Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ አዋጅ በምክር ቤቱ ውስጥ የተመራበት ሒደት ቅሬታ ፈጠረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ማሻሻያ አዋጁ ጤናን የሚጎዱ ምርቶችን ያበረታታል የሚል ተቃውሞ አስነሳ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊፀድቅ የተዘጋጀው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፣ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የተመራበት ሒደት፣ ሁለት ቋሚ ኮሚቴዎችን አከራከረ፡፡ የአንደኛው ቋሚ ኮሚቴ አባላትም ‹‹በተገቢው መንገድ ሐሳብ እንዳንሰጥበት አልተደረገም›› በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በምክር ቤቱ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቶ ግብዓት እንዲታከልበት ከተመራ በኋላ የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ለሁለቱም ቋሚ ኮሚቴዎች አለመመራቱ ስህተት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አዋጁ ሕዝብ ውይይት እንዲያካሂድበት የተመራለት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋዊ የሕዝብ ውይይት አካሂዶ ነበር፡፡ በውይይቱም የሚመለከታቸው አካላት ተካፍለው የነበረ ሲሆን፣ በአብዛኛው መንግሥት በ2012 ዓ.ም. ጥሎት የነበረው የኤክሳይስ ታክስ ጤናን የሚጎዳ ምርቶች ላይ አጥብቆ የነበረውን ሕግ እንዲያላላ የሚያደርግና በማኅበረሰቡ ጤና አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ሲሉ የተሻሻለውን አዋጅ ተችተዋል፡፡

ጤና ላይ የሚሠሩ የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት፣ ግለሰብ የጤናና የሕግ አማካሪዎች፣ ምርቶቹን የሚያመርቱ ድርጅቶችና ማኅበራት፣ እንዲሁም በርካታ የሚመለከታቸው አካላት በስብሰባ ተካፍለው ስለማሻሻያውና አጠቃላይ ኤክሳይስ ታክስን በሚመለከት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ አዋጁን ያረቀቀው የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎችም በሥፍራው በመገኘት የማሻሻያው አስፈላጊነት ላይ ሰፊ ማብራሪያና ለተሰነዘሩት አስተያየቶችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የጤና ዘርፉ ንዑስ ኮሚቴ አባል የሆኑና ከሌላ መድረክ ተሳትፎ በኋላ በዚህኛው መድረክ መሀል ላይ የተገኙ ሦስት አባላት በስብሰባው ላይ ካነሷቸው አስተያየቶች መካከለ፣ የአዋጁ ማሻሻያ ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ አዋጁ ወደእነሱ ቋሚ ኮሚት ሳይመራ ቀርቶ መድረኩን ላዘጋጀው ኮሚቴ ብቻ መመራቱንም ተቃውመው አሁንም ተቀራርበው መሥራት እንዳልባቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹የአካሄድ ይሁን የሥነ ሥርዓት ችግር አላውቅም፡፡ ከዚህ በፊት የሕግ መፃረር ያለባቸው የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓቶችን ምክር ቤቱ ለሁለት ወይም ለሦስት ቋሚ ኮሚቴዎች ይመራ ነበር፤›› ሲሉ ያስታወሱት የንዑስ ኮሚቴው አባል የሆኑት የጤና ባለሙያው አብዱልሰመድ ሁሴን (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ‹‹እንደ ምክር ቤት ተወካይ አብረን ብንሆንም ሲመራ ግን ለሁለታችንም መመራት ነበረበት፤›› ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡ አብሮ የመሥራትና የመቀራረብ ዕድሉ አሁንም እንዳለ የተናገሩት አብዱልሰመድ (ዶ/ር)፣ እንደ ጠቃሚ ምክር ብቻ ሳይሆን እንደ ግዴታም ሊታይ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

አባሉ አክለው ሲገልጹም፣ ከአዋጁ አካሄድ ሥነ ሥርዓት ችግር በተጨማሪ የአዋጁ ይዘት ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለውን የአሥር ዓመት የጤና ስትራቴጂ የማያግዝና ‹‹በመንግሥት የዜጎችን ጤናማ ሕይወት የመምራት ኃላፊነት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የጤና ባለሙያው የምክር ቤት አባልና የጤና ዘርፉ ንዑስ ኮሚቴ የሆኑት አብዱልሰመድ፣ በተጨማሪ እንዳስረዱት፣ እንዲፀድቅ የቀረበው ማሻሻያ ለኅብረተሰቡ ጤና ሥጋት ሆኖ እንዳገኙት፣ ከበፊቱ አዋጅ ጋር ሲነጻጸርም የሕዝብን ጤና ይጠብቃል ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአገሪቱ የጤና ሥርዓት ላይ መዶሻ እንደወረደ›› እንደሚቆጥሩትም ገልጸዋል፡፡ በሌላ ተጨማሪ የሕዝብ መድረክ ላይም ቢሆን እርሳቸው ባሉበት ቋሚ ኮሚቴ ተዘጋጅቶ አስተያየት እንዲሰበስብ የጠየቁት አብዱልሰመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ቁጭ ብለን መነጋገር አለብን የሚል እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

በጤና ዘርፉ ላይ የሚሠራውን ቋሚ ኮሚቴና በርካታ የሲቪክ ማኅበራትን ጠንካራ አስተያየት እንዲሰጡ የገፋቸው የአዋጁ ማሻሻያ፣ ጤናን የሚጎዱ ምርቶች ላይ የታሪፍ ቅናሽ በመደረጉ ሲሆን፣ ይህም ምርቶቹን መጠቀም የበለጠ ያበረታታል በሚል ዕሳቤ ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም. አዋጁ ሲፀድቅ ማኅበራዊ ሕይወትንና ጤና ላይ ጉዳት ያስከትላሉ የሚባሉት ምርቶችን ፍጆታ እንዲቀንስ በመታቀዱ ነበር፡፡

