Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣ የእለት ጉርሳቸውን ምፅዋት ለማግኘት ለወጪ ወራጁ እጃቸውን በሚዘረጉ፣ ኑሮ ይሁን ወይም የዘመኑ ሁኔታ አቅላቸውን አሳጥቷቸው ከራሳቸው ጋር እያወሩ በሐሳብ በሚነሆልሉ፣ ለይቶላቸው በሳቅ ወይም በቁጣ ድምፃቸውን ከጣሪያ በላይ አድርገው በሚጮሁ፣ በዚህ መሀል ደግሞ ይህንን ሁሉ ትዕይንት እያዩ በሚገረሙና በሚቆዝሙ ተሞልቷል፡፡ እንደ ዘንዶ የተጠመጠመው የታክሲ ጠባቂዎች ሠልፍ ደግሞ ራሱን የቻለ ድራማ ይወጠዋል፡፡ አንገቱን እንደ ሰጎን ወደ ላይ አንጠራርቶ አሻግሮ የሚያይ መስሎ በሐሳብ ዥው ብሎ የሄደ፣ የልጆቿ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ጭንቅ ያላት እናት ፍዝዝ ብላ፣ የሥራ ወይም የቀጠሮ ሰዓት ረፍዶባቸው የሚነጫነጩ አፍላ ወጣቶች፣ የታክሲ ዝር አለማለት ያበሳጫቸው ጎልማሶች፣ ምድር ከፍ ሰማይ ዝቅ ቢሉ ምንም የማይገርማቸው የሚመስሉ ፌዘኞች፣ ከወጪ ወራጁ ጋር እየተለካከፉ አፍ የሚካፈቱ ነገረኞችና ዕድሜና ኑሮ ያጎበጣቸው አዛውንቶች መታከት በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የታክሲ ተራው ሠራዊት ደግሞ በስኮርት ሾፌሮችና ወያሎች፣ በተራ አስከባሪዎችና በኪስ አውላቂዎች ራሱን የቻለ ትርዒት ይታይበታል፡፡ አጃኢብ ነው!

የረገጠውን መሬት በእግሮቹ እየተመተመ የታክሲ ዕጦትን ከፖለቲካ ትንተና ጋር ያዛመደው፣ ‹‹ለዚህ ሁሉ ችግር ብቸኛ ተጠያቂው ሕዝብ ነው…›› ብሎ የክርክር መድረክ ከፈተ፡፡ ከእሱ አፍ ከመውጣቱ በአየር ላይ የቀለበው አንድ ቀልደኛ መሳይ ደግሞ፣ ‹‹ወንድሜ እውነትህን ነው፣ ሁለት ዓመት ሙሉ በመድፍና በታንክ፣ በዲሽቃና በድሮን ሲከሻከሹ ከርመው ፕሪቶሪያ ሲታረቁ እኮ ተጠያቂ ያደረጉት ሕዝብን ነው…›› ሲለው አንዷ ድንገት ዘው ብላ ገብታ፣ ‹‹…እኛ እኮ ድሮም ወንድማማቾች ነበርን ሕዝቡ ነው እንጂ ያጣላን ያሉት ነው አይደል…›› ብላ ከት ብላ ሳቀች፡፡ ግንባሩ ኮምተር ብሎ ፊቱ መጠጥ ያለ ጎልማሳ፣ ‹‹እንዲህ ዓይነት ጎምዛዛ ቀልድ አያስቅም፡፡ ማንም እንደ ማስቲካ ሲያላምጠው የከረመውን ቀልድ እዚህ እንደ አዲስ እያደረጋችሁ ስታቀርቡ ማፈር ነው ያለባችሁ…›› ከማለቱ አንድ ልጅ እግር ቢጤ፣ ‹‹ጋሼ እውነትህን ነው፡፡ ግን ያልገባኝ ነገር እዚህ አገር ለሚፈጠር ችግር ሁሉ ሕዝብ ተጠያቂ ነው ማለት ምንድነው…›› እያለ ሳለ አሥራ አምስት ሰዎች ተቆጥረን የመጣው ዶልፊን ታክሲ ውስጥ እንድንገባ ተደረገ፡፡ ጉዞ ሊጀመር ነው ማለት ነው!

