Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየተዘነጋው የከተሞች ሥራ የመፍጠር ተልዕኮ

የተዘነጋው የከተሞች ሥራ የመፍጠር ተልዕኮ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

አሁን አሁን የአገራችን የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ አንገብጋቢና ሊታሰብበት የሚገባ አጀንዳ እየሆነ ነው፡፡ ከዓመት ዓመት እየተጠራቀመ ከመጣው ተምሮ ቁጭ ካለ ኃይል አንፃር ብቻ ሳይሆን፣ ሳይማርም ሥራ አልባ ከሆነው አኳያ የሥራ አጥነት ችግር ካለሳሰበ ምን ሊያሳስብ ይችላል፡፡ በተለይ በየከተሞቻችን ያለው የሥራ ፈላጊ ቁጥር መጨመር የመንግሥትና የሚመለከታቸው አካላትን ርብርብ የሚሻ ብቻ ሳይሆን፣ በየምዕራፉ እልባት እየተሰጠው ካልሄደም ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ መጋበዙም አይቀርምና ትኩረት ይሰጠው እላለሁ፡፡

በመሠረቱ ሥራ ማለት በአጭሩ ሁሉም ነገር ማለት ነው፡፡ ሥራ ማለት ገቢ ነው፡፡ ገቢ ማለት ደግሞ በልቶ ማደር፣ ቤት አግኝቶ (ተከራይቶ) መኖር፣ ወልዶ አሳድጎ መዳር፣ ራስ መማርና ልጆችን ማስተማር… ለብሶ መንቀሳቀስ፣ ቤተሰብን ማኖር መቻልና ዋስትና ማግኘት ማለት ነው፡፡ ሥራ እንዴት ነው? ብሎ ሲጠየቅ እኮ ሌላ ምንም ማለት አይደለም፣ ገቢ አለህ ወይ? ራስህን ችለሃል ወይ? ችግር የለብህም ወይ? መዋያ አለህ ወይ? ማለት እንጂ ሌላ ምን ማለቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ሥራ ማለት ገንዘብ ነው፡፡

- Advertisement -

ገንዘብ ማለት ደግሞ ሁሉም ነገር ነው፡፡ በእርግጥ በሥራ አማካይነት ስለሚገኘው ገንዘብ እንጂ፣ ገንዘብ የሚገኘው በሥራ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ ማጅራት መቺዎችና ሌቦች፣ ዘራፊዎችና ሙሰኞች፣ አወናባጅ ደላሎች፣ አጭበርባሪዎችና የመሳሰሉት ጥሩ የሚባል ገንዘብ አላቸው፡፡ እነሱም በበኩላቸው ‹‹ሠርተን ነው ያገኘነው›› ባዮች ናቸው፡፡ እየሰረቀ (በሙስናም ቢሆን) ልጆቹን ጥሩ ትምህርት ቤት የሚያስተምር ሌባ አለ፡፡ ስርቆት ያልቀናው ቀን ‹‹ዛሬ ሥራ የለም›› ይለናል፡፡ ሐሰተኛ የትምህርት፣ የጉዞና ሌሎች ሰነዶችን አቀባብሎ ገንዘብ ያገኘ ፎርጀሪ ‹‹ሠርቼ አገኘሁ›› ባይ ነው፡፡

እነዚህን የመሳሰሉትን ከንቱዎች ለጊዜው ወደ ጎን ትተን ወደ መደበኛ ሥራ ሁኔታ ስንመለስ፣ በከተሞቻችን ያለው የሥራ አጥነት ተባብሶ እየታየ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ አብዛኞቹ የአገራችን ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው የሚሆን ሥራ የላቸውም፡፡ ‹‹እኛ አንዳንድ የሥራ ኃላፊዎችን እንደ ዜጋ ሥራ አምጡ፤›› ስንላቸው፣ ‹‹የለንም ብትፈልጉ ፍጠሩና ሥሩ የሚል መልስ ይሰጡናል፤›› ይላሉ ሥራ ፈላጊዎች፡፡ ነገሩ እውነታቸውን ነው፣ ሥራ የላቸውም፡፡ የሌላቸውን ደግሞ ከየት ያምጡት? እኛም ቸግሮናል፣ እነሱም ቸግሯቸዋል፡፡ ተቸግረን አስቸገርናቸው እስከ ማለት የሚደርሱም አሉ፡፡

እንደ አገር በተለይ ከቅርብ የለውጥ ዓመታት ወዲህ ማለት ይቻላል፣ በሥራ አጥነት ረገድ ያሉት አብዛኞቹ ችግሮች ከፖሊሲና ከአፈጻጸም ጉድለት ጋር የሚያያዙ ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ከፀጥታና ከደኅንነት ሥጋት፣ ከባለሀብቶች እንቅስቃሴ መዳከም፣ ከመንግሥት ሰፋፊ ፕሮጀክቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ መስኮች ማነስ፣ እንዲሁም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አዳዲስ የሥራ ፈጠራ ሥልቶችን ነድፈው ካለመንቀሳቀስ ጋርም ይገናኛሉ፡፡ አንዳንዶቹን እንመልከት፡፡

ተምረው ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶች መበራከት

በቀደሙት ሥርዓቶች በየዓመቱ የሚወድቀው ተማሪ ቁጥር ይበዛል፡፡ የነበረው የትምህርት ፖሊሲ ብዙ ተማሪዎችን ለብሔራዊ ፈተና አስቀምጦ ጥቂቱን ብቻ የማሳለፍ አባዜ የተጠናወተው ነበር፡፡ ሁለት መቶ ሺሕ ተማሪዎች አስፈትኖ ስድስት ሺሕ ብቻ አሳልፎ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ያስገባል፡፡ አሁን ፈጣሪ የተመሠገነ ይሁን ተፈታኙ ቢበረክትም ሰፋፊ የትምህርት ዕድሎችም አሉ፡፡ የሥራ ነገር ግን መና ቢስ እየሆነ ነው፡፡

ከላይ በተጠቀሰው አብነት የተቀሩት አንድ መቶ ዘጠና አራት ሺሕ ወዳቂዎች የት ይግቡ? የትምህርት ዕድላቸው በሩ የተዘጋ በመሆኑ ሥራ ፍለጋ ከያሉበት ወደ ከተማ ይጎርፋሉ፡፡ ሥራ ፍለጋ ይንከራተታሉ፡፡ የሥራ ፈላጊው ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ያብጣል፡፡

አሁን ያለው ሁኔታ ደግሞ ከዚህ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ እየተመረቀም ያለ ሙያው ሥራ ፍለጋ የሚኳትነው እጅግ ተበራክቷል፡፡ መሐንዲስ፣ መምህር፣ የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኚ ወይም ኢኮኖሚስት ሆኖ ሥራ ፍለጋ እግሩ እስኪቀጥን የሚዞረው ትንሽ አይደሉም፡፡ የመጀመርያ ዲግሪና አንዳንዴም ማስተርስ ዲግሪ ይዞ አስተናጋጅነትና ያነሰ ሥራ የሚቀጠረው ብዙ ነው፡፡ በከተሞች ደግሞ በኢሕአዴግ ጊዜ እንኳን የነበረው የሥራ ዕድል ፈጠራ ተዳክሟል፡፡

ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት (ከዘንድሮ በስተቀር) ከሚወድቀው ተማሪ የሚያልፈው ቁጥር ይበልጣል፡፡ ኧረ እንዲያውም የሚወድቅ የለም ይባል ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ የሚያልፈውና ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገባው ተማሪ ቁጥር መብዛቱ ግን የተረጋገጠ ነው፡፡

ፈተና እየሆነ ያለው ተመርቆ የሚወጣውን ኃይል የሚሸከም የሥራ ዕድል አለመገኘቱ ነበር፡፡ ይህን ተግዳሮት በመንግሥት አቅም ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ቤተሰብም ለመቅረፍ መነሳት የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት መሆንም ነው ያለበት፡፡ አንዳንዴ የጥገኝነት አስተሳሰቡ አለመቀየሩ እንጂ፣ በየደጁ ሁሉም ያሉትን ዕድሎች መጠቀም ቢጀምር ለውጥ መምጣት በጀመረ ነበር፡፡

አንዳንዴ በጥሞና ካጤንነው ተማሪው ዩኒቨርሲቲ ይገባና የቆየውን ያህል ቆይቶ ተመርቆ ያለ ተወዳዳሪነትና የተሟላ ብቃት ይወጣል፡፡ ታዲያ ለዚያ ሁሉ ተመራቂ የሚሆን ሥራ ከንቲባው (ከተማው) ከየት ያመጣል? ሥራ አለመኖሩን ያልሰማው ተማሪ ሲቪውን አዘጋጅቶ በፎቶ ኮፒ አባዝቶ በፖስታ እያደረገ ለየመሥሪያ ቤቱ ሲያድል ይውላል፡፡ መሥሪያ ቤቶች የመጣውን የተማሪ የሥራ ማመልከቻ እየተቀበሉ ያከማቻሉ፡፡

ለአንዲት ክፍት የሥራ ቦታ እስከ አንድ ሺሕ የሚደርስ ሠልፈኛ ይገጠገጣል፡፡ የሥራ ፈላጊው መብዛት ለሥራው የሚከፈለውን ደመወዝ ዝቅተኛ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ‹‹በነፃ ገብቼ ልሥራ› እያሉ ዋጋ የሚሰብሩ አመልካቾችም አሉ፡፡ ‹መዋያ ላግኝ እንጂ የፈለጋቸውን ይክፈሉኝ› የሚሉም አሉ፡፡ ምን ያድርጉ ወደው እኮ አይደለም፡፡ የት ይግቡ? ሥራ መፍጠር የሚችሉ ጥቂት ዕድለኞች አይኖሩም አይባልም፡፡ የሥራ እጥረትን ለማቃለል የሚኖራቸው ሚና ግን አነስተኛ ነው፡፡

በእርግጥ መንግሥት ዋና ሥራ አቅራቢ የሚሆንበት ምክንያት፣ በየዓመቱ ለተለያዩ ሥራዎች የሚመድበው በጀት ስላለውና ታላላቅ ብሔራዊ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት ስላለበት ጭምር ነው፡፡ በኢኮኖሚ ሥራዎች ውስጥ መንግሥት ከፍተኛውን ሚና የመጫወቱን አማራጭ እስከያዘ ድረስ የሥራ ፈላጊውን ጥያቄ ለማሟላት ሥራ የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡ በተለይ የከተማ አስተዳደሮች ይህን ሀቅ ከዘነጉ ትንፋሻቸው እንዲቆም እያደረጉ መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም፡፡

በእርግጥ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚፈልገው በላይ የሆነ የተማረ የሥራ ኃይል ማምረትና መርጨት ችግር ማስከተሉ አይቀርም፡፡ እንደ እዚያኞቹ የተማረ ኃይል ንፉግ መሆን ባያስፈልግም፣ እንደ ዛሬው በገፍ እያመረቱ ከገበያው ፍላጎት በላይ የሆነ ሥራ ፈላጊ ማቅረብ (ከልጅነቱ ጀምሮ የአባቱን ሥራ እየሠራ እንኳን እንዳያድግ) በሥራ ላይ ባለው ሠራተኛ ላይ ጭምር አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራልና ቢታሰብበት አይከፋም፡፡ በከተሞች የተንሰራፋው ልግምና ሱሰኝነት

በተለይ በአገራችን ከተሞች ሥራን እንደ እርግማን የሚቆጥሩ፣ ጥሮ ግሮ መኖርን እንደ አለመታደል የሚያዩ ወጣቶች እየተበራከቱ ነው፡፡ እነዚህ ‹‹ሥራ ጠል›› በሚባለው ፍረጃ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ እርግማን ማለት ፈጣሪ በሰጣቸው ጉልበትና ዕውቀት ሠርተው ለመኖር ‹‹እንቢ አሻፈረኝ›› ማለታቸው ነው፡፡ ይህን አስተሳሰብ የማረም ተግባር የቤተሰብ፣ የማኅበረሰብና የመንግሥት ጭምር መሆኑን ልብ ማለት ያሻል፡፡

ሌሎች ደግሞ ደመወዝ በሚከፍላቸውና መተዳደሪያቸውን በሚያስገኝላቸው ሥራ ላይ የሚለግሙ፣ አርፍደው ገብተው ከሥራ መውጫ ሰዓት በፊት ቀድመው የሚወጡ አልምጦች አሉ፡፡ በእንጀራቸው ላይ እየቀለዱ መሆናቸውን አይገነዘቡም፡፡ ይህ ፀባያቸው የሚያስከትልባቸውን መዘዝ ከወዲሁ ለማየት ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ይህን የቢሮክራሲ ዳተኝነት ማስተካከል ያለበት ደግሞ ራሱ መንግሥት ብቻ ነው፡፡

በሥራ መምረጥ በሽታ የተለከፉም አሉ፡፡ ሥራ እያላቸው የተሰጣቸውን ሥራ መሥራት ትተው በየጋዜጣውና በየዌብሳይቱ ‹‹ክፍት የሥራ ቦታ›› ማስታወቂያዎችን ሲያገላብጡ የሚውሉ አሉ፡፡ ልባቸው ሁልጊዜም ወደ ውጭ በመሆኑ (የውስጡን የመሥሪያ ቤታቸውን) ሥራ አይሠሩም፣ ወይም በሚገባ ጨርሰው በተቀመጠላቸው የማስረከቢያ ጊዜ ውስጥ አያቀርቡም፡፡

ሥራ ለመፍጠር ብዙ እየተደከመ፣ የአገኘውን ሥራ የሚቀልድበት ብዙ ጉደኛ አለ፡፡ ሥራውን ላለመሥራታቸው ማለቂያ የሌለው ሰበብ ሲደረድሩ መዋል ይቀላቸዋል፡፡ አሠሪው በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ተከታትሎ ይደርስባቸዋል፡፡ ሕጉን ተከትሎ ቀይ ካርድ ያወጣባቸዋል፡፡ ይኼን ጊዜ ለቅሶና ዋይታ ይሆናል፡፡ ‹‹የቤተሰብ ኃላፊ ነኝ… የልጆች አባት ነኝ… እናትና አባት ጧሪ ነኝ… ወዘተ.›› ይላሉ፡፡ አማላጅ ሲያንጋጉ ይከርማሉ፡፡ መታም ያለበት ግን አመለካከትን ማስተካከል ላይ ሊሆን ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሠራተኞችን ያውም ደመወዝ እየከፈለ መሸከም የሚችል የአሠሪ ትከሻ ደግሞ አይገኝም፡፡ ብዙዎችን ታዝበናል፡፡ ምንም ሥራ የሌላቸው ወይም ሥራ ፈልገው ማግኘትን ሲያስቡት ልባቸው ከወዲሁ የሚደክም፣ በውጭ አገር ካሉ ዘመዶቻቸው በሚላክላቸው ገንዘብ የሚኖሩ ሰዎች እናውቃለን፡፡ እነዚህን ሥራ እንስጥ ብሎ ከመጨነቅ ይልቅ እንደ ማኅበረሰብ ከድርጊታቸው እንዲታረሙ ማድረግ ነው የሚበጀው፡፡

በሌላ በኩል ሥራ አለመሥራት ለልመና ከሚዳርጉ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡ መለመን ደግሞ የሰው ፊትና የሰው እጅ ማየት ነው፡፡ ልመና በጣም አዋራጅና ክብረ ነክ ድርጊት ነው፡፡ የሰው ልጅ እንኳንስ ጤና እያለው ቀርቶ የአካል ጉዳተኛ እንኳ ሆኖ ብዙ ሥራ ይሠራል፣ ቤተሰብ ያስተዳድራል፣ ለሌሎች አርዓያ ይሆናል፡፡ ይህን የማኅበረሰብ ዝንፈት አርሞ ሁሉንም ሥራ ሳይንቅ በየአቅሙ ሠርቶ የመኖር ባህልን እንዲያዳብር፣ መንግሥት በተለይ ከተማ አስተዳደሮች ያለባቸውን ኃላፊነት መዘንጋት የለባቸውም፡፡

   ከገጠር ወደ ከተማ የተባባሰው ፍልሰት

የመሬት መጣበብ ችግር በቁራሽ የእርሻ መሬት ላይ የሚሰፍረው ሰው ብዛትና የነፍስ ወከፍ መሬት ድርሻ በየጊዜው ማነስ በገጠር ሥራ አጥነትን እያስፋፋ ነው፡፡ በዚህ ላይ ክልሎች በቂ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ባለመሆናቸው ወጣቱ ያለ ሥራ መቀመጥ አብዝቷል፡፡ በዚህም ብዙ የሥራ ኃይልና ጉልበት ይወዘፋል፡፡ ወደ ከተማ መፍለስ ይባባሳል፡፡ አሁን በገጠር ያለው ያለ ሥራ የተቀመጠ ጉልበት (Surplus Labour) ከ600 ፐርሰንት) በላይ መሆኑ ይነገራል፡፡ በዚህ ላይ በየአካባቢው ያለው የደኅንነት ሥጋትና የፍትሕ ዕጦት በርካታ ሰዎችን ወደ ከተማ ያውም ወደ አገሪቱ መዲና እየገፋቸው ነው፡፡

በዚህ ላይ ከእነ ጉድለቱ እየታየ ያለው ኢንቨስትመንት ትኩረቱ ከተማ ውስጥ ብቻ ከሆነ፣ ሥራውም ያለው እዚሁ በመሆኑ የገጠሩን ጉልበት ወደ ከተማ ይስበዋል፡፡ በመሆኑም በከተሞች ውስጥ የነበረው የሥራ አጥነት ችግር አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የገጠር ኢንቨስትመንትን ማጠናከር፣ በየአካባቢው በሰላምና በነፃነት ሠርቶ መኖርን ተባብሮ ማጠናከር ከመፍትሔዎቹ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ እየሆነ ባለመሆኑ ነው ከተሞችን ወደ አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተ ያለው፡፡

በአንድ በኩል ሲያዩት የገጠር ኢንቨስትመንት ቢስፋፋም እንኳን የከተሞች ችግር ላይቃለል የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ የገጠር ልማት ሲመጣ ገበሬው ኑሮ ሲሟላለት ከተማ መጥቶ መኖር፣ ልጆቹን በከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ማስተማር ይፈልጋል፡፡ ከተሞች ደግሞ ለዚሁ የሚሆን ቤት፣ ትምህርት ቤት፣ ሥራ፣ ወዘተ. ማዘጋጀት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይኼ ተፈጥሯዊ ዕድገት በመሆኑ ሊገደብ አይችልም፡፡ ለማንኛውም ከተማ ወይም ገጠር ላይ ብቻ አተኩሮ ከመሥራት ገጠርና ከተማ ተጓጓዥነት፣ ተደጋጋፊነት ያለው (Complimentary) የተመጣጠነ የዕድገት አቅጣጫ ይዘው እንዲሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል የሚለውን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ምክር መከተል ነው የሚበጀው፡፡

   ሁሉንም የሥራ ዕድሎች አለመጠቀም

እስካሁን ባለው አካሄድ የአገሪቱን ግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር አቅጣጫ ለማስቀጠል ሲባል፣ ሥራዎች ሁሉ በካፒታል የጠነከሩ (Capital Intensive) እንዲሆኑ ይታሰባል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ብቻውን ከገጠር ለሚመጣ ጉልበት የሥራ ዕድል አይፈጥርም፡፡ እንዲያውም አብዛኛው ሥራ በፋብሪካ የሚሠራና በአነስተኛ ጉልበት የሚሸፈን፣ ያውም የቴክኒክ ዕውቀት ተጨምሮበት የሚከናወን እንደ መሆኑ በከተሞች ለሚታየው ሥራ አጥነት የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉ አይቀርም፡፡

ከዚህ ይልቅ መነሳት ያለበት የከተሞች አስተዳደር ኢመደበኛ የሥራ መስኮችን (Informal Sector) ማበረታታቱ ላይ ትኩረት መስጠት ነው የሚበጀው፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙዎቹ የአገራችን ከተሞች የየራሳቸውን ሥራ እየፈጠሩ ሸቀጦችን፣ ፍራፍሬ፣ አትክልት ወዘተ. በጉልትም ሆነ በመንቀሳቀስ በየጎዳናው ክፍት (ገላጣ) በሆኑ ሥፍራዎች ላይ እየዘረጉ በመሸጥ የራሳቸውን መተዳደርያ ለመፍጠር የሚተጉ ዜጎች አሉ፡፡ ይኼ እንደ ቀላል መታየት የለበትም፡፡

እናም ከእነዚህ ጋር እንደ አይጥና ድመት መባረር አያስፈልግም፡፡ ሠርተው እንዲበሉ ቢያንስ ራሳቸውን ከከተሞች ትከሻ ላይ እንዲያወርዱ ዕድል መስጠት ይገባል፡፡ በእርግጥ ሁኔታው ችግር አይኖረውም ማለት አይደለም፡፡ ግብር በሚከፍለው ነጋዴ ላይ ተፅዕኖ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ቀረጥ ተከፍሎበት የመጣ ዕቃ እያለ በኮንትሮባንድ ለመጣ ሸቀጥ ቅድሚያ መስጠት ላያስፈልግ ይችላል፡፡ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች በታክስ ሥርዓቱ ውስጥ ካልገቡ የከተማው አስተዳደር (መንግሥት) ከዘርፉ ማግኘት ያለበትን ገቢ ሊያጣ ይችላል፡፡

