Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ያቀረበው ሪፖርት በሚገባ መፈተሽ አለበት ተባለ

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ያቀረበው ሪፖርት በሚገባ መፈተሽ አለበት ተባለ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ባለፉት ስድስት ወራት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ፣ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ያቀረበው ሪፖርት በሚገባ መፈተሽ አለበት ተባለ፡፡

ይህ የተገለጸው የአዲስ አበበ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የስድስት ወራት ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡

‹‹የቀረበው ሪፖርት መቶ በመቶና ከዚያ በላይ ሆነው የተመዘገቡ አፈጻጸሞች በስፋት የታዩበት ሲሆን፣ ቅድመ መከላከል ላይ ያልተከናወኑ ሥራዎች ሪፖርቱን አሳብጠውታል፤›› ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሰላምና ፀጥታ ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡

መቶና ከዚያ በላይ ሆነው የቀረቡ አፈጻጸሞች ከየት እንደመጡ ወይም ሌላ ነገር ካለ መፈተሽ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ቤት አፈረስንና ንብረት ወረስን ከሚለው ቁጥር በላይ ቅድመ መከላከል ላይ ተጨባጭ ውጤቶችን በሪፖርት ላይ ማሳየት ተገቢ ነው፤›› ያሉት አቶ ሙሉነህ በቀጣይ ሪፖርት ይህ ይታሰብበት በማለት አሳስበዋል፡፡

በደንብ ማስከበርና በባለድርሻ አካላት መካከል መገፋፋት የሚፈጥሩ ሁኔታዎችን ማስቀረት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች እየተዘጋጁ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

‹‹ደንቦች በሥራችን ላይ ጣልቃ እየገቡብን ነው›› በማለት ቅሬታ የሚያቀርቡ አካላት እንዳሉ፣ በሌላ በኩል ‹‹ሥራው አይመለከተኝም የደንቦች ነው›› ብለው ጥግ ይዘው የሚቆሙ አካላት መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

እየተዘጋጀ ያለው የሕግ ማዕቀፍም እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

አቶ ሙሉነህ እንዳሉት በትልልቅ ሆቴሎች ሐሺሽና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን ከመጠቀም ባሻገር፣ ግብረ ሰዶም ይፈጸምባቸዋል የሚባሉ ሆቴሎችን ከምክር ቤቱ አባላት ጋር በመሆን ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ የድርጊቱ ተዋንያን እነ ማን ናቸው የሚለውን ለይቶ ማወቅ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ከመሬት ዕግድ ጋር በተያያዘ ትልቅ ችግር እየገጠመን ነው፤›› ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ኃላፊ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ናቸው፡፡ ‹‹ከፍትሕ ቢሮ ጋር በቅርበት እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን የዕግድ ጉዳይ ትልቅ ችግር እየፈጠረብን ነው፤›› ብለዋል፡፡  

ባለሥልጣኑ ባዶ ቦታዎችን ለይቶ እንደሚያውቃቸውና ጥበቃ እንደሚያደርግባቸው፣ ነገር ግን በሌሊት ከየት እንደመጣ ባልታወቀ አካል ታጥረውና ተከልለው እንደሚገኙ ሻለቃ ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡

ጨለማን ተገን አድርገው ለታጠሩ መሬቶች የፍትሕ ቢሮ ዕግድ የሚያወጣባቸው ቀድመው እንደተያዙ በማድረግ በመሆኑ፣ ዕርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ መሆኑን ሻለቃ ዘሪሁን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ለግንባታ ተብሎ በ2013 ዓ.ም. ለተሰጠ የመሬት ካርታ እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ የግንባታ ፈቃድ ሳያወጡ መሬቱን ከልለው የሚገኙ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በወረዳና በክፍለ ከተማ ያሉ አካላት ምን ያህል አገራዊና ከተማዊ ዕሳቤ ኖሯቸው ይሠራሉ የሚለው አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹በቀጣይ ሁላችንም በጋራ መፈተሽ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

በልመና የሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ ቀጣይነት ባለው አሠራር ከመንገድ ላይ አለማንሳትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች በመድረኩ ተነስቷል፡፡

ለከተማ ግብርና ተብለው የተሰጡ ቦታዎች ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ ሲውሉ የሚመለከተው አካል በቸልታ እያለፋቸው መሆኑንና መስተካከል እንዳለበትም በውይይቱ ወቅት ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ከ250 ሺሕ በላይ በሚሆኑ ሕገወጥ ድርጊቶች ላይ ባለሥልጣኑ ዕርምጃ መውሰዱን በሪፖርቱ ገልጿል፡፡

ከእነዚህ መካከል ከ35 ሺሕ በላይ የጎዳና ላይ ንግድ፣ ከአምስት ሺሕ በላይ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣ እንዲሁም 1,727 አዋኪ ድርጊቶች ላይ መሆኑን ባለሥልጣኑ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

መቶ በመቶና ከዚያ በላይ ተከናውነዋል ከተባሉ ተግባራት ውስጥ ሕገወጥ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን መቆጣጠር፣ የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎችን ማስነሳትና ወደ መጡባቸው አካባቢዎች መመለስ፣ እንዲሁም በተለያዩ አዋኪ ድርጊቶች ላይ ዕርምጃ መውሰድ የሚሉትና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

ባለሥልጣኑ በግማሽ ዓመቱ ከደንብ ተላላፊዎች ከተወረሱ ዕቃዎች 4,260,000 ብር ማስገኘቱን፣ እንዲሁም በቅጣት ከ11 ሚሊዮን ብር ባለይ መሰብሰቡንና በአጠቃላይ ከ15,200,000 ብር በላይ ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ ማድረጉን በሪፖርቱ ገልጿል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...