የተሳፈርንበታ ታክሲ መሙላቱ ተረጋግጦ ወያላው ‹‹ሳብ!›› ከማለቱ የተጀመረው ወግ እንዲቀጥል ነው መሰል አንዱ፣ ‹‹ማነህ ጩጬው፣ ሠልፍ ላይ ሆነህ ያቀረብከው ጥያቄ እኔንም እየከነከነኝ ስለነበር መልስ አስፈላጊ ነው…›› ብሎ ወደ ወግ ጀማሪዎቹ አማተረ፡፡ በዚህ መሀል ወያላው፣ ‹‹ደጅ የጀመራችሁትን እዚያ ነው መጨረስ የነበረባችሁ፡፡ እዚህ ታክሲ ውስጥ ምርጥ ምርጥ ሙዚቃዎችን እየሰማን ነው የምንጓዘው…›› ብሎ ማሳሰቢያ ከመንገሩ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተቃውሞ ገጠመው፡፡ ‹‹ሁሌም የምንጓዝበት ታክሲ ከአንድ ቦታ ተነስተን ሌላ ቦታ የምንደርስበት ብቻ ሳይሆን ደስታችንን፣ ብሶታችንን፣ ያለፈውን፣ የአሁኑንና የወደፊቱን ነገራችንን የምንነጋገርበት ነፃ መድረካችን ነው፡፡ አንተ ማን ሆነህ ነው ይህንን የምክክር መድረክ ለመዝጋት ሴራ የምትሸርበው…›› ብሎ አንዱ ጎረምሳ ከመሀል ወንበር ቱግ ሲልበት፣ ‹‹ወዳጄ ተረጋጋ፣ ከፈለጋችሁ ሙዚቃ ካልፈለጋችሁ ደግሞ ንትርክ መምረጥ መብታችሁ ነው…›› ብሎ ሾፌሩ ሰላምና መረጋጋት ሲፈጥር ወያላው ደግሞ፣ ‹‹እኔ ከአሥር ዓመት በላይ ሆኖኛል የዚህ አገር ሰው ወሬ ከትናንት ዛሬ ተሻሽሎ ሰምቼ አላውቅም…›› እያለ ያጉተመትም ጀመር፡፡ ጉድ ነው!

‹‹እዚያ ሠልፍ ላይማ የተነሳው ሐሳብ ለታክሲ ዕጦቱ ከሕዝብ በላይ ተጠያቂ የለም የሚል ነበር መሰለኝ የተባለው…›› ብለው አንድ አዛውንት መድረኩ በይፋ ተከፍቷል የሚል ዓይነት ቃና ያለው አስተያየት አቀረቡ፡፡ ‹‹ማንም እየተነሳ ሕዝብ ላይ ያግሳ እንጂ ዘንድሮ፡፡ ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ መከበርና መታፈር ሲገባው እንዴት ሆኖ ተጠያቂ እንደሚሆን እንጃ…›› በማለት ፊቱ ላይ ምሬት የሚታይ ከወጣትነት ወደ ጎልማሳነት እየተሸጋገረ የሚገኝ ረጅምና ቀጭን ሰው ሲናገር፣ ‹‹በድምፁ ሆ ብሎ መርጦ የሾማቸው መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማሟላት ሲያቅታቸው፣ ነጋ ጠባ አገሩን የጭቅጭቅና የአምባጓሮ ምድጃ ሲያደርጉትና ይህም አልበቃ ብሏቸው በነፃነት ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስና የመሥራት መብት ሲገድቡ ሕዝብ ዝም ካለ ማን ተጠያቂ ሊሆንልህ ነው ታዲያ…›› ብሎ ያ የመጀመሪያው የአጀንዳ ቆስቋሽ አሁንም ዙሩን አከረረው፡፡ በዚህን ጊዜ ታክሲዋ በአንድ እግሯ የቆመች እስከምትመስል በድጋፍና በተቃውሞ ድምፆች ተርገፈገፈች፡፡ መደማመጥ እስከሚያቅት ድረስ ጩኸቱ በዛ፡፡ ጠባብ ቦታ ውስጥ እንዲህ ከተሆነ ሰፋ ቢል ኖሮ ምን ይፈጠር ይሆን ያስብላል፡፡ ይገርማል!