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ጤና ላይ የሚሠራው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ላነሷቸው የአሠራር ችግር ምላሸቸውን ሰጥተዋል፡፡ ቅሬታ ያቀረቡት የቋሚ ኮሚቴ አባላት የረቂቅ አዋጁ ቅጂ ከሁለት ወር በፊት ደርሷቸው እንደበረና፣ በቅጂው መነሻ መሠረት ተዘጋጅተው ያላቸውን አስተያየት በጽሑፍ ማቅረብ እንደነበረባቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹አዋጁ ቶሎ እንዲፀድቅ ይፈልጋል፡፡ አጠቃላይ አስተያየት ከመስጠት አሁንም ቁጭ ብላችሁ ምከሩ፣ የሚሻሻሉትንና የሚያመጡትን ጉዳቶች ለዩና ከእኛ ኮሚቴ ጋር እንነጋገር፤›› በማለት ለተነሳው ቅሬታ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ እንደሚጠቁመው ተደራራቢ የኤክሳይስ ታክስ የሚከፈልባቸው ምርቶች ላይ የታሪፉ ምጣኔዎች ተሻሽለዋል፡፡ እነዚህ ምርቶችም ማኅበራዊ ኑሮ ላይ ችግር ያስከትላሉ የተባሉት የአልኮል፣ ትንባሆና ስኳር ምርቶች ናቸው፡፡

ምንም እንኳን የመጨረሻ ደረጃ ምርቶቹ ላይ የሚከፈለው የኤክሳይስ ታክስ መጠን ላይ ማሻሻያ ባይደረግም፣ ለምርቶቹ ማምረቻ የሚውሉት ግብዓቶች ላይ ግን ከፍተኛ ቅናሽ ተደርጓል፡፡ በዚህ የታክስ መደራረብ በተወዳዳሪነታቸው ላይ ጫና ይፈጥርባቸው እንደነበረና አሁን በማሻሻያው ተወዳዳሪነታቸው እንደሚጨምር ረቂቅ ሰነዱ ይገልጻል፡፡

የአልኮል ምርቶች ለግብዓት የሚጠቀሙበት ንፁህ አልኮል ላይ 60 በመቶ፣ እንዲሁም በመጨረሻው ምርት ላይ ደግሞ 80 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ ይጣል ነበር፡፡ በተደረገው ማሻሻያ ለግብዓት የሚውለው ንፁህ አልኮል ላይ የሚጣለው ኤክሳይስ ታክስ ወደ አሥር በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ስኳር የታከለባቸውን ምርቶች የሚያመርቱ እንደ ከረሜላ ዓይነት አምራቾች ለስኳር ግብዓቱ የሚከፍሉት 20 በመቶ የኤክሳይስ ታክስ መጠን ወደ አሥር በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡

በተጨማሪም ደግሞ የአስተዳደር ችግር ገጥሟቸው ሊሳኩ ያልቻሉና በ2012ቱ አዋጅ ኤክሳይስ ታክስ እንዲከፍሉ፣ ነገር ግን በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነፃ እንዲሆኑ የታሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ያደርሳሉ የተባሉት ምርቶች ናቸው ተቃውሞ የገጠማቸው፡፡

ለምግብነት ከተዘጋጀ 100 ግራም ውስጥ 40 ግራም ያህሉ ወይም የበለጠ ሳቹሬትድ ስብ የያዘ የአትክልትና የእንስሳት ዘይት ላይ ተጥሎ የነበረው ኤክሳይስ ታክስ፣ ምግቦቹ ምን ያህል ስብ እንዳላቸው የመለየቱ ሥራ ላይ የማስፈጸም ችግር በመግጠሙ ታክሱ እንዲነሳ ሆኗል፡፡ በዚህም የአዋጁ ማብራሪያ ሰነድ እንደገለጸው ይህን የማጥራት ኃላፊነት ያለበት የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ይህን ለማከናወን አቅም እንደሌለው ነው፡፡

የሳቹሬትድ ስብ መጠንን በሚመለከት ተጥሎ የነበረውን ታክስ መነሳቱ ቅሬታ ላቀረቡት የስብሰባው ተሳታፊዎች፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎች መልስ ሰጥተውበታል፡፡ የሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሰጡት መልስ እንደገለጹት፣ የስብ መጠኑን እንዲለኩ የተመደቡት ተቋማት የአፈጻጸም ውስንነት ስላለባቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች በተደጋጋሚ እንዲለኩላቸው ሲጠይቋቸው ሊሳካ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

‹‹አተገባበር ላይ ችግር ስላየንበትና የሚያስፈጽሙት ተቋማትም አቅም እስኪያጎለብቱ ድረስ የማናስፈጽመውን ሕግ አሁንም አውጥተን ችግር ውስጥ ከምንገባ ነው የወጣው›› ሲሉ ኢዮብ (ዶ/ር) ለተሳታፊዎች ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው እንደጠቆሙትና ምክር ቤቱም ፈቃዱ ከሆነ አዋጁ ላይ ‹‹አተገባበሩን በተመለከተ አስፈጻሚዎች አቅም ሲፈጥሩ ተግባራዊ ይደረጋል፤›› የሚል ድንጋጌ እንዲቀመጥ መክረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች