Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቤት አውቶሞቢሎች የታክሲ አገልግሎት በሚሰጡ ላይ ዕርምጃ መውሰድ ሊጀመር ነው

በቤት አውቶሞቢሎች የታክሲ አገልግሎት በሚሰጡ ላይ ዕርምጃ መውሰድ ሊጀመር ነው

ቀን:

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የአሌክትሮኒክስ ታክሲ ስምሪት ምዝገባ ሳያደርጉ፣ በሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ ለመሰማራትና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ ሳይኖራቸው በከተማዋ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ባለንብረቶች ላይ ዕርምጃ ሊወሰድ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከትራንስፖርት ቢሮ ፍቃድና ዕውቅና ውጪ የኤሌክትሮኒክስ የታክሲ ስምሪት ፍቃድና የምዝገባ ሠርተፊኬት ሳይኖራቸው እንዲሁም በኮድ-2 የሰሌዳ ቁጥር ከዘርፍ ፍቃድ ውጪ በከተማዋ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙ የትራንስፖርት ቢሮው መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ገልጿል፡፡

በከተማዋ የትራንስፖርት አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን በበላይነት የመምራትና የመቆጣጠር፣ በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ማኅበራትን፣ ተቋማትንና ግለሰቦችን እንዲያደራጅ የአሠራር ሥርዓቶችን የመቀየስና የመተግበር ኃላፊነት በትራንስፖርት ቢሮ አዋጅ ቁጥር 74/2014 እንደተሰጠው ያስታወቀው ቢሮው፣ ከእርሱ ፍቃድና ዕውቅና ውጪ የታክሲ አገልግሎት በሚሰጡት የኮድ-2 ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ላይ ህጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ እስካሁን ድረስ ኮድ-2 የመኪና ሰሌዳ ያላቸው ተሽከርካሪዎች፣ የኤሌክትሮኒክ ታክሲ ሥራ ላይ እንዲሠማሩ የሚያስችል አሠራር አለመዘርጋቱን፣ እስከ አሁን ባለው አሠራር የኤክትሮኒክ ታክሲ ሥራን ለመሥራት የተፈቀደላቸው ኮድ-3 ሰሌዳ ኖሯቸው የንግድ ፈቃድ ያወጡና ኮድ-1 ሆነው የታክሲ ቀለም የተቀቡ ተሽከርካሪዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኮድ-2 ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙ ከዚህ ቀደም ያስታወቁት፣ ዛይ ራይድና ወዝ የተሰኙት የኤሌክትሮኒክ ታክሲ ስምሪት ድርጅቶች፣ ከእነዚህ ተሽከርካሪዎች ግማሽ ያህሉ እንኳን በመንገዳቸው ተሳፋሪዎችን በመጫን ከፍተኛ የሰው ቁጥር ማዘዋወር እንደሚቻል፣ ‹‹መንግሥትም ከኤሌክትሮኒክ ታክሲዎች የሚሰበስበውን ግብር በዓመት ከሦስት ቢሊዮን ወደ ስድስት ቢሊዮን ማሳደግ ይችላል›› ሲሉ መንግሥትም ተጠቃሚ ነው የሚል ሐሳባቸውን አስታውቀው ነበር፡፡

የዛይራይድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ታደሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮድ-2 ተሽከርካሪዎች ግብር ከፋይ የሚሆኑበትን እንዲሁም በከተማው ውስጥ ጉልህ ለሆነው የትራንስፖርት ፍላጎትና አቅርቦት ችግር ማቃለያ መሆን እንደሚችሉ፣ በተጨማሪም የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የሚጫወቱትን ሚና አስመልክቶ ፕሮፖዛል ቀርቦ ነበር፡፡

ሆኖም በትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች መለዋወጥ ምክንያት ጅማሬ ላይ የነበሩትን ነገሮች ከማስቀጠልና ያሉትን ችግሮች ከማሻሻል ይልቅ ሕገወጥ ነው በሚል እንቅስቃሴውን የመግታት ውሳኔ መወሰኑን ያስረዱት አቶ ሀብታሙ፣ ከእነዚህ ተሽከርካሪዎች ጋር ተያይዞ የነበረው ጥያቄ ግብር ከፋይ እንዴት ይሁኑ? በመሆኑ፣ ተሽከርካሪው ሳይሆን ግለሰቡ ግብር ከፋይ የሚሆንበት ሥርዓት በተመለከተ ለቢሮው ፕሮፖዛል ቢቀርብም ‹‹ጥናቱን እያየነው ነው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይመለሳል›› በሚል በይደር መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የትራንስፖርት ቢሮው በኮድ-2 የሰሌዳ ቁጥር የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ዕርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ ትክክለኛ ካለመሆኑ ውጪ አገሪቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሕገ አልወጣም እየተባለ በሚተላላፉ ውሳኔዎች ከሌላው አገር እኩል እንዳትራመድ እያደረጋት መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

ዛይራይድንም ጨምሮ ሌሎች የኤሌክትሮኒክ ታክሲ ስምሪት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር  እንቅስቃሴ እንደጀመሩና ለተያዘው ሳምንትም ቀጠሮ መያዛቸውንም ለማረጋጥ ተችሏል፡፡

‹‹የኮድ-2 ተሽከርካሪዎች ለመንግሥት የሚገባውን ታክስ አንከፍልም አላሉም፣ አብዛኞቹ ትርፍ ሰዓት ሾፌሮች ናቸው፣ ባገኙት የተጨማሪ ሰዓት ገቢ ልክ ለመክፈል ዝግጁ ናቸው፣ እኛም የዘረጋነው ሲስተም ያንን የሚሳይ ነው›› ሲሉ አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል፡፡

ዛይራይድ ብቻውን ለአንድ ሺሕ የተጠጉ የኮድ-2 ተሽከርካሪዎችን እንደመዘገበ፣ ከዚህ ውስጥ ብዙኃኑ ስሪታቸው እ.ኤ.አ የ2020/21 የሆኑ፣ በባንክ ብድር የተገዙ እንደመሆናቸው የትራንስፖርት ቢሮ ውሳኔ ባለንብረቶቹ በትርፍ ጊዜያቸው ሠርተው ለመክፈል የሚያደርጉትን ጥረት የሚገታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኤሌክትሮኒክ ታክሲ ስምሪት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች በቀጣይ ማኅበር በመመሥረት ከዚህ ቀደም የቀረበውን ጥናት የትራንስፖርት ቢሮ በደንብ ተመልክቶ የሚያመጣውን ጥቅምና ችግር ምንድነው? የሚለውን በመመዘን  ውሳኔ እንዲሰጥ ጥረት እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡

ሪፖርተር የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ይፋ ካደረገው ማሳሳቢያ ጋር በተያያዘ አጠቃላይ ጉዳዩን በተመለከተ የቢሮውን የሥራ ኃላፊዎች ለማነጋጋር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...