ጉዞው ቀጥሏል፡፡ በመሀል ወጪና ወራጆች ቢኖሩም ብዙዎች ወደ ፒያሳ ስለሚሄዱ፣ በመደማመጥ መጥፋት ለጊዜው የተቋረጠው ወግ በሌላ አጀንዳ ተጠለፈ፡፡ ‹‹ሕወሓት ጦሩን ሙሉ በሙሉ ሳያሰናብትና የታጠቀውን ሳይፈታ ከሽብርተኝነት መዝገብ መፋቁ ምን ሊያስከትል ይችላል…›› የሚል ድንገተኛ ዱብ ዕዳ መሳይ ጥያቄ የቀረበው ከአንዲት ምስኪን መሳይ ሴት ነበር፡፡ ‹‹የጥያቄው አቀራረብ ፓርላሜንታዊ ቢመስልም ውስጡ ሥጋት ያዘለ በመሆኑ እኔም የምጋራው ነጥብ ነው…›› እያለች አንዲት ቆንጆ በቪፒኤን ከለላ ዓይኗን ከተከለችበት የፌስቡክ ገጿ ላይ ቀና ብላ በኩራት ተናገረች፡፡ ከአጀንዳው በፍጥነት መለወጥ የአጀንዳ ነጠቃ ስሜት ያለው አነጋገሯን በማድነቅ፣ ‹‹እህቴ ከጥያቄው በላይ አንቺ ረቀቅ አድርገሽ ያቀረብሽበት ምሁራዊ ትንተና ዓይነት ጋባዥ አስተያየት በእውነቱ ለውይይት የሚያነሳሳ ነው…›› እያለ ዓይኖቹን እያስለመለመ አንዱ ወጣት አይሉት ጎልማሳ ቢጤ ሲያዳንቅ፣ ከዳር እስከ ዳር የተቀበለው ጭብጨባ ሳይሆን የለበጣ ሳቅ ነበር፡፡ በእሱ ቤት አራዶ ሆኖ የዚያቺን ምስኪን ሴት መሠረታዊ ጥያቄ በማጣጣል፣ ይህችኛዋን ቀዘባ ለማብሰል የሄደበት ርቀት ትዝብት ላይ ነበር የጣለው፡፡ አጉል ድርቅና!

ከሾፌሩ ጀርባ ያለው መቀመጫ መስኮቱን ተደግፈው የተቀመጡ እናት፣ ‹‹ልጄ ሥጋት ያዘለው ጥያቄሽ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እስከ መቼ ነው እኛ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ መተማመን አቅቶን ስንጫረስ የምንኖረው፡፡ ሁለት ዓመት ሙሉ ተፋጅተን ክንዳችን ሲዝል እኮ ነው ፈረንጆቹ አስገድደው የሰላም ስምምነቱን ያፈራረሙን፡፡ ስምምነቱ ደግሞ የሕወሓቶች ጦር እንዲበተን፣ ትጥቁን ፈቶ እንዲያስረክብ፣ እንዲሁም ሕወሓት ከሽብር መዝገብ እንዲሰረዝና የመሳሰሉት ስለሆነ ከዚያ ሲያፈነግጥ ተው በስምምነቱ እርጋ፣ ታልሆነ ግን ዋ እያሉ አደብ ማስገዛት ነው፡፡ ፈረንጆቹን ልብ በሉ እያሉም ሙያ በልብ ማለትም ብልጠት ነው፡፡ ይኸው ጊዜያዊ መሪያቸውንም ዶ/ር ዓብይ አይደሉም እንዴ ያፀደቁት፡፡ ልጄ ሥጋትሽ ተገቢ ቢሆንም መንግሥት ደግሞ ለራሱ ህልውና ሲል ይህ አይጠፋውም…›› ብለው ያቺን ምስኪን ሴት እያግባቡ ሲናገሩ ብዙዎች ከማዳመጥ ውጪ ምንም የሚሉት አልነበራቸውም፡፡ ያ ነገረኛ ግን፣ ‹‹ማዘር እንግዲህ እንደ ፍትሕ ዕጦቱ፣ እንደ ኑሮ ውድነቱ፣ እንደ ውኃና ኤሌክትሪክ መጥፋት፣ እንደ ትራንስፖርት አጥቶ በውርጭና በፀሐይ መደብደብ ይህንንም ቻሉት እያሉ ይመስላሉ…›› ሲላቸው፣ ‹‹እኔ አንተን ብሆን ሁሉንም ነገር ሌላ አካል ላይ ከማላከክ፣ እኔ ነኝ ያለ ተፎካካሪ ፓርቲ መሥርቼ ችግሮችን ሁሉ ደህና ሰንብቱ የሚያደርግ አማራጭ ፖሊሲ ይዤ እቀርብ ነበር…›› ሲሉት ኃፍረት ፊቱን ሲያቀላ በግልጽ ይታይ ነበር፡፡ ንገሩኝ ባይ!

ከወደ ገቢና አዲስ ወሬ መሰማት ጀመረ፡፡ ሁለት ወጣቶች እርስ በርስ ስለቴክኖሎጂ ያወራሉ፡፡ አንደኛው፣ ‹‹ጂፒቲ ፎር ይዞት የመጣው ጉድ ዓለምን በቅርቡ ግልብጥብጧን ያወጣዋል፡፡ ዕድሜ ለአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ገና ምን የማናየው ጉድ አለ ብለህ ነው…›› ብሎ ለጓደኛው ሲነግረው፣ ‹‹ዚስ ዋን ኢዝ ኢንክረደብሊ አሜዚንግ…›› ብሎ ይመልስለታል፡፡ ‹‹እነዚህ ጎረምሶች ምን ጉድ ቢገጥማቸው ነው እንዲህ ምኑም የማይገባ ነገር የሚያወሩት…›› ብሎ አንዱ አጠገቡ የተቀመጠውን ወዳጁን ሲጠይቀው፣ ‹‹እነሱ ቢያንስ ኮሌጅ ገብተው ተምረው ዓለም ምን እየሆነች እንዳለች ተግባብተው እያወሩ ነው፡፡ እኛ አለን አይደል ከምኑም የሌለንበት የማናውቀውን ፖለቲካ ማጡ ውስጥ ገብተን እያቦካን የረባ ነገር ጠብ የማናደርግ…›› ብሎ በንዴት ቱግ አለ፡፡ ‹‹በጂፒቲ ቻት ስንገረም ገና ስንትና ስንት አስደማሚ ነገር መጥቶ አጀብ ያሰኘናል…›› ብሎ እንደገና ወጣቱ ወጉን ሲቀጥል፣ ‹‹እኛ ሼርና ላይክ የምናደርገውን ማወቅ ተስኖን ስንወዛገብ፣ የነገው ትውልድ ግን ከቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች እኩል ይራቀቃል…›› የምትለው ያቺ ምስኪን ነበረች፡፡ ምስኪን መስላ ጣል የምታደርጋቸው ባለፒኤችዲዎችን ያስንቃሉ፡፡ እንዲያ ነው እንጂ!

ጉዞአችን እየተገባደደ ነው፡፡ ከነባር ተሳፋሪዎች ግማሽ ያህሉ እስካሁን አሉ፡፡ ወያላው ገና ከመጀመሪያው ከደረሰበት የነገር ምት ያገገመ አይመስልም፡፡ ሾፌሩ በስሱ ከፍቶ ከሚሰማው ሙዚቃና ከመንገዱ ውጪ ምንም ማየትም ሆነ መስማት አልፈለገም፡፡ ወጪና ወራጅ ተሳፋሪዎች የያዝነው ወግ ሳይመስጣቸው ቀርቶ ወይም በመታከት ይሁን ድምፃቸው አልተሰማም፡፡ በዚህ መሀል ነበር አዛውንቱ፣ ‹‹ልጆች የሚያዋጣው መማር ብቻ ነው፡፡ የተማረ ከዘመኑ ጋር እኩል ከመራመድ በተጨማሪ ዘመኑ ይዞት የሚመጣውን በረከት ለመቋደስ አይቸገርም፡፡ በአቋራጭ ጊዜ ተመቸን ተብሎ የሚገኝ ሀብት ሥር የለውም፡፡ ጊዜ ዘንበል ሲል ጠያቂ አለበት፡፡ ዋናው ቁምነገር ሥጋንም ሆነ ነፍስን በሐሴት ከሚያረሰርሰው ዕውቀት ጋር መጣበቅ ነው የሚያዋጣው፡፡ ፈረንጅ መኪና፣ ባቡር፣ መርከብ፣ አውሮፕላን፣ ስልክ፣ የተለያዩ ማሽኖችንና የመሳሰሉትን የፈለሰፈው ራሱን ከድንቁርና አላቆ ነው፡፡ ከዱር ፍሬ ለቃሚነትና ከአውሬ አዳኝነት የተላቀቀው ዕውቀት ጨብጦ እንጂ፣ ከድንቁርና ጋር ተጣብቆ ቢኖር ኖሮ ልክ እንደ እኛ ምግብ ለማኝ ይሆን ነበር…›› ሲሉ ታክሲያችን የቸርችል ጎዳናን ዳገት ወጥታ ጨርሳ ፒያሳ ደርሳ ‹‹መጨረሻ!›› ተብለን ተሸኘን፡፡ አይ የእኛ ነገር! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት