Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ሁለት ሚሊዮን ኢንተርፕራይዞች የመክሰም አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ 40 ባለሙያዎች ወደ ጀርመን ሊላኩ ነው

በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑና በተለያዩ ዘርፎች ከተሰማሩ የቢዝነስ ኢንተርፕራይዞች፣ አብዛኛዎቹ የመክሰም አደጋ እንደተጋረጠባቸውና ከዕለት ጉርስ ማለፍ እንደተሳናቸው ተገለጸ፡፡

በአመዛኙ የሚመሠረቱት ኢንተርፕራይዞች መንግሥት እንደሚያቀርብላቸው የፋይናንስ፣ የመሥሪያ፣ የመሸጫ ቦታና ድጋፍ የሚመመዘኑ ቢሆኑም፣ በርካቶቹ ግን የሰው ሕይወት የሚቀይሩ አለመሆናቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ካሉት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ኢንተርፕራይዞች መካከል 74 በመቶ የሚሆኑት ጥቃቅን፣ 18 በመቶ የሚሆኑት በአነስተኛ ደረጃ፣ ስድስት በመቶ የሚሆኑት በመካከለኛ ደረጃ፣ እንዲሁም ሁለት በመቶ ብቻ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ መሆናቸው የተገለጸው፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የስምንት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡

አቶ ንጉሡ እንደገለጹት፣ ከአነስተኛዎቹ ከፍተኛ ወደ የሚባሉት ኢንተርፕራይዞች ሲኬድ ቁጥራቸው እየሰፋና አቅማቸው እየጠነከረ ከመሄድ ይልቅ፣ ባሉበት እየከሰሙና ቁጥራቸው እያነሰ የዕለት ጉርስ ማግኛ ብቻ እየሆኑ መቅረት የኢንተርፕራይዞች መደበኛ ባህሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ ብዙዎቹ መክሰማቸው እንደ ተጨባጭ ችግር ቢታይም፣ ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ የሆኑና ተስፋ ሰጪ ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የእነዚህን ኢንተርፕራይዞች ቁመና ማሻሻል፣ አቅማቸውን መገንባትና በግብዓት አቅርቦት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ድጋፍ በማድረግ፣ ከመክሰምና ከመሞት እንዲድኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን ወደ ገበያ አቅርበው አትራፊና አሸናፊ እንዲሆኑ፣ መንግሥት እጃቸውን ይዞ ዳዴ ከሚሉበት በእግራቸው እንዲሄዱ የሚያስችል ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አቶ ንጉሡ አሳስበዋል፡፡

በአጠቃላይ ለኢንተርፕራይዞች የተመቸ አካባቢና ሁኔታ መፍጠር ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለ፣ ይህንን ለማስተካከል የኢንተርፕራይዞች ዕሳቤና ቁመና ለመቀየር የሚያስችል የኢንተርፕራይዝ ልማት የሚባል የመሥሪያ፣ የመንቀሳቀሻና የማሰባሰቢያ ቦታ እንዲሆን ተደርጎ ተቋቁሟል ብለዋል፡፡

ኢንተርፕራይዞች ወደ ሥራ እንዲገቡ ሊያደርግ የሚያስችል ፋይናንስ ለማቅረብ መንግሥት ዋስትና ወስዶ ከአቅራቢ አካላት አግኝተው ሥራቸውን በማንቀሳቀስ፣ ብድራቸውን የሚመልሱበትና ኪሳራ ቢመጣ እንኳ በመንግሥት በኩል መጋራት የሚቻልበት አሠራር እንዲኖር፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ለኢንተርፕራይዞች የሚሆን የዋስትና ማዕቀፍ ለመዘርጋት ጥናት ስለመጀመሩ ሚኒስትር ደኤታው አብራርተዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የስምንት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ በስምንት ወራት ውስጥ ለ2.6 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለሁለት ሚሊዮን ዜጎች መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ ወደ 3.8 ሚሊዮን ሥራ ፈላጊዎች ለመመዝገብ ታቅዶ ከስድስት ሚሊዮን በላይ መመዝገባቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ የተፈጠረው አጠቃላይ የሥራ ዕድል የአገልግሎት፣ የኢንዱስትሪ፣ የግብርና ዘርፎች እንደ ቅደም ተከተላቸው 41 በመቶ፣ 19.7 በመቶና 39.2 በመቶ ናቸው ብለዋል፡፡

አቶ ንጉሡ የሥራ ዕድል ፈጠራን አስመልከተው ሲያብራሩ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች የሚፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ዳቦ በልቶ ከማደር በላይ መሆን እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ ባለፉት ስድስት ወራት ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሥራ አጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአገር አቀፍ ደረጃ መፈጠር የቻለው 2.3 ሚሊዮን የሥራ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በስምንት ወራት ውስጥ በውጭ አገሮች የሥራ ሥምሪት ከ46 ሺሕ በላይ ዜጎች ወደ ሥራ መሰማራታቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በትንሹም ቢሆን የተወሰኑት የሠለጠኑ ናቸው ብለዋል፡፡

የመዳረሻ አገሮች እየሰፉ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ሙፈሪያት በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ እንዲሁም በእስያ ከአሥር አገሮች ጋር ንግግር መጀመሩንና በተወሰኑት ደግሞ ስምምነት እየተፈጸመ መሆኑን አክለዋል፡፡

በውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ለሠለጠኑ ኢትዮጵያውያን ጥሩ የሚባል ተስፋ እንዳለ የገለጹት ወ/ሮ ሙፈሪያት በኩዌት፣ በሊባኖስ፣ በባህሬን፣ በኦማን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በደቡብ ኮሪያ፣ በእስራኤል፣ በጀርመንና በሌሎች አገሮችም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ንግግር መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ከጀርመን የኮንስትራክሽን ተቋራጮች ፌደሬሽን ጋር ባደረገው ስምምነት 19 ዜጎች ከኦሮሚያ፣ 21 ደግሞ ከአዲስ አበባ በመምረጥ በሙከራ ደረጃ ለመላክ የጀርመንኛ ቋንቋ ሥልጠና እየወሰዱ እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች