Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየረቂቅ ሙዚቃ ፈር ቀዳጇ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ (1916-2015)

የረቂቅ ሙዚቃ ፈር ቀዳጇ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ (1916-2015)

ቀን:

‹‹…የሙዚቃ ሥራዎቼን ለአድማጭ የማድረስ ፍላጎቴን እኔ ከመረጥኩት መንገድ በተለየ ጎዳና ተጉዤ እውን እንዳደርግ የፈቀደልኝ የፈጣሪ ጸጋ ነው። የተከተልኩት ጎዳና ‹መጀመሪያ የእግዚአብሔርን መንገድ ፈልግ፤ ከዚያም የፈለግኸው ሁሉ ይሰጥሃል› የሚለውን የወንጌሉን ቃል የሚያንጸባርቅ ነው። ሕይወቴ በብዙ ውጣ ውረዶች የተሞላ ነበር። መንፈሳዊና ሰላማዊ ሕይወት እመራ ዘንድ ታድያለሁ። እና ደግሞ በቸርነቱ ሙዚቃን ተቀብቻለሁ።››

የረቂቅ ሙዚቃ አውራዋ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ከስምንት ዓመታት በፊት ተምሳሌት ዕፁብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች› በሚል ርዕስ ለታተመው መጽሐፍ አዘጋጆች  ስለታሪካቸው የነገሯቸው፡፡

ባለፈው ነሐሴ 2014 ዓ.ም. የእኚህን ታላቅ የሙዚቃ ሰው ሙዚቃዊ ሰብዕናና 99ኛ ዓመታቸውን አስመልክቶ ዴብ ግራንት የተባለ ጸሐፊ፣ ቢግ ኢሹ በተሰኘ ድረ ገጽ ላይ ‹‹የእማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ የሕይወት ታሪክ እንደ ሙዚቃቸው አስደናቂ ነው›› ብሎ ‹‹አስደሳችና ሕይወትን የሚያፀና ድምፅ ወዳለው ኢትዮጵያዊ የጃዝ ሙዚቃ ከእሳቸው የተሻለ መግቢያ ሊኖር አይችልም›› ሲል ገልጿል፡፡

ለስምንት አሠርታት በረቂቅ የፒያኖ ሙዚቃ ሥራዎቻቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዕልና ያገኙት እማሆይ ጽጌ ማርያም፣ ለሦስት አሠርታት በኖሩበት በእስራኤል መዲና በኢየሩሳሌም በምትገኘው የደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ባለው መኖሪያቸው ዜና ዕረፍታቸው ተሰምቷል፡፡

እኚህ በልዩ የፒያኖ ቅንብርና በበጎ አድራጎ ሥራቸው የታወቁት እማሆይ ጽጌ ማርያም በ99 ዓመታቸው እሑድ መጋቢት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ማረፋቸውን ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል፡፡ ለኅትመት እስከገባንበት ድረስ ሥርዓተ ቀብራቸው መቼና የት እንደሚፈጸም አልተገለጸም፡፡

ዜና፣ ሕይወትና ጥበብ፣ ሙዚቃና ሌሎች መሰናዶዎች የሚቀርቡበት ኤንፒኤር (NPR)፣ መርሐ ግብሩን ከአንዱ ርዕሰ ጉዳይ ወደ ሌላው ሲሸጋገር የሚያሰማው የመሸጋገሪያ ሙዚቃ፣ የበለጠ ለመስማት እንድትፈልግ የሚያደርግ፣ የተለመደው የፒያኖ ሙዚቃ የእማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ነው፡፡

በእማሆይ ዜና ሕይወት ላይ እንደተገለጸው፣ አንደኛው ሙዚቃቸው እ.ኤ.አ. በ2020 በኦስካር የታጨው የኔፍሊክስ ‹ፓሲንግ› (Passing) ዶክመንተሪ ድራማ ላይ በማጀቢያነት ውሏል፡፡

እማሆይ ጽጌ ማርያም የመጀመርያ አልበማቸውን ያወጡት እ.ኤ.አ. በ1967 ሲሆን ገቢው ለተቸገሩ ወገኖች እንዲውል አድርገዋል፡፡

100 ዓመት ሊሞላቸው ዘጠኝ ወር ግድም የቀራቸው እማሆይ ጽጌ፣ የሙዚቃ ፍቅር ያደረባቸው በሕፃንነታቸው ከወላጆቻቸውና በልጅነት ከኖሩበት አካባቢ እንደነበር በተምሳሌት እንደሚከተለው ገልጸው ነበር፡፡       

‹‹የሙዚቃ ፍቅር በውስጤ ያደረው ገና በልጅነቴ ነው። እናቴ ካሳዬ የሌምቱ ትነግረኝ እንደነበረው አባቴ በአገር ገዥነት ተሹሞ ይሠራ በነበረበት በወለጋ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ እያለን አዳኞች ግዳይ ጥለው እየዘፈኑ በቤታችን በኩል ሲያልፉ በዜማቸው እየተማረኩኝ ተከትያቸው እሄድ ነበር። እናቴ በገና ደርዳሪ አባቴ ደግሞ የክላሲካል ሙዚቃ አፍቃሪ ነበሩ።››

ዜና ሕይወት ዘእማሆይ ጽጌ ማርያም

ከአሥር ዓመት በፊት በኢየሩሳሌም ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሰዋስው ብርሃኑ ደስታ፣ ‹‹የሁለት ዓለም ሰው›› በሚል ርዕስ የዕውቋን የሙዚቃ ሰው እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ የሕይወት ታሪክና ሥራ የሚያትት መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ ከመመንኮሳቸው በፊት የውብ ዳር ይባሉ የነበሩት እማሆይ፣ ከሙዚቃው ባሻገር በገጣሚነት፣ በደራሲነትና በሠዓሊነትም ይታወቃሉ፡፡ ከመጽሐፉ የቀሰምነውን ዜና ሕይወታቸውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡  

የውብ ዳር ገብሩ የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ ታኅሣሥ 3 ቀን 1916 ዓ.ም. ነው፡፡ ወላጆቻቸው አባታቸው ከንቲባ ገብሩ ደስታና እናታቸው ካሣዬ የሌምቱ ሁለቱም ከመኳንንቱ ወገን ናቸው፡፡ የውብ ዳር እስከ አምስት ዓመታቸው ያደጉት በወለጋ ቄለም ውስጥ በመሆኑ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ኦሮምኛ ነበር፡፡ ታላቅ እኅታቸው ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ ለትምህርት ስዊዘርላንድ መሄዳቸውን ተከትሎ በስድስት ዓመታቸው አብረው በመጓዛቸው አዳሪ ትምህርት ቤት በመግባታቸው ቫዮሊንና ፒያኖ ተምረዋል፡፡ በ10 ዓመታቸውም ኮንሰርት አቅርበዋል፡፡ ሙዚቃን ለመማር ያነሳሳቸው አጋጣሚ የተፈጠረው በትምህርት ቤቱ አንድ ዓይነ ስውር የቫዮሊን ኮንሰርት ባቀረበበት ጊዜ ነው፡፡

በአዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ [ዓይን ስውር] ቫዮሊን ተጫዋች ኮንሰርት ተዘጋጅቶለት ለመጫወት መጣ፡፡ ሲጫወት ዝም ብለው ያለቅሱ ነበር፡፡ ኮንሰርቱ አልቆ ሰው ሁሉ ሲወጣ እሳቸው ብቻ ቁጭ ብለው ቀሩ፡፡ ሞግዚታቸው ተነሽ እንሂድ ምን ሆነሻል ስትላቸው አበባ ልሰጠው እፈልጋለሁ ይላሉ፡፡ በዚህ የክረምት ወራት አበባ የለም በማለት ወደ ሰውየው ወስዳ ሁኔታውን ታስረዳና ታስተዋውቃቸዋለች፡፡ ሙዚቀኛውም ራሳቸውን ደባብሶ ‹‹አበባውን እንደተቀበልኩ ቆጥሬዋለሁ፤ አንችም ሙዚቃ ለመማር ተጣጣሪ›› በማለት አበረታትቷቸው ሄደ፡፡ ከዚያ አጋጣሚ በኋላ ነው የየውብ ዳር የሙዚቃ ፍቅርና ፍላጎት በውስጣቸው የተጠነሰሰው፡፡

እማሆይ የስዊዝ ቆይታቸው ከአራት ዓመታት አላለፈም፡፡ ምክንያቱም ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ ትምህርታቸውን በማጠናቀቃቸውና ኢትዮጵያ ለመመለስ በመወሰናቸው ነው፡፡ እማሆይ እዚያም መቆየቱን ስላልፈለጉ አዲስ አበባ በ1925 ዓ.ም. እንደመጡ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርታቸውን ቀጥለዋል፡፡

የፋሺስት ጣሊያን ወረራን ተከትሎ በ1929 ዓ.ም. ከንቲባ ገብሩ ከነቤተሰባቸው በጦር እስረኛነት ወደ ጣሊያን አሲናራ ደሴት ሲጋዙ እማሆይ ጽጌ ማርያም ነበሩበት፡፡ ከአሲናራ ሌላ ኔፕልስ አጠገብ በምትገኘውም መርኮሊያኖ ኖረዋል፡፡

ድኅረ ጦርነት

እማሆይ ፋሺስት ኢጣሊያ አገር ለቆ ከወጣ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ዘመናዊ አስተዳደር ሲዘረጋ በመጀመርያው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት (ሚኒስቴር) ሚኒስትር የነበሩት የዶ/ር ብላቴን ጌታ ሎሬንሶ ታዕዛዝ የመጀመርያ ጸሐፊት ነበሩ፡፡ በመጽሐፉ ላይ እማሆይ እንዳሉት፣ ‹‹እኔና አንድ ዘበኛ በመሆን ነበር ከዶ/ር ሎሬንዞ ጋር ሥራውን የጀመርነው፤ ለጥቂት ሳምንታት ተላላኪም ጸሐፊም እኔው ነበርኩ ማለት ይቻላል፡፡››

እማሆይ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱን ከለቀቁ በኋላ የሙዚቃን ትምህርት ለመማር ያመሩት ወደ ካይሮ ነበር፡፡ ትምህርቱን እየወደዱት ቢመጡም የካይሮን ከፍተኛ ሙቀት ባለመቋቋማቸውና አስተማሪያቸው የኢትዮጵያ ክብር ዘበኛ ሠራዊት የሙዚቃ ክፍልን ለማስተማር እርሳቸውን ይዞ በመምጣቱ ትምህርታቸው ተቋረጠ፡፡ ይህ ሁኔታ በጣም ያሳዝናቸዋል፡፡ በግልጽ ነግሯቸው ቢሆን ኖሮ ካይሮ  ባይስማማቸውም ወደ ሌላ አገር ከዚያው ከካይሮ በመሄድ መቀጠል ይችሉ ነበር፡፡

ከካይሮ መልስ የውብዳር ጊዜያቸውን በብቸኝነትና በትካዜ ቢያሳልፉም በመካከሉ በለንደን የሙዚቃ አካዴሚ የትምህርት ዕድል አግኝተው ከአንድ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል የቅድሚያ ክፍያ ቢከፈላቸውም በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባለመፍቀዱ ይታመማሉ ይላል መጽሐፉ፡፡

‹‹ለ12 ቀናት ከቡና በስተቀር እህል ውኃ ሳይቀምሱ ይሰነብታሉ፡፡ የሚፈልጉት ሞትን ብቻ ነበር፡፡ ቤተሰብ በሙሉ ተጨነቀ፡፡ በጣም ሲደክሙ ወደ ቀድሞው ቤተሳይዳ በኋላም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያሁኑ የካቲት አሥራ ሁለት ሆስፒታል ወሰዷቸው፡፡ ‹የሆስፒታሉ ጣሪያ በላየ ላይ የሚወድቅ ይመስለኝ ነበር፡፡ ሞቴ የተቃረበ መሆኑን በማመን እንዲያቆርቡን ጠየቅሁ›… ያሉ እማሆይ፣ ከሆስፒታሉ አልጋ ላይ አንስተው በመውሰድ አቆረቡና መለሷቸው፣ ቆርበው ከመጡ በኋላ ሃያ አራት ሰዓታት ያለማቋረጥ ረዥም እንቅልፍ ተኙ፡፡ ሲነቁ ፍጹም ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባቸው አዲስ ፍጥረት ሆነው እንደተነሱ እንዲህ በማለት ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ከእንቅልፌ ስነቃ የተሰማኝ የሚያስገርም ሰላም ነበር፡፡ ሕይወቴን የቀየረ ሰላም፡፡››

ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ በሚገኘው ክብር ዘበኛ ሠራዊት ጠቅላይ መምርያ ውስጥ በጸሐፊነት ለሁለት ዓመት በሚሠሩበት ጊዜ በባለወልድ ቤተ ክርስቲያን የሰርክ ቅዳሴ ስለሚደረግ ሁልጊዜ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እዚያው ያድሩ ነበር፡፡ የማደራቸው ዋናው ምክንያቱ የቅዳሴ ማሕሌቱንና ዜማውን ለማዳመጥና ለመቀበል ነበር፡፡ ‹‹መንፈሴን ደስ ይለዋል፡፡ እመሰጣለሁ መግለጽ የማልችለው ሰላምና ደስታ በውስጤ ይሞላል›› ይላሉ እማሆይ፡፡

ይህም የየውብ ዳር መንፈሳዊ ሕይወት ወደ ምንኩስና ጉዞ የተጀመረበት አጋጣሚ ሲሆን በ21 ዓመታቸው ግሸን ማርያም ገዳም ለመመንኰስ ይበቃሉ፡፡

እማሆይ ካዩዋቸው ብዙ ህልሞች መካከል ከምንኩስናቸው ሦስት ዓመት በፊት ያዩት አንድ ህልም በመጽሐፉ እንዲህ ሰፍሯል፡፡

‹‹በጣም ረዥም አዳራሽ ውስጥ እመቤታችን ቅድስት ማርያም የምትሄድ ይመስለኛል፡፡ መልካቸው ቻይናዎች የሚመስሉ እየተከተሉ የረገጠችውን ይረግጣሉ፡፡ ዞራ አታይም ቀጥ ብላ ትሄዳለች፡፡ እኔም እከተላታለሁ፡፡ ሄዳ ሄዳ የእንጨት ደረጃ ላይ ወጣች፡፡ እኔም እሷ በወጣችበት ልወጣ ስል በዚያ በኩል ሂጅ ብሎ አንደኛው ሌላ መንገድ ሲያመለክተኝ፣ ቦታው የፍራፍሬ ቆሻሻ አለበት፡፡ እኔ በዚያ አልሄድም ብዬ እምቢ አልኩና እሷ በወጣችበት ወጣሁ፡፡ ስወጣ ደረጃው የብረት ደረጃ መሆኑን አየሁ፡፡ እሷ ሄዳለች ሦስት ደረጃ ሲቀር ጠፋችብኝ፡፡ እኔም ደረጃውን ጨርሸ ስወጣ ቤቱ ጣራ የለውም፤ ሰማዩ ከዋክብት ተሞልቶ ይታያል፣ ደረጃው አጠገብ መካከሉ ላይ በጣም ወፍራም የብረት ምሰሶ አለ፡፡ ከዚህ አልወርድም በማለት የብረት ምሰሶን ጥምጥም አድርጌ እንደያዝኩ ነቃሁ፡፡››

እማሆይ ከግሸን ማርያም ከወጡ በኋላ በጎንደር አምስት ዓመታት ተቀምጠዋል፡፡ በተለይ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያሳልፉ የነበረው ግን ግምጃ ቤት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ በዚያም ያሬዳዊ ዜማን አጥንተዋል፡፡ በግምጃ ቤት ማርያም ያለውን የድንግል ማርያም ሥዕል በማየት የራሳቸውን ሥዕል ሥለዋል፡፡ ባሕር ዳርንና ጢስ ዓባይንም በጎበኙበት ጊዜም ሰለዓባይ ወንዝ ‹‹The Song of Abay›› ዜማንም ደርሰዋል፡፡

በጎንደር ከተማና በዙሪያዋ ባሉት ቤተ ክርስቲያናት የቤተ ክህነት ትምህርት ዜማና ቅኔ አድናቆት ያድርባቸውና የቆሎ ተማሪዎች የዕለት ጉርስ ለማግኘት ያለባቸውን ችግር አይተው መርዳት አለብኝ ብለው ሲነሱ መፍትሔ ብለው ያሰቡት ሙዚቃቸውን ማሳተም ስለነበር ወደ ጀርመን ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ሁለት አልበሞቻቸውንም ያሳትማሉ፡፡

ደራሲዋ ወ/ሮ ሰዋስው እማሆይን በወጣትነት ዘመናቸው የወንድ ጓደኛ (ጓደኞች) ነበረዎት?›› ብለው ለጠየቋቸው የሰጧቸውም ምላሽ አለ፡፡

‹‹በመጀመርያ እስከ አሥራ አንድ ዓመቴ ስዊዝ ስለነበርኩ የአሥር ዓመት ልጅ እያለሁ ኮንሰርት ያሳየነው ሁለት ወንዶችና እኔ ነበርን፤ በልምምዱ ወቅት ከነሱ ጋር ጥቂት ጊዜ አብረን ተለማምደናል፡፡ ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስን በኋላ እቴጌ መነን የሴቶች ትምህርት ቤት አዳሪ ገባሁ፡፡ ከዚያም ጣሊያን ገባ ስደት ሄድን፡፡ ባጭሩ ለእንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ጊዜ አልነበረኝም ኃይለኛም ስለነበርሁ ይፈሩኛል፡፡››

የማሻሻያ ሐሳብ

እማሆይ ለሠላሳ ዓመታት በኖሩበት ገዳም ሊሻሻል የሚገባው ነገር እንዳለ ደራሲዋ  ለጠየቋቸው ጥያቄ እንዲህ መለሱ፡-

‹‹በሥጋዊ ነገር የሚጎድለን የለም የዓመት ልብስ የዕለት ጉርስ ይሰጠናል፡፡ ሥጋ ከዚህ በላይ ምን ይፈልጋል? በመንፈሳዊ ነገር ግን መሻሻል ያለበት ብዙ ነገር አለ፡፡ አንድ ወታደር ወታደር የሚያሰኘው መሣሪያ ስለያዘ ብቻ አይደለም፡፡ መለዮ ወይም ዩኒፎርም ስለለበሰ ብቻም አይደለም፡፡ ማንነቱንና የሠለጠነበትን ቦታ የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ሲኖረው በተለይም በወታደራዊ ዲሲፕሊን ከሠለጠነ ወታደር ነው ማለት ያስደፍራል፡፡ ገዳም ውስጥም የሚቀበሏቸውን መነኮሳት በዚህ ወታደራዊ መንፈስ መሆን እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ እኛ እኮ የእግዚአብሔር ወታደሮች ነን፣ ሥነ ሥርዓቱን አውቀን ለሌሎች ምሳሌ መሆን ያለብን፡፡ የእምነቱም ሆነ የገዳሙ ሕግ አስከባሪዎች መሆን ያለብን ይመስለኛል፡፡

‹‹ቆብ ገዝቶ የመነኩሴ ልብስ ለብሶ የመጣውን ሁሉ ሳይጣራ መቀበል በውስጥ ለምንኖረውው የህሊና ቁስል በውጭም ለሚያይ መሰናከያ እንድንሆን ያደርጋል ብየ አስባለሁ፡፡ ይህን ማንሳት የፈለግኩት ብዙ ሰዎችን ያነካካ ክስ ድረስ የተደረሰበት ክስተት በዚሁ በገዳሙ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረ በመሆኑ ነው፡፡ የት እንደተማሩ የትኛው ገዳም ውስጥ እንደመነኮሱ፣ ያመነኮሳቸው አባት ማን እንደሆኑ መረጃ አቅርበው በውጭ ሆነው የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸው ተመርምረው ነው ወደ ገዳም መግባት ያለባቸው የሚል አቋም አለኝ፡፡

‹‹ሌላው ሥጋ የዕለት ምግብ እንደሚያስፈለገው ነብስም እንዲሁ ምግብ ያስፈልጋታል፡፡ የነብስ ምግቡ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ አዎ በየቀኑ የሚደገሙ መጻሕፍት አሉ፣ በቅዳሴ ጊዜ በየቀኑ በፕሮግራም መስጠት አለበት፡፡ ቃሉን መማር በቃሉ ለመኖር ይርዳናል ለሌሎችም ምሳሌ መሆን ያስችለናል፡፡ አኗኗራችን በመካከላችን በሚታየው ፍቅር እርስ በርስ በሚኖር መቀባበልና መተሳሰብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ገልጠን ማሳየት መቻል አለበት፡፡ እኛ እኮ ሌላ ሥራ የለንም፣ ሥራችንም ሕይወታችንም ቃሉን ማወቅ ነው፡፡ ካልተማርን አናውቅም፣ ካላወቅነን እንደሚገባን አንኖርም ማለት ነው፡፡

‹‹ማታ ማታ ከራት በኋላ የንስሐ ጸሎት ያስፈልጋል፤ ሰው ተኝቶ አድሮ ጧት ለመነሳቱ ዋስትና የለውም፣ በየዕለቱ ከመኝታ በፊት ንስሐና ተገብቶ ማደር አለበት፡፡ ሰዎች ነንና ባንድ ግቢ ባንድ ገዳም ስንኖር ለሚፈጠሩ ቅያሜዎች በራሳቸው አነሳሽነት ይቅር የሚባባሉ መነኩሴዎች ከሌሉ ይቅር የሚያባብል ኮሚቴ መኖር አለበት፡፡ ያለንበት ጊዜና ቦታ ፈተና የበዛበት ነው፣ ስለዚህ በመንፈሳዊ ሕይወታችን በየሰዓቱ ልንበረታ ስለሚገባ ትምህርት ያስፈልጋል፡፡

‹‹የተማሩ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ መጻሕፍት ቤት ሁልጊዜ ክፍት ሆኖ ሰዎች ቁጭ ብለው ማንበብ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም ነው፡፡ የተማሩ ሰዎችን የምንፈራባት ምክንያት ለኔ ግልጽ አይደለም፡፡ ከሌሎች ባካባቢያችን ካሉ ገዳማት ብዙ ልንማር እንችላለን፡፡ አለበለዚያ ገዳሟ ለነብሳቸው ያደሩ መነኮሳትን ሳይሆን አዳሪ የገዳም አባላትን ጠባቂ እንዳትሆን ያሠጋል፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...