ዋናው ነገር የዜጎች በልቶ የማደርና ሠርቶ የመኖር ጉዳይ በመሆኑ፣ ይህን ኢመደበኛ የሥራ ዘርፍ እንደ ክፉ ጠላት መቁጠርና ማሳደድን ቀንሶ በወጉ የሚያዝበትና የሚበረታታበት ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ መንገድ ላይ ጫማ ጠርገው፣ ጀብሎ (ሱቅ በደረቴ) ቸርችረው፣ ተሽከርካሪ ጠብቀውና አጥበው፣ የሸክም ሥራ ሠርተው (አሁን አሁን በጉልበት አስፈራርቶ ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቅ ቢለመድም) የሚኖሩ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡

የከተማ አስተዳደሮች በእነዚህ ወገኖች ረገድ ማድረግ ያለባቸው ማደራጀት፣ በሕግና ሥርዓት እንዲንቀሳቀሱ መደገፍ፣ ሠልጥነው ቆጥበውና ተደራጅተው የተሻለ ሥራ እንዲጀምሩ ማድረግና የሚያገለግሉትን ሕዝብ በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ ማድረግ እንጂ ማሳደድ ሊሆን አይገባም፡፡ ቁጭ ብሎ የሚያወናብድና ማጅራት መቺን ትቶ ጀብሎ ማሳደድ በምንም መለኪያ ትክክል ሊባል አይችልምና፡፡

     የፖለቲካ ዝግጁነት አለመኖርና አለመስተካከል

እውነት ለመናገር በፊትም ሆነ አሁን መንግሥት በከተሞች የራስ ጉዳይ ውስጥ አዘውትሮ ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታ አለ፡፡ ለከተማ አስተዳደሮች ነፃነት አይሰጥም፡፡ ‹ይህን አድርጉ፣ ያን አታድርጉ፣ ለዚህኛው ቅድሚያ ስጡ…› ወዘተ. እያለ በእሱ (በመንግሥት) ፖሊሲ መሠረት ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል፡፡ ሰንጎ ይዞ ይቆጣጠራቸዋል፡፡ ይህ በራሱ የሚገድበው የሥራ ዕድል ተስፋ እንዳይኖር መፈተሽ ግድ ይላል፡፡

ምክንያቱም አካሄዱ በራሳቸው ሐሳብ፣ ዕቅድና አሠላለፍ እንዳይጫወቱ የራስ ገዝ ኦቶኖሚ ሜዳቸውን ያጠብባቸዋል፡፡ ሰማይ ላይ ያለውን ፖሊሲ አንጋጠው ሲያዩ እዚህ እግራቸው ሥር መሬቱ ላይ ያለውን አደጋ ማየት ይሳናቸዋል፡፡ ለነገሩ መንግሥት እጁን ከላያቸው ላይ ቢያነሳላቸው እንኳ አሁን በየአካባቢው ያሉት የእኛዎቹ የከተማ አስተዳደሮች በራሳቸው ዕቅድ ለመሥራት ብቃት ያላቸው መሆኑም ያጠራጥራል፡፡

አብዛኞቹ ከተሞችና አመራሮች ከተማን በገጠር ዕሳቤ አካሄድ ልምራ የሚሉ በመሆናቸው፣ በቂ ለውጥ ሲያመጡ ዓይታዩም የሚሉ ምሁራን መደመጥ አለባቸው፡፡ በዚህ ላይ ብሔርተኝነቱና የራስ ወገንን ማማተሩ ካልተገራ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ድህነት ቅነሳውንም አስተሳስረው ለመተግበር ይጥራሉ እንጂ አይችሉበትም፡፡ ከዚህ አንፃር ብርቱ፣ ማሻሻያና ጠንካራ ጥረት መደረግ ይኖርበታል፡፡

ከተሞቻችን ብቃትና ተራማጅነት ያላቸው፣ ሆደ ሰፊና አገራዊ ሥነ ልቦና ያላቸው ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ አተያይን የገነቡ መሪዎችን ማግኘት አለባቸው፡፡ ባለሀብቶችንና የሥራ ዕድል ፈጠራ አውድማዎችን የሚፈለፍሉ፣ ድህነት ቅነሳና ችግርን አምርረው የሚጠሉ እንዲሆኑ የሚሠራ መንግሥትና ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን “ውኃ ቢወቅጡት እምቦጭ” መሆኑ አይቀርም፡፡

በአጠቃላይ ከተሞች ሆይ ሥራ የመፍጠርና የማበረታታት ዋነኛ ተልዕኳችሁን አስታውሱ፣ ተግታችሁ የተከማቸውን ጫና አቃሉ ነው ማሳረጊያዬ፡፡

      ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...