Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊወጣቶችን ከሱስ የመታደግ ክዋኔ

ወጣቶችን ከሱስ የመታደግ ክዋኔ

ቀን:

በኢትዮጵያ ጫት፣ ሲጋራ፣ አልኮልና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ይታመናል፡፡ በተለይ ወጣቶች የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ከሥረ መሠረቱ በሥነ ምግባር የታነፁ ዜጎችን ለማፍራት ወጥ የሆነ አሠራር አለመኖሩና መንግሥት ዘርፉ ላይ ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራቱ ችግሩን አባብሶታል፡፡

ችግሩን ለመፍታት፣ ዘርፉ ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማሳየትና በከተማዋ ከመጠን በላይ በሱስ ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ ወጣቶችን ከገቡበት ሱስ ለማውጣት ‹‹እሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሸን›› የተሰኘ ድርጅት ለወጣቶች ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሥልጠናውን ካገኙት መካከል ወጣት ጌታሁን ብርሃኑ ይገኝበታል፡፡

ወጣት ጌታሁን በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ 02 ኪዳነ ምሕረት ሠፈር በሚባል አካባቢ ተወልዶ ያደገ ሲሆን ጫት፣ ሲጋራ፣ አልኮልና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆች መጠቀም ከጀመረ አሥራ አምስት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

ወጣቱ በሚኖርበት አካባቢ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች ወጣቶች መሆናቸውን የሚናገረው ይህ ወጣት፣ ተማሪ በነበረበት ጊዜ ሱስ ውስጥ መዘፈቁን ያስረዳል፡፡ ተማሪ በነበረበት ወቅት እንደ ቀልድ የጀመረው ሱስ እንደፀናበትና በዚህም የተነሳ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እንደተገለለ ይናገራል፡፡

በሱስ ውስጥ በነበረባቸው ጊዜያት ሱሱን ለማስታገስ የሚሆን ገንዘብ እንደማያጣና ከጓደኞቹም ጋር ሆኖ አንዱ የሌላውን ወጪ በመሸፈን እርስ በእርስ እንደሚገባበዙ ያስረዳል፡፡ በተለይ ሱስ አማጭ ዕፆችን መጠቀም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከቤተሰቦቹ ጋር እንደማይግባባ ከአንድም ሁለት ጊዜያት ውጪ ማደሩን ያስታውሳል፡፡

ከሁሉም በላይ የእጅ ሙያውን ተጠቅሞ የተሻለ ኑሮ መኖር ሲችል፣ ሱስ ውስጥ መዘፈቁ ዛሬ ላይ እንዳበሳጨው የሚናገረው ወጣት፣ በአንድ ባልታሰበ ጊዜ ‹‹እሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን›› በተሰኘ ድርጅት አማካይነት ሥልጠና አግኝቶ ከነበረበት ሱስ ሊወጣ መቻሉን ያስረዳል፡፡

ሥልጠናውን ለአንድ ሳምንት ያህል ከወሰደ በኋላ ከሱስ አገግሞ የተሻለ ኑሮ እንደሚኖርና በአሁኑ ወቅትም ቤተሰቦቹም ሆኑ እሱ ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራል፡፡  አብዛኛውን ጊዜ ሱስ ውስጥ ተዘፍቀው የሚኖሩ ሰዎች ካሉበት ችግር መውጣት እንደሚፈልጉና ይህንንም ታሳቢ በማድረግ መንግሥት ወጣቶች ላይ መሥራት እንዳለበት ይጠቁማል፡፡

በተለይ ‹‹ከሥር መሠረቱ ሱስን ለማስቀረት ትምህርት ቤቶች ላይ መሥራት ይኖርበታል፤›› የሚለው ወጣቱ፣ መንግሥትም ሆነ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሔ በማበጀት የወጣቱን ሕይወት መታደግ ያስፈልጋል ብሏል፡፡

በሌላ በኩል በሲጋራና በአልኮል ሱስ ሁለት ዓመት ሙሉ ተጠምዳ የነበረችው ወጣት ሔቨን አሸናፊ ናት፡፡ ወጣት ሔቨን በሱስ ተዘፍቃ መኖር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ትምህርቷንና ሥራዋን ሙሉ ለሙሉ ማቆሟን ትናገራለች፡፡ ቀን ቀን የንግድ ሥራ እየሠራች፣ ማታ ማታ ደግሞ ትምህርቷን የምትማረው ይህች ወጣት፣ በጓደኞቿ ግፊት የተነሳ ሱስ ውስጥ መግባቷን ታስረዳለች፡፡

ለሲጋራና ለመጠጥ የሚሆን ገንዘብ እንደማታጣና ከዚህ በፊት ሠርታ ያጠራቀመችውን ገንዘብ በማውጣት ሌሊቱን ሙሉ ‹‹አሸሼ ገዳሜ›› ትል እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ሱስ ውስጥም እያለች ከቤተሰቧ፣ ከዘመዶቿና ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር መጣላቷንና አዲስ ባህሪ መያዟን ለሪፖተር ታስረዳለች፡፡

በተጠመደችው ሱስ የተነሳም የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዳገለላት፣ በአንድ አጋጣሚ በአጎቷ ምክንያት ወደ ሥልጠና ገብታ ከሱስ ራሷን ማግለሏን ተናግራለች፡፡ ከዚህ በፊት አብዛኛውን ጊዜ ከስሱ ለመውጣት ሙከራ ብታደርግም ሊሳካላት አለመቻሉን የምትናገረው ሔቨን፣ ባልታሰበ መንገድ ሙሉ ለሙሉ ከሱስ ውስጥ ወጥታ ራሷን ማየቷ ደስተኛ እንዳደረጋት ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች ሱስ ውስጥ በመዘፈቃቸው፣ መንግሥት ካሉበት ችግር ለማውጣት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብላለች፡፡ በተለይ በርካታ ወጣቶች በተለያየ የሙያ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ናቸው የምትለው ወጣት፣ ይህንንም ሙያቸውን ተጠቅመው ቀጣይ ሕይወታቸውን ማስተካከል ይኖርባቸዋል ብላለች፡፡

የእሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ አብዛኛውን ቁጥር የያዙት ወጣቶች ሱስ ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡

በተለይ በ14 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች በአሁኑ ወቅት ሱስ ውስጥ መዘፈቃቸው ችግሩን እንዳባባሰው የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ እነዚህንም ልጆች ሆነ ወጣቱን ከዚህ ችግር ለማውጣት ተቋሙ ፕሮጀክት ቀርፆ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለ50 ወጣቶች ሥልጠና በመስጠት ከሱስ ውስጥ እንዲወጡ መደረጉን፣ በትምህርት ቤቶችና በሌሎች ቦታዎች በመንቀሳቀስ ወጣቶች ከሱስ እንዲወጡ የግንዛቤ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከወረዳ ጀምሮ እስከ ላይ የመንግሥት ተቋሞች ድረስ በመሄድና ኮሚቴ በማዋቀር ሱስ ውስጥ የተዘፈቁ ሰዎች ግንዛቤ እንዲሁም ሥልጠና የሚያገኙበት መንገድ እየተፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ሦስት ሺሕ ወንዶችና ሁለት ሺሕ ሴት ሱሰኞች ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉንና ለዚህና ለሌሎች ተግባራት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ፈሰስ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ተቋሙ እስካሁን በአሰላ፣ በአዳማ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየሠራ መሆኑንና በቀጣይም ደሴ ላይ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...