Tuesday, September 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የጽንፈኝነት መጨረሻው ተያይዞ መውደቅ ነው!

ዓለም ከዕለት ወደ ዕለት እጅግ በተራቀቁ የቴክኖሎጂ ዕውቀቶች በከባድ ፍጥነት ወደፊት መግፋቱን እየቀጠለ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ዘመኑን በማይመጥኑና በታሪክ ተጠያቂ በሚያደርጉ ውዝግቦች ተጠምደን አገራችንን ወደ ገደል እየገፋናት ነው፡፡ በዕድገት ወደፊት የገፉትና ለማደግ የሚፍጨረጨሩ አገሮች ዜጎች ከዘመኑ አስደማሚ ቴክኖሎጂ ተቋዳሽ ለመሆን፣ በተለይ እጅግ የተራቀቀው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሲስተም ውጤት የሆኑ ግኝቶች ስለሚኖራቸው ጥቅምና ጉዳት ለማጤን፣ እንዲሁም ቢያንስ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በዓለም ላይ ሊከሰት ስለሚችለው መጠነ ሰፊ ለውጥ ከወዲሁ ዝግጅት ለማድረግ እየተጣደፉ ነው፡፡ እኛ ግን ከዕውቀቱም ሆነ ከማስተዋሉ አፈንግጠን ፋይዳ ቢስ በሆነው የብሔር ማንነት ስም በጽንፈኝነት እየተገፋፋን ነው፡፡ ሰብዓዊ ፍጡራንን ሊፈታተኑ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ አነጋጋሪ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ እኛ ከዓለም ጋር አብረን የማንኖርና የበረከቱም ሆነ የጥፋቱ ተቋዳሽ የማንሆን ይመስል በጽንፈኝነት ፖለቲካ ጠላትነትን እያባዛን ነው፡፡ ወትሮም ለሰከነ ንግግር፣ ድርድርና ዕርቅ የማይመቸው ጽንፈኛው የፖለቲካ ዓውዳችን አሁን ብሶበት አገር ማፍረሻ ቡልዶዘር እየሆነ ነው፡፡ ተያይዞ መጥፋት የተመረጠበት ጽንፈኝነት የወጣቶችን ተስፋ ጭምር እያጨለመ ነው፡፡   

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ዓውድ ንግግርም ሆነ ክርክር ከምክንያታዊነት እየራቀ በስሜታዊነት ሲወረር፣ ለሐሳብ ልዕልና መሰጠት ያለበት ሥፍራ እያደር እያዘቀዘቀ ሲሄድ፣ ተቀራርቦ በጋራ ችግሮች ላይ ከመወያየት ይልቅ መነቃቀፍና መሰዳደብ ድረስ ሲዘለቅና ሕዝብና አገር እየተረሱ ሥልጣን ላይ ብቻ ሲተኮር ከዴሞክራሲያዊ ዕሳቤዎች በመሸሽ ጽንፈኝነት ውስጥ መዘፈቁ ይቀጥላል፡፡ ጽንፈኝነት በባህሪው ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች ደንታ የሌለው፣ ለሕግ የበላይነት መስፈን ሳይሆን ሕገወጥነትን የሚያበረታታ፣ ለሐሳብ ነፃነት ጥብቅና ከሚቆም ለመድፈቅ የሚሽቀዳደም፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ መስፈን ሳይሆን ለቆመለት ጎራ የበላይነት መቀዳጀት ዕልቂትና ውድመት የሚያስከትሉ ግጭቶችን የሚቀሰቅስ፣ ለግልጽነትና ለተጠያቂነት መርህ የማይገዛና በአጠቃላይ ለመብትና ለነፃነት ጀርባውን የሚሰጥ አቋም የሚራመድበት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካው መንደር ውስጥ ከሚሳተፉ ዋና ተዋንያንና አጃቢዎቻቸው አብዛኞቹ፣ ለአገርና ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ፋይዳ ያለው አስተዋጽኦ ለማበርከት ፈቃደኛ አይመስሉም፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሆነው የሚያራምዱት ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ዓይነት አስተዛዛቢ ፖለቲካ ጽንፈኝነት እየተቀፈቀፈበት ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ አገር ሰላምና መረጋጋት እያጣች ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሎ ላይ ከተነሱ ጥያቄዎችና ከተሰጡ ምላሾች በመነሳት አንዳንድ ጉዳዮችን ስንቃኝ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማጠንጠኛዎች ከዋነኞቹ አሳሳቢ ጉዳዮች ይልቅ የተለመደው ማብቂያ የሌለው ንትርክ ላይ የባከነው ጊዜ ያሳዝናል፡፡ ይህ አሳዛኝ ክስተት በአንድ የምክር ቤት አባልና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄና ምላሽ ሳያበቃ፣ ኢትዮጵያ ምንም ችግር የሌለባት ይመስል በተለይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች የተስተዋለው ጽንፈኝነት ሊኖር በሚገባው ተስፋ ላይ አሉታዊነት አንፀባርቋል ቢባል የተጋነነ አይሆንም፡፡ ለምሳሌ በአሁኗ ኢትዮጵያ የሕዝባችን ዋነኛ ችግሮች የፀጥታ ሥጋት፣ የኑሮ ውድነትና የመሠረታዊ አገልግሎቶች መቆራረጥ ናቸው፡፡ በዚህ ላይ ከ20 ሚሊዮን በላይ ወገኖች የሚቀምሱት አጥተው የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ያለህ እያሉ ናቸው፡፡ የተዝረከረከውን ፖለቲካ ፈር አስይዞ ኢትዮጵያን የመሰለች በተፈጥሮ ሀብቶችና በወጣት የሥራ ኃይል የታደለች አገር በቅጡ ማሳደግ እየተቻለ፣ በማንነትና በሃይማኖት ጽንፈኝነት ውስጥ ተጀቡኖ አገር ማተራመስ የተመረጠ ይመስላል፡፡ ጽንፈኞች ተማሩም አልተማሩም የሚፈልጉትን ለማግኘት የንፁኃን ደም ከማፍሰስና የደሃ አገር ንብረት ከማውደም አይመለሱም፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሚፈለግባቸው ልክ የሚያረኩ ጥያቄዎችን ባያነሱም ለአገርና ለሕዝብ ሰላም፣ ደኅንነትና ለኑሮው በመጨነቅ ሥጋት ያዘሉ ወቅታዊ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ነበሩ፡፡ ከሥልጣን ትለቃለህ ወይስ አትለቅምና የተጠያቂነትና የኃላፊነት ጉንተላው ላይ ብዙዎች ትኩረት በማድረጋቸው፣ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ የሚያሳስባቸው ተወካዮች ጥያቄዎች ሜዳ ላይ የባከኑ ያህል የጽንፈኝነት ንትርኩ አላስታወሳቸውም፡፡ በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጤፍና መሰል የምግብ ግብዓቶች እንዳይገቡላቸው ተደርጎ ለዋጋ ንረት መጋለጣቸውን፣ ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ ሕጋዊ መብታቸውን መነፈጋቸውን፣ ለዓመታት ከኖሩበት ጎጆአቸው በሕገወጥነት ስም ተፈናቅለው የወደቁ ወገኖችን፣ ማንነትን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች ንፁኃን መገደላቸውንና ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን፣ ግለሰቦች በጠራራ ፀሐይ ከመንገድ እየታፈኑ መታገታቸውን፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆን ተብሎ ክፍፍል እንዲፈጠር መደረጉንና የመሳሰሉ ጉዳዮች ትኩረት አልተሰጣቸውም፡፡ በምክንያታዊነት የሚመራ የፖለቲካ ዓውድ ሳይኖር ሲቀር ደርዝ ያላቸው ንግግሮችም ሆኑ ክርክሮች ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ይልቁንም የጽንፈኝነት ፖለቲካ አራማጆች ዓውዱን ይቆጣጠሩና ከሐሳብ ይልቅ ግብግብ ላይ ይተኮራል፡፡  

ጽንፈኝነት ያለ ከልካይ እየተስፋፋ ያለው ሥልጣን ላይ ያሉትም ሆኑ ለሥልጣን የሚፎካከሩት፣ በኃላፊነት ስሜት የፖለቲካ ምኅዳሩን ሁሉንም ወገን በነፃነት አሳታፊ ለማድረግ የሚያስችል መደላድል ለመፍጠር ባለመቻላቸው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ምኅዳር ለመፍጠር ያን ያህል የሚያስቸግር ነገር ባይኖርም፣ በኢትዮጵያ ግን ከማንም በላይ የሥልጣን መንበሩን የተቆጣጠረው ኃይል ተግዳሮት በመፍጠር ተወዳዳሪ አልነበረውም፡፡ ይህ ሁነት በዚህ ዘመን ለተወሰነ ጊዜ የመሻሻል አዝማሚያ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ሲመዘን ተመልሶ ወደ ነበረበት በፍጥነት እየተመለሰ ነው፡፡ በተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩልም በጣም ጥቂት ከሚባሉት ውጪ፣ አብዛኞቹ ለፖለቲካ ምኅዳሩ መዘመንና መለወጥ ፋይዳ ቢስ ሆነዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሐሳብ ድርቅ መቶት የስድብና የዕርግማን መናኸሪያ ሆኗል፡፡ የደረጀ ሐሳብና ሙግት ሲጠፋ ደግሞ የድንቁርና ካባ የለበሰው ጽንፈኝነት በየስርቻው ይባዛል፡፡ በተለያዩ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችንና መፍትሔዎችን ማመንጨት የሚችሉ እየተገፉ፣ ለዕልቂትና ለውድመት የሚያመቻቹ ቅስቀሳዎች ከየጎራው ይደመጣሉ፡፡

ብዙዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ዓይነት ርዕዮተ ዓለም እንደሚያራምዱ በግልጽ አይታወቅም፡፡ በደፈናው ለዚህኛው ወይም ለዚያኛው ብሔር ወይም ማኅበረሰብ እታገላለሁ ከማለት ውጪ፣ ማንን ማኅበራዊ መሠረታቸው እንዳደረጉ አይታወቅም፡፡ በርዕዮተ ዓለም ላይ ሊመሠረቱ የሚገባቸው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ፣ የዲፕሎማሲና የሌሎች ዓበይት ጉዳዮች ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን የያዘ ማኒፌስቶ ያላቸው በሚያሳዝን ሁኔታ ከአንድ እጅ ጣት ያንሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ግን ከ100 በላይ ፓርቲዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ከሙያ ወይም ከሲቪል ማኅበራት ያነሰ ቁመና ይዘው፣ ለአገርና ለሕዝብ ዕድገት የሚያግዙ የፖሊሲ አማራጮችን ማቅረብ ተስኗቸዋል፡፡ ብዙዎቹ የአባላቶቻቸውንና የደጋፊዎቻቸውን ብዛት አስታውቁ ሲባሉ አያውቁትም፡፡ የረባ ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ በመቸገራቸውም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ማግኘት አልቻሉም፡፡ ገዥው ፓርቲም ቢሆን በውስጡ የሐሳብና የተግባር አንድነት በማጣቱ ምክንያት፣ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ቅርንጫፎቹ መካከል የሚስተዋለው ሽኩቻ ብዙ የሚናገረው አለው፡፡ በየጊዜው ችግሩን እያድበሰበሰ የአንድነት መግለጫዎችን ቢያወጣም፣ የሻከሩ ልቦች ግን ያለውን በጽንፈኝነት የታጀበ ቅራኔ መደበቅ አልቻሉም፡፡ የጽንፈኝነት መጨረሻው ተያይዞ መውደቅ እንደሆነ ይታወቅ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...