Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትእየታደሱ ያሉ ስታዲየሞችና የካፍ ምልከታ

እየታደሱ ያሉ ስታዲየሞችና የካፍ ምልከታ

ቀን:

ኢትዮጵያ ማንኛውንም ዓለም አቀፍ እግር ኳስ እንዳታስተናግድ ከታገደች ሁለት ዓመታትን ተሻግራለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመደበኛው አኅጉራዊ ውድድር ዝግጅት ከማድረጉ በላይ ‹‹ጨዋታውን የሚያደርግበት አገር የበለጠ የመለየት ሥራ ላይ ሲጠመድ መመልከት ተለምዷል፡፡  

ቀድሞ ‹‹ስደተኛው ብሔራዊ ቡድን›› የሚል ቅፅል ስም የተሰጠው የዋሊያዎች ስብስብ፣ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን በሞሮኮ በተደጋጋሚ ማድረጉን ተከትሎ እንደ ሁለተኛ አገሩ ተደርጎ ተቆጥሯል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የባህር ዳርና ዕድሜ ጠገቡን የአዲስ አበባ ስታዲየም መሠረታዊ የስታዲየም ደረጃዎችን ባለማሟላታቸው፣ ማንኛውንም የእግር ኳስ ውድድሮች እንዳያከናውኑ ማገዱ ይታወሳል፡፡ በተሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት የባህር ዳር ስታዲየም የመጀመርያ ምዕራፍ ዕድሳት አጠናቆ የካፍ የግምገማ ቡድን ምልከታ ቢያደርግም፣ ስታዲየሙ ሙሉ በሙሉ መሥፈርቶቹን ባለማሟላቱ ሌላ ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡

የመጀመርያውን ምዕራፍ ምልከታ ተከትሎ በቅርቡ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ተጨማሪ በጀት በመመደብ ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ መጀመሩን ይፋ አድርጎ ወደ ዕድሳቱ ከገባ ወራት ተቆጥረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከሁለት ዓመታት በፊት ዕድሳቱን የጀመረው የአዲስ አበባ ስታዲየም የመጀመርያውን ምዕራፍ ቢያጋምስም፣ የሁለተኛ ምዕራፍ ዕድሳትን ባለመጠናቀቁ ግንባታው ዳግም ተራዝሟል፡፡

የግንባታውን መንቀራፈፍ አንድም ከዲዛይን ችግር እንዲሁም ከበጀት እጥረት እንደሆነ ሲነሳ የከረመ ሲሆን፣ በቅርቡ ሁለቱም ችግሮቹ ተፈትተው ዕድሳቱ በመጠናቀቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ምንም እንኳን በግንባታው ሒደት  የተስተዋሉት የዲዛይንና የበጀት ችግር መፈታታቸው ቢነገርም፣ የዕድሳቱ ጥራትና ካፍ ያስቀመጣቸውን መሥፈርቶች በአግባቡ ተመልክቶ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ካፍ ከዚህ ቀደም በርካታ የአፍሪካ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የቻለውን የባህር ዳር ስታዲየም ሲያግድ፣ ስታዲየሙ ሰባት መሠረታዊ ደረጃዎችን ማሟላት እንደተሳነው መግለጹ ይታወሳል፡፡

ይህም ከስታዲየሙ ግዙፍነትና ግንባታ አንፃር ጥራትና ደረጃውን ግምት ውስጥ ሳይከት የተገነባ እንደሆነ ተጠቅሶ ነበር፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ የተገነቡ ስታዲየሞች በርካታ ዝርዝር ደረጃዎችን፣ እንዲሁም የካፍ መሥፈርቶችን ጠብቀው ከመገንባት ይልቅ፣ ሜዳው ላይ ብቻ የማተኮር አባዜ እንዳለባቸው የሚያወሱ አሉ፡፡

ካፍ በቂ የልምምድ ሥፍራ፣ ጥራቱን የጠበቀ ሳር፣ የሕክምና ክፍል፣ የተጫዋች ልብስ መቀየሪያ፣ የሚዲያ ሥፍራ፣ ቪአይፒና ንፁህ የመፀዳጃ ሥፍራ  በትኩረት ከሚመለከታቸው ደረጃዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የባህር ዳርና የአዲስ አበባ ስታዲየሞችን ጨምሮ ግንባታው እየተጠናቀቀ የሚገኘው የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም ሌላው አማራጭ ሆኖ ቀርቧል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ አማካይነት እየተገነባ የሚገኘው የአቃቂ ቃሊቲ ስታዲየም የካፍ ደረጃን ለማሟላት ዲዛይኑ እንደገና ተጠንቶ፣ በ688 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ነው፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ስታዲየሙ የካፍ ደረጃን ጠብቆ እየተገነባ መሆኑንና አለመሆኑን በካፍ የክለብ ላይሰንሲንግ ባለሙያ የመጀመርያው ምልከታ ተደርጎበታል፡፡

አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየምና የአቃቂ ስታዲየም የካፍ መሥፈርቶችን ያሟሉ ሆነው እንዲጠናቀቁ የቅርብ ክትትል እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዘርፉ ዋና ተቆጣጣሪ የሆነው የካፍ ክለብ ላይሰንስ ዲፓርትመንት ኃላፊ የሆኑት መሐመድ ሲዳትን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማድረግ ስታዲየሞቹን እንዲጎበኙ ማድረጉን አስታውቋል።

በጉብኝት መርሐ ግብሩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መስፍን ቸርነት (አምባሳደር)፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የክለብ ላይሰንሲንግ መምርያ ኃላፊ አቶ አምኃ ተስፋዬና የግንባታ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተገኝተዋል።

በቅድሚያ የአዲስ አበባ ስታዲየምን የተመለከቱት መሐመድ በጉብኝታቸው የስታዲየሙ ዕድሳት በጥሩ ሁኔታ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ መስተካከል በሚገባቸው የተጫዋቾች መግቢያ፣ የመኪና ማቆሚያና የመልበሻ ክፍል ወለሎች ላይ ጥቆማ ከመስጠታቸው በተጨማሪ፣ የመጫወቻ ሜዳው በድጋሚ ማስተካከያ እንዲደረግበት ጠቁመዋል። የቦታ ሽግሽግ ሊደረግባቸው የሚገባቸው ክፍሎች እንዲሁም የሚዲያ ትሪቡን፣ ቪአይፒና ቪቪአይፒ ትሪቡኖች ላይም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም ጉብኝት የታዘቧቸውን ጉዳዮች በሚቀጥለው ሳምንት ሪፖርት እንደሚልኩ የገለጹት መሐመድ፣ የማጠናቀቂያ ሥራዎች በከፍተኛ ትኩረት እንዲሠሩና የተሰጡ የማስተካከያ ሐሳቦች ከተተገበሩ መሥፈርቱን ማሟላት እንደሚቻል ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡

በመቀጠል በግንባታ ላይ የሚገኘው የአቃቂ ስታዲየም ጉብኝት ተደርጎበታል። አስፈላጊ ክፍሎችና የተለያዩ አካላት መግቢያዎች የተመለከቱት የካፍ ተወካይ በግንባታ ላይ የሚገኝ ስታዲየም ከመሆኑ አንፃር፣ ለማስተካከያ ሥራ ምቹ መሆኑን ገልጸው የመልበሻ ክፍል፣ የሚዲያ፣ የቪአይፒና ቪቪአይፒ ትሪቡኖችና ሌሎች አስፈላጊ ክፍሎች ሊቀመጡባቸው የሚገባቸውን ሥፍራ ከማቀያየር ውጪ በጥሩ ሁኔታ መገንባታቸውን ተናግረዋል። የመጫወቻ ሜዳው ግንባታ ግን ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የዘርፉ ፈቃድ ባላቸው ኩባንያዎች እንዲገነባ መክረዋል።

በአጠቃላይ የተሠሩት መሠረታዊ ሥራዎች በቂ ጊዜና ትኩረት በመስጠት እንዲሁም ጥሩ ቁሳቁሶች በመጠቀም የማጠናቀቂያ ሥራዎች ማከናወን ከተቻለ የካፍን መመዘኛዎች በቀላሉ ማሟላት እንደሚቻል ገልጸዋል። በየሦስት ወሩ የዙም ውይይት በማድረግም የሥራ ሒደቱን እንደሚከታተሉ ማከላቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን በድረ ገጹ አሥፍሯል።

በቀጣይ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት ስታዲየሞች በተጨማሪ፣ የባህር ዳር ስታዲየም የካፍ የግምገማ ቡድን ይመለከተዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...