- ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው?
- ምነው?
- ምክር ቤቱም ሆነ አባላቱ የተከበሩ ተብለው የሚጠሩት በምክንያት አይደለም እንዴ?
- ትክክል ነው። ምክንያቱም፣ ምክር ቤቱ ትልቁ የሥልጣን አካል ነው፣ አባላቱም የሕዝብ ተወካዮች በመሆናቸው የተከበሩ ተብለው ነው የሚጠሩት።
- ታዲያ ዝም ማለት ተገቢ ነው፣ መገሰጽ የለብንም?
- ምኑን?
- የተከበረው ምክር ቤት አባል ያቀረበውን ጥያቄ ‹‹ጥሩ ቀልድ ነው›› ሲሉ ዝም ማለት ተገቢ ነው?
- እርስዎም እኮ በማይመጣው ነው የመጡት።
- እንዴት?
- ሥልጣን ይልቀቁ ነዋ ያሉት?
- እንደዚያ ከሆነ ምክር ቤቱ አንድ ቋሚ ኮሚቴ ሊያቋቁምልን ይገባል።
- የምን ቋሚ ኮሚቴ?
- የቀልድ ጉዳዮች!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ ሠራተኞች ማኅበር ጋር ስለ የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ሽያጭ እየተወያዩ ነው]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ሰላም፡፡
- በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት።
- አዎ። ይህንን ደብዳቤ እየውና በጠየቁት መሠረት ይፈጸምላቸው።
- ጉዳዩ ምንድነው?
- ከኦሮሚያ ክልል የመጣ ደብዳቤ ነው። የተቋማችንን ትብብር ይፈልጋሉ።
- የምን ትብብር ነው የጠየቁት?
- የመደመር ትውልድ መጽሐፍን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማት ለሚገኙ ሠራተኞች በመሸጥ ገቢውን እንድናስገባላቸው ነው የጠየቁት።
- ምን…?
- የመደመር ትውልድ መጽሐፍን ለተቋማችን ሠራተኞች እንድንሸጥላቸው ነው የጠየቁት። ከደብዳቤው ጋር አያይዘውም ሁለት ሺሕ መጽሐፍቶችን ልከውልናል።
- ክቡር ሚኒስትር ማለት የምችለው አንድ ነገር ብቻ ነው።
- ምን?
- አድርሰናል!
- እንዴት? ምን ማለትህ ነው?
- ተመሳሳይ የትብብር ጥያቄ ሰሞኑን ቀርቦልን አስተናግደናል።
- ማነው የጠየቀው?
- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር።
- ይህንኑ መጽሐፍ እንድንሸጥ ነው የጠየቁት?
- አዎ። እነሱም ሁለት ሺሕ መጽሐፍ ነበር የላኩት።
- እና ምን ምላሽ ሰጣችኋቸው?
- በዋናው መሥሪያ ቤትና በተጠሪ ተቋማት ያሉ ሠራተኞችን አስቸግረን ከሞላ ጎደል ያቀረቡት መጽሐፍ ተሽጦላቸዋል።
- በፌዴራል ተቋማት እንዲሸጡ ማን ፈቀደላቸው?
- እንዴት?
- መሸጥ የነበረባቸው በተከማ አስተዳደሩ ተቋማት ሥር ለሚገኙ ሠራተኞች እንጂ በፌዴራል ተቋማት ውስጥ ሽጡ አልተባሉማ፡፡
- ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ወደ እኛ ተቋም መላክ አልነበረበትም።
- እንዴት?
- መጽሐፉን በራሱ ክልል ውስጥ ሸጦ ገቢውን ለተባለው ፕሮጀክት እንዲያውል ነዋ የታዘዘው።
- አዲስ አበባ የክልሉ መንግሥት መቀመጫ መሆኗን እያስተዋልን እንጂ?
- መቀመጫ መሆኗንማ አውቃለሁ።
- ታዲያ ምንድነው የምትለው?
- መቀመጫ ብቻ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የመጽሐፍ ሽያጭን አስታከህ የሕገ መንግሥት ጥያቄ እያነሳህ ነው?
- የሕገ መንግሥት ጥያቄ?
- አዎ። ዳርዳር እያልክ ያለኸው ምን ልታነሳ እንደሆነ ያስታውቃል።
- ኧረ እኔ ዳርዳር አላልኩም፣ የማነሳው ጥያቄም የለኝም።
- አዲስ አበባ መቀመጫ ብቻ ነች አላልክም።
- እሱንማ ብያለሁ።
- ታዲያ ይኼ ምን ማለት ነው?
- ምን ማለት ነው?
- አዲስ አበባ የኦሮሚያ አይደለችም እያልክ ነዋ!
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እንደዚያ አልወጣኝም፣ አላልኩም!
- መቀመጫ ብቻ ነች ማለት ምን ማለት ነው ታዲያ?
- ክቡር ሚኒስትር የተፈለገው የመደመር ትውልድ መጽሐፍን መሸጥ አይደል?
- የጠየቁት እሱን ነው!
- ስለዚህ በሐሳብ መለያየት ያለብን አይመስለኝም። በዚያ ላይ…
- እ… በዚያ ላይ ምን?
- የመጽሐፉ ይዘትም ተደመሩ ነው የሚለው።
- ስለዚህ?
- መከራከራችን ትክክል አይደለም፣ ይጋጫል።
- ከምንድነው የሚጋጨው?
- ከመጽሐፉ መንፈስ ጋር ይጋጫል። አብሮ አይሄድም።
- ስለዚህ መጽሐፉ እንዲሸጥ ታደርጋለህ።
- ያው ሠራተኛው አንድን መጽሐፍ ለሁለተኛ ጊዜ ግዛ ብንለው የሚሰጠው ምላሽ ይታወቃል።
- ምን ሊል ይችላል?
- አንብቤ ስጨርስ ፓስታ ይሆናል እንዴ ብሎ ማሾፉ አይቀርም።
- ስለዚህ?
- እኔ ሌላ መፍትሔ እፈልጋለሁ።
- ምን ዓይነት መፍትሔ?
- ከድርጅቱ ወጪ ሆኖ መጽሐፉን በሠራተኞች ስም እንገዛለን።
- መጽሐፍ ለመግዛት የተፈቀደልን በጀት የለማ፣ ኦዲት ስንደረግ ምን ልትል ነው?
- ወጪውን ለመጽሐፍ ግዢ የዋለ አንለውም።
- እና ምን ልትለው ነው?
- ለመደመር ብለን እንመዘግበዋለን።
- ኦዲተሩ ቢጠይቅስ?
- ወጪው በመደመር ስም ተይዞ?
- እ…?
- አይጠይቅም!
- እንደዚያ ከሆነማ ሃያ ሺሕ አድርገው።
- ምኑን?
- የመጽሐፉን ብዛት!