ‹‹ወይ ከንቱነት …›› እያሉ ነበር የሚያልፉት፡፡ በመሞቻቸው ሰሞን፣ ‹‹አደራ ከግል ጥቅም ባሻገር የወደፊቱን ትውልድ ጥቅም አሸጋግራችሁ እዩ እንጂ፣ ከንቱ ውዳሴና ዝና ፍለጋ ውስጥ አትግቡ…›› ያሉን ትዝ አለኝ፡፡ እኔም ይህንን አባባል ስለወደድኩላቸው ለእናንተ እንዲህ አደረስኩት፡፡

(ሳምሶን ዓይናለም፣ ከብሥራተ ገብርኤል) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...